5debrezeit

ደብረ ዘይት(ለሕጻናት)

መጋቢት 06/2004ዓ.ም

በቴዎድሮስ እሸቱ

 

5debrezeit

ልጆች እንኳን ለጾመ እኩሌታው /ለደብረ ዘይት/ በሰላም አደረሳችሁ፡፡ ይህ አምስተኛው ሳምንት ደብረ ዘይት ይባላል፡፡ የጾሙ እኩሌታ በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ በዓል ነው፡፡ ልጆች በዚህ ቀን ጌታ በደብረ ዘይት ስለዳግም ምጽአቱ ያስተማረው ትምህርት ይነገራል፡፡ ጌታ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ለሁሉም እንደየሥራው ለመክፈል፣ በግርማ መንግሥቱ ይመጣል፡፡

 

በዚህ ዓለም ሰው ከአባት ከእናቱ ተወልዶ ሲወርድ ሲወጣ ኖሮ ይሞታል ሞቶ ግን አይቀርም በዳግም ምፅአት ጊዜ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ደጉ ደግነቱ ክፉውም ክፋቱን ይዞ ይነሣል፡፡ ወንዱ የሰላሳ ዓመት ጎልማሳ፣ ሴቷ የአሥራ አምስት ዓመት ኮረዳ ሆነው ጻድቃን ብርሃን ለብሰው ከፀሐይ 7 እጅ አብርተው፣ ኀጥአን ጨለማ ለብሰው ፍጹም ዲያብሎስን መስለው ይነሣሉ፡፡

 

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ጻድቃንን “ብራብ አብልታችሁኛል ብጠማ አጠጥታችሁኛል ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን ዓለም ሳይፈጠር ያዘጋጀሁላችሁን መንግሥቴን ውረሱ” ብሎ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳቸዋል፡፡ ኀጥአንን ደግሞ “ሒዱ ከእኔ ለሰይጣንና ለመልእክተኞቹ ወደተዘጋጀው ዘለዓለማዊ እሳት ግቡ” ብሎ ገሀነምን ያወርሳቸዋል፡፡ ጻድቃን ደስ ይላቸዋል፤ ኀጥአን ግን ያዝናሉ ዋይ ዋይ እያሉ ያለቅሳሉ፤ እንባቸውን ያፈሳሉ ግን አይጠቅማቸውም፡፡

 

ልጆች እናንተም በዳግም ምጽአት ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን ከሚላቸው ከጻድቃን ወገን እንድትሆኑ ለተራበ አብሉ፤ አጠጡ፤ ደግ ደግ ሥራ ሥሩ፡፡ ሁላችንንም “ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን ብሎ ከሚጠራቸው ተርታ ያቁመን!