የዐቢይ ጾም ስብክት (ክፍል 5)

መጋቢት 7/2004 ዓ.ም.

በአያሌው ዘኢየሱስ

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

 

የዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት ሰንበት «ደብረ ዘይት» ተብሎ ይጠራል፡፡ ደብረ ዘይት ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ ተራራው በዚህ ስም የሚጠራው ለዘይት የሚሆን የወይራ ተክል በብዛት ስለሚበቅልበት ነው፡፡ ጌታችን ቀን ሲያስተምር ውሎ በደብረ ዘይት ያድር ነበር፡፡ ለደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ በምሳሌ ያስተማረውን ይተረጉምላቸው ነበር፡፡ የዓለም ፍጻሜና የዳግም ምጽአቱን ምልክት ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማራቸው በዚሁ ተራራ ላይ ነውና የጌታን ዳግም ምጽአት የምናስብበት አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሰንበት ስሙን ከተራራው ወስዷል ማለት ነው፡፡ ደብረ ዘይት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ «እኩለ ጾም» ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህ ስያሜ የሚጠራውም የጾሙ ሳምንታት አጋማሽ ወይም እኩሌታ ስለሆነ ነው፡፡ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶች መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ እሑድ፣  የደብረ ዘይት ዕለት ይመጣል ብለው ስለሚያስተምሩ በዚህ ሰንበት የሚበዙት ምዕመናን ዕለቱን በታላቅ ዝግጅት ማለትም በንስሓና በቅዱስ ቁርባን ይቀበሉታል፡፡ በዚህ ዕለት የሚሰበከው ምስባክ፣ የሚሰጠው የወንጌል ትምህርትና የሚነበቡት የሐዋርያት ሥራና የመልእክታት ንባባት በሙሉ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሁለተኛ አመጣጥ የሚናገሩ ናቸው፡፡

ከአራቱ ወንጌላውያን (ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ፣ ዮሐንስ) ስለ አምላካችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለተኛ አመጣጥ እና ስለ ዕለተ ደይን ማለትም ስለ ፍርድ ቀን በስፋትና በጥልቀት የጻፈው ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ነው፡፡ በመሆኑም በአምሳ አንድ ቁጥሮች የተከፋፈለው ሃያ አራተኛው ምዕራፉ ሙሉ ለሙሉ የሚናገረው ስለ አስፈሪውና ስለ አስደንጋጩ የክርስቶስ ሁለተኛ አመጣጥ ነው፡፡ ምዕራፉን በሦስት ዐበይት ክፍሎች ሥር ማሰባሰብ ይቻላል፤ኢየሱስ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት፣ በመጣ ጊዜ እና ከመጣ በኋላ በምድርና በሰማይ ላይ የሚከሰቱ ክስተቶች በማለት፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ አጭር ጽሑፍ ውስጥ የሚገኙትን አምሳ አንድ ቁጥሮች ኀይለ ቃላት አድርጎ መስበክ ስለማይቻል አንዱን ቁጥር ርእስ አድርገን በመውሰድ ለመማማር እንሞክራለን፡፡

ከላይ ርእስ ተደርጎ የተወሰደው “እነዚያ ቀኖች….” የሚለው ነው፡፡ «እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል፡፡» (ማቴ 24፥13) የሚለው ነው፡፡ አስቀድመን እንደ ተናገርን አምላካችን ከመምጣቱ በፊት፣ በመጣ ጊዜ እና ከመጣ በኋላ በምድርና በሰማይ የሚታዩ ታላላቅ ምልክቶች ተከስተው እስከሚያበቁ ድረስ በሰው ልጆች ዘንድ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ጽናት ስለሚያስፈልግ ነው መድኀኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ መጨረሻ የሚጸና እርሱ ይድናል በማለት በግልጥ ያስተማረው፡፡ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሲፈርስ፣ እኔ ክርስቶስ ነኝ ብለው የሚያውጁ አሳቾች ሲነሡና ብዙዎችን ሲያስቱ፣ ጦርንና የጦር ወሬን መስማት ተደጋጋሚ ዜና ሲሆን፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ መነሳቱ ቀላል ነገር ሲሆን፣ ረሀብ ቸነፈርና የምድር መናወጥ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ላይ ሲመጣ የሚመለከቱ የሰው ልጆች መጽናት ስለሚያስፈልጋቸው ነው እስከ መጨረሻ የሚጸና እርሱ ይድናል ተብሎ የተነገረው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የእግዚአብሔር ልጆች በማያምኑ ሰዎች ሲጠሉ፣ ለመከራ ተላልፈው ሲሰጡና ሲገደሉ፣ ሰዎች እርስ በእርሳቸው ተላልፈው ሲሰጣጡ፣ እርስ በእርሳቸው ሲጣሉ፣ ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት ሲነሡና ብዙዎችን ሲያስቱ፣ ዓመጻ ሲበዛና የሰው ልጆች ፍቅር ሲቀዘቅዝ ወይም ሲጠፋ፣ ከዓለም መጀመሪያ እስከዚያ ቀንድ ድረስ ያልሆነ ከእንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ሲሆን፣ አሳቾችና ሐሰተኞች ክርስቶሶች ለእግዚአብሔር የተመረጡትን ሰዎች እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ሲያሳዩ የሚመለከቱ ሰዎች ከሃይማኖታቸውና ከእምነታቸው ሳይናወጡ እስከ መጨረሻው ድረስ በጽናት እንዲቆዩና እንዲድኑ ነው ጌታ እስከ መጨረሻ የሚቆይ እርሱ ይድናል በማለት የተናገረው፡፡

ከዚህ ሌላ የጥፋት ርኵሰት በተቀደሰችው ስፍራ (በቤተ ክርስቲያን) ቆሞ ሲታይ፣ ፀሐይ ስትጨልም፣ ጨረቃ ብርሃንዋን አልሰጥም ስትል፣ ከዋክብት ከሰማይ ሲወድቁ፣ የሰማያት ኀይላት ሲናወጡ፣ የሰው ልጅ (ኢየሱስ ክርስቶስ) ምልክት በሰማይ ሲታይ፣ የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ሲሉ፣ ወልደ እጓለመሕያው ኢየሱስ ክርስቶስ በኀይልና በብዙ ክብር መምጣቱ ሲታይ፣ መላእክቱ ከሰማያት ዳርቻ እስከ ዳርቻው ድረስ ለእርሱ የተመረጡትን ቅዱሳን ሲሰበስቡ የሚመለከትና በጽናት የሚቆይ ሰው እርሱ ይድናል ማለት ነው፡፡

ከዚህ በላይ የተመለከትናቸውና ወንጌሉ ምንም ሳያስቀር ፍንትው አድርጎ ያሳየን የዳግም ምጽአት የመጀመሪያ፣ የቀጣይና የመጨረሻ ምልክቶች በሙሉ አሳሳቢ፣ አስፈሪና አስደንጋጭ ምልክቶች ስለሆኑ እምነትና ሥራ የሌለው ሰው ካልሆነ በስተቀር ማንም ቢሆን እስከ መጨረሻው ድረስ በጽናት ሊቋቋማቸው አይችልም፡፡ በተለይም የጥፋት ርኵሰት በተቀደሰችው ቦታ ላይ ሲቆም፣ አሳቾች ለእግዚአብሔር የተመረጡትን ሰዎች እስከሚያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ሲያሳዩ መመልከትና ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብትና የሰማያት ኀይላት  ብርሃናቸውን ሲነፍጉ፣ ከሰማይ ሲረግፉና ሲናወጡ መስማትና ማየት በሃይማኖትና በምግባር የማይኖረውን ሰው ሊያጸናው አይችልም፡፡ ዛሬ በተቀደሰችው ቦታ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የጥፋት ርኵሰት መቆሙን የሚያመለክቱ ብዙ ምልክቶች በገሃድ እየታዩ ነው፤ከሊቅ እስከ ደቂቅ በጥፋትና በርኵሰት ሥራ እንጂ በእምነትና በጽድቅ ሥራ ላይ ወይም ኢየሱስ ክርስቶስን ለመቀበል በሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ሲተጋ አይታይምና፡፡ በመሆኑም አምና እና ዘንድሮ አሳቾች መናፍቃን የክርስቶስ ነን ወይም ክርስቶስ ከእኛ ጋር ነው እያሉ ብዙዎችን ሲያስቱ፣ መንግሥት በመንግስት ላይ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሲነሣ፣ በዓለማችን የተለያዩ ቦታዎች ላይ ምድር ስትናወጥ፣ ረሀብና ቸነፈር ሲሠለጥኑ እየተመለከተ ያለ ሰው በዚሁ ምክንያት በሃይማኖቱ ሊጸና ስላልቻለ የምጥ ጣር መጀመሪያ በተባሉት በእነዚህ ምልክቶች ሲፈናቀል እየታየ ነው፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት በፊት በሚታዩት እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያዎች ወይም የመጀመሪያ ምልክቶች መታየት ሃይማኖቱን የሚለውጥ ከሆነ የጥፋት ርኩሰት በቤተ ክርስቲያኑ ዓውደ ምሕረት ላይ ቆሞ ስለ ጥፋት ሲሰብክ ሲመለከት እንዴት ነው ሊጸና የሚችለው? እነዚህን ምልክቶች የተለመዱ የሰዎችና የተፈጥሮ አደጋዎች ናቸው ብሎ የሚያምንና በዚያ ዙሪያ መፍትሔ ለመስጠት የሚራወጥ ሰው ይህ ሊሆን ግድ ነውና ከጥፋት ተጠበቁ እንዲሁም ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው የሚለውን አምላካዊ ቃል በጽናት ሊያምንና ሊተገብር የሚችለውስ እንዴት ነው? ዲያቆን እገሌ ወይም ቄስ እገሌ ወይም አባ እገሌ ሰው በመሆናቸውና ደካማ የሆነውን ሥጋ በመልበሳቸው የሚፈጽሙአቸውን ስሕተቶች ሲመለከት ሃይማኖቱን ረግሞ ከመናፍቃን ጋር ጽዋውን ሊያነሣ የሚጣደፈው ሰው ነገ ያሳሳቱት አሳቾች የተመረጡትን ሰዎች እስከ ማሳሳት ሲደርሱ ሲመለከት እንዴት አድርጎ ነው ሊጸና የሚችለው? እዚህ ላይ ንባባችሁን ጥቂት በማቆም በተመስጦ ውስጥ ሁኑ እና ራሳችሁን በክርስቶስ ቃል እንዲህ ብላችሁ ጠይቁት፡- «ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?» ሉቃ 18፥8፡፡

ይህ ቃል አስፈሪ ቃል ነው! ይህ ቃል ውስጣችንን የሚመረምር ቃል ነው! ይህ ቃል ማንነታችንን የሚያሳይ ቃል ነው! ይህ ቃል ማንነታችንን የሚገልጥ ቃል ነው! ይህ ቃል እምነትና ጽናት በእኛ ዘንድ እንደሌለ የሚመሰክር ቃል ነው! ይህ ቃል ባዶ መሆናችንን የሚያሳውቅ ቃል ነው! ይህ ቃል እውነት ነው! ይህ ቃል የእውነት አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ነው! ዛሬ እምነት ከሰው ልጆች ዘንድ እየመነመነ ነው፡፡ በእምነት የሚፈጸሙ ተግባራት እየጠፉ ነው፡፡ እምነት ስለሌለም ጽናት እየጠፋ ነው፡፡ ጽናት  ስለሌለም ሰው ሁሉ እየጠፋ ነው፡፡ «እምነትን ያገኝ ይሆንን?» የሚለው ቃል «ያገኛል» ማለት አይደለም፤«አያገኝም» ማለት ነው እንጂ፡፡ «በመጣ ጊዜ» የሚለው ቃልም ለሁለተኛ ጊዜ ለፍርድ ሲገለጥ ወይም በዳግም ምጽአቱ ሲገለጥ ማለት ነው፡፡ የሚመጣውም እስከ መጨረሻው ድረስ በእምነትና በጽናት በመቆየት መንግሥቱን ሊያወርሰን የሚፈልገው መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ሰዎች እምነትና ሥራን አስተባብረው ካልያዙ ግን መንግሥቱን አያወርሳቸውም፡፡ በሰዎች ዘንድ በእምነትና በሥራ የሚገለጥ ጽናት ከሌለም መንግሥቱን ሊወርሱ አይችሉም፡፡ እምነት ብቻ አያድንም! ሥራ ብቻ አያድንም! በባዶ ነገር ላይ መጽናትም አያድንም! እምነትንና ሥራን አስተባብሮ በመያዝ በእነዚህ በሁለቱ ላይ መጽናት ግን ያድናል!! ሰው እምነትና ሥራን አስተባብሬ ይዤአለሁ እያለ በእነዚህ ላይ ሊጸና ካልቻለና በትንሹም ሆነ በትልቁ ምክንያት ወይም ፈተና የሚወድቅ ከሆነም አይድንም፡፡

ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እስከ መጨረሻው ድረስ ሊጸኑ የቻሉና ያልቻሉ ብዛት ያላቸው ሰዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ፡- ጻድቁ ኢዮብ፣ ነቢዩ ኤልሳዕና ሐዋርያት ለጽናት ልዩና ድንቅ ምሳሌዎቻችን ናቸው፡፡ ጻድቁ ኢዮብ ቤቱን፣ ንብረቱን፣ ከብቶቹንና አሥር ልጆቹን በአንድ ቀን ውስጥ ያጣ ሰው ነበር፡፡ ይህ ሳይበቃውም መላው ሰውነቱ በከባድ ቁስል ተመትቶ ከፍተኛ መከራና ሥቃይ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ፈተና ያመጣበት ሰይጣን ሲሆን ምክንያቱም እርሱን በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት በሥራና በጽናት መግለጽ አይችልም በማለት ተስፋ ስላደረገ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የኢዮብ አሳብና የሰይጣን አሳብ፤የኢዮብ እምነትና የሰይጣን እምነት፣ የኢዮብ ሥራና የሰይጣን ሥራ፣ የኢዮብ ጽናትና የሰይጣን ጽናት አንድ ሊሆን ስላልቻለ ኢዮብ ሰይጣንን በአራቱም ውጊያዎች ፈጽሞ አሸንፎታል፡፡ በአሳብ፣ በእምነት፣ በሥራና በጽናት፡፡

እንደ ሰው ሰውኛው (እንደ እኛ) አስተሳሰብ ኢዮብን የገጠሙት ፈተናዎች በእምነቱና በሥራው እስከ መጨረሻው ድረስ ሊያጸኑት የሚችሉ አልነበሩም፡፡ እኛ ያሉኑን ነገሮች ማለትም ሀብታችንን፣ ንብረታችንን፣ ልጆችንንና ጤናችንን አጥተን አይደለም እነዚህ ሁሉ ተሟልተውልን እግዚአብሔርን ልናምነው፣ እርሱን ደስ የሚያሰኙትን የጽድቅ ሥራዎች ልንሠራና በእነዚህ ላይ ልንጸና አልቻልንም፡፡ ሁሉንም ነገር ሰጥቶን እኮ ነው የለህም የምንለው! ሰዎች ያላቸውን ሳያጡ እኮ ነው እርሱን የሚክዱት! ሰዎች ራሳቸውን ወይም ሆዳቸውን ጥቂት ካመማቸው እኮ ነው እግዚአብሔርን የለህም ለማለት የማይሰንፉት! ኢዮብ ግን አሥር ልጆቹን ጨምሮ ሁሉንም ነገር ቢያጣና እርሱ ራሱ የቆሰለ ገላውን በገል እስከ መፋቅ ቢደርስም እንዲህ ነበር ያለው፡- «. . . እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔርም ነሣ፤የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን፡፡» ኢዮ 1፥21፡፡

ያለ ነገርን ሙሉ ለሙሉ አጥቶ እግዚአብሔርን ማመስገን መቻል በእምነትና በሥራ ላይ የተመሠረተ ጽናት ነው፡፡ የቆሰለ አካልን ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ጠጉር ድረስ በገል እየፋቁ የእግዚአብሔርን ስም ለማመስገን መነሣት በእምነትና በሥራ ላይ የተመሠረተ ጽናት ነው፡፡ እስከ መጨረሻ ድረስ በእምነት መጽናት ደግሞ ድኅነትን ስለሚያሰጥ ጻድቁ ኢዮብ ከልጆቹ ቁጥር በስተቀር የነበሩት ነገሮች ሁለት እጥፍ ሆነው ተመልሰውለታል፤የልጅ ልጆቹንም እስከ አራት ትውልድ ድረስ ሊያይ ችሏል፣ ሸምግሎና ዕድሜ ጠግቦም ሞቷል፡፡ የሚጸና ሰው ዋጋ እጥፍ ነው፡፡ የሚያዳክሙና ከእግዚአብሔር ሊለዩ የሚሞክሩ ሚስቶችን እንደ ጻድቁ ኢዮብ «አንቺ ከሰነፎቹ ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፤ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፤ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን?»  (ኢዮ 2፥10) ማለት እምነት ነው! ሥራ ነው! ጽናትም ነው! በእምነትና በጽናት ላይ የሚመጡ ባልንጀራዎችን “የምታዳክሙ ባልንጀራዎች” ማለትም ጽናት ነው!

ኤልሳዕ መምህሩ ኤልያስ ከእርሱ ተለይቶ በእሳት ሰረገላና ፈረሶች ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ከቤቴል እስከ ዮርዳኖስ ማዶ ድረስ በሚገኙት አራት ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ የነቢያት ልጆች «እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ እንዲወስደው አውቀሃልን?» (2ኛ ነገ 2፥3እና5) በማለት ጽናቱን አናውጠው ከጌታው ከኤልያስ ሊለዩትና በመጨረሻ ሊያገኘው የነበረውን እጥፍ መንፈስ ሊስቀሩበት ሞክረው ነበር፡፡ ኤልሳዕ ግን ጽናቱን «አዎን አውቄአለሁ፤ዝም በሉ፤. . .» (2ኛ ነገ 2፥3እና5) በማለት አረጋግጦላቸዋል፡፡ ከቤቱ ወጥቶ እግዚአብሔር ወደሚመለክበት ሥፍራ በመሔድ ላይ ያለ ወጣትን ባልንጀሮቹ ዛሬ እኮ «አርሴ» እና «ማንቼ» ግጥሚያ እንዳላቸው አላወቅህምን? ሲሉት «አዎን አውቄአለሁ፤ዝም በሉ» በማለት ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት በእምነቱና በሥራው ላይ እስከ መጨረሻ ድረስ በመጽናት መንገዱን የማይቀጥል ከሆነ እምነቱን በሥራና በጽናት አልገለጠምና በፍርድ ቀን የጌታውን መንግሥት ሊወርስ አይችልም፡፡ ይህን የምለው የነጮቹን ኳስ ግጥሚያ ለማየት ሲሉ የተሰጣቸውን የስብከት ወይም የሰዓታት ወይም የማኅሌት አገልግሎት ሰርዘው ወደዚያው የሔዱ ሰዎችን ስለማውቅ ወይም ራሳቸው ስለ ነገሩኝ ነው፡፡ እንብላ፣ እንጠጣ፣ እንቃም፣ እናጭስ፣ እንጨፍር፣ እንሴስን. . . ወዘተ የሚሉትንም በጽናት «ዝም በሉ!» በማለት አልፎ መምጣት እስከ መጨረሻው ድረስ መጽናት ካልተቻለ የሰዎች ውድቀት የከፋ ነው የሚሆነው፡፡

የሐዋርያት ጽናትም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ እነርሱ ሁሉንም ነገር ትተው መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በጽናት ከተከተሉት በኋላ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደ አረጋዊነቱ እነርሱን በመወከል «እነሆ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን?» (ማቴ 19፥27) የሚል መሠረታዊ ጥያቄ ለጌታ አቅርቦለት ነበር፡፡ አምላካችንም ለቅዱስ ጴጥሮስ ብቻ ሳይሆን እርሱ ለወከላቸው ለአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት እንዲህ የሚል መልስ ሰጥቶአቸዋል፡- «እውነት እላችኋለሁ፡- እናንተስ የተከተላችሁኝ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ፡፡» ማቴ. 19፥28፡፡ ጌታ ይህን ከነገራቸው በኋላ ያለውን ሁሉ የተወ ሰው እንደ ኢዮብና እንደ ኤልሳዕ ሁለት እጥፍ ዋጋ እንደሚቀበሉ እንዲህ በማለት አስረግጦ ነግሮአቸዋል፡- «. . . የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል፤የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል፡፡» ማቴ.19፥29፡፡

አስቀድመን እንደ ተናገርን የሚጸና ሰው ዋጋ እጥፍ ድርብ ወይም መቶ እጥፍ ነው፡፡ በክርስትና ሳይተዉ መቀበል አይቻልም፡፡ ዛሬ ብዙዎች ያላቸውን ሀብት፣ ቤት፣ ንብረት፣ ልጆች. . . ወዘተ ሊተዉ አልቻሉም፡፡ ይህ በእግዚአብሔር ፈቃድ ለዚህ አገልግሎት ለተመረጡ አባቶች ብቻ ስለሆነና ሁሉም ያለውን ትቶ በምንኩስና ሕይወት እርሱን እንዲከተሉት ስላልፈቀደ ሁሉም መነኩሴ ወይም መነኩሲት ሊሆን አይችልም፤በግድ ልሁን ቢልም አይሳካለትም፡፡ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር አምላክ ሰዎች ሁሉ አጥብቀው እንዲተዉለት የሚፈልገው ነገር አለ፤እርሱም ኀጢአት ነው፡፡ ዛሬ ብዙዎችን እስከ መጨረሻው ድረስ እንዲጸኑ፣ እንዲድኑና ዘላለማዊ ሕይወት እንዲወርሱ የማያደርጋቸው ኀጢአት ነው፡፡ አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባል ወደ ክርስትና እምነት የተጠራው እስከ ሞት ድረስ በመጽናት የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ስለሆነ ከኀጢአት መሸሽ እንጂ ኀጢአትን መከተል አልተፈቀደለትም፡፡ «እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን፤የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ፡፡» (ራእ 2፥10) በማለት የተናገረው እኮ የእግዚአብሔር አብ እና የድንግል ማርያም ልጅ ጌታችን፣ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ጽናትና መታመን ከኀጢአትና ከጥፋት ጋር ሊስማሙ አይችሉም፡፡ ኀጢአት እስከ ሞት ድረስ የታመንን እንድንሆን አያደርገንም፡፡

ኢዮብ፣ ኤልሳዕና ሐዋርያት በእምነት፣ በሥራና በጽናት የሕይወትን አክሊል ተቀብለዋል፡፡ ሶምሶን፣ ግያዝና ዴማስ ግን እስከ መጨረሻ ድረስ ሊጸኑ ስላልቻሉ ሊጸድቁ አልቻሉም፡፡ በአንድ ወቅት ታላላቅ መንፈሳዊ አባቶች ተብለው የተጠሩ እነዚህ ሰዎች በፈተና ሊጸኑ ስላልቻሉ ለሌሎች ሁለት እጥፍ ሆኖ የተሰጠውን ዋጋ ሊቀበሉ አልቻሉም፤ አልተባረኩምም፡፡ መጽሐፍ ጽናት ስለሚያሰጠው በረከት ሲናገር እንዲህ ብሏል፡- «በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፡፡» ያዕ 1፥12፡፡ ለመባረክም መጽናት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ በፍርድ ቀን «ኑ፤ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ፡፡» (ማቴ 25፥34) የሚለውን የእግዚአብሔር ቡራኬ ለመቀበል እስከዚያው ቀን ድረስ በእምነትና በሥራ በጽናት መቆየት ያስፈልጋል፤ማስፈለግ ብቻ ሳይሆን ግድ ነው!!

ስለሆነም ዛሬ በዐቢይ ጾም አምስተኛ ሰንበት ላይ ሆነን የደብረ ዘይትን በዓል ስናከብር እስከ ጌታችን ዳግም ምጽአት ድረስ በእምነት፣ በሥራና በጽናት እንድንቆይ እርሱን «አንተ አድነን!» ልንለው ይገባናል፡፡ እንደ ጸኑት ሁለት እጥፍ ዋጋ እንዳናገኝ ዓለም በአናንያ፣ በአዛርያና በሚሳኤል ዙሪያ ያነደደችውን የፈተና እሳት በእኛም ሕይወት ዙሪያ አንድዳለችና በእሳቱ ከመሟሟቅ ይልቅ እሳቱን የምናጠፋበትን የእምነት ጽናት እንዲያድለን እንጠይቀው፡፡ ዛሬ በእምነትና በእምነት ሥራ የምናየውና የምንሰማው ዜና ሁሉ ተስፋ የሚያስቆርጥ እንጂ የሚያጸና ስላልሆነ እግዚአብሔር አምላክ ተስፋችንን እንዲሁም ጽናታችንን እንዲያለመልመልን እንጠይቀው፡፡ የሰዎች ዐይኖች በእግዚአብሔር ሥራዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ በዲያብሎስ ሥራዎች ላይ እጅግ አተኩረዋልና ዐይኖቻቸውን ከዚህ ክፉ ሥራ መልስ እንበለው፡፡

የደብረ ዘይት በዓል የዝግጅት በዓል ነው፡፡ የደብረ ዘይት ከእግዚአብሔር ጋር የምንሆንበትን ቀን የምንናፍቅበት በዓል ነው፡፡ የደብረ ዘይት በዓል ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የምንሆንበት በዓል ነው፡፡ ዳግም ምጽአት ከእግዚአብሔር ዋጋ የምንቀበልበት ቀን ነው፡፡ ዳግም ምጽአት ከእግዚአብሔር በስተ ቀኝ የምንቆምበት ቀን ነው፡፡ ዳግም ምጽአት ዐይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውንና በልቦናም ያልታሰበውን የእግዚአብሔር መንግሥት ለመውረስ የምንሸጋገርበት ቀን ነው፡፡ ስለሆነም ቀኑን በፍጹም እምነት ከልባችን ሆነን በመጾም፣ በመጸለይ፣ በመስገድና በመመጽወት እናንክብረው እንጂ ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ዘይት ወጣ ብለን ለመዝናናት፣ ያገኘነውን ለመብላትና ለመጠጣት እንዲሁም ከዕለቱ በዓል ጋር የማይገናኙ ተራ ወሬዎችን ለማውራት እንዳናደርገው እንጠንቀቅ!! የአምላካችን የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከእኛ ጋር ይሁን፤አሜን፡፡

ይቆየን፡፡

በጎውን ሁሉ ለእኛ ያደረገና የሚያደርግ እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን፤አሜን፡፡