የ፳፻፱ ዓ.ም ዓቢይ ጾም መግቢያን በማስመልከት ቅዱስ ፓትርያርኩ የሰጡት ቃለ ምዕዳን

የካቲት ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

%e1%8d%93%e1%89%b5%e1%88%ad%e1%8b%ab%e1%88%ad%e1%8a%ad

የተወደዳችሁ ምእመናን! የ፳፻፱ ዓ.ም ዓቢይ ጾም የካቲት ፲፫ ቀን ይገባል፡፡ የጾሙን መግባት በማስመልከትም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የካቲት ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ጠዋት የጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የማኅበረ ቅዱሳን፣ የመንግሥት እና የግል መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች በተገኙበት በጽሕፈት ቤታቸው ቃለ ምዕዳን የሰጡ ሲኾን፣ የቅዱስነታቸውን ሙሉ ቃለ ምዕዳን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ በአተ ጾም ዓቢይ ዘእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምዕት ወተስዐቱ ዓመተ ምሕረት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

በአገር ውስጥና በመላው ክፍላተ ዓለም የምትገኙ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ!

ፍጥረቱን በምሕረት፣ በይቅርታና በርኅራኄ የሚጠብቅ፣ የሚመግብና የሚያስተዳድር፣ ከዅሉ በላይ የኾነ ኃያሉ አምላካችን እግዚአብሔር እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት መዋዕለ ጾም ዓቢይ በሰላም አደረሳችሁ!!

‹‹ቅረቡ ኀቤሁ ወያበርህ ለክሙ፣ ወኢይትኃፈር ገጽክሙ፤ ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችኋልም፤ ፊታችሁም አያፍርም፤›› (መዝ.፴፬፥፭)፡፡

የሰው ልጅ ከዐራቱ ባሕርያተ ፍጥረት በተገኘ ሥጋዊ ሕይወቱ፣ የዐራቱ ባሕርያት ውጤት የኾኑትን ማለትም እኽልን ውኃን፣ ነፋስንና እሳትን የመሻት ፍላጎቱ የላቀ እንደኾነ ዅሉ፣ ከእግዚአብሔር በተገኘ መንፈሳዊ ሕይወቱም እግዚአብሔርን የመሻት ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው፡፡

ከእግዚአብሔር የተገኘውን ይህን ሀብተ ተፈጥሮ ከሰው ባሕርይ መለየት የማይቻል በመኾኑ ሰብአዊ ፍጡር ዅሉ ከፈጣሪው ጋር ግንኙነት ለማድረግ ይጓጓል፡፡

ሰው ወደፈጣሪው ለመቅረብ ከሚፈልገው በላይ፣ ፈጣሪም ሰውን በእጅጉ ሊቀርበውና ማደርያው ሊያደርገው ይፈልጋል፤ በመኾኑም ሁለቱም ተፈላላጊ መኾናቸው በሕገ ተፈጥሮም ኾነ በቅዱስ መጽሐፍ የታወቀ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ሁለቱም እንዳይቀራረቡ የሚያደርጉ መሠረታውያን ነገሮች እንዳሉ ዅሉ እንዲቀራረቡ የሚያደርጓቸውም አሉ፤ ሁለቱንም ሊያቀራርቡ ከሚችሉት መካከል አንዱ ጾም ነው፡፡

እግዚአብሔር በዅለመናው ንጹሕ ቅዱስ ፍጹምና ክቡር በመኾኑ ለባሕርዩ ከማይስማሙ ድርጊቶችና ከአድራጊዎቻቸው ጋር ግንኙነት ሊያደርግ አይፈቅድም፡፡

ኾኖም ንስሐ ሲገቡና ጥፋታቸውን አምነው ሲጸጸቱ በይቅርታ የሚቀበል ርኅሩኅ፣ መሐሪና ይቅር ባይ አምላክ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የሚፈጠረውን ክፍተት ለማጥበብ ብሎም ለመዝጋት ንስሐ፣ ጾምና ጸሎት ቊልፍ መሣሪያዎች ናቸው፤ እኛ ክርስቲያኖችም ጾምን የምንጾምበት ዋና ምክንያት ይኸው ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ መንፈሳዊ ኃይል ያስፈልጋል፤ መንፈሳዊ ኃይል የሚገኘው ደግሞ ሥጋዊ ኃይል ሲገታ ነው፡፡ ጾም ይህን በማድረግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

ጾም ኃይለ ሥጋን በመግራት ኃይለ መንፈስ እንዲበረታ ያደርጋል፤ ጾም ራሳችንን ዝቅ አድርገን ለእግዚአብሔር እንድንገዛና ለቃሉ ታዛዥ እንድንኾን ያስችለናል፤ ጾም ሰከን ብለን ስለበደላችን እንድናስብና ለንስሐ እንድንፈጥን ያደርገናል፤ ጾም የእግዚአብሔርን ቸርነት በማሰብ ፍቅሩን እንድናውቅና እንድናመልከው፣ ለሰውም ጥሩ የኾነውን ብቻ እንድናስብ ያደርገናል፡፡

እነዚህ ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ ሥርፀት ሲያገኙ ወደ እግዚአብሐር የመቅረቡና የመገናኘቱ ዕድል ሰፊ ይኾናል፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ ኾነን ስለምንሻው ነገር እግዚአብሔርን ብንጠይቅ መልሱ ፈጣን ይኾናል፡፡ ከዚህ አንጻር የነነዌ ጾም ያስገኘው ፈጣን መልስ ማስረጃችን ነው፡፡ በጾም ኃይል አማካኝነት ከፈጣሪ ጋር የተገናኙ እነሊቀ ነቢያት ሙሴ፣ ነቢዩ ዳንኤልና ዕዝራም በዚህ ተጠቃሽ መምህሮቻችን ናቸው፡፡

ርኩስ መንፈስን ድል ለማድረግ፣ ሊጀመር የታሰበውን ዓቢይ ተግባር በስኬት ለማጠናቀቅ በጾም ረድኤተ እግዚአብሔርን መጠየቅ አስፈላጊ መኾኑን ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተግባርና በትምህርት አሳይቶናል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያትም ይህን በተግባርና በትምህርት ፈጽመውታል፤ ከዚህ አኳያ ጾምና ሃይማኖት የማይለያዩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መኾናቸውን መገንዘብ አያዳግትም፡፡

በመኾኑም ጾም ራሳችንን ለመቈጣጠር፤ የእግዚአብሔር ታዛዥ ለመኾን፤ ለጥያቄአችን ፈጣን መልስ ለማግኘት፤ ርኩስ መንፈስን ድል ለማድረግ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት የሚያገለግለን ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ መሣሪያ ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናን ወምእመናት

የጾም አስፈላጊነትና ውጤታማነት ከጥንት ጀምሮ በነቢያትና በሐዋርያት የታወቀ ነው፤ ከዅሉ በላይ ደግሞ እግዚአብሔር ራሱ፡- ‹‹በፍጹም ልባችሁ በጾም፣ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ፤ ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፡፡ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ነው፤ ቍጣው የዘገየ፣ ምሕረቱ የበዛ፣ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ፡፡ በጽዮን መለከትን ንፉ፤ ጾምንም ቀድሱ (ለዩ)፤ ጉባኤውንም አውጁ፡፡ ሕዝቡንም አከማቹ፤ ማኅበሩንም ቀድሱ፤›› ብሎ ጾምን በአዋጅ እንድንጾም አዞናል፤ (ኢዩ.፪፥፲፪-፲፰)፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ርኩስ መንፈስ ሊሸነፍና ድል ሊኾን የሚችለው በጾምና በጸሎት እንደኾነ አስረግጦ አስተምሮናል፤ (ማቴ. ፲፯፥፲፬-፳፩)፡፡

ይኹንና ጾም በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋም፣ መልስም፣ ኃይልም ሊያሰጥ የሚችለው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ማለትም እግዚአብሔር ባዘዘው ትእዛዝ መሠረት ሲከናወን መኾኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር የሚፈልገው ጾም እንዴት ያለ እንደኾነ እርሱ ራሱ እንዲህ ብሎናል፤ ‹‹እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እሥራት ትፈቱ ዘንድ፤ የቀንበርን ጠፍር ትለቁ ዘንድ፤ የተገፉትን አርነት ትሰዱ ዘንድ፤ ቀንበሩን ዅሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህን ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፤ ስደተኞቹ ድሆችን ወደቤትህ ታገባ ዘንድ፤ የተራቆተውን ብታይ ታለብሰው ዘንድ፤ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሸግ አይደለምን? የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ያበራል፤ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፤ ጽድቅህም በፊትህ ይሔዳል፡፡ የእግዚብሔርም ክብር በላይህ ኾኖ ይጠብቅሃል፤›› ብሎ ፈቃዱን ነግሮናል፤ (ኢሳ.፶፰፥፮-፰)፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

የጾም ዓቢይ ዓላማ ለእግዚአብሔር የሚታዘዝና የተሰበረን ልብ መፍጠር፤ በጾም፣ በጸሎት፣ በንስሐ፣ በስግደት በተመስጦ፣ በአንቃዕድዎ ለእርሱ መታዘዝና መገዛት፤ እርሱንም ማምለክ ነው፡፡

ከዚህም ጋር ጥልን በይቅርታ ማስወገድ፤ ሰላምን በማረጋገጥ ፍቅረ ቢጽን ገንዘብ ማድረግ፤ ራስን መቈጣጠርና መግዛት፤ ኃይለ ሥጋን መመከት፤ ኃይለ ነፍስን ማጐልበት፤ የእግዚአብሔርን እንጂ የሰውን አለማየት፤ የርኩሳን መናፍስትን ግፊት በመቋቋም ክፉ ምኞትን ድል ማድረግ፤ ቅዱስ ቊርባንን መቀበል፤ ኅሊናን ለእግዚአብሔር መስጠት፤ ያለንን ለነዳያን ከፍለን መመጽወት የመሳሰሉትን ዅሉ ዕለታዊ ተግባራችን በማድረግ ጾሙን ልንጾም ይገባል፡፡

በመጨረሻም

የጾም ዋና ዓላማ ለእግዚአብሔር መታዘዝ እንደ መኾኑ መጠን ምድርን እንድናበጃትና እንድናለማት ያዘዘንን ትእዛዝ ተቀብለን አካባቢያችንን በማልማት አገራችንን ውብና ለኑሮ የተመቸች በማድረግ፤ እንደዚሁም ከኃጢአት መከላከያዎች መካከል ዋናውና አንዱ ያለ ዕረፍት በሥራ መጠመድ ነውና ሕዝቡ ሥራ ሳይፈታ ፈጣሪውን በጾም እያመለከ፣ የተቸገረ ወገኑን ካለው ከፍሎ እየረዳ፣ ልማትንም እያፋጠነ የአገሩንና ሰላምና ፀጥታ እየጠበቀ መዋዕለ ጾሙን እንዲያሳልፍ በእግዚአብሔር ስም መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

ወርኀ ጾሙን አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም ያድርሰን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻ወ፱ ዓ.ም.

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ