የጽዮን ምርኮ – የመጨረሻ ክፍል

ኅዳር ፳፮ ቀን ፳፻፱ .

በመምህር ብዙነህ ሺበሺ

ታቦተ ጽዮን ከቤተ አሚናዳብ እስከ ዳዊት ከተማ ….

ወደ ታቦተ ጽዮን በተመለከቱ ፸ ቤትሳምሳውያንና ታቦቱን ለመያዝ እጁን በዘረጋ በዖዛ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ነድዶ ከቀሠፋቸው ‹‹ታቦት (ጽላት) አያስፈልግም!›› የሚሉ ተሐድሶ መናፍቃን የት ይኾን መገኛቸው? ዕድል ፈንታቸው፣ ጽዋ ተርታቸውስ ምን ይኾን? ዖዛ ሙሴንና አሮንን ይቃወሙ የነበሩ መሬት ተከፍታ የዋጠቻቸው የዳታንና አቤሮን፣ ሐዋርያትን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ በገንዘብ ሽጡልኝ በማለት የጠየቃቸው የሰማርያው መሠሪ (ጠንቋይ) ሲሞን፣ በሊቃውንት አባቶች ተወግዘው የተለዩ የአርዮስ፣ ንስጥሮስ፣ አቡሊናርዮስ፣ መቅዶንዮስ ወዘተ ምሳሌ ነው፡፡ እነሱ የማይገባቸውን ሽተው ከዕውቀታቸው በላይ የኾነውን እናውቃለን በማለታቸው በሥጋቸው መቅሠፍት፣ በነፍሳቸውም ሞት እንዳመጡ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ላለመስማት ጆሯቸውን በጣታቸው የደፈኑ አራዊተ ምድር ተሐድሶ ነን ባዮች መናፍቃንም አወዳደቃቸው የከፋ ይኾናል፡፡ አርዌ ምድር (እባብ) ሰው ነድፋ አዋቂ ደጋሚ ደግሞባት የተነደፈው እንዳይድን ድጋሙን ላለመስማት አንዱን ጆሮዋን ከምድር ታጣብቃለች፡፡ ቀሪውን በጅራቷ ትደፍናለች /መዝ. ፶፯፥፬-፭፣ አንድምታ ትርጓሜ/፡፡ ስብሐተ እግዚአብሔርን ላለመስማት ጆሮዋን እንደምትደፍን አርዌ ምድር የቤተ ክርስቲያንን የቀና ትምህርት እንዳይሰሙ ተሐድሶ መናፍቃን ጆሮአቸውን በምንፍቅና ትምህርት ደፍነዋል፡፡

ወደ ታሪኩ እንመለስና በዖዛ ስብራት ዳዊት ደነገጠ፤ ታቦተ እግዚአብሔርን ወደ መናገሻ ከተማው ይዞ ይሔድ ዘንድ ስለ ፈራ በአቢዳራ ቤት አኖሩአት፤ የአቢዳራም ቤት ተባረከ፡፡ አቢዳራ የወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ምሳሌ ነው፡፡ ታቦተ ጽዮንም የእመቤታችን ምሳሌ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ነያ እምከ፤ እነኋት እናትህ›› ብሎ እመቤታችንን አደራ ከሰጠው ጊዜ ጀምሮ እስከ ዕለተ ዕረፍቷ ድረስ ሲያገለግላት ኖሯል፡፡ ታቦተ ጽዮን የአቢዳራን ቤት እንደ ባረከች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም የዮሐንስን ቤት ባርካለች፡፡ ‹‹ሐዋርያው ለእጁ በትር ለእግሩ ጫማ የሌለው የቱን ሀብት ነው የባረከችው?›› የሚል ጥያቄ ከተነሣ በእርግጥ ቅዱስ ዮሐንስ የዚህ ዓለም ሀብት ንብረት የለውም፡፡ የጌታችንን መከራ መስቀል በማሰብ ቊፁረ ገጽ ኾኖ (ግንባሩን ቋጥሮ) በኀዘን እንደ ኖረ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ሀብት ሀብተ መንፈስ ቅዱስ የኾነው ወንጌልን ማስተማር፣ ነገረ እግዚአብሔርን ማመሥጠር፣ ድውይ መፈወስ፣ ወዘተ. ነው፡፡ ቅዱስ የሐንስ የጻፈው ወንጌል ከሦስቱ ወንጌላት ለየት ያለ ነው፡፡ ሦስቱ ወንጌላት የክርስቶስን የሰውነት ባሕርያት አጕልተው ሲያሳዩ የዮሐንስ ወንጌል ግን የመለኮትን ባሕርይ በጥልቀት ያስረዳል፡፡ በዚህም የተነሣ ወንጌላዊው ‹‹ዮሐንስ ታኦጐሎስ (ነባቤ መለኮት)›› የሚል ስም አግኝቷል፡፡ ስለ መለኮት አምልቶ አስፍቶ የጻፈ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስን በጸጋ እግዚአብሔር፣ በመንፈሳዊ ዕውቀት ያከበረው፣ የባረከው የእመቤታችን ወደ ቤቱ መግባት ነው፡፡

እመቤታችን በዓይኗ የምታየውን፣ ከመላእክት የተነገራትን በልቧ ጠብቃ ያኖረችውን የልጇን ባሕርየ መለኮት (አምላክነት) ለቅዱስ ዮሐንስ ነግራዋለች /አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ የመስቀል ጕዞ/፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ከጌታችን እግር ይቀመጥ ስለ ነበር በቅርብ ያየውን ነገረ እግዚአብሔር፣ ከእመቤታችን የተነገረውንም ምሥጢር በሰፊው ጽፏል፤ አስተምሯል፡፡ ከጊዜ እጥረትና ከአገልግሎት ብዛት የተነሣ ያልተጻፉ ምሥጢራትና ተአምራት እንዳሉም ‹‹ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ኾነ ታምኑ ዘንድ፣ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይኾንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፏል›› በማለት መስክሯል /ዮሐ. ፲፱፥፴-፴፩/፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ትውፊት የምትቀበልበት አንደኛው ማስረጃ ይህ ቃል ነው፡፡ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ መሠረት የኾነው ይህ ወንጌል ቅዱስ ዮሐንስ እመቤታችንን በመቀበሉ ያገኘው ሀብት ነው፡፡ አዕማድ የተባሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እነ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ቅዱስ ቄርሎስ፣ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ኤፍሬም ዘሶርያ፣ ያዕቆብ ዘሥሩግ፣ ባስልዮስ ጐርጐርዮስ (ነባቤ መለኮት)፣ ወዘተ. የድርሰታቸው፣ የትምህርታቸው መሠረት የዮሐንስ ወንጌል ነው፡፡ መናፍቃን የተረቱበት፣ አጋንንት የወደቁበት፣ ቤተ ክርስቲያን የጸናችበት ይህ ወንጌል ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በእመቤታችን ቃል ኪዳን የሚታመኑ ክርስቲያኖችን ይወክላል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ ብሎ በአማላጅቷ የሚተማመን፣ በቀናች ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የሚጸና ምእመን በወንጌል ትርጕም ግራ አይጋባም፡፡ ዮሐንስን የባረከች እመቤታችን ምሥጢሩን ትገልጽለታለችና፡፡ የወንጌሉ ትርጕምና ምሥጢር የተደፈነባቸው (የተሰወረባቸው) ተሐድሶ ነን ባዮች መናፍቃን በድንግዝግዝ ጨለማ እየተደናበሩ የሚገኙትና ስተው የሚያስቱት እመቤታችንን ባለመቀበላቸው ነው፡፡ እመቤታችንን በቤቱ ተቀብሎ ቅዱስ ዮሐንስ በብዙ ሀብታተ መንፈስ ቅዱስ እንደ ተባረከ ዛሬም እርሷን እናቴ፣ እመቤቴ ብሎ የሚቀበል በሥጋም በነፍስም ይባረካል፡፡ ምድራዊ ቤቱ በሀብት፤ የእግዚአብሔር መቅደስ የኾነው ሰውነቱም በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ይሞላል፡፡ የአቢዳራ ቤት በታቦተ ጽዮን እንደ ተባረከ በሰማ ጊዜ ቅዱስ ዳዊት መንፈሳዊ ቅናት ቀንቷል፡፡ ‹‹ቅንዑ ለእንተ ተዓቢ ጸጋ፤ ለምትበልጠው ጸጋ ቅኑ›› እንዲል፡፡ ቅዱስ ዳዊት በታቦተ እግዚአብሔር ፊት በእግሩ እያሸበሸበ፣ በጣቱ በገና እንደረደረ ሲያመሰግን በንቀት የተመለከተችው ሜልኮል ማኅፀኗ ደርቋል፡፡ ቅዱስ ዳዊት የትሑታን ካህናት፣ መዘምራን በአጠቃላይ የትሑታን ክርስቲያኖች ምሳሌ ሲኾን፣ ሜልኮል ደግሞ የመናፍቃንና የአፅራር ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡

ሜልኮል እስከ ዕለተ ሞቷ መካን ኾና እንደ ቀረች የእመቤታችንን ክብር የሚያቃልሉ መናፍቃንም የመንፈስ ቅዱስ ፍሬን ከማፍራት የመከኑ ናቸው /ገላ. ፭፥፳፪/፡፡ አንድም ሜልኮል ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ትዕቢተኞች ምሳሌ ናት፡፡ ጌታችን በምሳሌነት የጠቀሰው ፈሪሳዊ ራሱን ጸሎተኛ፣ ሃይማኖተኛ የሚያደርግና ሌላውን የሚንቅ ነበር፡፡ በዚህ ፈሪሳዊ የተናቀው ስለ ኃጢአቱ እያሰበ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ለማየት ያፍር፣ ይሸማቀቅ የነበረው ቀራጭ ድኅነት አግኝቶ ሲመለስ ፈሪሳዊው ግን በነበረው ኀጢአት ላይ የትዕቢት ኀጢአት ጨምሮ እንደ ተመለሰ በቅዱስ ወንጌል ተጽፏል /ሉቃ. ፲፰፥፲-፲፬/፡፡ ‹‹አመ ሜጠ እግዚአብሔር ፄዋ ጽዮን ወኮነ ፍሡሐነ፤ እግዚአብሔር የጽዮንን ምርኮ በመለሰ ጊዜ ደስተኞች ኾንን›› በማለት በደስታ የዘመሩት ቅዱስ ዳዊትና ቤተ እስራኤል በረከት እንዳገኙ ዅሉ እኛ ምእናንም ታቦተ እግዚአብሔር ከመንበረ ክብሩ ወጥቶ በሚከበርበት ዕለተ በዓል በተሰጠን ጸጋ ዘምረን (አመስግነን) በረከት እንድናገኝ እግዚአብሔር ትሑት ልቡና፣ ቅን ሕሊና ይስጠን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡-

ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ ከኅዳር ፩ – ፲፮ እና ከ፲፮ – ፴ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም፡፡