የጽዮን ምርኮ – ክፍል አራት

ኅዳር ፳፬ ቀን ፳፻፱ .

በመምህር ብዙነህ ሺበሺ

 ለታቦተ ጽዮን ካሣ እንደ ተሰጣት ….

 ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹አመ ሜጠ እግዚአብሔር ፄዋ ጽዮን ወኮነ ፍሡሓነ አሜሃ መልአ ፍሥሓ አፉነ ወተሐሥየ ልሳንነ፤ እግዚአብሔር የጽዮንን ምርኮ በመለሰ ጊዜ እጅግ ደስተኞች ኾንን፡፡ በዚያን ጊዜ አፋችን ደስታን አንደበታችንም ሐሤትን ሞላ፤›› /መዝ. ፻፳፭፥፩-፪/ በማለት እንደ ተናገረው በሰማይ በማኅበረ መላእክት፤ በምድር በደቂቀ አዳምና ከሲዖል በወጡ ነፍሳት ዘንድ ትልቅ ደስታ ኾነ፡፡ የጽዮን ምርኮ የተባሉት ለጊዜው ታቦተ ጽዮንን ጨምሮ የአይጥና የእባጭ ወርቆች ሲኾኑ ፍጻሜው ግን የሲዖል ነፍሳት ከዲያብሎስ ምርኮ መመለሳቸውን ያመለክታል፡፡ ታቦተ ጽዮን በምድረ ፍልስጥኤም የኖረችው ሰባት ወራት ነው፡፡ እመቤታችንም በግብጽ በስደት የኖረችው ሰባት መንፈቅ (ሦስት ዓመት ከስድስት ወር) ነው፡፡ ‹‹እስመ ኍልቊ ሳብዕ ፍጹም ውእቱ በኀበ ዕብራውያን፤ ሰባት ቍጥር በዕብራውያን ዘንድ ፍጹም ነውና›› እንዲል፡፡ ጽዮን ሰባት ወር በፍልስጥኤም ኖራ የወርቅ ካሣ ይዛ በድል እንደ ተመለሰች እመቤታችንም ለሰባት መንፈቅ በግብጽ ኖራ ሞተ ሄሮድስን በመልአክ ተበሥራ በደስታ ወደ አገሯ ገሊላ ናዝሬት ተመልሳለች፡፡

ታቦተ ጽዮን ከፍልስጥኤም በሁለት ላሞች በሚጐተት ሠረገላ ተጭና ስትመጣ ሳይገባቸው ሳጥኑን ከፍተው በማየታቸው ከ፭፻ ቤትሳምሳውያን መካከለል ፸ ሰዎች ተቀሥፈዋል፡፡ ዛሬም ቤተ ክርስቲያንን የሚዳፈሩ በደዌ ሥጋ እየተመቱ በነፍሳቸውም ከእግዚአብሔር ጸጋ ምሕረት የራቁ ብዙዎች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ያከበራትን ታቦት በመደፋፈራቸው በሞት እንደ ተቀጡ ቤትሳምሳውያን ዛሬም እግዚአብሔር ባከበራቸው ቅዱሳን ይልቁንም መልዕልተ ፍጡራን መትሕተ ፈጣሪ በኾነችው በእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ላይ የድፍረት ቃል የሚሰነዝሩና ጣታቸውን የሚቀስሩ ተሐድሶአውያን መናፍቃንና ተላላኪዎቻቸው ከእግዚአብሔር ምሕረት፣ ቸርነት፤ ከቅዱሳኑም በረከት ርቀው መርገመ ጌባል እየተጐነጩ ይገኛሉ፡፡ በሥጋ ይንቀሳቀሱ እንጂ በነፍሳቸው ሙታን ናቸው ‹‹ሞታ ለነፍስ ርኂቅ እምእግዚአብሔር፤ የነፍስ ሞቷ ከእግዚአብሔር መራቅ ነው›› ተብሎ ተጽፏልና፡፡

ወደ ታቦተ ጸዮን በመመልከታቸው ቤትሳምሳውያን ከተቀሠፉ አማናዊት ጽዮን በኾነችው በእመቤታችን ላይ እባብ ምላሳቸውን የሚያውለበልቡ መናፍቃንማ ዕድል ፈንታቸው ጽዋ ተርታቸው እንዴት የከፋ ይኾን! የአሚናዳብ ልጅ አልዓዛር ታቦተ ጽዮንን እንዲያገለግል እንደ ቀደሰ (እንደ ተመረጠ) በሐዲስ ኪዳንም ቤተ መቅደሱን የሚያገለገሉ በአንብሮተ እድ የተሾሙ ካህናት ናቸው እንጂ ማንም ወደ ታቦተ እግዚአብሔር መቅረብ አይችልም፡፡ ታቦት ወጥቶ በክብረ በዓል ጽላተ ኪዳን ወደ ተሸከሙ ቀሳውስት የሚጠጉ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ አስተባባሪዎች እንዲርቁ ቢነግሩአቸውም አይሰሙም፤ እነዚህ ሰዎች ከቤትሳምሳውያን ቅሥፈት መማር አለባቸው እንላለን፡፡ የሚገባውን ክብር በፍርሃትና በፍቅር ካደረግን እግዚአብሔር ደግሞ ያከብረናል፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው የምንጓዝ ከኾነ በበረከት ፋንታ መርገምን፣ በሕይወት ፋንታ መቅሠፍትን ሊያደርስብን ይችላልና እንጠንቀቅ፡፡

ታቦተ ጽዮን ከቤተ አሚናዳብ እስከ ዳዊት ከተማ /፩ኛ ሳሙ. ፯፥፩-፪፣ ፪ኛ ሳሙ. ፮፥፩-፳፫/

ታቦተ ጽዮን በኮረብታማው አገር በአሚናዳብ ቤት ለሃያ ዓመት ኖራለች፡፡ ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጣ ዘንድ ሠላሳ ሺሕ ሠራዊት ይዞ ወደ አሚናዳብ ቤት ወጣ፡፡ የአሚናዳብ ልጆች አሕዮና ዖዛ ታቦቱን በአዲስ ሠረገላ ጭነው ሲሔዱም ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ዅሉ በቅኔና በበገና፣ በመሰንቆም፣ በከበሮም፣ በነጋሪትና በጸናጽል በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኀይላቸው ይዘምሩና ያሸበሽቡ ነበር፡፡ ሠረገላውን የሚጐትቱ በሬዎች ይፋንኑ (ይቦርቁ) ነበርና ዖዛ እጁን ዘርግቶ የእግዚአብሔርን ታቦት ያዘ፡፡ ስለ ድፍረቱም እግዚአብሔር በዚያው ቀሠፈው፡፡ ያ ቦታም እግዚአብሔር ዖዛን ሰብሮታልና ‹‹የዖዛ ስብራት›› ተባለ፡፡ ዳዊትም በኪሩቤል ላይ በተቀመጠ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም የሚጠራውን ታቦት ወደ ከተማው ይወስድ ዘንድ ስለ ፈራ በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት አስቀመጠው፡፡

ታቦተ እግዚአብሔር በቤተ አቢዳራ ለሦስት ወራት ተቀመጠች፤ የአቢዳራም ቤት ተባረከ፡፡ ዳዊትም የአቢዳራ ቤት እንደ ተባረከ በሰማ ጊዜ ታቦተ እግዚአብሔርን ወደ ከተማው ያመጣ ዘንድ ብዙ ሠራዊትና ሌዋውያን ካህናትን አስከትሎ ወደ አቢዳራ ቤት ሔደ፡፡ ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ዅሉ ታቦቱን ይዘው ሲመለሱ ስድስት ርምጃ በሔዱ ጊዜ አንድ በሬና ፍሪዳ ይሠዉ፤ ቀንደ መለከትም ይነፉ ነበር፡፡ ዳዊት የበፍታ ኤፉድ ለብሶ ‹‹አመ ሜጠ እግዚአብሔር ጼዋ ጽዮን ወኮነ ፍሡሓነ አሜሃ መልአ ፍሥሓ አፉነ ወተሐሥየ ልሳንነ፡፡ እግዚአብሔር የጽዮንን ምርኮ በመለሰ ጊዜ ደስተኞች ኾንን፡፡ በዚያን ጊዜ አፋችን ደስታን፣ አንደበታችንም ሐሤትን ሞላ፤›› በማለት በታቦተ ጽዮን ፊት በጣቱ በገና እየደረደረ፣ በእግሩ እያሸበሸበ ሲዘምር አይታ ሚስቱ የሳዖል ልጅ ሜልኮል በልቧ ናቀችው፤ አቃለለችው፡፡ በዚህ ምክንያትም ማኅፀኗ ስለ ደረቀ ሜልኮል መካን እንደ ኾነች ሳትወልድ ሞተች፡፡ በዚህ ረጅም ታሪክ ውስጥ የሚገኘውን ተግሣፅ፣ ትምህርትና ምሳሌ ከዚህ ቀጥለን እንመለከታለን፡፡

ታቦተ ጽዮን በኮረብታማው አገር በቤተ አሚናዳብ እንደ ኖረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በተራራማው አገር በቤተ ዘካርያስ ቤት ሦስት ወራት ተቀምጣለች /ሉቃ. ፩፥፴፱፣፶፮/፡፡ ሁለቱ በሬዎች ታቦተ ጽዮን የተቀመጠችበትን ሠረገላ ሲጐትቱ የፋነኑበት (የቦረቁበት) ምክንያት ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹በሬ የገዢውን፣ አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ፤›› /ኢሳ. ፩፥፫/ እንዳለው የእግዚአብሔር የኪዳኑን ታቦት እንደ ተሸከሙ ስላወቁ ደስታቸውን ለመግለጥ ነው፡፡ ጌታችን በቤተልሔም በከብቶች በረት በተወለደ ጊዜ እስትንፋሳቸውን የገበሩለት አምላክነቱን አውቀው ነበር፡፡ ሁለቱ በሬዎች ታቦተ ጽዮንን ተሸክመው ከቤተ አሚናዳብ ወደ ቤተ አቢዳራ እንደ ተጓዙ ዮሴፍና ሰሎሜም የእመቤታችን የስደቷ ተካፋይ ኾነዋል፡፡ ሁለቱ በሬዎች በደስታ እየቦረቁ ሠረገላውን እንደ ጐተቱ ዮሴፍና ሰሎሜም የእመቤታችን የስደቷ አጋር ኾነው ሲሔዱ ሳይጕረመርሙና የስደቱን መከራ ሳይሳቀቁ በፍቅር ኾነው  እመቤታችንን አገልግለዋል፡፡

ዖዛ ታቦተ ጽዮንን በመንካቱ የእግዚአብሔር ጣ በእርሱ ላይ ነደደ፤ ተቀሠፈም፡፡ ዖዛ የእመቤታችን አስከሬን የተቀመጠበትን የአልጋ ሸንኮር በመያዝ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እጁን በሰይፍ የቀጣው የታውፋንያ ምሳሌ ነው፡፡ አንድም ዖዛ የዮሳ ምሳሌ ነው፡፡ ዖዛ የእግዚአብሔርን ታቦት በመያዙ ተሰብሯል (ተቀሥፏል)፤ ዮሳም እመቤታችንን በማስደንገጡ ድንጋይ ተንተርሶ ቀርቷል (ተቀሥፏል)፡፡ ታሪኩም እንዲህ ነው፤ እመቤታችን ከሄሮድስ ሠራዊት ሸሽታ ዮሴፍን፣ ሰሎሜን እና ዮሳ ወልደ ዮሴፍን አስከትላ የስደት ጕዞዋን ጀመረች፡፡ መሽቶባቸው ከሶርያው ገዥ ከጊጋር ቤት አደሩ፤ በዚያም ዮሳ ታሞ ቀረ፡፡ ‹‹ዘመዶቼ ምን ደርሶባቸው ይኾን?›› ብሎ ወደ መንገድ ቢወጣ ሰይጣን በሰው አምሳል ተገልጦ ‹‹የሄሮድስ ሠራዊት ቀድመው ሔደዋል›› አለው፡፡ ዮሳም በፍጥነት መንገዱን ይዞ በፍጥነት ተከተላቸው፡፡ ደክሟቸው በአንድ ዛፍ ጥላ ሥር አርፈው ባገኛቸው ጊዜ ‹‹እናንተ በሰላም ተቀምጣችኋል፤ ሕፃን በጀርባዋ ያዘለች፣ በክንዷ የታቀፈች ሴት በኢየሩሳሌም አትገኝም፡፡ ሄሮድስ ሕፃናትን አስፈጅቷል፡፡ አሁንም ወደ እናነተ ሠራዊቱን ልኳል›› በማለት እመቤታችንን አስደነገጣት፡፡ ጌታችንም ‹‹ዮሳ አመጣጥህ መልካም ነበር፤ እናቴን አስደንግጠሃታልና በዳግም ምጽአት አስነሥቼ ዋጋህን እስከምሰጥህ ድረስ ይህችን ድንጋይ ተንተርሰህ ተኛ›› ብሎት በዚያው አሳርፎታል፡፡

የዖዛና የዮሳ ታሪክ ተመሳሳይ ነው፡፡ ዖዛ የተቀሠፈው በሬዎቹ ስለሚቦርቁ ታቦተ ጽዮን ከሠረገላው እንዳትወድቅ ለመደገፍ በማሰቡ ነበር፡፡ ዮሳም መልካም ዜና ያመጣ መስሎት ነው እመቤታችንን ያስደነገጣት፡፡ ‹‹ዮሳ ወልደ ዮሴፍ ምንተ ገብረ ኃጢአተ ዘያደነግፀኪ ዜና በይነ ዘአምጽአ ግብተ፤ የዮሴፍ ልጅ ዮሳ ምን በደል ሠራ የሚያስደነግጥሽ ዜናን በድንገት በማምጣቱ እንጂ›› እንዳለ ደራሲ፡፡ ስለዚህ ‹‹መክፈልት ሲሹ መቅሠፍት›› እንዲሉ መልካም ያደረግን እየመሰለን ስሕተት ልንሠራ ስለምንችል የምንሠራውን ሥራ ቆም ብለን ልንመረምር ይገባናል፡፡ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መልካም የሠሩ እየመሰላቸው የእግዚአብሔርን ሕግ ስለሚጥሱ አይሁድ ‹‹ይመስሎ ከመ ዘመሥዋዕተ ያበውእ ለእግዚአብሔር፤ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት የሚያቀርብ ይመስለዋል›› በማለት ተናግሯል /ዮሐ. ፲፮፥፪/፡፡

ይቆየን