የትንሣኤው ብሥራት

በመ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስ አሳሳችነት አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ሕግ በመተላላፋቸው ሞተ ሥጋና ሞተ ነፍስ ተፈርዶባቸው ነበር፡፡ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ካለው ፍጹም ፍቅር የተነሣ የተፈረደባቸውን ሞት በሞቱ ሊደመስስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ (ዮሐ. ፩፥፩)፡፡ ሠላሳ ዓመት ሲሞላው በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡ እንደ ተጠመቀም ልዋል ልደር ሳይል ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሔደ፡፡ በዚያም ጾመ፤ ጸለየ፡፡ በዲያቢሎስም ተፈተነ፡፡

ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ካስተማረ በኋላ የአዳምና የሔዋንን ዕዳ ደምስሶ ነጻ ሊያደርጋቸው በገባው ቃል ኪዳን መሠረት መከራ ተቀበለ፡፡ በአይሁድ ሸንጎ ፊት ቆመ፤ ምራቅ ተተፋበት፤ ተገረፈ፤ በገመድ ታሥሮ ተጎተተ፤ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞተ፡፡ በሞቱ ሞትን ድል አድርጎ የአዳምን፣ የሔዋንንና የልጆቻቸውን ዕዳ በደል ደመሰሰ (ማቴ. ፳፯፥፳፰)፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ “ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤” በማለት እንደ ገለጸው (ሮሜ. ፮፥፭)፣ ሞቱ ሞታችን፤ ትንሣኤው ትንሣኤያችን ነውና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች በየዓመቱ ጌታ የጾመውን ጾም በመጾም፣ በሰሙነ ሕማማት ደግሞ መከራውንና ስቃዩን በማሰብ የክርስቶስን ቤዛነት እንዘክራለን፤ የነጻነትና የድል በዓላችንንም እናከብራለን፡፡

“በጥንተ ጠላታችን ምክንያት አይሁድ ክብርህን ዝቅ ቢያደርጉ፣ ቢያዋርዱህ፣ ቢገርፉህ፣ ርቃንህን ቢሰቅሉህና ቢገድለህ እኛ ግን ‹ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለም ዓለም አማኑኤል አምላኪየ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለም ዓለም ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለም ዓለም – ኃይሌ፣ መከታዬና ረዳቴ ለኾንኸው ለአንተ ለአምላኬ ለአማኑኤል ለጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ምስጋና ጽናትም ለዘለዓለሙ ይገባሃል›፤” እያልን አምላካችንን እናመሰግነዋለን፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ፫፥፲ ላይ “እርሱንና የትነሣኤውን ኃይል እንዳውቅ በመከራወም እንድካፈል ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢኾንልኝ በሞቱ እንደመስለው እመኛለሁ፤” በማለት እንደ ተናገረው ምእመናን እንደ አቅማቸው እያዘኑ፣ እያለቀሱ፣ ከምግብ እየተከለከሉ፣ ጸጉራቸውን እየተላጩ የአምላካንን መከራ ያስባሉ፡፡

“ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቷል!” የሚለውን የምሥራች ከቤተ ክርስቲያን ለመስማት በናፍቆት ይጠባበቃሉ፡፡ የትንሣኤውን ብሥራት ሰከሙ በኋላም “ጌታ በእውነት ተነሥቷል!” እያሉ ትንሣኤዉን ይመሰክራሉ፡፡ የጌታችን ትንሣኤ፣ የድኅነታችን ብሥራት በመኾኑ ለአምሳ ቀናት ያህል በቅዳሴው፣ በማኅሌቱ፣ በወንጌሉ፣ በሌሎችም ቅዱሳት መጻሕፍት በልዩ ሥርዓት ይዘከራል፡፡ በየአብያተ ክርስቲያኑ “ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን በዓቢይ ኃይል ወሥልጣን አሠሮ ለሰይጣን አግዐዞ ለአዳም ሰላም እምይእዜሰ ኮነ ፍሥሐ ወሰላም” እየተባለ ሞት መደምሰሱ፣ ነጻነት መታወጁ ይበሠራል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡