የተዘጉ በሮች ይከፈቱ

ብዙዎቻችን ከእኛ ውጭ ስላሉ አካላት ሲነገረን ለማድመጥ የምንፈልገው የሆኑትንና እውነታውን ሳይሆን እኛ ሊሆኑት የምንፈልገውን ነው፡፡ ስለዚህም ስለምንነቅፋቸው አካላት የሚከሰሱበትንና የሚጐነተሉበትን እንጂ እውነታውን መስማት አሁን አሁን የኮሶ ያህል የሚሰቀጥጥ፣ የሞትም ያህል የሚያስደነግጥ ሆኖአል፡፡ እንዲህ ያሉት ነገሮች የሚከሰቱት ደግሞ በሁሉም ማኅበረሰብ መሆኑ ነገሩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡
ፖለቲከኞች፣ የማኅበረሰብ መሪዎች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት ሰባክያንና መዘምራን፣ … እንዲሁም ሌሎችም ከዚህ ወጥመድ ሊያመልጡ አልቻሉም፡፡ ለምሳሌ ያህል የእስልምና መምህራኑ ስለ ክርስትና የሚሰሙት ክርስቲያኖች የሚሉትን ሳይሆን የአሉባልታ ዶክመንቶች የሚሉትን መሆኑ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የሃይማኖት ልዩነት በሌለበት እንኳ አንዱ ስለሌላው የሚናገረውና ሊሰማ የሚፈልገው አሁን አሁን አስፈሪነት እየታየበት ነው፡፡
 
ችግሩ የሐሳብ፣ የአመለካከት፣ የሃይማኖት፣ የርእዮተ ዓለም ልዩነት መኖሩ አይደለም፡፡ አንዱ የሌላውን በትክክል ተረድቶ ተጠየቃዊ በሆነ መንገድ የሐሳብ ክርክር መኖሩም ችግር ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲያውም ጤናማ በሆነ አመለካከትና መረጃዎችን በመተንተን ላይ የተመሠረተ ከሆነ ልዩነትን አንጥሮ ለማወቅ ብቻ ሳይሆን በሐሳብ ለመሳሳብና ለመቀራረብም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ በሃይማኖትም ቢሆን አንዱ ሌላውን ሳይሰድብ የሚያምነውን በትክክል ተረድቶ ያንን እምነት እንዴት ስሕተት እንደሆነ ማሳየትም የሚጠበቅና ጤናማ ጠባይ ነው፡፡ ችግሩ ግን ሁሉም ስለሌላው የሚናገረው እምነቱን የሚመራበትን መጽሐፍ ለራሱ አሳብ አስረጂ አድርጎ በማቅረብ ብቻ ነው፡፡ ሊሆን የሚገባው ግን መጽሐፉ የሚያስተላልፈውን ትርጉም በአማኞቹ ዘንድ ያለውንም በመረዳት ጭምር ቢሆን ነበር፡፡
 
ከዚህም አልፎ በአንድ ተቋም ሥር ያሉ አስፈጻሚዎች እርስ በርሳቸው በተለያዩ የሐሳብ ማዕዘናት ላይ ተቀምጠዋል፡፡ አንዱ ሌላውን በጐሪጥ ከማየት አልፎ ለሚሠራው ሥራ ሁሉ የሚሰጠው ትንታኔ አንድን ዘውግ መሠረት ያደረገ ይሆናል፡፡ ሌላው ደግሞ ያን ሸሽቼ አመልጠዋለሁ በማለት ሌላ ጽንፍ ውስጥይወድቃል፡፡ … መንገዱ ሁሉ የዳጥና የመሰናክል፤ የተዛባ ትርጓሜና ጽንፈ ኝነትና ጎጠኝነት የበረዙት ሆኖአል፡፡
 
እነዚህን ችግሮች የማይቀበልም ያለ አይመልስም፡፡ ፖለቲከኞችም፣ የሃይማኖት ሰዎችም፤ ሌሎች ማኅበራትና ተቋማትም ችግሮቻችን ከእነዚህ የሚመነጩ እንደሆኑ ይስማማሉ፡፡ ሁሉም በሁሉም ላይ ሐሳብ ይሰጣል፡፡ ሌሎችን ችግሩ ውስጥ አሉ ይላል፤ ራሱ ግን ነጻ ነው፡፡ ሌሎች ከችግራቸው እንዲወጡ ሐሳብ ያቀርባል፤ ርእዮቱን፣ ትንታኔውንም ያቀርባል፤ ከዚህም አልፎ ስለሀገሩም ሆነ ስለሌላው ሐሳብ ሲሰጥ በሐዘንና በቁጭት ነው፡፡ እጅግ የሚያዝነውም ሌሎቹ የእርሱን ሐሳብ ለመስማት ባለመዘጋጀታቸው ነው፡፡ እርሱ ራሱም ግን በሌሎቹ እንዲህ እንደ ሚታዘንበት ትንሽ እንኳ ግምትና ጥርጣሬ የለውም፡፡ ሌሎች እርሱን በተሳሳተ መንገድ እንደሚረዱትና የትንታኔያቸውም ስሕተት ከዚህ እንደሚመነጭ ይጠቅሳል፡፡ የእርሱ ትንታኔ እንደዚህ ዓይነት ችግር ሊኖርበት እንደሚችል ግን አይገምትም፤ ቢነገሩትም አይሰማም፤ ቢሰማም አያዳምጥም፤ ቢያዳምጥም አይቀበልም፡፡ በሐሳብና በአመለካከት ወጪ እንጂ ገቢ የለውም፡፡
 
የዚህ ሁሉ ችግሩ ምንድን ነው? መደማመጥስ እንዴት ጠፋ? መመለሻውስ ምን ይሆን) … ብዙ ጥያቄዎችን እንድናነሣ እንገደዳለን፡፡ ችግሩ አንድና አንድ ነው፡፡ በየሰው ልቡና የተዘጉ በሮች አሉ፡፡ እነዚያ መከፈት ይገባቸዋል፡፡ ካለበለዚያ ደረቅ ጩኸትና ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡
 
አይሁድ ጌታን /የስም አጠራሩ ከፍ ከፍ ይበልና/ አንዴ የዮሴፍ ልጅ ነው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጋኔን ያደረበት ነው፤ ሌላ ጊዜ በዓል ይሽራል፤ … እያሉ በእርሱ አምነው ከመጠቀም የተከለ ከሉት ሊሰሙት የሚፈልጉት ይህንኑ ብቻ በመሆኑና እውነቱን ለማድመጥ ደግሞ የልባቸው በር ስለተዘጋ ነበር፡፡ መዘጋቱን የማይቀበሉት ደግሞ ለእግዚአብሔራቸው የበለጠ የቀኑ ስለሚመስላቸው ነበር፡፡ ይህን በመንፈስ ቅዱስ የተመለከተው ቅዱስ ዳዊት «መኳንንት ደጆቻችሁን ክፈቱ፣ የክብር ንጉሥ ይግባ» ሲል ተናግሮአል፡፡ መዝ.23-2  በርግጥም የብዙዎቻችን ችግር ይህ ነው፡፡ እንደተጻፈውም እውነት የሆነው ጌታ ብቻ ነው፡፡ ያለ እውነት እርሱን ልናገኝም፤ ያለእርሱም እውነተኞች ልንሆን አንችልም፡፡ እርሱን ለመቀበል፤ እውነቱንም ለመረዳት ግን የልቡናችን በር ተዘግቷል፤ ተቆልፎአልም፡፡
 
ጌታ ለዮሐንስ ወንጌላዊ እንደገለጸው «በደጅህ ቁሜ አንኳኳለሁ፤ ለሚከፍትልኝ ሁሉ ወደ እርሱ እገባለሁ …» ብሎናል፡፡ ራዕ3-20 በርግጥም አሁን እግዚአብሔር የትው ልዱን የተቆለፈ ደጅ እየመታ ነው፡፡ መገናኛ ብዙኅኑም፣ ቃለ እግዚአብሔርም፣ ሌላውም ሁሉ ሳያውቁትም ቢሆን እንደነ ሊቀ ካህናት ሀናና ቀያፋ እውነቱን የሚናገሩበት አጋጣሚ አልጠፋም፡፡ ነገር ግን ስለመቻቻል የሚሰብኩት ሲችሉ አይታዩም፤ ስለ እውነት የሚሰብኩትም እውነት መናገር ተስኖአቸዋል፡፡ ስለ ፍቅር የሚነግሩን በጥላቻ ሰክረዋል፤ ስለነጻነት የሚተርኩልንም በቂም አርግዘዋል፤ አፋቸው ተከፈተ እንጂ የልቡናቸው በር አሁንም እንደተዘጋ ነውና፡፡
 
ስለዚህ መፍትሔው የልቡናችን በር መክፈት ነው፡፡ በዘረኝነት፣ በጎሰኝነት፣ በዘውገኝነት፣ በጽንፈኝነት፣ በጥላቻና በመሳሰሉት የተዘጉት ሁሉ መከፈት አለባቸው፡፡ ይምረረንም፣ ይጣፍጠንም፣ እስኪ ልቡናችንን ከፍተን አእምሮአችንን ከጥመት፣ ከፍርሃትና ከጥርጣሬ አጽድተን እናዳምጥ፡፡ በርግጥስ እውነታው የቱ ነው) በትዕግሥትና በበጎ ኅሊና ካደመጥን ሌሎቹ እንኳ ተሳስተው ከሆነ ቢያንስ ስሕተታቸውን በትክክል ለመረዳት ያስችለናል፡፡ ይህ ደግሞ ስሕተታቸው የምንለውን ገልጦ ለማስረዳትና በሐሳብ ለመሳሳብ ወደ አንድነትም ለመምጣት ይረዳናል፡፡ ያ እንኳ ባይሆን ባልሆኑት እንዳንነቀፍ ለመጠበቅ ያስችለናል፡፡

በሀገር ላይ ለውጥ ይምጣ፣ መነቃቀፎችና መጠላላቶችም ባሉበት ይቁሙ የምንል ከሆነ የተዘጋ ልቡናችን መከፈት ይኖርበታል፡፡ በጊዜው ያልተከፈተ የተዘጋ ደጅ ደግሞ በኋላ ቢከፈት እንኳ እውነቱን ለመረዳት ያስቸግረናል፡፡ በመኃልየ መኃልይ ላይ እንደተገለጸው «እግሬን ታጥቤያለሁ እንዴት አቆሽሸዋለሁ? ልብሴን አውልቄያለሁ እንዴት እለብሰዋለሁ? ተኝቻለሁ እንዴት እነሣለሁ?…» እያልን ምክንያቶችን በመደርደር ደጃችንን ካልከፈትን የእውነት ጌታ ከእኛ ይሔዳል፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ «ብንፈልገውም አናገኘውም»፡፡ መኃ.5-2-7 ከዚህም አልፎ የከተማው ጠባቂዎች የተባሉት ክፉዎች መናፍስት አግኝተው ይቀጠቅጡናል፡፡ ስለዚህም ወደባሰ የኅሊና ጉዳትና ቁስል እንሸጋገራለን፡፡ ያን ጊዜ «… ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው» የተባለው ይፈጸምብናል፡፡ ሮሜ1-28 ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ጆሮአችን ይስማ፤ አእምሮአችን ያድምጥ፤ ልቡናችንም ያስተውል፤ ያን ጊዜ የተዘጋው በር ይከፈታል፤ የቆመውም ጌታ ወደ ልቡናችን ይገባና እንፈወሳለን፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በተለያየ የፍልስፍና ቁልፎች የዘጋነውን የልባችን ደጆች እንክፈት፡፡ አርኅው ልኀተ መኳንንት ይባዕ ንጉሠ ስብሐት፤ መኳንንት ደጆቻችሁን ክፈቱ፤ የክብር ንጉሥ ይግባ፡፡ መዝ.23-7፡፡