ብፁዓን ገባርያነ ሰላም

ጥር 3 ቀን 2005 ዓ.ም.


በፍጡርና በፈጣሪ፤ በፍጡርና በፍጡር መካከል ችግሮችና አለመግባባቶች መፈጠራቸው የዚህ ዓለም ባሕርያዊ ግብር ነው፡፡ በተለይም የሰው ልጅ አለመግባባቶችን ዕለታዊ ባሕርዩ ወደ ማድረግ የደረሰም ይመስላል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም የእነዚህን ችግሮች ክሡትነት መጠቆማቸውም የሚሰወር አይደለም፡፡

 

አስቀድመን እንደገለጽነው ሰው በሰብአዊነቱ ከራሱ ጋር፣ ከፈጣሪው ጋርና ከሌሎቹም ሥነ ፍጥረታት ጋር የሚያጋጩት ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከዚህም የተነሣ “ለምን ግጭት ተከሠተ” ብሎ መሞገት ጊዜ መጨረስ ሲሆን “ለምን አልታረቅሁም” ብሎ ራስን መጠየቅ ግን አግባብ ነው፡፡ ምክንያቱም የዕርቀ ሰላም መንገዶች እንደ ግጭቱ መንገድ የተንዛዙ ሳይሆኑ የተቆጠሩና የተሰፈሩ የተለኩ ሃይማኖታዊ እሴቶች ናቸውና፡፡

እነዚህ የተለኩ እሴታዊ የዕርቀ ሰላም መንገዶች ከየትኛውም አቅጣጫ ሊጀምሩ ይችላሉ፡፡ ምንም እንኳን ይቅርታ መጠየቅ ከአዳም ቢጀመርም የዕርቁ ሂደት የተጀመረው ግን ከእግዚአብሔር ነው፡፡ በፈራጅነቱ የሚታወቀው እግዚአብሔር በቸርነቱ፣ በከሃሊነቱና በምሕረቱ ሰውን ሊታረቅ ፈቃዱ ሆኗልና፡፡

 

በዚህ መልኩ የሚመሩ የዕርቀ ሰላም ጉዞዎች ሁለት ነገር ያስፈልጋቸዋል እንላለን፡፡ የመጀመሪያው ሁሉንም ነገር ስለ እግዚአብሔር ብሎ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታና ስሌት ወይም ድርድር ይቅር ማለት ነው፡፡ “ይቅር ለእግዚአብሔር” የሚለው ኀይለ ቃል ዐረፍተ ነገሩ እንደማጠሩ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ውሳኔን የሚጠይቅ የታላላቅ ሰዎች መገለጫም ነው፡፡

 

እንደሰማይ ከዋክብት እንደ ምድር አሸዋዎች የበዙ የግጭት ምክንያቶችን ሁሉ ስለ እግዚአብሔር ወይም ስለ ማምነው ፈጣሪ ስል ትቼዋለሁ ብሎ ወደ ዕርቀ ሰላም ዐደባባይ መዝለቅ የመንፈሳውያን ሰዎች ቁርጠኛ ውሳኔ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

 

ሁለተኛው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት፣ ለምንኖርባት ምድር በጎነት፣ ለምእመን ፍቅር ስንል “ይቅር ለእግዚአብሔር” ማለት በእጅጉ ይገባናል፡፡ ይህን ማድረግ በራሱ የቸር እረኛነት ማሳያ መነጽር ነው፡፡ ይህን ስንል በግጭትና በጭቅጭቅ ከሚገኝ ትርፍ ይልቅ በይቅርታና በሰላም የሚያጋጥም ኪሣራ/ ካለም/ የበለጠ ትርፋማ መሆኑን ስለምናምን የበለጠም መንፈሳዊ ፍሬ እንደሚገኝ ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡

 

እንደነዚህ ዓይነቶችን የዕርቀ ሰላም ማውረጃ መንፈሳዊ እሴቶች ወደ ጎን በመግፋታችን አንዲቷ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከተፈጥሮአዊ ባሕርይዋ ውጭ ተከፈለች መባሉ በራሱ አንገት አስደፊ መርዶ ነው፡፡

 

ከዚህ አኳያ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በብዙ ምክንያቶች ላለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት በአንድነቷ፣ በአገልግሎቷ፣ በሥርዐቷና በቀኖናዋ ላይ ጥቂት የማይባሉ ችግሮቹ በዚሁ እንዲቀጥሉ ከፈቀድንላቸው አሁን ከምንገኝበት የበለጠና የከፋ ችግር ተሸክመው ሊመጡ እንደሚችሉ መገመቱን ቀላል ያደርገዋል፡፡

 

በተለይም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን “ስደተኛ ሲኖዶስ” እና “የአገር ቤቱ ሲኖዶስ” በማለት የነገር ብልት ለሚያወጡ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ጀርባዋን ለግርፋት አመቻችታ እንድትሰጥ ማድረግ ነውና ዕርቀ ሰላሙን ማስቀደም የሁላችንም ተግባር ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ መሆኑ ደግሞ በመንፈሳዊነትና በአሳታፊነት እናከናውነዋለን ለምንለው የፓትርያርክ ምርጫውም ሆነ ለተቋማዊ ለውጥ የተመቻቸና የተሻለ መንገድ እንደሚሆን እናምናለን፡፡

 

በይበልጥ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ብፁዓን አበው የአንድነቱን ሁለንተናዊ ጥቅም በመመልከትና የዕርቀ ሰላሙ ድርድር ውጤት አልባነት ክትያዎች በምእመኑ መካከል የሚያስከትሉትን ጉዳቶች በማስተዋል ለዕርቀ ሰላሙ ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል፡፡

 

አንድ ቦታ ላይ አቁመን የትናንቱን የውዝግብ አጀንዳ እንዝጋው፡፡ መቃቃርና መገፋፋት በተጠናወተው መንፈስ ስለትናንት ጥፋት ብቻ መነጋገር አቁመን ስለ ነገም የቤተ ክርስቲያን ዕድገት እንምከር፡፡ ትናንት በታሪክ አጋጣሚ ብንቀያየምም ዛሬ ግን በዕርቀ ሰላም በአንድነት መጓዝ እንችላለን፡፡ ይህም ሊሆን የሚችለው ነገ ዛሬ ሳንል በጨዋነትና በግልጽ ተወያይተን፣ ችግሮቻችንን ለይተን ስለ ሰላም ይቅር ስንባባል ብቻ መሆኑን ከአባቶቻችን ይሰወራል ብለን አናምንም፡፡

 

ከይቅርታና ከይቅር ባይነት የበለጠ ነገር በቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ስለሌሉና ስለማይኖሩ ለዕርቀ ሰላሙ ድርድር ውጤታማነት ትኩረት ሰጥተው ቢሠሩበት እንላለን፡፡

 

ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምእመናንም እስከአሁን እየተከናወነ ያለውን በጎ ተግባር በመደገፍ ለወደፊቱም ለቤተ ክርስቲያናችንና ለምእመናን አንድነትና ሰላም በጸሎት መበርታት ይገባናል፡፡ የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ድርድር ከውጤት እንዲደርስ የድርሻቸውን እያበረከቱ የሚገኙ በሁለቱም በኩል ያሉትን ተደራዳሪ አባቶች፣ አደራዳሪ ሽማግሌዎችና የተለያዩ ግለሰቦችን በምንችለው ሁሉ ልንደግፋቸው ይገባል፡፡

 

በወንጌል እንደተጻፈው ሰላምን የሚያደርጉ ብፁዓን፣ ንዑዳን ናቸው መባሉ ሁላችንንም የሚመለከት የበጎ ተግባር ምስክርነት ስለሆነ ለዕርቀ ሰላሙ ድርድር ውጤታማነት የድርሻችንን ልንወጣ ያስፈልሪጋል እንላለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  • ምንጭ፡- ጽምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 20ኛ ዓመት ቁ.8 2005 ዓ.ም.