merecha

የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ውሎ

የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

merecha

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስድስተኛውን ፓትርያርክ ለመምረጥ በዛሬው ዕለት ከሌሊቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ መራጮች የምርጫ ካርዳቸውን ይዘው በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በመግባት ተጀመረ፡፡ ወደ አዳራሹ ሲገባ ከመድረኩ በስተግራና ቀኝ በምድብ ሀ እና ምድብ ለ በኩል የመራጮችን ዝርዝር የሚመዘግቡ አገልጋዮች መዝገቦቻቸውን ይዘው የተዘጋጀላቸውን ሥፍራ ይዘዋል፡፡ አጠገባቸው መራጮች  የመራጭነት ካርዳቸውን ሲመልሱ የሚያኖሩባቸው ሁለት የታሸጉ ሳጥኖች ይታያሉ፡፡  በተወሰኑ ሜትሮች ርቀት ደግሞ መራጮች በምስጢር ድምፅ የሚሰጡበት የተከለለ ስፍራ ይገኛሉ፡፡ መራጮችም ቀስ በቀስ በመግባት በተዘጋጀላቸው ስፍራ ላይ ዐረፍ ብለዋል፡፡ የምርጫው ታዛቢዎች፤ ምርጫውን የሚያስፈጽሙ አገልጋዮች በተመደቡቡት የሥራ ድርሻ ሁሉም ዝግጅታቸውን አጠናቀው የምርጫውን መጀመር በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ አስመራጭ ኮሚቴውም ያዘጋጀውን ስለ አምስቱ እጩ ፓትርያርኮች ማንነት የሚገልጽ መጽሔት ለሁሉም እንዲሰራጭ ተደረገ፡፡

 

ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ሲሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ጨምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወደ አዳራሹ በማምራት በመድረኩ ላይ በተዘጋጀው ልዩ ስፍራ ላይ ዐረፍ ብለዋል፡፡ ከመድረኩ ወረድ ብሎም ከመራጮች ፊት ለፊት ሁለት ባለ መስታወት የምርጫ ሳጥኖች ይታያሉ፡፡

 

ከጠዋቱ አንድ ሰዓት በኋላ በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል መሪነት ውዳሴ ማርያም፤ የኪዳን ጸሎትና ጸሎተ ወንጌል ከደረሰ በኋላ መራጮች በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ አማካይነት ቃለ መሐላ ፈጽመዋል፡፡ ወደ ምርጫው ከመገባቱ በፊትም ለመራጮች ተጨማሪ ግንዛቤ ለመስጠት በምርጫውና በአመራረጡ ዙሪያ ማብራሪያ ከአስመራጭ ኮሚቴው ተሰጥቷል፡፡

 

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ አስመራጭ ኮሚቴው የምርጫ ታዛቢዎች፤ መራጮች ባሉበት ሁለቱ የምርጫ ሳጥኖች እንዲታሸጉ ተደረገ፡፡ የምርጫ ሳጥኖቹ መታሸጋቸው ከተረጋገጠ በኋላ በቀጥታ ወደ ምርጫ ሥነ ሥርዓቱ የተገባ ሲሆን በቅድሚያ በመምረጥ ምርጫውን ያስጀመሩት ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ናቸው፡፡ በመቀጠልም ብፀዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የመምሪያ ሓላፊዎች፤ የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችና ሌሎችም በቅደም ተከተል መታወቂያቸውንና የምርጫ ካርዳቸውን በመያዝ ከመዝገባቸው ጋር በማመሳከር ከተረጋገጠ በኋላ የምርጫ ወረቀቱን በመውስድ በምስጢር ድምፅ ወደሚሰጡበት ቦታ በመግባት ወረቀቱን ለአራት በማጠፍ ፊት ለፊት ከሚገኙት የምርጫ ሳጥኖች ውስጥ በግልጽ በመጨመር የምርጫው ሥነ ሥርዓት ቀጠለ፡፡

 

የምርጫው ሥነ ሥርዓት እየተከናወነ ሳለ ከግብፅ ተወከወለው የመጡ በብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ የቀድሞው የግብፅ አቃቤ መንበረ ፓትርያርክ የሚመራው አምስቱ ልዑካን ወደ አዳራሽ በመግባታቸው የምርጫው ሥነ ሥርዓት እንዲቆም በማድረግ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡

 

ከግብፅ የመጡት አባቶችም፡- ብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ፤ ብፁዕ አቡነ ቢሾይ፤ ብፁዕ አቡነ ሄድራ፤ ብፁዕ አቡነ ቢመን፤ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ሲሆኑ ምርጫውን ከማካሔዳቸው በፊት ብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ ቃለ ምእዳን ሰጥተዋል፡፡ በሰጡት ቃለ ምእዳንም “የመጣነው ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ጋር በአሉን ለማክበር ነው፡፡ ይዘን የመጣነው የግብፅ ቅዱሳንን ቡራኬ ነው፡፡ እኛ የቅዱስ ማርቆስ ቡራኬ ይዘን መጥተናል፤ ከኢትዮጵያ ደግሞ የጻድቁ አባት አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ቡራኬ ይዘን እንሄዳለን፡፡ እኅት ለሆነችውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ኢትዮጵያውያን ታላቅ ፍቅር አለን” በማለት ተናግረዋል፡፡ግብጻውያን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫውን በማከናወን ከተሸኙ በኋላ ምርጫው ቀጥሏል፡፡

የከስዓት በኋላውን ሥነ ሥርዓት እንደደረስ እናቀርብላችኋለን፡፡