‹‹የሰው ሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል›› (መዝ. ፻፵፬፥፲፭)

በዝግጅት ክፍሉ

ኅዳር  ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ተስፋ ሲኖረን የነገን ለማየት እንናፍቃለን፤ ዛሬ ላይም በርትተን ለመጪው እንተጋለን፤ የመልካም ፍጻሜችንም መድረሻ በተስፋችን ይሰነቃልና፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፤ አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ። ቀኝ እጅህን ትዘረጋለህ፤ በሥርዓትህ ለሚኖሩ እንስሳ ሁሉ ታጠግባለህ፡፡  እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ ነው፤ በሥራውም ሁሉ ቸር ነው። እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፥ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው። ለሚፈሩት ምኞታቸውን ያደርጋል፥ ልመናቸውንም ይሰማል፥ ያድናቸዋልም። እግዚአብሔር የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል፤ ኃጢአተኞችንም ሁሉ ያጠፋል›› በማለት ገልጿል፡፡ (መዝ.፻፵፬፥፲፭-፳)

እግዚአብሔር አምላክ በእርሱ ፈቃድ ለሚኖሩ ሰዎች ተስፋቸው ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊትም በታመነለት አምላኩ ያጣው አንዳች ነገር እንደሌለ መስክሯል፡፡ ከእረኝነት አንሥቶ ለንግሥና አብቅቶታልና፤ በምድራዊው ሕይወቱ በፈቃዱ እንዳኖረው ሁሉ ዘለዓለማዊ ርስትን አውርሶታል፡፡ ነቢዩ ኤርምያስም ‹‹በእግዚአብሔር የሚታመን፥ ተስፋውም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው›› ብሎ ነግሮናል፡፡ (ኤር.፲፯፥፯)

የሰዎች ተስፋ እውነትም ሕይወትም በሆነው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ እርሱ ለእኛ ሲል በመስቀል ተሰቅሎ ነፃ አውጥቶናልና፤ በቃሉ ኖረን በጽድቅ መንገድ በመላለስ የዘለዓለም ተስፋችን በሆነው በጌታችን ልናምን እንዲሁም መስቀሉን ተሸክመን ልንጓዝ ይገባል፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን በመጽሐፈ ምሳሌ ላይ ‹‹በሥራ ዐዋቂ የሆነ የሚያዳምጥ መልካም ነገርን ያገኛል፤ በእግዚአብሔር የታመነ ብፁዕ ነው›› በማለት ልንታመን እና በተስፋ ልንኖር የሚገባው በዕውቀታችን፣ በሀብታችን ወይም በሥልጣናችን ሳይሆን የዘለዓለም ተስፋችን በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሊሆን እንደሚገባ አስቀድሞ ነግሮናል፡፡ (ምሳ. ፲፮፥፳)

በክርስትና ሕይወት ውስጥ በመንፈሳዊነት ዕድገት የጽድቅን ፍሬ ማፍራት ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ዘመኑን በመዋጀት እና በበጎ ተግባር በመጠመድ እግዚአብሔር አምላካችን ለአዳም የሰጠውን ተስፋ እንዲፈጽምለት የእኛንም ተስፋ ፍጹም ያደርግልናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ ‹‹.…በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ትጉ›› በማለት ይህን አስረድቷል፡፡ (ሮሜ ፲፪፥፲፪)

አባታችን አዳም ዕፀ በለስ በልቶ ከገነት ሲሰደድ ተስፋው ጨልሞ በምድር ሲሠቃይ ኖሯል፡፡ ነገር ግን ከፈጣሪው ይቅርታን ያገኝ ዘንድ ይማጸን ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ቸርነቱ የበዛ ቁጣው የራቀ በመሆኑ በፈጠረው ፍጥረት ሳይጨክን ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ›› የሚል የምሕረት ተስፋ ሰጠው። አዳምም ተስፋውን እየጠበቀ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ያህል ምሕረቱን ተስፋ አድርጎ ኖረ። (መጽሐፈ ቀሌምንጦስ፣ ዘፍ ፫፥፲፮)

ለአዳም የተሰጠው ብቸኛው ተስፋ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም መወለድ ያጣውን የልጅነት ጸጋ ለመመለስ እና ዕዳውን እንዲከፍልለት የገባለት ቃል ለሰው ዘር በሙሉ የድኅነት ተስፋ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ መልእክቱ ስለተከፈልን ዋጋ እንዲሁም የዘለዓለማዊ ሕይወታችን ስለማሰብ በተስፋ እንድንኖር እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡ ‹‹እኛ ግን የቀን ልጆች ስለሆን እንንቃ፤ የሃይማኖትንና የፍቅርን ጥሩር እንልበስ፤ ተስፋ ያለበት የመዳንን ራስ ቊርም እንቀዳጅ፡፡ እግዚአብሔር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለሕይወት ደኅንነት እንጂ፥ ለጥፋት አላደረግንምና። የምንነቃ፥ ወይም የምናንቀላፋም ብንሆን፥ ሁላችን ከእርሱ ጋር በሕይወት እንኖር ዘንድ፥ ስለ እኛ ቤዛ ሆኖ ሞተ፡፡››  (፩ተሰ. ፭፥፰-፲)

ዓለም በጭንቅና በጣር ተይዛ ሰዎች የነገን ማየት ይችሉ እንደሆነ እርግጠኝ መሆን ባልቻልንበት በዚህ ጊዜ ተስፋ ማጣት ሊያስጨንቀን ይችላል፡፡ ሰላም አጥተን የግጭትና የጦርነት ወሬ ከዳር እስከ ዳር በየዕለቱ በሚነገርበት ወቅትም መልካም ነገርን ለመስማት እንናፍቃለን፤ የመኖራችን ትልም የሚወሰነው በዛሬው ሕልውናችን እንደመሆኑም ልንመካበት እና ተስፋ ልናደርገው የምንችለው የድኅነት መንገድ መኖሩን ልንረዳ ይገባል፡፡

በዚህች በጨለማ ዓለም ውስጥ ተውጠን ነገን በተስፋ የምንጠብቀው እግዚአብሔር አምላካችንን በማመን እና በእርሱ በመመካት ነው፡፡ ስለሆነም ወደ እርሱ ልንቀርብና ልንማጸን ይገባል፡፡   ተስፋም እግዚአብሔር ለእኛ በሰጠን በአንድ ልጁ አማካኝነት ስለሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለዱን፣ መጠመቁን፣ መከራ መቀበሉን፣ መሰቀሉን፣ መሞቱን እንዲሁም መነሣቱን ከዚያም ማረጉን በማመን እርሱን ተስፋ አድርገን መኖር አለብን፡፡ የደኅንነታችን ተስፋ እርሱ መሆኑንም በመቀበል በጾምና በጸሎት ልንተጋ ይገባል፡፡ ‹‹የሚያድነው የእግዚአብሔር ጸጋ በሰው ሁሉ ዘንድ ታውቋልና፡፡ እርስዋም ከኃጢአትና ከዓለም ፍትወት እንለይ ዘንድ፥ በዚህ ዓለምም በጽድቅ፥ በንጽሕና በፍቅር እንኖር ዘንድ ታስተምራለች፡፡ የተመሰገነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ከኃጢአት ይቤዠን ዘንድ፥ በበጎ ምግባር የሚፎካከር አዲስ ሕዝብንም ለእርሱ ይመረጥ ዘንድ ስለ እኛ ራሱን አሳልፎ የሰጠ፡፡ ለሁሉ ራስህን ዝቅ እያደረግህ ይህን ለሁሉ ምከርና አስተምር፤ ገሥጽም፤ የሚያስትህ አይኑር›› እንዲል፡፡ (ቲቶ. ፪፥፲፩-፲፭)

በሕይወት ለመኖር ተስፋ እንከምንቆርጥ ድረስ ከዐቅማችን በላይ የሆነ ጽኑ መከራ ሊደርስብን ይችላል፤ በዚህ ወቅት በየአካባቢው ተፈናቅለውና መጠጊያ አጥተው የሚገኙ ሰዎች ጥቂት አይባሉም፡፡ እነርሱ ደግሞ ምግብ መጠለያ ማግኘት የማይችሉ ድኃዎች ወይንም አቅመ ደካሞች በመሆናቸው የሌሎችን ርዳታ ሌት ከቀን ይጠባበቃሉ፤ ሆኖም ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ምሕረቱ የበዛ አምላክ በመሆኑ በእርሱ የታመኑትን በቸርነቱ ያኖራቸዋል፡፡ ተርበው ከመሞት ያድናቸዋልና ወደ ፊትም በእርሱ ቸርነት እንደሚኖሩ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

በእርግጥ ምድራችን በፈተና ተከባና በሥጋት ተውጣ ባለበት በአሁኑ ጊዜ መፍትሔ ለማግኘትና ችግርን ለመፍታት ተጨንቆ ማሰብ አይቀሬ ነው፡፡ ሆኖም ግን አይደለም ከጊዜያዊ ችግር ይቅርና መድኃኒት አልተገኘላቸውም ከተባሉ በሽታዎች እንኳን በእምነት መዳን እንደሚቻል በገሀድ ያየነው እውነት ነው፡፡ ይህም በዘመናት የተከሠቱና እጅጉን ተሰራጭተው የሰዎችን ሕይወት ያጠፉ በሽታዎች በጸበል ሲድኑ ሰምተንም አይተንም ሊሆን ይችላል፡፡ ከኤች አይ ቪ ወይንም ከካንሰር እንዲሁም እስከ አሁን ድረስ ወረርሽኙ ያልቆመው ከኮሮና በሽታ ጨምሮ ሰዎች እንደተፈወሱ ሰምተናል፡፡  ስለዚህም ‹‹እምነትስ ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የምታረጋግጥ፥ የማናየውንም ነገር የምታስረዳ ናት›› እንደተባለው እግዚአብሔር አምላክን ተስፋ በማድረግ ከየትኛውም በሽታ እንደምንፈወስ፣ ማንኛውንም ችግርም ሆነ መከራ እንደምንቋቋም እና እስከመጨረሻም በተስፋ ተጉዘን ከተስፋይቱ መንደር እንደምንደርስ ልናምን ይገባል፡፡ ‹‹እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን፥ በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እናገኛለን፡፡ በእርሱም አማካኝነት ወደቆምንበት ወደ ጸጋው በእምነት ተመራን፤ በእግዚአብሔር ክብር ተስፋ እንመካለን፡፡ የምንመካ በእርስዋ ብቻ አይደለም፤ በመከራችን ደግሞ እንመካለን እንጂ፤ መከራ ትዕግሥትን እንደሚያደርግ እናውቃለንና፡፡ ትዕግሥትም መከራ ነው፡፡ በመከራም ተስፋ ይገኛል፤ ተስፋም አያሳፍርም›› እንዲል፡፡ (ሮሜ ፭፥፩-፭)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ እንደገለጸው በምድራዊ ሕይወታችን በጽድቅ እና በእውነት መኖር አለብን፡፡ ይህም ተስፋችን ፍጹም እንዲሆን በዚህ በነቢያት በጾም በጸሎት ልንተጋ፣ በጽድቅ ልንጓዝ፣ በሃይማኖት ልንጸናና በተስፋ ልንኖር ያስፈልጋል፡፡

የነቢያትን ጾም በሰላም አስጀምሮ ያስፈጽመን ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁንልን፤ የቅድስተ ቅዱሳን የቅዱሳት ድንግል ማርያም ምልጃና በረከቷ አይለየን፤ አሜን፡፡