‹‹የምሥራች እነግራችኋለውና አትፍሩ›› (ሉቃ.፪፥፲)

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ታኅሣሥ ፳፰፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች እንዴት አላችሁ? እንኳን አደረሳችሁ! የልደት በዓል ዝግጅት እንዴት ነው? ልጆች ትምህርተስ እየበረታችሁ ነውን? አሁን የዓመቱ አጋማሽ የፈተና ወቅት በመሆኑ መምህራን ሲያስተምሩን ከመጻሕፍት ስናነብ የነበሩትን ምን ያህሉን እንደተረዳን የምንመዘንበት ጊዜ ነው! መቼም በርተታችሁ ስታጠኑና ያልገባችሁን ስትጠይቁ ስለ ነበር በፈተና የሚቀርቡላችሁን ጥያቄዎች በትክክል እንደምትመልሱ ተስፋችን እሙን ነውና በርቱ! ያለንበት ጊዜ ደግሞ የበዓላት ወቅት ስለሆነ በዚህ እንዳትዘናጉ፣ ከሁሉ ቅድሚያ ትኩረት ለትምህርት መስጠት አለባችሁ።፡ ነገ አገር ተረካቢዎችና ታሪክን ጠባቂዎች ስለምትሆኑ በርቱና ተማሩ!

ታዲያ ልጆች ዕውቀት ማለት በተግባር መተርጎም መሆኑን እንዳትዘነጉ! አንድ ሰው ተማረ፤ አወቀ ማለት ክፉ ነገር ከማድረግ ተቆጠበ፤ ሰዎችን ረዳ (ደገፈ)፤ ለሰዎች መልካም ነገርን አደረገ፤ ሌላውን ወደደ ማለት ነው፤ መማራችሁ ለዚህ መሆን አለበት፡፡ ቅን፣ ደግ፣ አስተዋይ እንዲሁም ወገኑን የሚወድ ሰዎች ሆናችሁ ለመኖር ሁል ጊዜ መበርታት አለባችሁ:: መልካም ልጆች! ዛሬ ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንማራለን!

አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን በገነት በደስታ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ሲኖሩ አትንኩ የተባሉትን ዕጸ በለስ የተባለ ፍሬ እንዲበሉ ሰይጣን ባታለላቸው ጊዜ ትዕዛዝን በመተላለፋቸው አምላክ ቀጣቸው፡፡ ከምድርም ተባረው በምድር ላይ ብዙ መከራ ደረሰባቸው፡፡ ልጆች ታላላቆቻችን (ወላጆቻችን፣ መምህራኖቻችንን…) አንድን ነገር አታድርጉ ሲሉን እኛን ለመጥቀም እንጂ ሊጎዱን አይደለምና ትዕዛዛቸውንና ምክራቸውን ልንሰማ ይገባል! አለበለዚያ ግን እንጎዳለን፡፡ ወላጆች ሁል ጊዜ ለእኛ መልካም ነገርን የሚያስቡ የሚጠቅመንን ነገር የሚነግሩን ናቸውና ትዕዛዛቸውን እንፈጽም፡፡ አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን ፈጣሪያችን አታድርጉ ያለውን አድርገው ከገነት በወጡ ጊዜ ሰይጣን ብዙ መከራ አደረሰባቸው፡፡ ከዚያም ይቅር በለን ብለው ወደ እግዚአብሔር በንስሓ በመመለስ “ማረን፣ ይቅር በለን፣ አጥፍተናል” አሉ።፡

ከዚያም ጌታችን ከሰማያት ወርዶ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል ኪዳን ገባለት፡፡ አዳምና ልጆቹ እመቤታችንን በተስፋ እየጠበቁ በጾም በጸሎት መኖር ጀመሩ፡፡ ልጆች! አዳምን “አድንሃለው” ባለው ቃል ኪዳን መሠረት ፶፻፭፻ (አምስት ሽህ አምስት መቶ) ዘመን ሲፈጸም ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን በቤተልሔም ተወለደ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! አዳም አባታችንና እናታችን ሔዋን ስለተጸጸቱ ይቅርታ እንደተደረገላቸው ተረድተን እኛም ምን ጊዜም ስናጠፋ ቶሎ ብለን ይቅርታ መጠየቅ አለብን፡፡ ልጆች እንደመሆናችን ልንሳሳት እንችላለን፡፡ ታዲያ ከወላጆቻችንና ከመምህራን ብንደብቅ ጥሩ አይደለም፡፡ ቶሎ ብለን ይቅርታ በመጠየቅ ወደ ሌላ ጥፋት እንዳንሄድ መከልከል አለብን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ነቢዩ ዳዊት በትንቢት ‹‹..እነሆ በኤፍራታ ሰማነው፤ በዱር ውስጥም አገኘነው…›› ብሎ እንደተናገረው እመቤታችን ጌታችንን በኤፍራታ በቤተልሔም በከብቶች ግርግም (በረት) በወለደችው ጊዜ የጨለመው ዓለም በራ፤ ፍጥረት ሁሉ ተደሰተ፡፡ (መዝ.፻፴፩፥፯) ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደምትወልድ እንዳበሠራት አሁን ደግሞ በወለደች ጊዜ በቤተልሔም በጎቻቸውን በሌሊት ከሚመጣ አውሬ በንቃት በመጠበቅ ላይ ለነበሩ እረኞች ‹‹የምሥራች፣የምሥራች›› እያሉ የጌታችንን መወለድ አበሠራቸው፡፡ እረኞቹም ይህን ሲሰሙ ደነገጡ፤ ቅዱስ ገብርኤልም ‹‹እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ፥ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፡፡ ይኸውም ጌታ እና እግዚአብሔር የሆነ መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እናንተም ባገኛችሁት ጊዜ ምልክቱ እንዲህ ነው፡፡ ሕፃን በጨርቅ ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ ተኝቶ ታገኙታላችሁ፤ ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ መላእክት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ›› አላቸው፡፡ (ሉቃ.፪፥፲-፲፫) እነርሱም ደስ እያላቸው፤ ወደ ቤተልሔም ሄዱ፤ በዚያም ሕጻኑ ክርስቶስን ከእመቤታችን ጋር ከቅዱስ ዮሴፍ ጋር በበረት አገኙት፤ እጅግም ደስ ተሰኝተው ሰገዱለት፤ ከቅዱሳን መላእክት ጋር አብረው ‹‹በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን፤ በምድርም ለሰው ልጆች በጎፈቃድ ሆነ›› እያሉ አመሰገኑ፡፡ (ሉቃ.፪፥፲፭-፲፰)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የጌታችን ልደት ሰላም የሰፈነበት፣ እርቅ የተደረገበት እንዲሁም የሰው ልጆች ከዲያቢሎስ ባርነት ነጻ የወጣንበት የፍቅር የደስታ በዓል ነው፡፡ ጌታችን በመወለዱ እኛ ከአምላካችን ጋር ታርቀናል፤ ከቅዱሳን መላእክት ጋር ታርቀናል፤ በመካከላችን የነበረው ጠብ (ጥላቻ) ተወግዶና ሰላም ሰፍኖ አብረን አመስግነናል፡፡ ስለዚህ በዓሉን ስናከብር የተቀየምናቸው ሰዎች ካሉ ይቅርታ ልናደርግላቸው እኛም ካስቀየምን ይቅርታ ልንጠይቅ ይገባል፤ የጌታችንን የልደት በዓል ማክበራችን ዓላማው ይሄ ነውና እርሱ ይቅር እንዳለን እኛም እርስ በእርሳችን ይቅር መባባል አለብን፤ ይህ በዓል የጌታችንን ውለታ የምናስብበትና ለእኛ ያለውን ፍቅር የምናስታውስበት በመሆኑ ይህን የምንገልጠው ሰዎችን በማስታረቅ፣ ለሰዎች መልካም በማድረግና ካለን ላይ ለሌላቸው ስናካፍል ነው፡፡ ሌላው ልጆች! ጌታችን በተወለደ ጊዜ ሰባ ሰገል (ሦስቱ ነገሥታት) ከሩቅ አገር እጅ መንሻ (ስጦታ) ይዘው በመምጣት ለጌታችን ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤ ሰጥተውታል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ ጌታችን እኛን ከወደቅንበት ሊያነሣን በትሕትና በቤተልሔም በኤፍራታ እንደተወለደልን እኛም እርሱን አርአያ አድርገን በሕይወታችን ታዛዦች፣ ለሰዎች የምናዝን፣ መልካም ነገርን የምናደርግ፣ አስተዋይና ብልህ እንዲሁም ቅን ልጆች ልንሆን ይገባናል፡፡

አምላካችን ፈጣሪያችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከበዓለ ልደቱ ረድኤት በረከቱን ይክፈለን (ይስጠን) አሜን!!! ቸር ይግጠመን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!