0202023 1

የመስቀል በዓል አከባበር በዩኔስኮ ቅርስነት ተመዘገበ

 ኅዳር 26 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

  • የመስቀል በዓል አከባበር ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው 10 ቅርሶች መካከል የመጀመሪያው የማይዳሰስ ቅርስ በመባል መመዝገቡን አስመልክቶ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ፡፡

 0202023 1
የኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የኢትዮጵያ የመሰቀል በዓል አከባበር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ ቅርሶች (Intangible) በቅርስነት መመዝገቡን አስመልከቶ ኅዳር 26 ቀን 2006 ዓ.ም. በባለሥልጣኑ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ፡፡

አቶ ዮናስ ደስታ የፌደራል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ዳይሬክተር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “የመስቀል በዓል አከባበር በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ (Intangible) ሆኖ የተመዘገበው ዩኔስኮ የሚጠይቀውን ሒደት ጠብቆና የተለያዩ የግምገማ መሥፈርቶችን አልፎ አዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ ከኅዳር 23 – 28 ቀን 2006 ዓ.ም. እያደረገ ባለው ስምንተኛው የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጉባኤ ላይ በትናንትናው ዕለት ተቀብሎ አጽድቆታል”  በማለት ገልጸዋል፡፡

አቶ ዮናስ የመስቀል በዓል አከባበርን በቅርስነት ለማስመዝገብ የተደረገውን ጥረት ሲገልጹ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባለሙያዎች አማካይነት ጥናቱ ተከናውኖ ሰነዱ ለዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ኖሚኔሽን  በ2004 ዓ.ም. መቅረቡን አውስተዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲመዘገቡ ለጉባኤው ከቀረቡት 31 የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል 23ቱ ሲመረጡ የመስቀል በዓል አከባበር ከተመረጡት ውስጥ አንዱ በመሆኑና እውቅና ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡

0202023 2አቶ ዮናስ የመሰቀል በዓል አከባበር በዓለም አቀፍ ደረጃ የመመዝገቡ ፋይዳን ሲገልጹም ቅርሱን የተመለከቱ መረጃዎች በዩኔስኮ ድረ ገጽ ላይ የሚለቀቅ በመሆኑ ሀገረ አቀፍና ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ እንደሚረዳው፤ የቱሪስት መስህብ መሆኑ፤ ከቀድሞ በተሻለ እንክብካቤ የሚደረግለትና ለትውልድ እንዲተላለፍ እገዛ ማድረጉን፤ ዓለም አቀፍ አጥኒዎችና ተመራማሪዎችን መሳቡ ዋና ዋናዎቹ  ጥቅሞች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የሰሜን ተራሮች፤ አክሱም ጸዮን ሐውልቶች፤ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፤ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ፤ ጢያ ትክል ደንጋዮች፤ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፤ ሐረር ጀጎል፤ የኮንሶ ባሕላዊ መልክአ ምድር እና  የፋሲል ግቢ ኢትዮያ ከዚህ ቀደም ያስመዘገበቻቸው የሚዳሰሱ (tangible) ቅርሶች መካከል ዘጠኙ ሲሆኑ ብቸኛው የመስቀል በዓል አከባበር ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል ይመደባል፡፡