የሐዋርያት ጾም

መምህር አምኃ በላይ

ሰኔ ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ሐዋርያት ወንጌለ መንግሥት እንዲስፋፋና በሕዝብም ሆነ በአሕዛብ ዘንድ አገልግሎታቸው የሠመረ እንዲሆን መንፈስ ቅዱስን በተቀበሉ በበዓለ ሃምሳ ማግሥት  ጾም ጀመሩ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ በሰጣቸው ሥልጣን ድውያንን መፈወስና አጋንንትን ማውጣት እንዲሁም የተለያዩ ገቢረ ተአምራትን ይፈጽሙ ዘንድ ጸሎትና ጾም ያስፈልጋቸው ነበርና፡፡ በማቴዎስ ወንጌል እንደተጻፈው ጌታችን ጋኔን ያለበትን ልጅ ካዳነው በኋላ ሐዋርያቱ ስለምን እነርሱ ጋኔን ከሰው ማውጣት እንዳልቻሉ በጠየቁት ጊዜ እንዲህ ሲል መልሶላቸዋል፤ ‹‹…ይህ ዓይነቱ ግን ያለጾምና ጸሎት አይወጣም፡፡›› (ማቴ.፲፯፥፳፩)

ሐዋርያት ጌታችን ኢየሱስ ገቢረ ተአምራትን ሲፈጽም፣ ሲጾምና ሲጸልይ አብረውት ሆነው አይጾሙም ነበር፤ በዚያን ጊዜም የሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙርት ወደ እርሱ ቀርበው ‹‹እኛና ፈሪሳውያን ብዙ እንጾማለን፤ ደቀ መዛሙርትህስ ለምን አይጾሙም›› ብለው ጌታችንን ጠየቁት፡፡ ጌታችንም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ ‹‹የሙሽራው ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ አይችሉም፤ ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤ ያንጊዜም ይጾማሉ፡፡ (ማቴ.፱፥፲፬-፲፭)   

ሙሽራ የተባለውም ጌታችን ኢየሱስ በምድር ላይ ነገረ ድኅነትን ፈጽሞ እስኪያርግና መንፈስ ቅዱስ ሚዜዎቻቹም በተባሉት ሐዋርያት ላይ እስኪያድር ድረስ አልጾሙም፤ ከዚህ በኋላ ግን ጾማቸውን እንደሚጀምሩ ጌታችን አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ ያለ ጾምና ያለ ጸሎት አገልግሎት ሊሰምር አይችልም፤ ጠላታችን ዲያብሎስንም ማሸነፍ አይቻለንም፡፡  ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ላይ ‹‹መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው?›› ብሎ እንደተናገረው ሐዋርያት በዓለም ዙሪያ በ፸፪ ቋንቋ ማስተማር የቻሉትና ተልእኮአቸው የሠመረላቸው አስቀድመው በመጸለያቸውና መጾማቸው ነው፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መገለጥ፣ ስለ መዋዕለ ትምህርቱ፣ ስለ ስቅለቱ፣ ስለ ትንሣኤው፣ ስለ ዕርገቱ እንዲሁም ስለ ዳግም ምጽአቱ ካስተማራቸው በኋላ በአንድ ቀን ፫ ሺህ ሰዎች አምነው ተጠምቀዋል፡፡ እናም ሐዋርያዊ ተልኦካችንን ለማሳካት አገልግሎታችንን በጾምና በጸሎት ልናጠነክር ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ወርኃዊ ደሞዝተኞች እንጂ ባለ ትሩፋት አንሆንም፡፡ ደሞዝተኝነት ደግሞ ቅጥረኝነት ስለሆነ መሪም ተመሪም መሆን አይቻልም፡፡ ሰዎችን አይደለም ወደ ወንጌለ መንግሥት ለማድረስ ይቅርና ምድራዊ በሆነው አኗኗር እንኳን አጽንቶ መኖር አይቻልም፡፡ መንግሥተ ሰማያትን ተስፋ በማድረግ መኖር ካልተቻለ ሰብአዊነት ሊኖረን አይቻልም፡፡ (ሮሜ ፲፥፲፭)

ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹ሰው ግን ክቡር ሲሆን አላወቀም፤ ልብ እንደሌላቸው እንስሶችም ሆነ፥ መሰላቸውም›› ብሎ እንደተናገረው ሰው ካልጸለየና ካልጾመ እንደ እንስሳ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ልብ የሌላቸው እንስሶች ደግሞ ያገኛቸው አውሬ ሁሉ የሚዘነጥላቸው ናቸው፡፡ (መዝ. ፵፰፥፳)

ዛሬ ብዙዎች ከጸሎትና ከጾም ስለተለዩ የአምላክን ቃል መጠበቅም ሆነ በድኅነት መንገድ መጓዝ ትተው የሥጋ ድሎታቸውን ለሟሟላት ዘወትር ይዳክራሉ፡፡ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስም በፈተናችን እንድንወድቅና ለሥጋ ፍላጎታችን ብቻ ተገዝተን እንድንኖር የሚፈታተነን በሆዳችን ነው፡፡ በአጽዋማት ወቅትም ሆነ በሌላ ጊዜ ለምግብ የተለየ ትኩረት እንድናደረግና ሥጋችንን በርኃብ ከመቅጣት ይልቅ እንድናደልበው ይገፋፋናል፤ በተለያዩ የምግብ ዓይነትም አምሮት ያነሣሣብናል፡፡ ስለዚህም ዲያብሎስን ድል ለመንሣት ጾምና ጾሎት ያስፈልጋል፡፡   ጾም ሥጋን አድክሞ መንፈስን የሚያጎለብት በመሆኑ የሥጋዊ ፍላጎት አምሮትን የምንገለገልበትና የምንናገርበት ነውና፡፡

ነገር ግን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹እነዚህም ፍጻሜያቸው ለጥፋት የሆነ፥ ሆዳቸውን የሚያመልኩ፥ ክብራቸው ውርደት የሆነባቸው፥ ምድራዊውንም የሚያስቡ ናቸው›› በማለት እንደተናገረው ለከርሣቸው የሚኖሩ ክብራቸውን ያጡ ሰዎች በርካቶች ናቸው፤ ሰው እግዚኢብሔር አምላኩን የሚተወው ራሱን ለሥጋ ምግቦች አዘጋጅቶ ለሆዱ ብቻ ሲኖር ነው፡፡ ለጾም ያደሉ ቅዱሳን ግን ፊታቸው የሚያበራ፣ በጥላቸው ድውይ የፈወሱ፣ ሙት ያነሡ፣ በመቅደሱ ገብተው ከእናታቸው ማኅፀን ጀምሮ ሽባ የሆኑትን ሰዎች በመፈወስ ያዳኑ ናቸው፤ (ፊል.፫፥፲፱)

ሐዋርያት በጾምና በጸሎታቸው ወንጌለ መንግሥት እንዲፋጠን ከአምላካቸው እግዚአብሔር የተሰጣቸውን መመሪያ ይዘው ተጉዘዋል፡፡ እኛም በጾምና በጸሎት ተግተን ጌታችን ኢየሱስ በመሠረተልን የድኅነት መንገድ ተጉዘን ወደ እግዚኢብሔር ክብር ራሳችንን በንስሓ መለወጥ እንችላለን፡፡

በአሁኑ ጊዜ በየቀኑ ኃጢአት የበዛውና ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ሸሽተው ዓለማዊነትን የተለማመዱት ከጾምና ከጸሎት እንዲሁም ከቅድስና ሕይወት በመራቃቸው ነው፡፡ ስለዚህም ከቅዱሳን ሐዋርያት አባቶቻችን አኗኗር ልንማር ይገባል፤ ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ እንዲህ ሲል ተናግሯል፤ ‹‹የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ የኑሮአቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው፡፡›› የኑሮ ፍሬ የተባለውም ጾም ነው፡፡ የአባቶቻችንን የእምነት ፍሬ እየተመለከትን ጸንተን እንድንኖር የሐዋርያት ጾም ያስተምረናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ጾሞ ጾምን እንደመሠረተላቸው እነርሱንም እንዲጾሙ ባዘዛቸው መሠረት በመኖርና እስከመጨረሻው በመጽናት የሰማዕትነትን አክሊል እንደተቀዳጁ ሁሉ እኛም በጾምና በጸሎት በመትጋት እስከ ሕልፈተ ሕይወታችን በሃይማኖት ልንጸና ይገባል፡፡ (ዕብ.፲፫፥፯)

ነፍስን የሚያለመልምና በቅድስና ሕይወት የሚያኖር መብላት መጠጣት ሳይሆን በወንዝ ዳር እንደተተከለችና ሁል ጊዜ ፍሬዋን እንደምትሰጥ ዛፍ ነፍሳችን እንድታፈራ የሚያደርግ ጾም በመሆኑ ሁላችን ልንጾም ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በየዓመቱ የሐዋርያትን ጾም በማወጅ ሕዝበ ክርስቲያን እንዲጾሙ ታደርጋለች፤ በዚህ ዓመትም ጾሙ ከሰኔ ፲፬ ቀን እስከ ሐምሌ ፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. ድረስ በመሆኑ ሁላችን ልንጾመው ይገባል፡፡

በጾምና በጸሎት ተወስነን፣ ቅዱሳን ሐዋርያት የኖሩበትን የሕይወት ፍሬ እየተመለከትን፣ በእምነታችን ጸንተን እንድንኖር የእግዚአብሔር አምላክ ቅዱስ ፍቃዱ ይሁንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር