የሃይማኖት አባቶች የቀድሞ የደርግ ባለሥልጣናትን ወክለው ይቅርታ አቀረቡ።

መ/ር መንግስተአብ አበጋዝ

የአራት የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች የቀድሞ የደርግ ባለሥልጣናትን የይቅርታ ጥያቄ ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት አቀረቡ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ እና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሃይማኖት መሪዎች ቅዳሜ ታኅሳስ 9 ቀን 2003 ዓ.ም በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ተገኝተው በሰጡት የጋራ መግለጫ ይህን የታሪክ ጠባሳ በአገራዊ ይቅርታና ዕርቅ መጨረስ ከሁሉ በላይ ታላቅ መንፈሳዊ አንድምታ ይኖረዋል ብለዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ጉባኤውን ወክለው ባቀረቡት መግለጫ ላለፉት ሁለት ዓመታት ለጉዳዩ ስኬታማነት ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በሚያገኙት ይሁንታ ታኅሣሥ 21 ቀን 2003 ዓ.ም አጠቃላይ ሀገራዊ እርቅ እንደሚካሄድ ተናግረው፥ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንኑ መንፈሳዊ ጥሪ ተቀብሎ በጎ ምላሽ እንደሚሰጠን በመተማመን ይህን የሰላምና የዕርቅ ሐሳብን ይዘን ቀርበናል በማለት አስረድተዋል።

«ብፁዓን ገባርያነ ሠላም፥ እስመ እሙንቱ ውሉደ እግዚአብሔር ይሰመዩ።
የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና»  ማቴ 5፥9