ዝክረ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጻድቅ

ታኅሣሥ ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

t

ቅዱሳን ጻድቃን በመንፈሳዊ አርአያነታቸው፣ በጸሎታቸውና በትምህርታቸው ከከበቡን የነፍስ ጠላቶች፤ ከርኲሳን መናፍስትና ከጨለማው ልጆች፣ ከክፉ ሰዎች ሽንገላና ተንኰል ለመሰወርና ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር የተቀበሉት ሥልጣን ምን ጊዜም ይሠራል፡፡ በጻድቃን መኖር ሀገር ከጥፋት ትድናለች፡፡ የጻድቃንን ስም ጠርቶ እግዚአብሔርን በመለመን በረከትና ረድኤት ይገኛል፡፡ ስለ ጻድቃን ብሎ እግዚአብሔርም ምሕረቱን ያድላል፡፡ ጻድቃንን ማሰብ ሥራቸውን መዘከር ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን ያጐለምሳል፡፡ በነፍስ በሥጋ ይታደገናል፤ ይረባናል፤ ይጠቅመናል፡፡

ስለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያናችን ጻድቃንን እንድናስባቸው፣ በስማቸውም ለድሆችና ለጦም አዳሮች እንድንመጸውት፣ መታሰቢያቸውን እንድናደርግ የምትመክረን፤ የምታስተምረን /ማቴ.፲፥፵፩-፵፪/፡፡ ቅዱሳን ጻድቃን በሕይወተ ሥጋ ሳሉም ኾነ ከሞቱ በኋላ በዐጸደ ነፍስ ኾነው በጸሎታቸው ለሚታመኑ፣ በቃል ኪዳናቸው ለሚማጸኑ ምእመናን በመጸለይና ወደ እግዚአብሔር በማማለድ ድኅነተ ሥጋ፣ የድኅነት ነፍስን የሚያስገኙልን የችግር ጊዜ አማላጆቻችንና አስታራቂዎቻን ናቸው፡፡ ከእነዚህ ቅዱሳን መካከል ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንደኛው ናቸው፡፡

‹ተክል› ማለት ፍሬያማ ዕንጨት፣ ዛፍ፣ ቅመም፣ ቅጠላ ቅጠል፣ የሚበላ፣ የሚሸተት፣ ገነታዊ ዕፅ፣ እንዲሁም ሕግ ሥርዓት ማለት ነው /ማቴ.፲፭፥፲፫/፡፡ ‹ሃይማኖት› ማለት ደግሞ በሀልዎተ እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር የዅሉ አስገኚ መኾኑን፣ በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት፣ በቅዱሳን ተራዳኢነት ማመን አምኖም መመስከር ማለት ሲኾን ተክለ ‹ሃይማኖት› የሚለው ሐረግም የሃይማኖት ተክል፣ ይኸውም የጽድቅ ፍሬን ያፈራ፣ ከኃጢአት ሐሩር ማምለጫ ዛፍ፣ ምእመናንን በቃለ ወንጌል ያጣፈጠ ቅመም፣ መዓዛ ሕይወቱ የሚማርክ፣ ቢመገቡት ረኃበ ነፍስን የሚያስወግድ ቅጠል፣ የጻድቃን መጠለያ ዕፅ የሚል ትርጕም አለው፡፡ ገድለ ተክለ ሃይማኖትም ‹‹ተክለ ሃይማኖት ማለት የአብ፣ የወልድ፣ የመንፈስ ቅዱስ ተክል ማለት ነው›› ሲል የጻድቁን ስም ይተረጕመዋል፡፡

ጻድቁ አባታችን ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደ ገበሬ ታጥቀው፣ ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና በመኖራቸው፤ እርሳቸው በአሚነ ሥላሴ ጸንተው ሌሎችንም እንዲጸኑና እንዲያምኑ በማድረጋቸው፤ እንደዚሁም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ በመስበክ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሰባኬ ወንጌል በመኾናቸው ‹‹ተክለ ሃይማኖት›› ተብለው ይጠራሉ፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት በእግዚአብሔር ድንቅ ጥበብ፣ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ብሥራት፤ በኢትዮጵያ ምድር በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ልዩ ስሙ ኢቲሳ በሚባል ቦታ ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኀረያ መጋቢት ፳፬ ቀን ተፀንሰው ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ፲፪፻፲፪ ዓ.ም ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስተኛው ቀን እሑድ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው ‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ፤ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፤ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤ አንዱ አብ ቅዱስ ነው፤ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ነው›› በማለት ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስም ‹‹ፍሥሐ ጽዮን›› የሚል ሲኾን ‹‹ተክለ ሃይማኖት›› ደግሞ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ያወጣላቸው ስም ነው፡፡ በተወለዱ በ፲፭ ዓመታቸው ዲቊናን፤ በ፳፪ ዓመታቸው ደግሞ ቅስናን ከግብፃዊው ጳጳስ ከአባ ጌርሎስ (ቄርሎስ) ተቀብለዋል፡፡

አንድ ቀን ወደ ጫካ ለአደን በሔዱበት ዕለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱ ክርስቶስ ተገልጦላቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱን ካሰደረባቸው፤ እንደዚሁም ሐዲስ ሐዋርያ› ብሎ ወንጌል ወዳልተዳረሰበት ቦታ እንደሚልካቸው ከነገራቸው፤ ቅዱስ ሚካኤልም ከአውሬ አዳኝነት ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመመለስ እንደ ተመረጡና አጋንንትን የማውጣት፣ ተአምራትን የማድረግ ሥልጣን እንደ ተሰጣቸው፤ ስማቸውም ተክለ ሃይማኖት እንደሚባልና ትርጓሜውም ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት እንደ ኾነ ካስረዳቸው በኋላ ወደ ቤታቸው ተመልሰው ያላቸውን ንብረት ኹሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ሰጥተው ‹‹አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደ ተከፈተ ተውኩልህ›› በማለት ቤታቸውን ትተው ወንጌልን ለማስተማር ፈጥነው ወጡ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረው በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ ብዙ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም አንጸዋል፡፡ ‹ሐዲስ ሐዋርያ› የተባሉትም በዚህ ተልእኳቸው ሲኾን፣ ትርጕሙም ሐዲስ ኪዳንን ወይም ሕገ ወንጌልን እየተዘዋወረ የሚያስተምር ሰባኬ ወንጌል፤ በክርስቶስ ስም ድንቅ ድንቅ ተአምራትን የሚደርግ የክርስቶስ ተከታይ (ሐዋርያ) ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደገበሬ ታጥቀው ይህንን ዓለም ንቀው በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና ከመኖራቸው በተጨማሪ እንደቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፣ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሚታወሱባቸው በዓላት መካከልም ታኅሣሥ ፳፬ ቀን የሚከብረው በዓለ ልደታቸው አንደኛው ነው፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር ዜና ልደታቸውን ሲናገር ‹‹ብፁዕ ወቅዱስ ሐዲስ ሐዋርያ›› በማለት በክብር ጠርቷቸዋል፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፡፡ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል፡፡ ማንም ከእነዚህ ከተናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋው አይጠፋበትም፤›› /ማቴ.፲፥፵-፵፪/ በማለት የተናገረውን መለኮታዊ ቃል ኪዳን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መሠረት አድርጋ መጋቢት ፳፬ ቀን ፅንሰታቸውን፤ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ልደታቸውን፤ ጥር ፳፬ ቀን ስባረ ዐፅማቸውን፤ ግንቦት ፲፪ ቀን ፍልሰተ ዐፅማቸውን፣ ነሐሴ ፳፬ ቀን ደግሞ ዕለተ ዕረፍታቸውን በመንፈሳዊ ሥርዓት በደስታ ታከብራለች፡፡

የአቡነ ተክለ ሃይማኖትና የኹሉም ጻድቃን ጸሎትና በረከት ረድኤትና ምልጃ በመላው ሕዝበ ክርስቲያን ላይ ለዘለዓለሙ ጸንቶ ይኑር፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡-

መለከት መጽሔት ፲፰ኛ ዓመት፣ ቍጥር ፱፡፡

መጽሐፈ ስንክሳር (ታኅሣሥ ፳፬፣ ጥር ፳፬፣ መጋቢት ፳፬፣ ግንቦት ፲፪ እና ነሐሴ ፳፬ ቀን)፡፡

ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፡፡