ትውልዱን ከሱስ ለመታደግ የቤተ ክርስቲያን ሚና

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል አማካይነት በተዘጋጀው የዐውደ ጥናት ጉባኤ ታኅሣሥ ፳፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በማኅበሩ ሕንጻ ፫ኛ ፎቅ አዳራሽ በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ከሱስ የነጻ ትውልድ ለመፍጠር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሚና ከፍተኛ መኾኑ ተገለጸ፡፡

ዶ/ር

ዶክተር ጃራ ሰማ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ

በጉባኤው ‹‹ከሱስ የነጻ ትውልድ ለመፍጠር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሚና›› በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት የሕክምና እና የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያው ዶክተር ጃራ ሰማ የአልኮል መጠጦች፣ አደንዛዥ ዕፀዋት፣ አሽሽ፣ ትንባሆ፣ ሻይ፣ ቡና፣ የለስላሳ መጠጦች፣ ልዩ ልዩ መድኀኒቶችና የመሳሰሉት ልምዶች፤ እንደዚሁም የኢንተርኔት አገልግሎት፤ በተመሳሳይ መልኩ ሰዶማዊነት፣ ወደ ዝሙት ተግባር የሚወስዱ ፊልሞችን በዓይን ማየትና በድምፅ መስማት፣ እንደዚሁም ራስን ለፍትወተ ሥጋ ማነሣሣት በተደጋጋሚና በብዛት ከተወሰዱ ወይም ከተተገበሩ ሱስ ሊያስይዙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

ከዚሁ ዅሉ ጋርም ሳውና ባዝ፣ ስቲም ባዝና ሞሮኮ ባዝን ጨምሮ ሌሎች የመታሻ ሥፍራዎችና ጂም ቤቶችም ሱስን ሊያስይዙ የሚችሉ የምቾትና የድሎት አገልግሎቶች መኾናቸውን ጥናት አቅራቢው አስረድተዋል፡፡ ሱስ በድርጊት በመፈጸምና በመቅመስ ብቻ ሳይኾን በማየት፣ በመስማት፣ በመዳሰስ ወይም በመንካት እንደሚፈጸም ያስረዱት ጥናት አቅራቢው በማሽተት ከሚፈጸሙ ሱስ አምጪ ተግባራት መካከልም ቤንዚን፣ ትምባሆ፣ ሲጋራና ማስቲሽ የማሽተት ሱስን እንደ ምሳሌ አድርገው አቅርበዋል፡፡

ሱስ የሰውን ልጅ አእምሮውንና አካሉን በአግባቡ የማይጠቀም፤ የፈዘዘ፣ የደነዘዘ እንዲኾን ያደርጋል ያሉት ባለሙያው ሱሰኝነት ትዳር እንዲፈርስ፣ ቤተሰብ እንዲበተን፣ ክርስቲያናዊ ሕይወት እንዲላላ፣ የማይታመን ራእይ አየን የሚሉ የሐሰት ባሕታውያን እንዲበዙ፣ ሽብርተኝነት እንዲስፋፋ፣ ወዘተ. በማድረግ ከግለሰብ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያንና በአገር ላይ የሚያደርሰው ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት ከፍተኛ መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡

የአእምሮ መታወክ፣ ጭንቀትና ውጥረት፣ የአስተዳደግ ችግር፣ የጓደኛ ተፅዕኖ፣ ቤተሰባዊ ግጭት፣ ሴሰኝነት፣ በኑሮ የሚያጋጥም ዕዳና ኪሳራ፣ ሥራ አጥነት፣ ወዘተ የመሳሰሉት አጋጣሚዎች ለሱስ የሚዳርጉ መሠረታዊ ጫናዎች መኾናቸውን ያመላከተው የዶ/ር ጃራ ጥናት ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ፣ የግብረ ገብ ትምህርቶችን በመማርና ሥልጠናዎችን በመውሰድ አመለካከትን መለወጥ (የእይታ አድማስን ማስፋት)፤ እንደዚሁም ማኅበራዊ ግንኙነትን ማሳመርና ሓላፊነትን ማሳደግ ከሱስ የማምለጫ መንገዶች መኾናቸውን ያስረዳል፡፡

tinat

የጥናቱ ታዳሚዎች በከፊል

የሰው ልጅ ከአምላኩ ውጪ በእርሱ ላይ አንዳች ኃይል ሊሠለጥንበት የማይችል በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ከፍጡራን ዅሉ የላቀ ክቡር ፍጥረት መኾኑን በጥናታቸው ያስታወሱት ዶ/ር ጃራ ሰማ የሰው ልጅ ክብሩን አዋርዶ ይሠለጥንባቸው ዘንድ የተሰጡት ፍጥረታት በእርሱ ላይ እንዲሠለጥኑ ከፈቀደ በምድር በኀጢአት አረንቋ ወድቆ እንደሚኖር፤ በዚህም ራሱን እንደሚበድልና የፈጠረውን አምላክም እንደሚያሳዝን ገልጸው ትውልዱ የተፈጠረለትን ዓላማ በመረዳት ወደ ሱስ ከሚወስዱ ነገሮች ራሱን መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ምእመናንን ከልጅነታቸው ጀምሮ በሰንበት ት/ቤት፣ በማኅበር፣ በዐውደ ምሕረት፣ በኅትመት ውጤቶችና በሌላም ልዩ ልዩ መንገድ ግብረ ገብነትን በማስተማር፤ ወደ ሱስ የገቡትንም በሱባዔ፣ በቀኖና፣ በንስሐ፣ በጠበልና በሥጋ ወደሙ አማካይነት ፈውስን እንዲያገኙና በመንፈሳዊውም ኾነ በዓለማዊው ሕይወታቸው ጤናማ ኾነው እንዲኖሩ በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያበረከተችው ሚና ከፍተኛ መኾኑን የጠቀሱት ጥናት አቅራቢው ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል የተዘጋጀ መዋቅራዊ አደረጃጀት ባለመኖሩ፣ ካህናት ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር ተቀናጅተው ባለመሥራታቸው፣ ሱሰኞች ከሱስ ከወጡ በኋላ የሚቋቋሙበት ተቋም ባለመመሥረቱ፣ በጉዳዩ ላይ በቂ ጥናትና ምርምር ባለመደረጉ፣ የሚድያ ሽፋን ባለማግኘቱና በጀት ባለመመደቡ የተነሣ ቤተ ክርስቲያናችን ሓላፊነቷን በአግባቡ እንዳትወጣ ካደረጓት ምክንያቶች መኾነቻውን በጥናታቸው ዳሰዋል፡፡

ዶ/ር ጃራ ሰማ በጥናታቸው ማጠቃለያም ‹‹ምእመናን በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ብቻ ሳይኾን በማኅበራዊ ኑሯቸውም ከሌሎች ጋር ተስማምተው በፍቅር፣ በቅንነት፣ በሰላምና በአንድነት እንዲኖሩ የማስቻል ከማንም በላይ ከአምላክ ዘንድ የተሰጣት መንጋዋን ከጥፋት የመጠበቅ ከፍተኛ ሓላፊነት እንዳለባት ቤተ ክርስቲያናችን ተገንዝባ የአሠራር ችግሮችን በመቅረፍ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ሰጥታ መሥራት ይገባታል›› ብለዋል፡፡