ዘመነ ፍሬ

ዲያቆን ዘክርስቶስ ፀጋዬ

ከመስከረም ፱ እስከ ፲፭ ያሉት ዕለታት ዘመነ ፍሬ ተብለው ይጠራሉ፡፡ በእነዚህ ወቅት የሚዘመረው መዝሙርም ሆነ የሚነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እግዚአብሔር ለምድር ፍሬንና ዘርን የሚሰጥ የዓለም መጋቢ መሆኑን የሚያስገነዝቡ ናቸው፡፡ ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር አምላክ በጥንተ ፍጥረት በሦስተኛው ቀን /ዕለተ ሠሉስ/ ማክሰኞ  ‹‹ምድር ዘር የሚሰጥ ሳርና ቡቃያን ታውጣ›› በሚል ቃሉ ምድር እህል ዘርና አትክልትን በየወገኑ የሚያፈሩ ጠቅላላ የምድር እንጨትንና ሣርን ፈጥሯል፡፡ (ዘፍ.፩፥፲፩-፲፫)

የዚህ ዓለም አዝርዕትና አትክልት በራሳቸው ፍሬ የሚያፈሩ አሉ፤ በጎናቸው ፍሬ የሚያፈሩ አሉ፤ እንደዚሁ በሥራቸውም የሚያፈሩ አሉ፡፡ እነዚህ የሰው ልጆች በዚህ ዓለም ስለሚያፈሩት መልካም ፍሬ ማሳያዎችና ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እነርሱም፡- በራሳቸው የሚያፈሩት፤ በራሳቸው ምክር፤ ጥረት እግዚአብሔርን ረድኤት አድርገው ክብር የሚያገኙ ሰዎች ምሳሌ ሲሆኑ፤ በጎናቸው የሚያፈሩ በወንድማቸው፤ በዘመዳቸው ምክር በፈጣሪ ረድኤት ክብር የሚያገኙትን ያመለክታል፡፡ በሥራቸው የሚያፈሩት ደግሞ በልጆቻቸው፣ በሎሌዎቻቸውና በገረዶቻቸው ምክር ክብር የሚያገኙ ሰዎች ናቸው፡፡ እኛስ  በየትኛው ምክር ክብር የምናገኝ ነን? በራሳችን፣ በታላቆቻችን ወይስ በታናሾቻችን?

የዘመነ ፍሬ ንዑስ ክፍል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማርቆስ ወንጌል በምዕራፍ ፬፥፳፬ ላይ ስለ ዘርና ስለ መከር ያስተማረው ምሳሌያዊ ትምህርት የሚሰጥበት ወቅት ሲሆን የሚሰበከውም ምስባክ ‹‹ምድርኒ ትሁብ ፍሬሃ፣ ወይባርከነ እግዚአብሔር አምላክነ፤ ወይፈርህዎ ኲሎሙ አድናፈም ምድር፤ ምድር ፍሬዋን ሰጠች፤ እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል፡፡ የምድርም ዳርቻ ሁሉ ይፈሩታል፡፡›› የሚለው ነው፡፡ (መዝ. ፷፮፥፮፤ ፹፬፥፲፪) ይህም ምድር ፍሬዋን እንደምትሰጥ እግዚአብሔርም እየመገበ እንደሚባርከን ያስገነዝባል፡፡

በዘመነ ፍሬ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ምድር ስለምታበረክተው ፍሬ እግዚአብሔር ፍሬውን እንዲባርክና እንዲያበዛ ትጸልያለች፤ትዘምራለች፡፡ በምድር የበቀሉት አዝርዕቱና ዕፀዋቱ ፍሬ አፍርተው ፍሬያቸው ግልጽ ሆኖ አዕዋፍ የሚበሏቸው አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ፍሬ አፍርተው ፍሬያቸው ስውር ሆኖ አዕዋፍ ሳይጠረጥሯዋቸውና  ሳይበሏቸው የሚኖሩ አሉ፡፡  ፍሬን፣ አዝርዕቱና ዕፀዋቱ በዚህ መልክ ሲሰጡ፤ ከምድር የተገኘን እግዚአብሔር  እኛ የሰው ልጆች አሁን ባለንበት ዘመን ፍሬያችን ምን ይመስላል? በተለይ በጥምቀት ልጅነት ያገኘን እኛ? ፍሬያችን እንዴት ነው?  አምላካችን እግዚአብሔር የምንሰራውን ሥራ እንዲባርክልን፣ ዋጋችንንም በግልጥ እንዲከፍለን፣ ለንስሓ የሚገባውን ፍሬ ማፍራት እንድንችል በዘመነ ፍሬ ወቅት አዝርዕቱ፣ ዕፀዋቱ አትክልቱ እና የምድር አበቦች ያስተምሩናል፡፡

ቅዱስ ያሬድም በመዝሙሩ ‹‹እኩት አንተ ወስቡሕ ስምከ ወዐቢይ ኀይልከ፤ ዘተዐርፍ በአርያም ወትሴባሕ በትሑታን ዘአንተ ሠራዕከ ሰንበተ ለዕረፍት፣ወወሀብከ ሲሳየ ዘበጽድቅ ለኩሉ፡፡ እግዚኦ ባርክ ፍሬሃ ለምድር፡፡ መሓሪ ወጻድቅ መኑ ከማከ፣ዘታርኁ ክረምተ በጸጋከ፤ነፍስ ድኅነት ወነፍስ ርኅብት እንተ ጸግበት ተአኩተከ››፡፡ አንተ ምስጉን ነህ፤ስምህም የተመሰገነ ነው፤ኃይልህም ታላቅ ነው፡፡ በአርያም የምትኖር በትሑታን የምትመሰገን አንተ ነህ፡፡ ሰንበትን ለዕረፍት የሠራህ ለሁሉም በእውነት ምግብን የምትሰጠው አቤቱ የምድርን ፍሬ ባርክ፡፡ ቅዱስና መሓሪ አምላክ ሆይ! እንደ አንተ ያለ ማን ነው? ክረምትን በጸጋህ ታፈራርቃለህ፤ የዳነች ነፍስ በልታ የጠገበችና የተራበች ነፍስም አንተን ታመሰግናለች›› በማለት የእግዚአብሔርን መጋቢነት፣ ለምድር ፍሬን የሚሰጥ፣ ለተራቡት እንጀራን የሚመግብ፣ ክረምትን በጋን የሚያፈራቅ መሆኑን ቅዱስ ያሬድ ገልጾ  አመስግኗል፡፡

በመጽሐፈ ቅዳሴም ‹‹ትጸውር ኲሎ እንዘ ኢትደክም፤ ትሴሲ ለኩሉ እንዘ ኢተሐጽጽ፤ ትኄሊ ለኩሉ እንዘ ኢታረምም… ወበእንተ ፍሬ ማዕረር ዘአክሊለ ዓመት ከመ ይትባረክ በምሕረትከ….ሳትደክም ሁሉን ትሸከማለህ፤ ሳታጎድል ለሁሉ ትመግባለህ፤ ዝም ሳትል ለሁሉ ታስባለህ….. በየዓመቱ ስለሚያፈራ ስለመከሩ ፍሬ በምሕረትህ ይባረክ ዘንድ እንለምንሃለን….›› ቅዳሴ ዘወልደ ነጎድጓድ (ኅቤከ) በዚህ ወቅት የሚነበብ መጻሕፍት ሁሉ ዘመነ ፍሬን የሚያሳዩና ወርኀ ፍሬን የሚሰብኩ ናቸው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በየወቅቱ እግዚአብሔርን ታመሰግናለች፡፡ እኛም ዘወትር በሕይወታችን በምስጋና በውዳሴ በቅዳሴ ልንተጋ ይገባል፡፡

ዘመነ ፍሬ አሁን ባለንበት በዚህ ዘመን የእርስ በርስ መለያየት፣ ዘረኝነት፣ በበዛበት ጊዜ ኦርቶዶክሳዊነታችን ምን ዓይነት ፍሬ እያፈራ እንደሆነ እንድንመረምር ያሳስበናል፡፡ ሁለት ልብ ያለን በመንገዳችን እንዳንታወክ፣ ሥጋ የለበስን ሁላችን እንደ ምድረ በዳ አበቦች
ነንና እንዳንጠወልግ እንዳንደርቅም የሚገባውን (፴፣፷፣፻) ያማረ ፍሬ ለማፍራት በመልካምና በበጎ ልብ ቅዱስ ቃሉን መስማት፣ መጠበቅ እና መጽናት ይጠበቅብናል፡፡ ለምድር ፍሬን የሚሰጥ፣ ለገበሬ ዘርን፣ ዘመኑን ፍሬ ያስጌጠ፣ የፍሬን ዘመን ያዘጋጀ እንጀራን ከምድር የሚያበቅል መጋቢ እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባናል፡፡

መንፈሳዊ ፍሬ አፍርተን በምስጋና ተግተን ከቅዱሳን መላእክት እና ከጻድቃን ጋር እንድንደመር አምላከ ቅዱሳን ይርዳን፡፡