‹‹ዑራኤል የተባለ መላእክ ሊረዳኝ መጣ›› (ዕዝ.ሱቱ ፪፥፩)

ሐምሌ ፳ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በነገደ መላእክት ከተሾሙት ሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ቅዱስ ዑራኤል የቅዳሴ ቤቱ የሚከበርበትና ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል የዕውቀትን ጽዋ ያጠጣበት ዕለት ሐምሌ ፳፪ በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፡፡

በመከራ ጊዜ ረዳት የሆነው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ዑራኤል በዘመናት ለነገሡ የሀገራችን ነገሥታት ያደረገውም ውለታ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ዳግማዊ ቆስጠንጢኖስ የተባለ ንዋየ ማርያም በነገሠበት ዘመነ መንግሥት ቅዱስ ዑራኤል በጸሎቱ በመራዳትና እስከ ግዛቱ ፍጻሜ ባለመለየት ሀገሩን እንዲመራ አድርጓል፡፡ ንጉሡም ሃይማኖቱ የቀና እና የአምላክን እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የሚወድ ስለነበር ኢትዮጵያን በቀናች ሃይማኖት ሊመራት ችሏል፡፡

ይህም ንጉሥ አስቀድሞ በወንጌላዊው ሉቃስ እጅ የተሳሉትን የእመቤታችን ስዕሎች ከኢየሩሳሌም በማስመጣት አንዲቱን ስዕል ቅዱስ ዑራኤል በአምላካችን ደም በቀደሳት ጎጃም ውስጥ በምትገኘው ጀብላ ተብላ በምትጠራ ስፍራ አስቀምጦ ነበር፡፡ ሁለተኛውን ስዕል በደብረ ወርቅ ካስቀመጠ በኋላ ሦስተኛውን ደግሞ በሐይቅ ውስጥ አኑሯታል፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ የሳለውን የቅዱስ ዑራኤልን ስዕል ግን በከተማው ውስጥ በወርቅ ግምጃ በተሠራ ድንኳን ውስጥ ከእርሱ ጋር አኑሮታል፡፡ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቀይ ግምጃ ልብሱን ደግሞ ቅዱስ ዑራኤል በጌታችን ደም በቀደሳት በአምባሳል ሀገር በክብረ ነገሥት ደብር ውስጥ አስቀምጦታል፡፡ ደብሩም ከከበሩት አድባራት ሁሉ ይልቅ ክብሩ ከፍ ያለ ስለነበር ደብረ ከርቤ ተብሎ ተሰይሟል፡፡

ንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ደግሞ በዘመነ መንግሥቱ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና ቅድስት ድንግል ማርያም ስም ከሠራቸው ቤተ ክርስቲያናት በተጨማሪ በቅዱስ ዑራኤል ስም ቤተ ክርስቲያን በደብረ ብርሃን በማሠራት የመልእኩ ስም እንዲጠራና ክብረ በዓላቶቹ እንዲከበሩ አድርጓል፡፡ ይህም ንጉሥ እስላሞች የከበረ ወርቆችን ለመውሰድ ፈልገው ሳይሳካላቸው ሲቀር የእስክንድርያውን ሊቀ ጳጳ አባ ሚካኤልን አስረው በግብጽ የሚገኙ አብያተ ቤተ ክርስቲያናትን በእሳት ባቃጠሏቸው ጊዜ ሰምቶ ወደ ግብጽ በመሄድ ተዋጋቸው፡፡ በእመቤታችን ድንግል ማርያም ረዳትነትና በቅዱስ ዑራኤልም አማላጅነት የእስላሞቹን ንጉሥ አሕመድን እንዲሁም የአዳልንና የጥልጣል ባላባት በድላይንንም ገደላቸው፡፡ አባ ሚካኤልን ደግሞ ከእስራቱ ፈትቶ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ይዞት መጥቷል፡፡ መስቀሉንም አባቱ ዳግማዊ ዳዊት ባሳነጸው ሕንጻ ውስጥ በድብረ ከርቤ እንዲቀመጥ አድርጓል፡፡ ንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ንግሥት ዕሌኒ በእመቤታችን ስም ቤተ ክርስቲያናን እንድትሠራ ካደረገ እና ሥርዓተ ቅዳሴው ከተፈጸመ በኋላ ጌታችን ተገልጾላቸው በቀራንዮ በተሰቀለ ጊዜ ከጐኑ በፈሰሰው ደሙ ቅዱስ ዑራኤል ደብሯን ቀድሷታል፡፡

ከዚህም በመቀጠል ንጉሡ በደብረ ብሥራት ሁለት ቤተ ክርስቲያን ሠራ፡፡ እንዲሁም በቀኝዋ ሁለት ቤተ ክርስቲያናት በመሥራት አንደኛዋን ሰይፍ አጥራ ብሎ ሰይሟታል፡፡ የዚህም ምክንያት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኗ በተጀመረ ጊዜ ቅዱስ ዑራኤል ከእሳታውያን መላእክት እና ከእመቤታችን ጋር የእሳት ሰይፎችን ይዘው በክንፎቻቸው አጥረዋት ስለተመለከተ ነበር፡፡ ሁለተኛዋን ቤተ ክርስቲያን ደግሞ እድ አጥራ ብሎ ሰይሟታል፡፡ ንጉሡም ከዚህ በኋላ ሌሎች ቤተ ክርስቲያናትን ሠርቷል፡፡

የዚህም ንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ልጅ እደ ማርያም በነገሠ ጊዜ በቅዱስ ዑራኤል ስም ቤተ ክርስቲያንን አሠርቷል፡፡ ለበዓሉ መታሰቢያም ይሆን ዘንድ ለደብሩ ዐርባ ዐራት ርስተ ጉልትን ሰጥቷል፡፡ የደብሯንም ስም ምስዓለ ማርያም ብሎ ሰይሟታል፡፡ ይህም ንጉሥ የአባቱን ፈለግ ተከትሎ ሌሎችን ቤተ ክርስቲያናትን ሠርቷል፡፡ ከንጉሥ ይኩኖ አምላክ ጀምሮ እስከ ንጉሥ ናዖድ ድረስ ያሉትን ዘጠኙ ቅዱሳን አባቶችና ነገሥታት የሥራቸውን ዜናና የቀናች ሃይማኖታቸውን ጽንዓት በድርሳነ ዑራኤል ተጽፏል፡፡

የክርስቲያን ወገኖች የሆንን በሙሉ የዚህን ተረዳኢ መልእክ ቅዱስ ዑራኤል በዓል ልንዘክር ይገባል፤ እርሱ እኛን በግልጥና በስውር ከሚመጣ ጠላት ከክፉ ነገር ሁሉ የሚጠብቀን ነውና፤ እንደ ጥላና እንደ በረሃ አበባ ከሚጠፉው ከዚህ ኃላፊው ዓለምና ከጽኑ ጠላት ያድነናል፡፡ አምላካችን የድንግል ማርያም ልጅ በአባቱ ምስጋና በሚመጣበት ጊዜ በቅዱስ ዑራኤል አማካኝነት ከዘለዓለማዊ ሞት ይታደገናል፡፡

ዓለማችን በኃጢአት ማዕበል ተውጣ እንዲህ በጭንቅና ጣር ላይ ባለችበት በዚህ ጊዜ በውስጧ የምንኖር ሰዎች ይህን መከራና ሥቃይ ተቋቁመን ለማለፍ የሚቻለን በቅዱሳን አማላጅነት ተራዳኢነት ነው፡፡ በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ውሎ ማደር እንዲሁም መኖር ያቃተን እጅግ በርካታ ሰዎች ልንኖር እንችላለን፡፡ በዚህም ሳቢያ ተስፋ ቆርጠንና ከያዝነው እውነተኛ መንገድ ወጥተን ወደ ጨላማው ሕይወት እንዳንገባ ምርኩዝ ድጋፍ የሚሆነን የእነርሱ ጸሎት ነው፡፡ ምንም ቢሆን ከክፋት ለመራቅና በኃጢአት ከመውደቅም ሊጥለን የሚፈታተነን ጠላት መዋጋት ያስፈልጋል፡፡ መሣሪያችንም ጸሎት፣ ጾምና ስግደት በመሆኑ በእነዚህ ሁሉ ምግባራችንም የቅዱሳኑ አምላጅነት ስለሚያስፈልገን ተግተን እነርሱን ልንማጸናቸው ይገባል፡፡

የመላእክት አለቃ ቅዱስ ዑራኤል የጸሎቱና የረዳትነቱ ኃይል አይለየን፤ አሜን!

ምንጭ፡- ድርሳነ ዑራኤል ዘሐምሌ