ወጣትነት እና የኮሮና ቫይረስ በሽታ ስርጭት
 

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ

ሰው በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል ተፈጥሯል፣ይህም ከጥንተ ተፈጥሮ በበለጠ በአዲስ ተፈጥሮ እግዚአብሔር ሰውን ምን ያክል እንደወደደው በልጁ የማዳን ሥራው ላይ በወንጌል ተምረናል።

የሰው ልጅ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ከውሃ፣ ከነፋስ ከእሳት እና ከመሬት እንዲሁም ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ፣ ነባቢት ለባዊት ሕያዊት በሥላሴ እጅ የተበጃጀ ልዩ ፍጡር ነው። ከሥላሴ ልጅነትን ካገኘ በኋላ በምግባር በትሩፋት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚጓዝ እና የሚመራ ከሆነ መንፈሳዊ ሰው ይባላል። ወደ ዋናው ጉዳይ ስንመጣ ወጣትነት ማለት ባሕርየ እሳት የሚሰለጥንበት፣የአሸናፊነት ዘመን ሲሆን ወጧቶች በዚህ ትኩስ ኀይላቸዉ እንደ ዳንኤል ሰበብና በደል የማይገኝባቸዉ ምስጉኖች፣ እንደ ዮሴፍ በጥበብና በሃየማኖት ለሀገር እና ለቤተ ክርስቲያን ፍቅር ያላቸው ሊሆኑ የገባል። (ዳን ፩÷፩-፵፱፣፫÷፩)

ኮሮና ቫይረስ (COVID-19) በሀገረ ቻይና ሁቤ ግዛት ሁዋን ከተማ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ታኅሳስ ፱ ቀን ፳፻፲፱ የተከሰተ ሲሆን በሽታውም የሰው ልጅን የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃ ብሎም ለሞት የሚዳርግ፣ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነ አደገኛ በሽታ ነው። ከበሽታው ዋና ዋና ምልክቶቹ መካከል አፍንጫን ማያረጥብ፣ ደረቅ ሳል፣ አልፎ አልፎ ማስነጠስ ፣ከፍተኛ የሙቀት መጠን[ትኩሳት፣የትንፋሽ ማጠር፣ እንዲሁም የጉሮሮ ሕመም የመሳሰሉት ናቸው። የመተላለፊያ መንገዶቹ ደግሞ በሽታው ከያዘው ሰው ጋር ንክኪ፣ በሽተኛው ከነካቸው ማናኛውም ቁሳቁሶች ጋር ንክኪ ካለ በአጠቃላይ በትንፋሽ እና በንክኪ ይተላለፋል። የመከላከያ መንገዶቹ ደግሞ እጅን ቶሎ ቶሎ ለ! ስኮንዶች ፍትግ አድርጎ መታጠብ፣ ከሚያስል እና ከሚያስነጥስ ሰው ቢያንስ ሁለት ሜትር መራቅ፣ አለመጨባበጥ እጅ መንሳት ፣ ባልታጠበ እጅ ዐይን፣ አፍንጫና አፍን አለመንካት፣ማስክ (የፊት መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ)፣ብዙ ሰው በተሰበሰበበት ቦታ አለመገኘት፣ የግልንም ሆን የአካባቢ ንጽሕናን መጠበቅ እንዲሁም ከቤት ባለመውጣት መከላከል እንችላለን። ከዚህ በተጨማሪ በጠቅላላ የ“መ”ሕጎችን ጠንቀቆ ማወቅና መተግበር አስፈላጊ ነው፡፡ የ “መ” ሕጎችን የምንላቸው ደግሞ መቆየት፤ መጠቀም፤ መታጠብ እንዲሁም መራራቅ ናቸው፡፡ እነዚህን ሕጎች በጥንቃቄ በመተግበር የበሽታውን ስርጭት መከላከልና መግታት ይቻላል፡፡
ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ በሽታው ከገባ ጀምሮ ስርጭቱ እየጨመረ መምጣቱ የሚታወቅ ሲሆን ለዚህ ዋነኛ ምክንያቶች ደግሞ በማኅበረሰባችን በተለይም በወጣቱ ትውልድ ቸልተኝነት “እኛን አይዘንም፣ቢይዘንም ለሞት አይዳርገንም “ብሎ መዘናጋት ፣ስለ በሽታው ወጥ የሆነ የግንዛቤ እጥረት አለመኖሩ ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው።

በዓለም ጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ትንተና መሠረት ፹% የሚሆኑት በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች በቀላሉ የጤና ባለሙያዎችን እገዛ እና ድጋፍ ሳያገኙ የሚድኑ ሲሆኑ፣ ፭% ደግሞ የጤና ባለሙያዎችን እገዛ እና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፣ ፭% ደግሞ በጽኑ ሕሙማን መታከሚያ የሚታገዙ ናቸው። እንደ ቻይና እና ጣሊያን እንዲሁም አሜሪካ ሪፖርት መሠረት አብዛኞቹ በበሽታው የሚጠቁትም ሆነ የሚሞቱት ዕድሜያቸው ከ፷ ዓመት በላይ የሚሆኑት ሲሆን እንደ እኛ ሀገር የበሽታው ስርጭት ደግሞ አብዛኞቹ የተያዙት ከ፲፬-፵ አመት ዕድሜ ያሉት መሆኑ የጤና ሚኒስተር እና የማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ያመለክታል፡፡ በዚህም መነሻነት አንዳንድ ወጣቶች በሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር እና በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ መመሪያዎችና መልእክቶችን ወደ ጎን በመተውና በሽታው ወጣትን አያጠቃም በሚል አጉል ብሂል በመነሳሳት ወጣቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተዘናጋ ይገኛል፡፡ የበሽታው እውነታ ግን ሌላ ነው፡፡ ኮሮና የትኛውንም የዕድሜ ክልል ማጥቃት እንደሚችል በሀገራችንም ሆነ በሌላው ዓለም መታዘብ ችለናል፡፡ በሽታው እንድሚታወቀው ዘር፤ ቀለም፤ የሀብት መጠን፤ እንዲሁም የዕድሜን ክልል የሚመርጥ አይደለም፡፡ ያገኘውን የሰው ዘር ሁሉ ያጠቃል፤ ባስ ሲልም ለአጣዳፊ ሕመምና ሞት ያጋልጣል፡፡ ይሁንና ዓለምን እያስጨነቀ ያለውን ይህን አደገኛ ወረርሽኝ ለመከላከል ወጣቶችም ሆኑ ሌላው የሰው ዘር ሁሉ ማድረግ የሚገባውን ነገር ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡

ሀ. ፈቃደኛ መሆን
ፈቃደኛ መሆን ማለት ማንኛውንም ነገር ለማከናወን እና እንዲከናወንልን ስንፈልግ በቅድሚያ የራስ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ መረዳት ያስፈልጋል። በወንጌል እንደተማርነው የእኛ የመዳናችን ምክንያት የሆነችው እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ ሲላት የእርሷ ፈቃደኝነት ወሳኙን ቦታ እንደያዘ እንረዳልን። እኛ ወጣቶችም በተለያዩ የሃይማኖት አባቶች እና የሕክምና ባለሙያዎች የሚነግሩንን እና የሚያስተላልፉልንን መልእክት መቀበልና መተግበር ይገባናል።

ፈቃደኛ ካልሆንን መዳን አንችልም። ‹‹እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤እምቢ ብትሉ ግን ብታምፁ ሰይፍ ይበላችኋል።›› እኔን፣እኛን ወጣቶችን አይዘንም በማለት በራስ የመተማመን ብቃት ብንይዝም የሚነገረንን በፈቃደኝነት መተግበር ካልቻልን አደጋው እየከፋ እንደሚሄድ መገንዘብ አለብን። (ሉቃ.፩፥፴፩፣ በኢሳ.፩፥፲፱-፳)

ለ. ከሌሎች መማር
ቅዱስ ዳዊት ‹‹ለድኅነቴም መታመኛን ሰጠኸኝ፣ ቀኝህም ትረዳኛለች፣ትምህርትህም ለዘለዓለም ታጽናናኛለች፤ተግሣጽህም ታስተምረኛለች›› እንዳለን እኛም አሁን ዓለም ባለችበት ደረጃ ብዙ የምንማራቸው ነገሮች አሉ። ሌሎች ሀገራት በሚያዩት ነገር ተምረው ማኅበረሰባቸውን ከወረርሸኙ መከላከል እንደቻሉ ሁሉ አንዳንድ ሀገራትም በመዘናጋት እና ከሌሎች ባለመማራቸው ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን ከሌሎች ተምረን ወገኖቻችንንና ሀገራችንን ከጥፋት የምንታደግበት ወቅት ላይ ነው የምንገኘው። (መዝ. ፲፯፥፴፭)

ጠቢቡ ሰሎሞን “መልካም ትምህርት እሰጣችኋለሁ ሕጌን አትተው” እንዳለን እኛም በተለያዩ ማስተማሪያ መንገዶች የሃይማኖት ተቋማት እና የጤና ባለሙያዎች አውጥተው እያስተማሩን ስለሆነ እኛም የሚያስተምሩንን እንደ ሕግ ወስደን ወረርሽኙን ልንከላከለው የገባናል። በዚህም ከሌሎች ጥፋት መማር ብልህነት ነው። (ምሳ. ፬፥፪)

ሐ. መወሰን
የሚወስን ሰው ፈቃደኛ ሆኖ ከሌሎች ተምሮ ነውና እኛም መወሰን ከቻልን የጤና ባለሙያዎችን እየረዳናቸው መሆኑን እንረዳለን፡፡ እነርሱን ስንረዳም በዙሪያችን ያሉና የምንወዳቸውን ወገኖቻችንን ከወረርሽኑ ታደግን ማለት ነውና፡፡ የወሰነ ማን ነው ይለናል ውሳኔ ብዙ ዓይነት ቢሆንም እኛም አሁን ዓለምን እያስጨነቀ ያለው ወረርሽንን ለማጥፋት ከራሳችን ጀምረን ልንወስን ይገባል። የዚህ ወረርሽን መከላከያ ናቸው ተብለው የተዘረዘሩትን ተግባራዊ በማድረግ በሽታውን በጋራ ሁነን ለማጥፋት የግል ድርሻችንን መወጣት ተገቢ ነው፡፡ (ኢሳ. ፳፫፥፰)

መ. በደስታ ማድረግ

ከላይ የዘረዘርናቸውን ተግባራዊ ስናደርግ ውስጣዊ ሰላም እና ደስታ ይሰማናል። ከሰው የሚጠበቀውና የሚፈለገው ትልቁ ውጤት ደግሞ ምግባር ነው፡፡ ‹‹ተርቤ አላበላችሁኝም›› ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም፣ ታርዤ አላለበሳችሁኝም፣ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝም፣ ታስሬ አላስፈታችሁኝም›› ነውና ተብሎ የተጻፈልን (ማቴ.፳፭፥፴፭-፴፮)፡፡ ይህ ሁሉ ምግባር ነው፡፡ የሐሳብ ጥያቄ ሳይሆን የሥራ ጥያቄ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ስለተራበ፣ ስለተጠማ፣ ስለታረዘ ሰምተዋል፡፡ ለእነዚህ ሰዎችም በጎ ሥራ መሥራት እንዳለባቸውም አምነዋል፣ ወስነዋል፡፡ ግን ካላደረጉት ጥቅም የለውም፡፡ አንድ ሰው ስላመነ፣ ስላወቀ፣ ስለተማረ፣ እና ስለ እግዚአብሔር ቃል በሚገባ ስላጠና የተማረውንና ያወቀውን ወደ ምግባር ካልቀየረው ምንም ጥቅም የለውም፡፡ ሆኖም ምንም ያለ ማድረግ ራሱ ኀጢያት መሆኑን የተገነዘበ ሰው ‹‹ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚያ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁ ለእኔ አደረጋችሁት›› ብሎ ያዘጋጀልንን መንግሥት በቸርነቱ እንድሚያወርሰን እያሰብ ለመልካም ይፋጠናል፡፡ እንደምንወርስ አስተምሮናል። ስለሆነም አምላካችን እግዚአብሔር የነገረንን ያስተማረንን ስንጠብቅ እሱ ይጠብቀናል ነገር ግን እኛ ወጣቶች ስለሆንን በሽታው አይዘንም፣ አያጠቃንም እና አንሞትም ሳንል በየጊዜው ለሚወጡ ሃይማኖታዊ እና የጤና ባለሙያ ሕጎች ፈቃደኛ በመሆን፣ ከስሕተቶቻችን በመማር እና በውሳኔያችን በመደሰት ሀገራችን ብሎም ዓለምን ከወረርሽኑ እንዲታደግልን አምላካችን እግዚአብሔርን በሙሉ ልባችን ልንማጸን ይገባል፡፡