ክርስቲያናዊ ኑሮ በዘመነ አስተምሕሮ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ታኅሣሥ ፲ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በቤተ ክርስቲያናችን የወቅት አከፋፈል ሥርዓት ከኅዳር ፮ እስከ ታኅሣሥ ፯ ቀን የሚገኘው ወቅት ‹ዘመነ አስተምህሮ› ይባላል፡፡ ቀጣዩ ወቅት (ዘመነ ስብከት) ዕለተ ሰንበትን ጠብቆ የሚገባ በመኾኑ ይህ ወቅት አንዳድ ጊዜ እስከ ታኅሣሥ ፲፫ ቀን የሚዘገይበት ጊዜም አለ፡፡ ‹ዘመነ አስተምህሮ› የሚለው ሐረግ ትርጕሙም በሃሌታው ‹ሀ› (‹አስተምህሮ› ተብሎ) ሲጻፍ የቃለ እግዚአብሔር ማስተማሪያ ማለትም የትምህርተ ወንጌል ዘመን ማለት ነው፡፡ ሥርወ ቃሉም ‹‹መሀረ/አምሀረ – አስተማረ፤ ለመምህር ሰጠ፤  መራ፤ አሳየ፤ መከረ፤ አለመደ›› ወይም ‹‹ተምህረ – ተማረ፤ ለመደ›› የሚለው የግእዝ ግስ ነው (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፭፻፸፱)፡፡ 

ይኸውም የእግዚአብሔርን ቸርነት፣ ርኅራኄ፣ ትዕግሥትና የማዳን ሥራውን የሚመለከት ትምህርት በስፋት የሚቀርበበት ጊዜ ነው፡፡ ቃሉ በሐመሩ ‹‹ሐ›› (‹አስተምሕሮ› ተብሎ) ሲጻፍ ደግሞ የምሕረት፣ የይቅርታ ዘመን ማለት ነው፡፡ ሥርወ ቃሉም ‹‹መሐረይቅር አለ፤ ዕዳ በደልን ተወ›› ወይም ‹‹አምሐረ – አስማረ፤ ይቅር አሰኘ፤ አራራ፤ አሳዘነ›› የሚለው የግእዝ ግስ ነው (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፭፻፹፬)፡፡

ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው ዘመነ አስተምሕሮ ስለ እግዚአብሔር ቸርነትና ርኅራኄ፤ እርሱ በደላችንን ዅሉ ይቅር እንደሚለን እኛ ምእመናንም እርስበርስ ይቅር መባባል እንደሚገባን ትምህርት የሚሰጥበት ጊዜ ነው፡፡

በቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍት እንደ ተቀመጠው በዘመነ አስተምሕሮ ውስጥ የሚገኙ ሰንበታት (እሑዶች) አስተምሕሮ፣ ቅድስት፣ ምኵራብ፣ መጻጉዕ እና ደብረ ዘይት ተብለው ይጠራሉ፡፡ ከመጀመሪያው ሳምንት (ከአስተምሕሮ) በቀር የአራቱ እሑዶቹ ስያሜ ከዐቢይ ጾም ሰንበታት ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡ የሰንበታቱ ስያሜ ከዐቢይ ጾም ሰንበታት ጋር ተመሳሳይ ይኹን እንጂ በእነዚህ ሳምንታት ሌሊት የሚዘመሩ መዝሙራት፣ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ ምንባባትና የሚቀርቡ ትምህርቶች ግን በምሥጢር ይለያያሉ፡፡

ትምህርቶቹ ይለያያሉ ስንልም በዚህ ወቅት የሚነገረው ምሥጢርና ይዘት በወቅቱ ላይ የሚያተኵር መኾኑን ለመግለጽ ነው እንጂ በየትኛውም ጊዜ በቤተ ክርስቲያናችን የሚቀርበው ትምህርት አንዱ የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው። ሳምንታቱን በዚህ መልክ የከፋፈለውም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ ይህንንም ከመጽሐፈ ድጓው መመልከት ይቻላል (ድጓ ዘአስተምህሮ)፡፡

ከዚህ ቀጥለን በእያንዳንዱ የዘመነ አስተምህሮ (አስተምሕሮ) ሳምንት የሚቀርበውን ትምህርት በቅደም ተከተል በአጭሩ እንመለከታለን፤

፩. አስተምሕሮ

የመጀመሪያው የዘመነ አስተምሕሮ ሳምንት አስተምሕሮ ይባላል፤ ይህም ከኅዳር ፮–፲፪ ያሉትን ሰባት ቀናት ያካትታል፡፡ በዕለቱ (እሑድ) የሚቀርበው የቅዱስ ያሬድ መዝሙር ‹‹ኢተዘኪሮ አበሳ ዚአነ ኢኀደገነ ፍጹመ ንማስን …. ኀጢአታችንን አላሰበብንም፤ እንጠፋ ዘንድም ፈጽሞ አልተወንም ….›› የሚለው ሲኾን፣ በተጨማሪም ‹‹ፈጽም ለነ ሠናይተከ እንተ እምኀቤነ …. በአንተ ዘንድ ያለችውን በጎነት ፈጽምልን ….›› የሚለውም እንደ አማራጭ ሊዘመር ይችላል፡፡ ምስባኩ ‹‹ኢትዝክር ለነ አበሳነ ዘትካት ፍጡነ ይርከበነ ሣህልከ እግዚኦ እስመ ተመንደብነ ፈድፋደ፤ የቀደመውን በደላችንን አታስብብን፡፡ አቤቱ ምሕረትህ ፈጥኖ ያግኘን፡፡ እጅግ ተቸግረናልና፤›› የሚለው የዳዊት መዝሙር ነው (መዝ. ፸፰፥፰)፡፡

ወንጌሉ ማቴዎስ ፮፥፭-፲፮ ሲኾን፣ ይኸውም ፊትን በማጠውለግና ጸሎተኛ በመምሰል ሳይኾን በፍጹም ፍቅርና ትሕትና መጾም መጸለይ እንደሚገባን የሚያስተምረው የወንጌል ክፍል ነው፡፡ እንደዚሁም ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታን ለማግኘት በመጀመሪያ እርስበርሳችን ይቅር መባባል ማለትም የበደሉንን ይቅር ማለት እንዳለብን ይህ የወንጌል ክፍል ያስረዳናል፡፡ ቅዳሴውም ቅዳሴ እግዚእ (የጌታችን ቅዳሴ) ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ነገረ ድኅነትን ከምሥጢረ ቍርባን ጋር በማስማማት የተዘጋጀውና ብዙ ምሥጢራትን ያካተተው ቅዳሴ ነው፡፡

በዚህ ሳምንት (በአስተምሕሮ) እግዚአብሔር አምላካችን ከአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመት የመርገምና የጨለማ ዘመን ዓለምን ማውጣቱ፤ ቸርነቱ፣ ርኅራኄውና ትዕግሥቱ፤ ምእመናንን ከሞተ ሥጋ ከሞተ ነፍስ ማዳኑ በሰፊው ይመሠጠርበታል፡፡ በየጊዜው እንደምንማረው እግዚአብሔር አምላካችን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከቅድስት ደንግል ማርያም ተወልዶ በአዳም በደል (የውርስ ኀጢአት) ምክንያት ከመቀጣት ማለትም ከሞተ ነፍስ (ከቁራኝነት) አድኖናል፡፡ ድነናል ስንልም ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከፈለው መሥዋዕትነት በቀደመው የአዳም በደል አንጠየቅም ማለታችን ነው፡፡

ይኹን እንጂ በየራሳችን በደል እንደምንጠየቅ መዘንጋት የለብንም፡፡ ስለዚህም ‹‹በጸጋው ድነናል›› እያሉ ከጽድቅ ሥራ ተለይተው በዘፈቀደ ምድራዊ ኑሮ ማለፍ ከሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎች የተሳሳተ ትምህርት መራቅ ይጠበቅብናል፡፡ ከዚሁ ዂሉ ጋርም ‹‹ድነናል›› ብለን ብቻ መቀመጥ ሳይኾን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንችል ዘንድ በየጊዜው ከሠራነው ኀጢአት በንስሐ መመለስ እንደሚገባንም መረዳት ይኖርብናል፡፡ ይኸውም (ምሥጢረ ንስሐ) እግዚአብሔር አምላካችን ለእኛ ለምእመናን የሰጠን ልዩ ጸጋ ነው፡፡

ይህን ያህል ጸጋ ከተሰጠን ለመኾኑ በምን ዓይነት ሕይወት እየኖርን ነው? በመንፈሳዊ ወይስ በዓለማዊ? በፈሪሃ እግዚአብሔር ወይስ በአምልኮ ባዕድ? በጽድቅ ወይስ በኀጢአት ሥራ? ጥያቄውን ለየራሳችን እንመልሰው፡፡ በፈቃዱ ከሞት ወደ ሕይወት የመለሰንን አምላክ በክፉ ግብራችን እንዳናሳዝነው ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በመልካምታችን ከዂሉም በፊት የምንጠቀመው እኛው ራሳችን ነንና፡፡

ስለዚህ በዚህ ወቅት እግዚአብሔር ያደረገልንን ዘለዓለማዊ ውለታ በማሰብ ይቅርታውን፣ ቸርነቱን ከማድነቅና እርሱን ከማመስገን ባሻገር በጽደቅ ሥራ ልንበረታ ይገባናል፡፡ ጊዜው የአስተምሕሮ ማለትም የምሕረት፣ ይቅርታ፣ የስርየተ ኀጢአት እንደዚሁም የምስጋና ጊዜ ነውና፡፡

፪. ቅድስት

ከኅዳር ፲፫–፲፱ ያሉትን ሰባት ቀናት የሚያካትተው የዘመነ አስተምሕሮ ሁለተኛው ሳምንት ቅድስት ይባላል፤ ቅድስት የተባለበት ምክንያትም ዕለተ ሰንበትን ለቀደሰ፣ ለመረጠ፣ ላከበረ ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ማቅረብ እንደሚገባ የሚነግርበት ሳምንት በመኾኑ ነው፡፡ በዚህ ዕለት (እሑድ) ‹‹ሎቱ ስብሐት ወሎቱ አኰቴት ለዘቀደሳ ለሰንበት …. ሰንበትን ላከበራት ለእርሱ ክብር ምስጋና ይኹን (ምስጋና ይድረሰው፤ ምስጋና ይገባዋል) ….›› የሚለው የቅዱስ ያሬድ መዝሙር ይቀርባል፡፡ በቅዳሴ ጊዜም ‹‹ኵሎ ዘፈቀደ ገብረ እግዚአብሔር በሰማይኒ ወበምድርኒ በባሕርኒ ወበኵሉ ቀላያት፤ በሰማይና በምድር፣ በባሕርና በጥልቆችም ዅሉ እግዚአብሔር የወደደውን ዅሉ አደረገ፤›› የሚለው ምስባክ ይሰበካል (መዝ. ፻፴፬፥፮)፡፡

የዕለቱ ወንጌል ዮሐንስ ፭፥፲፮-፳፰ ሲኾን፣ ይኸውም ስለ ሰንበት ክብር፣ እግዚአብሔር የሰንበት ጌታ ስለመኾኑና ሰንበትን ለሰው ልጆች ዕረፍት ስለ መፍጠሩ ያስረዳል፡፡ በዚህ ሳምንት ሰንበትን ስለ ቀደሰ እግዚአብሔር ቅድስና እና ሰንበት ቅድስት ስለመኾኗ ሰፊ ትምህርት ይቀርባል፡፡ በዕለቱ የሚቀደሰው ቅዳሴ አትናቴዎስም ነገረ ድኅነትን ከምሥጢረ ሥጋዌና ምሥጢረ ቍርባን ጋር በማስማማት የሚያትትና ክብረ ሰንበትን የሚያስረዳ ቅዳሴ ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ‹‹ሰንበት ተዐቢ እምኵሉ ዕለት ወሰብእ ይከብር እምኵሉ ፍጥረት፤ ከዕለታት ሰንበት ትበልጣለች፤ ከምድራውያን ፍጥረታትም የሰው ልጅ ይከብራል›› በማለት እንደ ዘመረው ዕለተ ሰንበት ከሳምንቱ ዕለታት ዂሉ ትበልጣለች፡፡ የሰው ልጅም ከምድራውያን ፍጥረታት የከበረ ነው፡፡ ሰንበት ስንል ሁለቱን ዕለታት (ቀዳሚት ሰንበት እና እሑድ ሰንበትን) ማለታችን ነው፡፡ የመጀመሪያዋ ሰንበት እግዚአብሔር ከሥራው ዂሉ ስላረፈባት፤ ሁለተኛዋ (እሑድ) ሰንበት ደግሞ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ተፀነሰባት፣ ከሙታን ተለይቶ ስለ ተነሣባት ከዕለታት ዂሉ ይበልጣሉ፡፡ ስለዚህም ከሌሎች ዕለታት አስበልጠን እናከብራቸዋለን፡፡

የሰው ልጆችም በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ እንደ መፈጠራችን ከፍጥረታት ዂሉ እንደምንከብር ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል፡፡ ኾኖም ብዙዎቻችን እግዚአብሔር የሰጠንን ክብር በራሳችን ኀጢአት ዝቅ አድርገነዋል፡፡ ማለትም በእግዚአብሔር አምሳል ከተፈጠረ፣ ለእግዚአብሔር ማደሪያነት ከተመረጠ ክቡር ሰው በማይጠበቅ ክፉ ግብር ወድቀናል፡፡ በዝሙት፣ እርስበርስ በመከፋፈል፣ በመገዳደል፣ በመተማማትና በሐሰት በመካከሰስ በጥቅሉ ለሰይጣናዊ ግብር በፈቃዳችን በመገዛት ራሳችንንና ሌሎችን የምንበድል፣ እግዚአብሔርንም የምናሳዝን ሰዎች ጥቂቶች አይደለንም፡፡ እግዚአብሔር ይቅር ብሎ ወደ ክርስቲያናዊ ሕይወትና ወደ መንፈሳዊ ሰብእና ይመልሰን እንጂ፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት፣ ይህን ዂሉ የሰው ልጅ በደል ሲያመላክት ‹‹ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ ወኮነ ከመ እንስሳ ዘአልቦ ልብ ወተመሰሎሙ፤ ሰው ግን ክቡር ኖ ሳለ አያውቅም፡፡ እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ፤›› በማለት ይናገራል (መዝ. ፵፰፥፲፪)፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት በትርጓሜአቸው ‹‹ዳዊት አክብሮ አጓዶ ተናገረ፡፡ ዕዝራ ግን ‹እንስሳት ይኄይሱነ፤ እነስሳት ይሻሉናል› ብሎታል›› በማለት ይህንን ኃይለ ቃል ያመሠጥሩታል።

ምሳሌውን ሲያብራሩም ‹‹እንስሳ ከገደል አፋፍ ኖ ሲመገብ ከገደሉ ሥር ለምለም ሣር፣ ጥሩ ው ቢያይ የረገጠው መሬት ከአልከዳው (ከአልተናደበት) በስተቀር ወርጄ ልመገብ፣ ልጠጣ አይልም፡፡ ሰው ግን ጽድቅ እንዲጠቅም ኀጢአት እንዲጎዳ እያወቀ ጨለማን ተገን አድርጎ ሊሠርቅ፣ ሊቀማ፣ የጎልማሳ ሚስት ሊያስት ይሔዳል›› ሲሉ ያብራሩታል (ትርጓሜ መዝሙረ ዳዊት)፡፡

በዚህ ዓይነት ኀጢአት ራሳችንን ያስገዛን ዂሉ፣ ከዚህ ክፉ ግብራን በመለየት በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ከፍጥረታት ከከበርን ከሰው ልጀች ይልቁንም ከክርስቲያኖች ይጠበቃል፡፡ ስለዚህም አሁኑኑ ወደ ይቅር ባዩ አምላካችን ቀርበን ይቅርታን፣ ስርየትን እንለምን፡፡ ጊዜው ዘመነ አስተምሕሮ (የይቅርታ ዘመን) ነውና፡፡

፫. ምኵራብ

ሦስተኛው የዘመነ አስተምሕሮ ሳምንት ምኵራብ የሚባል ሲኾን ይህም ከኅዳር ፳–፳፮ ያሉትን ሰባት ቀናት የሚያካትት ሳምንት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ጌታችን፣ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኵራበ አይሁድ ሕዝቡን እየሰበሰበ ማስተማሩ፤ ባሕርና ነፋሳትን መገሠፁ፤ አጋንንትን ከሰዎች ማውጣቱ ይነገራል፡፡

በዕለቱ (እሑድ) የሚቀርበው መዝሙር፡- ‹‹አምላክ ፍጹም በህላዌሁ ዘሀሎ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም …. ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ የነበረው አምላክ (እግዚአብሔር) በህልውናው (አነዋወሩ) ፍጹም ነው ….››  የሚለው ሲኾን፣ ምስባኩም፡- ‹‹ቅረቡ ኀቤሁ ወያበርህ ለክሙ ወኢይትኀፈር ገጽክሙ ዝንቱ ነዳይ ጸርሐ ወእግዚአብሔር ሰምዖ፤ ወደ እርሱ ቅረቡ፤ ያበራላችሁማል፡፡ ፊታችሁም አያፍርም፡፡ ይህ ችግረኛ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ሰማው፤›› የሚል ነው (መዝ. ፴፫፥፭-፮)፡፡ ወንጌሉም ከማቴዎስ ፰፥፳፫ እስከ መጨረሻው ድረስ ነው፡፡ ቅዳሴውም ቅዳሴ እግዚእ ነው፡፡

የዕለቱ ወንጌል ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመርከብ ውስጥ ሳለ መርከቢቱ እስክትናወጥ ድረስ ታላቅ ማዕበል መነሣቱን፤ ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹ጌታ ሆይ እንዳንጠፋ አድነን?›› እያሉ በመተማጸኑት ጊዜ ጌታችን ነፋሱንና ባሕሩን በመገሠፅ ጸጥታን፣ ሰላምን፣ መረጋጋትን ማስፈኑን የሚናገረው ክፍል ነው፡፡

በባሕሩ ዓለም ውስጥ የምትገኘው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰዎች በፈቃደ ሥጋቸው ተሸንፈው ባመጡት ጥላቻ፣ ኑፋቄ፣ ክህደት፣ ፍቅረ ንዋይ፣ በአጠቃላይ በልዩ ልዩ የኀጢአት ማዕበልና ሞገድ እየተናወጠች ናት፡፡ ይህን ማዕበልና ሞገድ ጸጥ በማድረግ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ሰላምንና ጽድቅን ማስፈን የሚቻለውን መድኀኒታችን ክርስቶስን እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት በአንድነት ኾነን ‹‹ጌታ ሆይ እንዳንጠፋ አድነን?›› እያልን እንማጸነው፡፡

የሰላሙ ዳኛ፣ የሰላሙ መሪ፣ የሰላሙ ጌታ፣ የሰላሙ ንጉሥ፣ የሰላሙ ባለቤት እርሱ ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን፣ መረጋጋትን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን ካወጀ በቤተ ክርስቲያናችን ፍቅር፣ አንድነት ሰላም ይሰፍናልና፡፡

፬. መጻጕዕ

ከኅዳር ፳፯ እስከ ታኅሣሥ ፫ ያሉ ሰባት ቀናትን የሚያጠቃልለው አራተኛው የዘመነ አስተምሕሮ ሳምንት መጻጕዕ ይባላል፡፡ የቃሉ ፍቺ ‹በደዌ ዳኛ፣ በአልጋ ቍራኛ የተያዘ በሽተኛ ማለት ነው፡፡ ዕለቱ መጻጕዕ ተብሎ መሰየሙም ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕውር ኾኖ የተወለደውን ጐበዝ ዓይን ያበራበትን ዕለት ለማስታወስ ነው፡፡

የዕለቱ (እሑድ) መዝሙር ‹‹ይቤሉ እስራኤል ኢርኢነ ወኢሰማዕነ ዘዕውሩ ተወልደ ወተከሥተ አዕይንቲሁ በሰንበት …. ዕውር ኾኖ ተወልዶ ዓይኖቹ በሰንበት የበሩለትን ሰው እስራኤልአላየንም፤ አልሰማንምአሉ ….›› የሚለው የእስራኤላውያንን በክርስቶስ ተአምር አለማመን የሚገልጸው የቅዱስ ያሬድ ድርሰት ነው፡፡

ምስባኩም ‹‹ደቂቀ ዕጓለ እመሕያው እስከ ማእዜኑ ታከብዱ ልበክሙ ለምንት ታፈቅሩ ከንቶ ወተሐሱ ሐሰተ አእምሩ ከመ ተሰብሐ እግዚአብሔር በጻድቁ፤ እናንት የሰው ልጆች፣ እስከ መቼ ድረስ ልባችሁን ታከብዳላችሁ? ከንቱ ነገርን ለምን ትወዳላችሁ? ሐሰትንም ለምን ትሻላችሁ? እግዚአብሔር በጻድቁ እንደ ተገለጠ ዕወቁ፤›› የሚለው እግዚአብሔር ለጻድቃኑ በሚያደርገው ድንቅ ሥራ ማመን እንደሚገባ የሚያስረዳው የዳዊት መዝሙር ነው (መዝ. ፬፥፪-፫)፡፡

ወንጌሉ ደግሞ ዕውር ኾኖ የተወለደውንና በጌታችን አምላካዊ ኃይል የተፈወሰውን ጐልማሳ ታሪክ የሚተርከው ዮሐ. ፱፥፩ እስከ መጨረሻው ያለው ኃይለ ቃል ሲኾን፣ የዕለቱ ቅዳሴም ቅዳሴ እግዚእ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት መድኀኒታችን የዕውሩን ዓይን ከማብራቱ ባሻገር ሕሙማነ ሥጋን በተአምራቱ፤ ሕሙማነ ነፍስን በትምህርቱ ስለ ማዳኑ የሚያወሳ ቃለ እግዚአብሔር ይቀርባል፡፡

ትምህርቱን ከእኛ ሕይወት ጋር አያይዘን ስንመለከተው፣ ብዙዎቻችን ዓይነ ሕሊናችን የጽደቅ ሥራ ብርሃንን ከማየት በመሰወሩ የተነሣ በልዩ ልዩ ደዌ ተይዘናል፡፡ በሐሜት፣ በኑፋቄ፣ በጥላቻ፣ በዐመፅ፣ በስርቆት፣ በውሸት፣ በዝሙት፣ ወዘተ. በመሳሰሉት ደዌያት የተለከፍን ጥቂቶች አይደለንም፡፡ ለዚህም በልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች የምንሰማውና የምናየው በቂ ማስረጃ ነው፡፡

ሰው በሰው ላይ በጠላትነት ሲነሣሣና ወንድሙን፣ እኅቱን በአሰቃቂ ኹኔታ ሲገድል፤ ተመሳሳይ ፆታዎች በሰይጣናዊ ፈቃድ ተሸንፈው ‹ጋብቻ› ሲመሠርቱ፤ አንዳንዶቹ ከሕግ ባሎቻቸውና ሚስቶቻቸው ውጪ ሲዘሙቱ፤ ከዚህ በባሰ ደግሞ እግዚአብሔር ምእመናንን እንዲመሩ የሾማቸው ካህናት ሳይቀሩ ክብረ ክህነትን በሚያስነቅፍ የስርቆትና ሌላም ወንጀል ተሰማርተው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ ሲመዘብሩ እየሰማን ነው፡፡

ከዚህ የሚበልጥ ደዌ ምን አለ? ከደዌ ሥጋ በጠበልና በሕክምና መፈወስ ይቻላል፡፡ በሽታው ባይድንም እንኳን ሕመሙን ለመቋቋም የሚያስችል መድኀኒት አይጠፋም፡፡ የኀጢአት ደዌ ግን መድኀኒቱ ንስሐ ብቻ ነው፡፡ ስለኾነም ከላይ በተጠቀሱትና በመሳሰሉት ደዌያት የምንሰቃይ ወገኖች ዂሉ ፈውሱ ዘለዓለማዊ ወደ ኾነው ወደ ወደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርበን እንፈወስ፡፡ እርሱ የነፍስ የሥጋ መደኀኒት ነውና፡፡

፭. ደብረ ዘይት

አምስተኛውና የመጨረሻው የዘመነ አስተምሕሮ ሳምንት ‹ደብረ ዘይት በመባል የሚታወቅ ሲኾን የሚያጠቃልለውም ከታኅሣሥ ፬ – ፮ ያሉ ቀናትን ነው፡፡ በዕለቱ (እሑድ) ‹‹ሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ ለእለ በሰማይ ወለእለ በምድር እግዚአብሔር በሰማይም በምድርም ለሚኖሩ ፍጡራን ሰንበትን ለዕረፍት ሠራ (ፈጠረ) ….›› የሚለው የቅዱስ ያሬድ መዝሙር ይዘመራል፡፡

‹‹ለነዳያኒሃኒ አጸግቦሙ እክለ ወለካህናቲሃኒ አለብሶሙ ሕይወተ ወጻድቃኒሃኒ ትፍሥሕተ ይትፌሥሑ፤ ባልቴቶቿን እጅግ እባርካቸዋለሁ፤ ድሆቿንም እኽልን አጠግባቸዋለሁ፡፡ ካህናቷንም ደኅንነትን አለብሳቸዋለሁ፡፡ ጻድቃኖቿም እጅግ ደስ ይላቸዋል፤›› የሚለው የዳዊት መዝሙር ደግሞ የዕለቱ ምስባክ ነው (መዝ. ፻፴፩፥፲፭-፲፮)፡፡

በዕለቱ የሚነበበው የወንጌል ክፍልም ሉቃስ ፲፪፥፴፪-፵፩ ሲኾን፣ ቅዳሴው ደግሞ ቅዳሴ አትናቴዎስ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ሰንበት የዕረፍት ዕለት መኾኗን ከሚያስገነዝቡ ትምህርቶች በተጨማሪ የደጋግ አባቶችን መንፈሳዊ ታሪክ፣ የወረሱትን ሰማያዊ ሕይወትና ያገኙትን ዘለዓለማዊ ሐሤት መሠረት በማድረግ እኛ ምእመናንም እንደ አባቶቻችን ለመንግሥተ ሰማያት በሚያበቃ ክርስቲያናዊ ምግባር ጸንተን መኖር እንደሚገባን የሚያተጋ ቃለ እግዚአብሔር ይቀርባል፡፡

በዕለቱ የሚነበበው የወንጌል ክፍል (ሉቃ. ፲፪፥፴፪-፵፩) የሰው ልጅ ዓለም የሚያልፍበትን ወይም ራሱ የሚሞትበትን ቀን አያውቅምና ዘወትር በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንቶ መኖር እንደሚገባው፤ እንደዚሁም በዚህ ምድር ሳለ ለሥጋው የሚጠቅም ኃላፊ ጠፊ ሀብት ከመሰብሰብ ይልቅ ለነፍሱ የሚበጅ የጽድቅ ሥራን ማብዛትና የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የሚያበቃ ክርስቲያናዊ ምግባርን መያዝ እንደሚጠበቅበት፤ በዚህም ሰማያዊውን መንግሥት ለመውረስ እንደሚቻለው የሚያስረዳ መልእክት አለው፡፡

እንግዲህ እንደ ታዘዝነው ነገ ለሚያልፍና ለሚጠፋ ምድራዊ ጉዳይ መጨነቃችንንና እርበርስ መገፋፋታችንን ትተን እግዚአብሔር አምላካችን ለፍርድ ሲመጣ ሰማያዊ ዋጋ ለመቀበልና የማያልፈውን መንግሥቱን ለመውረስ በሚያበቃን ክርስቲያናዊ ምግባር እንጽና፡፡ ‹‹ክርስቲያናዊ ኑሮ በዘመነ አስተምሕሮ›› ማለትም ይኸው ነው፡፡

የቀደመ በደላችንን ቈጥሮ ሳያጣፋን ዕድሜ ለንስሐ ሰጥቶ እስከ ዛሬ ድረስ የጠበቀን፤ ይቅርታ፣ ርኅራኄ፣ ቸርነት የባሕርዩ የኾነው አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር እንደ ቸርነቱ ዘለዓለማዊ መንግሥቱን ለመውረስ ያብቃን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡