ejig yetekeberu_yealemloriet

እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ አረፉ

ሚያዝያ 04፣ 2004ዓ.ም

እንዳል ደምስ

ejig yetekeberu_yealemlorietእጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ80 ዓመታቸው ሚያዚያ 2/2004 ዓ.ም. ምሽት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ከአባታቸው ከአቶ ተክሌ ማሞ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ፈለቀች የማታወርቅ በጥቅምት ወር 1924 ዓ.ም. በአንኮበር ከተማ ተወልደዋል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ፣ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርታቸውን በእንግሊዝ አገር በሚገኘው የሥነ ጥበብ አካዳሚ በሥነ ስዕል በቅርፃ ቅርጽና በሥነ ሕንፃ ዲዛይን ተከታትለዋል፡፡

በነበራቸው የሥነ ስዕል ዝንባሌ ታላላቅ ሥራዎችን የሠሩ ሲሆን በወጣትነት ዘመናቸው በ1957 ዓ.ም. ከክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል ጋር በኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ እጅ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ተሸላሚ ለመሆን ችለዋል፡፡ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የአራት ዓለም አቀፍ አካዳሚዎች አባል ሲሆኑ በተሰማሩበት የሥነ ሥዕል ጥበብ በዓለም ላይ ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱ ታላላቅ ሰዎች የሚሰጠውን የዓለም ሎሬት የተሰኘውን ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ እስካሁን ድረስም ከዘጠና ሰባት በላይ የዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ከተለያዩ ተቋማት አግኝተዋል፡፡

ጊዜ የማይሽራቸው ታላላቅ የሥዕል ሥራዎች ለዓለም ያበረከቱ ሲሆን በስዕሎቻቸውም ሥርዓተ አምልኮን፣ ማኅበራዊ አኗኗር የማኅበረሰቡን ደስታና ሃዘንና ጀግንነቱን ሥልጣኔውና ሀገር ወዳድነትን የሚያንጸባርቁ ሥራዎችን አበርክተዋል፡፡ በተለይም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካላቸው ጥልቅ ፍቅርና እምነት በመነጨ ለተለያዩ ቤተ ክርስቲያናት እንዲሁም በስቱዲዮአቸውና በጸሎት ቤታቸው የሚገኙ መንፈሳዊ ስዕላትን አበርክተዋል፡፡ ከሠሯቸው መካከልም በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ በግድግዳ ላይ የተሠሩ መንፈሳዊ ስዕላትን በቀለም ቅብ፣ በባለቀለም ጠጠሮች፣ በክርክም መስታወቶችና በሞዛይክ ከታወቁትና ስመ ጥር ከሆኑት ሰዓሊ ብላታ እምአዕላፍ ኅሩይ ጋር ሠርተዋል፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሙዚየሞች ውስጥም ስዕሎታቸው በክብር ተቀምጠውላቸው በጎብኚዎች እየታዩ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ረገድም በስዕሎታቸውና በቅርፃቅርጾቻቸው አማካይነት ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ሲሆን “ቪላ አልፋ” የተሰኘው ባለ 22 ክፍሎች መኖሪያ ቤታቸውና የግል ስቱዲዮአቸው ውስጥ ይህንኑ ለማንጸባረቅ ጥረት አድርገዋል፡፡

በቪላ አልፋ ስቱዲዮ ውስጥ የአክሱም ሐውልት፣ የጎንደር ፋሲለደስ፣ የሐረር ግንብ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ቅዱሳት ስዕላት፣ የተወለዱበት አንኮበር የሚገኘው ቤተ መንግሥት የሚያስደንቁ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ እሴቶችን አካቶ የያዘ ነው፡፡

በንግግራቸው ስመ እግዚአብሔርን መጥራት የሚያዘወትሩት እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በዋናው መግቢያ በራቸው ላይ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” የሚል ጥቅስ በትልቁ ጽፈዋል፡፡ “እንደማንኛውም ዓይነት የጥበብ ሥራ በሠራሁ ጊዜ እኔ በጥበቤ ታላቅ ነኝ የሚል ትምክህት እንዳይቀርበኝ ዘወትር እንዳነበው ነው የጻፍሁት” በማለት ከዚህ በፊት በማኅበረ ቅዱሳን ለሚታተመው ሐመር መጽሔት ጋዜጠኞች መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በዓለማችን ላይ ከሚገኙ ስመጥርና ታላላቅ ከተሰኙ 200 ሰዎች ጋር የሕይወት ታሪካቸውንና የኢትዮጵያ ባንዲራ በጨረቃ ላይ እንዲያርፍ የተደረገ ሲሆን በደረሰባቸው የጨጓራ አልሰር ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ80 ዓመታቸው ማክሰኞ ምሽት ይህችን ዓለም ተሰናብተዋል፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸው ሚያዚያ 6/2004 ዓ.ም. ቅዳሜ በቅድሥት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ይፈጸማል፡፡

ዝግጅት ክፍላችን ለመላው ቤተሰቦቻቸው ወዳጅ ዘመዶቻቸውና አድናቂዎቻቸው መጽናናትን ይመኛል፡፡