‹‹እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሓ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል›› (ሐዋ.፲፯፥፴)

ዲያቆን አቤል ካሣሁን

ቅዱስ ጳውሎስ ጣዖት ይመለክባት በነበረችው አቴና በታላቅ መንፈሳዊ ቅንዓት ስለ እውነተኛው አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሰብክ ትምህርቱን የሰሙ የአቴና ሰዎች አዲሱን የጳውሎስን ስብከት ለማድመጥ አርዮስፋጎስ ወደሚባል ስፍራ ወሰዱት፡፡ በዚያም ቦታ ለጆሮአቸው እንግዳ የሆኑ ነገሮችን መስማት ልማድ አድርገው ነበርና፤ ቅዱስ ጳውሎስ የማያውቁትን የጽድቅ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን ያስተዋውቃቸው ጀመር፡፡ (ሐዋ.፲፯፥፲፮-፴፩)

ለፍጥረታት ሁሉ ሕይወትን የሰጠ፣ ረዳት የማያሻው፣ የሰጣቸውን አእምሮ በመጠቀም በትሑት ልቡና ሆነው ለሚሹት ራሱን ከእነርሱ የማያርቅ፣ በዚህም ዓለም ካሉት ለእርሱ አምሳያ የሌለው የዘለዓለም አምላክ መሆኑን ሰበከላቸው፡፡ በዚህም ቃል ያለማወቅ ወራትን አሳልፎ፣ አሁን ንስሓ ይገቡ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር ትእዛዝ እንደሆነ አሳሰባቸው፡፡

ለጊዜው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ስብከት የሰበከው አሕዛብ ለነበሩ የአቴና ሰዎች ቢሆንም፤ ለእኛም ጭምር ትልቅ መልእክትን የያዘ ቃል ነው፡፡ በተለይም ‹‹እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሓ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤›› (ሐዋ.፲፯፥፴) የሚለው ቃል በቀጥታ እኛን የሚመለከት ነው፡፡ አሁን ላይ እየተከሰቱ ላሉ ጥፋቶች በቀጥታ ሰይፍ አንሥተን፣ እሳት ጭረን በቀጥታ ተሳታፊ አንሁን እንጂ በኃጢአት የተዘፈቀ ሕይወታችንና ከእግዚአብሔር መራቃችን ትልቅ አስተዋጽኦ ሳይኖረው አይቀርም፡፡

የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቄስ አታናሲኦስ እስካንደር እንደተናገሩት ገድዬ እጸድቃለሁ ብለው የሚያስቡ ወገኖች ምንም እንኳን አመለካከታቸው እጅግ የተሳሳተ ቢሆንም ግን ያመኑበትንና ያጸድቀኛል ያሉትን ነገር እያደረጉ ነው፡፡ በእኛ ሃይማኖት ደግሞ ‹‹ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሟችሁን መርቁ÷ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ÷ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ›› (ማቴ.፭፥፵፬‐፵፭) የሚል ትእዛዝ አለ፡፡ በርግጥ ሁላችንም በዚህ ቃል የምናምን ይሁን እንጂ ፤በተግባር ለመፈጸም ግን ብዙ እንቸገራለን፡፡ እኛ ክርስቲያኖች የሰማዕትነት አክሊል የሚሰጠን ገዳዮቻችንን በመርገም ሳይሆን ስለሚገድሉን ሰዎች በመጸለይ እና እውነተኛ ፍቅርን በማሳየት ነው፡፡

እግዚአብሔር ያለ ማወቃችንን ወራት ያሳልፍ ዘንድ በነቢያት፣ በሐዋርያት፣ በአበውና በየዘመኑ በተነሡ ሊቃውንት እስከዛሬ ድረስ ሲመክረን እና ሲገሥፀን ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ የቀደመውን የአባቶቻችንን ምክር ባለማስተዋላችን ምክንያት አምላካችን በመከራ ይቀጣናል፡፡ ስለዚህ ይህ ሁሉ ትምህርት ሆኖን መዳን እና ዕረፍት ወደሚገኝበት ንስሓ እንገስግስ፤ በበደል ምክንያት የሚመጣን ቅጣት በንስሓ ካልሆነ በሌላ መመለስ አይቻልምና፡፡