በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/በሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ -  ማኅበረ ቅዱሳን
  • ቀዳሚ ገጽ
  • ስለ ማኅበሩ
    • ማእከላት
      • ሰሜን አሜሪካ
      • አውሮፓ
      • ሩቅ ምሥራቅ
      • ደቡባዊ አፍሪካ
      • የካናዳ ማእከል
      • አዲስ አበባ ማእከል
        • የወርሃዊ አስተዋጽኦ መሰብሰቢያ
    • ኅትመት እና ሚዲያ
      • ሐመር እና ስምዐ ጽድቅ
      • ማኅበረ ቅዱሳን ቲቪ
      • የማኅበረ ቅዱሳን ዩቲዉብ
      • መጽሔተ ተልዕኮ
      • ማእከለ ሥዕላት
        • ካሜራው ምን ይላል
        • የቅዱሳት ሥዕላት ማኅደር
  • ትምህርቶች
    • የርቀት ትምህርት
    • ስብከት
    • መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች
  • ግቢ ጉባኤ
  • ሌሎች ድረ ገጾች
    • በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ ልዩ ጽ/ቤት ድረ ገጽ
    • በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ድረ ገጽ
    • በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ድረ ገጽ
  • ቋንቋ
    • አማርኛ
    • ትግርኛ
    • ወላይትኛ
    • ሲዳምኛ
    • Affan Oromo
    • English
  • ያግኙን
  • Click to open the search input field Click to open the search input field Search
  • Menu Menu

አገልግሎቴን አከብራለሁ!

You are here: Home1 / ክርስቲያናዊ ሕይወትና ሥነ ምግባር2 / አገልግሎቴን አከብራለሁ!

አገልግሎቴን አከብራለሁ!

ክፍል ሦስት
ጥር ፳፫፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ወንጌልን በዝማሬ

፩.መዝሙርና ኪነ ጥበባት አገልግሎት (መዝሙር በድምፅ ወምስል)

ማኅበሩ ከምሥረታው ጀምሮ የመዝሙርና ኪነ ጥበባት ክፍልን በማቋቋም በሰማያዊ የመላእክት ሥርዓት በተመሠረተ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ያሬዳዊ ዜማ የተለያዩ መዝሙራትን በተለያዩ ቋንቋዎች በልዩ ልዩ መንገዶች ለምእመናን ሲያደርስ ቆይቷል፡፡ በድምፅ እና በድምፅ ወምስል ካሴቶች፣ በተለያዩ ሐዋርያዊ ጉዞዎች በዐውደ ምሕረትና ታላላቅ የዐደባባይ በዓላት በዘመኑ ቴክኖሎጅ በመታገዝ በዩቲዩብ በሬድዮ እና በቴሌቪዥን ጭምር መዝሙራቱ ለምእመናን ተደራሽ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በበርካታ ቋንቋዎች (በተለያዩ ከ ፶/ሃምሳ) በላይ ቋንቋዎች) የመዝሙር አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ፻፳ (መቶ ሃያ) መዝሙራት ተመረጠው የትርጉም ሥራ በማሠራት ላይ ይገኛል፡፡

በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኦርቶዶክሳዊ ዜማ መሣሪያዎች (በበገና፣ በመሰንቆ፣ በዋሽንት፣ በከበሮ) በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሠልጣኞችን በማሠልጠን አገልግሎቱ እንዲሰፋ እና ውስን መንፈሳዊ አገልጋዮች ብቻ የነበሯቸው እንዲሁም የመጥፋት ስጋት ተጋርጦባቸው የነበሩ (እንደ በገና፣ መሰንቆ እና ዋሽንት) አገልግሎቶች እንዲጠናከሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል፡፡

ማኅበራችን የተለያዩ መነሻ ጥናታዊ ጽሑፎችን፣ የሥልጠና ማንዋሎችንና የድምጽና የምስል ዝግጅቶችን በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን እና ጉባኤያትን በማዘጋጀት ምእመናንና አገልጋዮች ኦርቶዶክሳዊ የመዝሙር ሥርዓትን እንዲለዩ እና እንዲጠብቁ ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፤ እያደረገም ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ቋንቋዎች ኦርቶዶክሳዊ ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት የጠበቁ መዝሙራትን በመምረጥ የተለያዩ የመዝሙር ጥራዞችንና መጽሐፍ በማዘጋጀት አገልጋዮች (በተለይ የማኅበሩ አባላትና የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች) መዝሙራትን በቀላሉ እንዲያገኙ በማስቻል የአገልግሎቱ ሥርዓት እንዲጠበቅ ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊ የኪነ ጥበባት አገልግሎትን በተለይም መንፈሳዊ ሥነ ጽሑፎችን፣ ተውኔቶችን እና ሥዕላትን በተመለከተ እንደ መዝሙር አገልግሎቱ ሁሉ መዋቅሩን በመጠቀም የኦርዶክሳዊ ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊትን በጠበቀ ሁኔታ አገልግሎት እንዲፈጸምና ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡
የማኅበሩ የመዝሙርና የኪነ ጥበባት አገልግሎት በዋና ማእከል ብቻ የተወሰነ ሳይሆን አጠቃላይ በሀገር ውስጥና በውጭ ባሉ ማእከላት እና በማእከላቱ ሥር በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት መዝሙርና ኪነ ጥበባት አገልግሎት ክፍላትን በማቋቋም ኦርቶዶክሳዊ መዝሙርን እንዲያጠኑና ሥርዓት ባላቸው መዝሙራት እንዲያገለግሉ አድርጓል፤ ከዚያም ባሻገር አባላቱ ወደ ሥራ በሚዘዋወሩባቸው በሀገር ውስጥና የውጭ አህጉረ ስብከት በሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በመቀላቀል የመዝሙር አገልግሎቱን እንዲደግፉ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከእነዚህ ግቢ ጉባኤያትና ማእከላት የወጡ ዘማርያንም የተወሰኑት በግል የመዝሙር አገልግሎት ውስጥ ናቸው፡፡

በተጨማሪ የማኅበራችን የመዝሙርና የኪነ ጥበባት አገልግሎት ከተለያዩ ከቤተ ክርስቲያናችን አካላት ጋር ማለትም ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ከማኅበራት እና ከግል አገልጋዮች ጋር በምክክርና በትብብር እየፈጸመ ይገኛል፤ ወደ ፊትም አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

፪.ትንሣኤ በገና

የዜማ መሣሪያዎችን በተመለከተ በግንቦት ፪፣ ፲፱፹፮ ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ከ፳፻፮ ዓ.ም. ጀምሮ በበገና፣ በመሰንቆ፣ በዋሽንት እና በከበሮ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ነገር ግን ለዚህ ሁሉ መነሻ የነበረው በጣም ተዳክሞ የነበረው የበገና አገልግሎት ማለትም በተወሰኑ ግለሰቦች እጅ ብቻ ስለነበረ ትንሣኤ እንደሚያስፈልገው በመታመኑ በየዓመቱ በሀገርም ሆነ በውጭ ማእካለትም በሰፊው እየተሰጠ እና በተለያዩ የዐደባባይ በዓለትም አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል። በጥቅሉ አዲስ አበባን ጨምሮ ከ፴ (ሠላሳ) በላይ ማእከላት ሥልጠናውን እየሰጡ ይገኛሉ። ከእነዚህም የሥልጠና ቦታዎች በአጠቃላይ በዓመት ከ፻፳፻ (መቶ ሃያ) በላይ ሠልጣኞችን አሠልጥኖ ያስመርቃል። በአጠቃላይ በዚህ አገልግሎት በዚህ ዓመት አንድ የአማርኛ፣ አንድ የኦሮምኛ እና አንድ የትግርኛ የበገና መዝሙር የድምጽ ቀረጻ ተጠናቅቆ የአርትዖት ሥራ በመሠራት ላይ ነው።

ሐዋርያዊ ጉዞ ወደ ጠረፋማ አካባቢዎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊትና ታሪካዊት ናት፡፡ አስተምህሮዋና መሠረተ እምነቷ ከአማናዊው መምህር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘ በመሆኑ አማናዊትና ርትዕት ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ‹‹ወርቃማ›› ዘመናትን ያሳለፈች ስትሆን በዚያው መጠን እጅግ ፈታኝ የሆኑ ጊዜያትንም አሳልፋለች፡፡ እነዚህም ወቅቶች ኢትዮጵያውያን አሕዛባዊ ጠባይን የተላበሰ የአኗኗር ዘይቤ እንዲከተሉ ከማድረጉም በተጨማሪ የተለያዩ እምነቶች ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ መንገድን አመቻችቷል፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹አባቴ እንደላከኝ እናንተንም እልካችኋለሁ›› እንዲሁም ‹‹ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው›› ሲል በአምላካዊ ቃሉ ያዘዘውን መሠረት በማድረግና የቅዱሳን ሐዋርያትን ፈለግ በመከተል ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በርካታ ሰባክያንን እያስተማረች በየቦታው ስታሰማራ ኖራለች፤ ወደፊትም ይህንን ተልእኮዋን አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡ (ዮሐ.፳፥፳፩፣ማቴ.፳፰፥፲፱)

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የማኅበረሰባችንን ችግር ምክንያት በማድረግ የተለያዩ እምነቶች አብዛኛውን የገጠርና ጠረፋማ አካባቢ ነዋሪዎች የተሳሳተ ትምህርት በማስተማርና በጥቅም በመደለል ከቤተ ክርስቲያኗ ሲያርቁት መመልከት የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለዚህም ለሦስት ተከታታይ ወቅቶች የተካሄዱት የሕዝብ ቆጠራ ውጤቶች ምስክሮች ናቸው፡፡ ይህ የሌሎች የእምነት ቤቶች ተጽእኖ፣ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በቂ አለመሆን እና የምእመናን የግንዛቤ ማነስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች በተካሄደው የሕዝብና ቤት ቆጠራ መሠረት ቁጥራቸው መቀነሰ ማወቅ ተችሏል፡፡ (በ፲፱፻፸፮ ዓ.ም. ከመቶ ስድሳ ያህል፣ በ፲፱፻፹፮ ዓ.ም. ከመቶ ኀምሳ መቶኛው እና በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. ዐርባ ሦስት ያህል ነው) ‹‹ድረሱልን፤ አስተምሩን፤ አስጠምቁን፤ እኛም እንደ እናንተ ክርስቲያን መሆንና መባል እንፈልጋለን›› ለሚሉ ወገኖችም መድረስ አልተቻለም ነበር፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ማኅበረ ቅዱሳን በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ አገልግሎት ከቤተ ክርስቲያን የኮበለሉትን በማስመለስ፣ አዳዲስ አማንያንን አስተምሮ በማስጠመቅና ያመኑትን በማጽናት በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

በክርስቲያናዊ ሕይወት ከሁሉም የቀደመ ተግባራችን ማመንና መጠመቅ እንደሆነ ‹‹ያመነ የተጠመቀም ይድናል›› በማለት እግዚአብሔር አምላካችን አስተምሮናል፡፡ ሰዎችን በተለይም ኢ- አማንያን ለሥላሴ ልጅነት በቅተውና በንስሓ ጥምቀትም ከኃጢአታቸው ነጽተው እንዲድኑ ማኅበሩ እጅጉን ይሻል፡፡ ኢትዮጵያ የሦስት ሺህ የእግዚአብሔር አምልኮት ታሪክ እንዳላት ሲነገር አስካሁን ድረስ ግን እግዚአብሔርን የማያውቁ ያላመኑ ያልተጠመቁ አባለት ብዙ ናቸው፡፡ ሌሎቹም በዘመኑ የኑፋቄ ትምህርት ተደናግረው የጠፉም ብዙ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት ማኅበራችን የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለመደገፍ በሚተገብራቸው ዓበይት ተግባራት መካከል በዋነኛነት ኢ-አማንያንንና መናፍቃንን ወደ ክርስትና ለማምጣት ወይም ለመመለስ ይተጋል፡፡ ለዚህም በቀዳሚነት አድርጎ የተንቀሳቀሰው በጥምቀት ልጅነት እንዲገኙ እነርሱን የማጥመቅ ተግባር ነው፡፡ (ማር.፲፮፥፲፮)

በትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት የስብከተ ወንጌል ማስፋፋት መርሐ ግብር በኩል አባላት አብያተ ቤተ ክርስቲያናት ባልተገነቡባቸውና ስብከተ ወንጌል ተደራሽ በማይሆንባቸው ወደ የተለያዩ ክፍለ ሀገራት በመሄድ በመጀመሪያ ትምህርተ ወንጌልን በማስተማር ኢ-አማንያኑን እያጠመቀ በርካቶችን ወደ ክርስትና እምነት እየቀየር ይገኛል፡፡ በተለይም ከ፳፻፪-፳፻፲፩ ባሉት ዓመታት በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ መተከል፣ አርባ ምንጭ፣ ጂንካ፣ ደቡብ ኦሞ እና ሌሎችም ክፍለ ሀገራት በመዘዋወር፣ በስብከተ ወንጌል በማነጽና በማጥመቅ ከፍተኛ ችግር ላለባቸው ሞያው ውስጥ ባሉ አባላት የምክር አገልግሎት ይሰጣል፡፡

በዚህም ሐዋርያዊ ተልእኮ ማኅበሩ በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተደራሽ ባለመሆናቸው ተስፋ በመቁረጥ የጠፉ ከቤተ ክርስቲያን የቀሩ ወጎኖችን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰብሰቧል፤ ጠፍተው የነበሩ እና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለዘመናት ተስፋ ሲያደርጉ የነበሩ ወገኖችን ተምረውና አምነው በመጠመቅ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባል እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ስመ እግዚአብሔር የማይጠራባቸውና ስብሐተ እግዚአብሔር ያልደረሰባቸው አካባቢዎች ስመ እግዚአብሔር መጠራቱ ስብሐተ እግዚአብሔር ተደራሽ እንዲሆን አስችሏል፤ ከአዳዲስ አማንያን መካከል አገልጋይ ሰባክያነ ወንጌልን፣ ዲያቆናትንና ካህናት አፍራቷል፤ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በሌሉባቸው አካባቢዎች የሕፃናትንና የወጣቶች ጉባኤዎች እንዲመሠረቱ ከማድረጉም ባሻገር የተመሠረቱትንም አጠናክሯል፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ወገኖች በሌሉባቸው አካባቢዎች የሐዋርያዊ አገልግሎት ተደራሽ በመሆኑ ኦርቶዶክሳዊ ትውፊትና ሥርዓት አስፋፍቷል፡፡

ማኅበሩ እነዚህን መንፈሳዊ አገልግሎት ተደራሽ ከማድረጉም በላይ አዳዲሲ አማንያኑ እንዲሁም ምእመኑ በሃይማኖት ጸንተው እንዲኖሩ ለማስቻል የተለያዩ መርሐ ግብራትንና ሥልጠና በማዘጋጀትና ተሳትፎአቸውን በመጨመር ያግዛቸዋል፡፡ በርካታ ኢ-መደበኛ አባላትንም በዚሁ የተነሣ ማፍራት በመቻሉ አገልግሎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምሯል፡፡

ወንጌል ቅዱስ በመገናኛ ብዙኃን (ቲቪ፣ማኅበራዊ ገጾች)

፩. የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥን ምሥረታ

ማኅበረ ቅዱሳን ስብከተ ወንጌል ከሚያስፋፋባቸው መንገዶች ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎቹ የጎላ ድርሻ አላቸው፡፡ ማኅበሩ በእነዚህ ሚዲያዎቹ የሚያስተላልፋቸውን ትምህርተ ሃይማኖት በተደራጀ መልኩ ወደ ምእመናን ለማድረስ ያመች ዘንድ የሚዲያ ዋና ክፍል ያዋቀረ ሲሆን ይህም የቴሌቭዥን አገልግሎት ተቋም ነው፡፡

የቴሌቭዥን ክፍል በሥሩ የሬዲዮ ዝግጅት ክፍል፣ በኢ-ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን የአየር ሰዓት ይቀርብ የነበረ የቴሌቪዥን ዝግጅት እና የቀጥታ የኢንተርኔት ሥርጭት ቴሌቪዥን ዝግጅት ክፍል ነበሩት፡፡ ማኅበሩ ክፍሉን ከማቋቋሙ በፊት በሰሜን አሜሪካ ባሉት ሁለት የመካከለኛ ሞገድ የሬዲዮ ጣቢያዎች፣ በአውሮፓ ማእከል በሚካሄድ ፓል ቶክ እና በሰሜን አሜሪካ ማእከል አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ ይሰራጭ በነበረው የአጭር ሞገድ የሬዲዮ ሥርጭት ስብከተ ወንጌልን ሲያስፋፋ ቆይቶል፡፡ ዛሬም ላይ የሬዲዮ መርሐ ግብሩን በኢንትርኔት እያስተላለፈ ይገኛል፡፡ ከየካቲት ወር ፳፻፭ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ኅዳር ፳፻፰ ዓ.ም. ድረስ በ ኢ-ቢ.ኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ መርሐ ግብሩን ሲያስተላልፍ ቆይቷል፡፡ በኢ-ቢ.ኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ ይተላለፍ የነበረው መርሐ ግብሩ ቢቋረጥም በ፲፩ (ዐሥራ አንድ) የውጭ ሀገራት በኢንተርኔት መረብ አማካኝነት መርሐ ግብሩ የቀደመ ይዘቱን ሳይለቅ ሲተላለፍ ቆይቷል፡፡

ከየካቲት ወር ፳፻፯ ዓ.ም. ጀምሮ የአገልግሎት አድማሱን ይበልጥ ተደራሽ በማድረግ በ የቀጥታ የኢንተርኔት ሥርጭት የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ያስተላልፍ ነበር፡፡ በአጠቀላይ ከ፳፻፯-፳፻፱ ዓ.ም. በአማርኛ ሳምንታዊ በኦን ላይን ቲቪ እና ሬዲዮ ላይ ብቻ ተወስኖ የነበረ አገልግሎት ነው፡፡ ይህም ጊዜ ወስዶ ጥራት ያላቸውን መርሐ ግብራት ለመሥራት ጥሩ አጋጣሚ ነበረ፡፡ ለዚህ አገልግሎትም በቂ የሰው ኃይል የነበረ በመሆኑ በመስክ ሥራም በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ እነዚህ ሥራዎችም በአሌፍ ቴሌቪዥን መርሐ ግብር ሲጀምር እንደመጠባበቂያ ሥራ ሁነዋል፡፡ በኦሮምኛ ቋንቋም በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ የነበረው ልምድ ቀላል አልነበረም፡፡በአጠቃላይ ይህንን መነሻ ልምድ ይዞ በመነሣት ከ ፳፻፲ ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አደረጃጀት በአሌፍ የቴሌቪዥን ጣብያ በትግርኛ በኦሮምኛ እና አማርኛ ቋንቋዎች ስብከተ ወንጌልን በሳምንት ለ፲፬ (ዐሥራ ዐራት) ሰዓት ሲያስተላልፍ ቆይቷል፡፡ በአሌፍ ቴሌቪዝን የአየር ሰዓት ክራይ አጀማመሩ በሰባት ሰዓታት ቢሆንም በያዘው ስልታዊ እቅድ መሠረት በየዓመቱ ሰዓቶችን በመጨመርና፣ የመርሐ ግብር ይዘት ጥራት ማሻሻያዎችን በማድረግ ወደ ፲፬ ሰዓት አድጓል፡፡

ማኅበሩ ይህን ክፍል በተቋም ደረጃ ባቋቋመ በአጭር ጊዜያት ውስጥ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሚጠቅሙ በርካታ ሥራዋችን ሠርቷል፡፡ ለብዙ ነፍሳትም የመዳን ምክንያት ሆኗል፤ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ምንነት ያልተረዱ ሰዎችም ማኅበሩን በግልጽ እንዲያውቁ አድርጓል፡፡ በመሆኑም አገልገሎቱን መጠቀም የሚፈለጉ አካልት ዕለት በዕለት በቁጥር እና በዓይነት በመጨመራቸው በዓለማዊ ሚድያ ላይ ተጨማሪ ሆኖ መንፈሳዊ መርሐ ግብር ማቅረብ ያስከተለው ክፍተት፣ የማኅበሩ የአየር ሰዓትን ለማሳደግ ፍልጎት በመጨመሩ በአሌፍ ቴሌቭዥን ጣቢያ ላይ የነበረውን የአየር ሰዓት ክራይ ለሁለት ዓመታት ሲጠቀም ቆይቶ ከ፳፻፲፪ ዓ.ም. ከመስከረም ወር ጀምሮ ሙሉ በሙሉ የራሱ የሆነ የ፳፬ (ሃያ ዐራት) ሰዓት መንፈሳዊ የቴሌቭዥነም ጣቢያ ሊከፍት ችሏል፡፡በዚህም ቀድሞ የነበረው አገልግሎት በቂ ባለመሆኑ እና የበለጠ አገልግሎቱን በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግ በልዑል እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን ቲቪ›› የሚል የሙሉ የ፳፬ ሰዓት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

በማኅበሩ የቴሌቭዥን ጣቢያም በአማርኛ፣ በትግርኛ፣ በኦሮምኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ተዘጋጀተው የሚቀርቡ መርሐ ግብራሮች (በመደበኛና ኦን ላይን የሚተላለፉ)፣ የሬዲዮ ፕሮገራሞች፣ በቪሲዲ የሚቀርቡ ልዩ ልዩ ትምህርቶች እና ስብከቶችን እንዲሁም ፊልሞች መምህራንንና ሌሎች አባላቱን በማስተባበር የስብከተ ወንጌል በአማርኛ፣ በግእዝ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛና በእንግሊዘኛ በዓላም ደረጃ እንዲስፋፋ የበኩሉን ጥረት አድርጓል፡፡

፪. ድረ ገጽ፣ ፌስ ቡክ፣ ቴሌግራም፣ ትዊተር እና ኢንስተግራም

ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ካለው ቁርጠኝነት የተነሣ ማኅበረ ቅዱሳን ከኅትመቱ መገኛኛ ብዙኃናቱ በተጨማሪ ባደራጀው የመዛግብት እና መረጃ ክፍል ሥር በ፲፱፻፺፩ ዓ.ም. የአማርኛ ድረ ገጽን በመዘርጋት አገልግሎቱን ቀጠለ፤ ብዙም ሳይቆይ ከኦሮምኛና ከእንግሊዘኛው ድረ ገጾች በተጨማሪ ፌስ ቡክ፣ ቴሌግራም፣ ትዊተር እንዲሁም ኢንስተግራም በመክፈት ወንጌልን ለአንባቢያን ተደራሽ እያደረገ እስከ አሁን ጊዜ ደርሷል፡፡ ማኅበሩ የሚያሠራጫቸው ትምህርተ ወንጌል የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓትና ትውፊት የሚጠብቁ፣ ታሪክ የማያፋልሱ፣ የምእመናንን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሕይወት የሚያሳድጉ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን የሚያስተምሩ እንዲሆኑ ለማድርግ የራሱን አርትዖት አገልግሎት ማስተባበሪያ አቋቁሞ በከፍተኛ ጥንቃቄ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

ሥነ ጽሑፎች (ኪናዊ) እና የሥነ ሥዕል አገልግሎት ሥራዎች በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃናት ወቅቱን ተከትሎ ለአንባቢያን ተደራሽ እንዲሆኑ እያደረገ ነው፡፡ በቴክኖሎጂ ዘመን ምእመናን ለማስተማርና በክርስትና ሕይወት ለማጽናት ቴክሎጂን በመጠቀም ሉሁሉም ባለበት ቦታና ሁኔታ ተደራሽ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አወቆ ዘመኑን በዋጀ መንገድ ብዙ ሥራዎችን ለማከናወን ሞከሯል፡፡

ይቆየን!

በፌስቡክ የትስስር ገጽ ያግኙን

Search Search

አዳዲስ ጽሑፎች

  • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
  • “ባለፉት 34 ዓመታት በአገልግሎት የራቁትን ማቅረብ፣ የቀረቡትን ደግሞ ለንስሐ ሕይወት ለእግዚአብሔር መንግስት ማብቃት ትልቅ ነገር ነው።” ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሶማሌ ጅግጅጋና የምሥራቅ አርሲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል
  • ማኅበረ ቅዱሳን 34ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አከበረ
  •  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
  • ፻፴፬ ኛው የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ምልአተ ጉባኤ ላይ በቅዱስነታቸው የተላለፈ አባታዊ መልእክት
  • በአሜሪካ ቦስተን ከተማ የበገና እና የመሰንቆ ተማሪዎች ተመረቁ
  • አዲስ አበባ ማእከል 26 ለሚሆኑ የአብነት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለተከታታይ አምስት ቀናት ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና መጠናቀቁን አስታወቀ
  • ለአንድ ወር ያክል ሲሰለጥኑ የቆዩ 28 ተተኪ አመራሮች መመረቃቸው ተገለጸ
  • አሜሪካ አቀፍ የአቡነ ጎርጎርዎስ ተማሪዎች ዓመታዊ ውድድር መካሄዱ ተገለጸ
  • ‹‹ዝክረ ጻድቅ ለዓለም ይሄሉ፤ የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል›› (መዝሙረ ዳዊት ፻፲፩፥፮)
  • ጾመ ነነዌ
  • “እግዚአብሔር ብርሃኔ ነው” ቅዱስ ዑራኤል
  • ጊዜ ዕረፍታ ለሶልያና
  • ሥዕለ አድኅኖ
  • ሕፃኑ ሰማዕት

የጽሑፎች ማውጫ – በወራት

© Mahibere Kidusan - All Rights Reserved. Website by MK-IT
  • Link to Facebook
Link to: ‹‹መልአከ ሞት አልነካኝም፤ የጨለማው አበጋዝም አልደረሰብኝም›› (ድርሳነ ማርያም) Link to: ‹‹መልአከ ሞት አልነካኝም፤ የጨለማው አበጋዝም አልደረሰብኝም›› (ድርሳነ ማርያም) ‹‹መልአከ ሞት አልነካኝም፤ የጨለማው አበጋዝም... Link to: ጋብቻና ጾታ Link to: ጋብቻና ጾታ ጋብቻና ጾታ
Scroll to top