አንዱን ደግፎ ሌላውን የመግፋት አሠራር እንዲቆም እንጠይቃለን

ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ

በሀገረ ስብከታችን በዓለ ጥምቀትን ለማክበር ወጥታችሁ የሰውን ልጅ ሁሉ እኩል ለማገልገል ኃላፊነት በተጣለበት የፖሊስ ኃይል ጭምር የተፈጸመባችሁ፤ አሁንም ጥቃት የፈጸሙት መታሰር ሲገባቸው በግፍ የታሰራችሁ የሐረር ከተማ ክርስቲያኖች አምላካችን እግዚአብሔር በዘመነ ሰማዕታት በክርስቲያኖች የተፈጸመባቸውን ግፍና መከራ እንደተቀበለ ግፉን ለበረከት እንደሚያደርግላችሁ በማመን እንድትጸኑ አባታዊ መልእክት እናስተላልፋለን፡፡ ቀደምት ክርስቲያኖች የተፈጸመባቸውን ግፍ ተቋቁመው ለክብር እንደበቁት እናንተም ለክብር እንደምትበቁ እምነታችን የጸና ነው፡፡

ክርስትና መከራን እያሸነፉ ለክብር የሚያበቁት እንጂ ሰዎችን እያሰቃዩ ጊዜያዊ ድሎት የሚያገኙበት ባለመሆኑ በእናንተ ላይ የተፈጸመው አላውያን ነገሥታት በክርስቲኖች ላይ ሲፈጽሙት እንደኖሩት ያለ በመሆኑ ክብር የምታገኙበት እንጂ የምትዋረዱበት አይደለም፡፡ በተደራጁ ነውጠኞችም ሆነ ወደ ሕዝብ ይተኩሱ በነበሩ የጸጥታ አካላት ተገፋፍታችሁ ወደ ሁከት እና ብጥብጥ እንድትገቡ ተጽዕኖ ቢደረግባችሁም ሁሉንም በትዕግሥት እና በጽንዓት ተቋቁማችሁ ቤተክርስቲያናችሁ የጽኑ ክርስቲያኖች እናት መሆኗን አስመስክራችኋል እና ደስ ይበላችሁ፡፡

በክርስቲያኖች ላይ ገሀድ የወጣ አድሎ እየፈጸሙ በሰላም መኖር ስለማይቻል መንግሥትም አሠራሩን እንደገና ዞር ብሎ እንዲመለከት እና ሀገርን እና ሕዝብን ለማስተዳደር የተቀበሉትን ኃላፊነት ሕዝብን ለማስለቀስ እና የራሳቸውን ሃይማኖት የሚያስፋፉትን ባለሥልጣናት እኩይ ድርጊት እንዲያስታግሥልን እንጠይቃለን፡፡

መንግሥት የኢትዮጵያውያን ሁሉ መሪ፣ ፖሊስም የሕዝብ ሁሉ አገልጋይ መሆኑ ቢታወቅም በሀገር ስብከታችን የተፈጸመው ከዚህ ተቃራኒ በመሆኑ አንዱን እየደገፉ ሌላውን እያሳደዱ መኖር ስለማይቻል ወደ ፊት ተመሳሳይ ጥፋቶች እንዳይፈጸሙ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

ከጥር 10-13 ቀን 2012 ዓ.ም. በክርስቲያኖች ላይ አካላዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፤ የ4 ክርስቲያኖች ንብረት ወድሟል፤ 17 ክርስቲያኖች በግፍ ታስረዋል፤ 246 ክርስቲያኖች በተፈጸመባቸው ዛቻ እና ማስፈራሪያ፣ ድብደባ እንዲሁም ዘረፋ ምክንያት ተፈናቅለው ሐረር በሚገኘው ደብረ አድኅኖ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ተጠግተው እንደሚገኙ ለፍትሕ የቆመ የሰው ልጅ ሁሉ እንዲያውቀው እንፈልጋለን፡፡

በመንግሥት ሥልጣን ላይ ተቀምጠው ሃይማኖታዊ ተግባር እየፈጸሙ በሰላም አብሮ የኖረውን ሕዝብ የሚያበጣብጡ አካላትን ለሕግ እንዲያቀርብልን መንግሥትን እየጠየቀን ጥፋተኞች እየተለቀቁ ግፍ የተፈጸመባቸው ክርስቲያኖች ራሳቸው ከሳሽ፣ ራሳቸው ምስክር በሆኑ አካላት ለእስራት እየተዳረጉ በመሆኑ ይህ እኩይ ድርጊት እንዲቆም እንጠይቃለን፡፡

የክልሉ መንግሥት ሰሞኑን በጥፋት ላይ ተሰማርተው የነበሩትን ነውጠኞች በቊጥጥር ሥር እያዋልኩ ነው በማለት በመገናኛ ብዙኃን መናገሩ መልካም ቢሆንም ክርስቶስን አስሮ በርባንን የመፍታት አካሔድ መስተካከል እንዳለበት ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

በአንድ በኩል የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት ከማይዳሰሱ ቅርሶች አንዱ ሆኖ ተመዘገበልን ብለን ደስ ሲለን በሌላ በኩል ደግሞ የቤተ ክርስቲያን በዓላት አሻራ ከዐደባባይ እንዲጠፉ እየተደረገ በመሆኑ የነበረውን አጥፍቶ በአዲስ አሻራ የመተካት ድርጊት እንዲቆም እንጠይቃለን፡፡

የፌደራል መንግሥት ሆነ የክልሉ መንግሥት ጥምቀትንም ሆነ ሌሎች የዐደባባይ በዓላትን ሌሎች እምነቶች የሃይማኖት በዓላቸውን በሰላም እንዲያከብሩ እንደሚያደርጉ ሁሉ ክርስቲያኖች በዓል ሲያከብሩ ብጥብጥ የሚፈጠርበትን ሁኔታ እንዲያስቆምልን እናሳስባለን፡፡

ሌሎች ቤተ እምነቶች በዐደባባይ በዓል ሲያከብሩ የሚሰፍነው ሰላም ክርስቲያኖች ሲያከብሩ የሚደፈርስበትን ምክንያት መንግሥት አጣርቶ መፍትሔ እስከሚሰጠን ጥያቄያችንን ደጋግመን ማቅረባችን እንደምንቀጥል እንዲያውቀው እንፈልጋለን፡፡

የክልሉ መንግሥት ወጣት ክርስቲያኖችን ምክንያት እየፈጠረ ከማሰር እና ከማሳደድ እንዲቆጠቡ እየጠየቅን ወጣት ክርስቲያኖች እየተደራጃችሁ ራሳችሁን እና ቤተ ክርስቲያናችሁን ከመጠበቅ በተጨማሪ የቤተክርስቲያንን ይዞታ ለመንጠቅ፣ በምእመናን ላይ አድሎ ለመፈጸም የሚሞክሩ አካላትን ኃላፊነት፣ ጥፋቱን መቼ እና እንዴት እንደፈጸሙት፣ የት ቦታ እንደፈጸሙት መረጃ መያዝ እንዳለባችሁ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

መንግሥት ለጥያቄያችን አፋጣኝ መልስ ካልሰጠን እና ለፍርድ መቅረብ ያለባቸውን እየተወ የተበደሉትን ክርስቲያኖች ማሰሩን እና ማንገላታቱን ከቀጠለ በቤተክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት አደራጅተን ለመላው የሀገራችን ሕዝብ፣ መንግሥታዊ ለሆኑ እና ላልሆኑ ድርጅቶች፣ ለዓለም አቀፍ ተቋማት ማሳወቃችንን እንቀጥላለን፤ በቅርብ ቀንም ሰላማዊ ሰልፍ እንደምናደርግ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ

የሶማሌ እና የሐረርጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ጥር 20 ቀን 2012 ዓ.ም

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ