‹‹አቤቱ፥ እስከ መቼ ፈጽመህ ትረሳኛለህ? እስከ መቼስ ፊትህን ከእኔ ትመልሳለህ?›› (መዝ. ፲፪፥፩)

መምህር ሚክያስ ዳንኤል

ሚያዚያ ፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በጸሎቱ እግዚአብሔር አምላክን ሲማጸን እንዲህ አለ፤ ‹‹አቤቱ፥ እስከ መቼ ፈጽመህ ትረሳኛለህ? እስከ መቼስ ፊትህን ከእኔ ትመልሳለህ? እስከ መቼ በነፍሴ ኀዘንን አኖራለሁ? እስከ መቼም ልቤ ሁልጊዜም ትጨነቅብኛለች?›› (መዝ. ፲፪፥፩-፪)

ነቢዩ ዳዊት ‹‹አቤቱ፥ እስከ መቼ ፈጽመህ ትረሳኛለህ?›› ብሎ ፈጣሪው እግዚአብሔርን የጠየቀው ጠላቶቹ በዝተውበት በመከራ ሆኖ ነው፡፡ በዚያን ዘመን የእስራኤል ንጉሥ ሳኦል በነበረበት ጊዜ ዳዊት ብላቴና፣ በቤቱም ከወንድሞቹ ይልቅ ታማኝ ስለነበር የአባቱን በጎች ይጠብቅ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም የመረጠው ሰው ስለ ነበር በዱር በሚሄድበት ጊዜ አራዊቱ በሙሉ በእርሱ ዘንድ ሲሰበሰቡ በስመ እግዚአብሔር ጸልዮም አሸንፎ ገዝቷቸዋል፡፡ ከዚያም በጊዜው የተፈራውን ጦረኛ ጎልያድን በጠጠር ድንጋይ ድል ካደረገ በኋላ እልፍ ሠራዊቱን ገደለ፡፡ ሕዝቡም በአንድናቆት በማመስገን ዘመሩለት፤ ንገሡ ሳኦል ግን የገደለው ሺ ሠራዊት ብቻ ስለነበር ዳዊት ብላቴና ሆነ ከእርሱ በመብለጡ ቀንቶበት ሊበቀለው ማሳደድ ጀመረ፡፡ (፩ኛ ሳሙ. ፲፰፥፮)

ንጉሡ ሳኦልም እርኩስ መንፈስ አድሮበት ነበርና ዳዊትን ሊገድለው ተነሣ፤ ‹‹ደግሞም ጦርነት ሆነ፤ ዳዊትም ወጥቶ ከፍልጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፤ ታላቅ ግድያም ገደላቸው፤ ከፊቱም ሸሹ፡፡ ሳኦልም ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው፡፡ ዳዊትም በእጁ በገና ይመታ ነበር፡፡ ሳኦልም ዳዊትን ከግንብ ጋር ያጣብቀው ዘንድ ጦሩን ወረወረ፤ ዳዊትም ከሳኦል ፊት ዘወር አለ፤ ጦሩም በግንቡ ውስጥ ተተከለ፤ በዚያም ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ›› እንዲል፤ (፩ኛ ሳሙ.፲፱፥፰-፲)

በዘመናቱ የተነሡ ነገሥታት ሰዎችን በግፍ ሲጨፈጭፉና ሕዝብ ለሕዝብ ሲያገዳድሉ የኖሩት እርኩስ መንፈስ በልባቸው ስላደረባቸው ነበር፡፡ ስለዚህም ነቢዩ ዳዊት ጦሩን አጎንብሶ እንዳሳለፈው ክርስቲያኖችም በመከራና በችግራቸው ጊዜ በእግዚአብሔር ታምነው በትዕግሥት ሊያሰልፉ ይገባል፡፡

በመቀጠልም ነቢዩ ዳዊት ‹‹ልቤም በማዳንህ ደስ ይለዋል፡፡ የረዳኝን እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ፤ ለልዑል እግዚአብሔር ስምም እዘምራለሁ›› በማለት ስለ አምላክ አዳኝነት መስክሯል፡፡ (መዝ. ፲፪፥፭)

በኀዘን፣ በችግርና በመከራ ውስጥ ብንሆን እንዲሁም በበሽታ ብንሠቃይ እንኳን እኛ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር አምላካችንን ማመስገን ይኖርብናል፡፡ ምስጋና በምቾት ወይንም በድሎት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በመከራና ችግር ጊዜም መሆን እንዳለበት ከነቢዩ ዳዊት ጸሎት እንረዳለን፡፡ በኀዘናችንም ሆነ በደስታችን ጊዜ ማመስገን አለብን፡፡ የክርስትናችን መገለጫና የመስቀሉን ክብር የምንረዳበትና የምናውቅበትም በመሆኑም ችግር ሲገጥመን ከማማረር ይልቅ መፈተናችን በምክንያት መሆኑን በማመን፣ አምላካችንን ስለ እኛ የተቀበለውን መከራና ለእኛ ያለውን ፍቅር በማሰብ ማመስገን ይገባናል፡፡

አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር መኖራችንን የረሳን ይመስለናል፤ መከራ ውስጥ ሆነን እንዲሁም ሥቃያችን በዝቶ ልንቋቋመው ከምንችለው በላይ ሲሆንብን እግዚአብሔር እንደረሳን እናስባለን፡፡ ‹‹እግዚአብሔር በእውነት እኔን ያውቀኛል? ያስታውሰኛልን?›› ብለንም በመጠራጠር እራሳችንን እንጠይቃለን፤ ‹‹ዓለም ላይ ከሚኖረው ሕዝብም ለይቶ አያውቀኝም›› ወደ ማለትም እንደርሳለን፡፡ ሆኖም ግን በእግዚአብሔር ዘንድ እንኳን ሰው እንስሳም ይታወቃል፡፡ በሕይወታችን ውስጥም የሚያጋጥሙን ችግርና መከራ እንዲቀርፍልን ለእግዚአብሔር በመስጠት እንጸልይ፤ ከመከራም እንዲያሳርፈን እንማጸነው፡፡

በዚህ ጊዜ ኀዘን በዝቶብናል፤ ወረርሽኙ ባስከተለው የገንዘብ እክል የተነሣ ሀብት ንብረታችን ጠፍቷል፡፡ ጐጠኝነቱ፣ ዘረኝነቱና ዝሙቱ በተባባሰበት ዘመን ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ነጻ ሊያወጣን አይችልምና አምላካችን ጸሎታችንን እንዲሰማን መጀመሪያ ከኃጢአት መንጻት አለብን፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ወደ እኛ ፊቱን እንዲመለስ አብዝተን እንጸልይ፤ እንጹም፤ እንስገድ፤ አብዝተንም እንመጽውት፡፡

ነቢዩ ዳዊት ጠላቶቹ በዝተውበት በጸለየ ጊዜ እግዚአብሔር አምላኩ እንዳዳነው እኛንም ውድቀታችንና ጥፋታችን ከሚመኙ ጠላቶቻችን ሁሉ አድኖ ለጠላት ከመሸነፍ እንዲታደገን ወደ እግዚአብሔር እንጩህ፤ በጸሎት እንማጸነው፤ ለእርሱም እንገዛ፡፡ ‹‹በመከራህ ቀን ትጠራኛለህ አድንህማለሁ…›› እንዳለውም መከራ በበዛብን ሰዓት ወደ እግዚአብሔር አብዘተን መጮህ አለብን፡፡ እርሱም ጸሎታችን እንደሚሰማን በነቢዩ ዳዊት ታሪክ ልንረዳ እንችላለን፡፡ ጆሮንና ዓይንን የፈጠረ አምላክ ጸሎታችን ይሰማናል፤ መከራችንንም ያያልና ወደ እርሱ እንጸልይ፤ እንማጸነው፡፡ (መዝ. ፵፱፥፲፭)

ምንም የማይሣነው ሁሉን ቻይ አምላክ በመሆኑም የእርሱን ርዳታ መጠየቅ የተገባ ነው፤ ‹‹ሁልጊዜ ማዳንህን የሚወዱ፥ “ዘወትር እግዚአብሔር ታላቅ ነው” ይበሉ፡፡ እኔ ችግረኛና ምስኪን ነኝ፤ እግዚአብሔርም ይረዳኛል፤ ረዳቴ መጠጊያዬም አንተ ነህ፥ አቤቱ አምላኬ አትዘግይ›› እንዲል፡፡ (መዝ. ፷፱፥፬-፭)

ብዙዎች በጸሎታችው ያሳሰቡት ነገር በቶሎ ሳይሳካ ሲቀር እግዚአብሔር የዘገየ ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን አምላክ ምንም ለማድረግ አይቸኩልም፡፡ ሁሉን ነገር የሚያደርገው ግን በጊዜውና በምክንያት ስለሆነ በትዕግሥት መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ዘወትር ከሚያጋጥመን ፈተና እንድንወጣ፣ እግዚአብሔር አምላክም ከጠላቶቻችን እንዲሰውረንና ድል እንዲነሣልን ለእርሱ መታመንና መማጸን አለብን፡፡

የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ በሙሉ መዝሙረ ዳዊትን ይደግሙ ዘንድ ፍትሐ ነገሥቱ ስለሚያዝም ከአቡነ ዘበሰማያት በመቀጠል መዝሙረ ዳዊትን እንድንደግምም ሥርዓት ስለተመሰረተልን ዘወትር ጸሎቱን ልናደርስ ይገባል፡፡ ጸሎታችንም ወደ እግዚአብሔር እንዲደርስና ምላሽም እንድናገኝ ነቢዩ ዳዊት እንዳዘነው አዝነን እንዲሁም በተሰበረ ልብ ሆነን ለችግራችን መፍትሔ እንዲሰጠንና ስለነፍሳችን ድኅነት መጸለይ አለብን እንጂ ሥጋዊ ድሎታችን ለሟሟላት መሆን የለበትም፡፡

ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ በኃጠአት ሊጥለን ሁልጊዜ ይጥራልና እግዚአብሔር አምላካችን ከጠላታችን እንዲጠብቀን መማጸን አለብን፡፡ ነቢዩ ዳዊትም ‹‹አቤቱ አምላኬ፥ ተመልከተኝ ስማኝም፤ ለሞትም እንዳያንቀላፉ ዐይኖቼን አብራቸው፡፡ ጠላቶቼ አሸነፈነው እንዳይሉ፥ የሚያስጨንቁኝም እኔ ብናወጥ ደስ እንዳይላቸው፥ እኔ ግን በቸርነትህ ታመንሁ›› በማለት ንጉሥ ሆነ በንግሥናው ወይንም ባለው ሀብት እንዲሁም በሠራዊቱ እንዳልታባዬ ተናግሯል፡፡ ባለጸጎች ባካበቱት ሀብት፣ መሪዎች በሥልጣናቸው፣ ሠራዊቶች ደግሞ በሚያነግቱት የጦር መሣሪያ እና በጉልበታቸው ይታበያሉ፡፡ ነገር ግን እኛም በእግዚአብሔር ቸርነት ልንታመን ይገባል እንጂ አላፊ ጠፊ በሆነ ግዑዝ ነገር መታበይ የለብንም፡፡ ምክንያቱም ምድር ላይ ያለ ማንኛውም ቁሳዊ ነገር በጊዜ ብዛት የሚበላሽና የሚጠፋም ከመሆኑ ባሻገር በከንቱ ሕይወታችንን እንድናባክን ያደርገናል፤ ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚሰጠን አምላካችን እግዚአብሔር ብቻ በመሆኑ በእርሱ መታመን ያስፈልጋል፡፡ (መዝ. ፲፪፥፫-፭)

በአሁኑ ጊዜ በሽታ በዝቷል፤ ኢትዮጵያ ሀገራችንም ልጆቿ ባለመስማማት በጎሳና በዘር ተከፋፍላለች፤ ሀገረ እግዚአብሔር ግን በመሆኗ ስለ ቅዱሳኑ፣ ስለ ሰማዕታቱና ስለ ሕፃናት ብሎ በቸርነቱ እንዲጎበኘን ወደ እርሱ ካለቀስን በጸሎታችን የመጣብንን ቊጣ መመለስ እንችላለን፡፡

እኛ ከኃጢአት ሳንነጻ ሀገር መስተካከል አትችልምና መፍትሔ ለማግኘት የሚያስፈልገው ስለ ችግሮቹ መብዛት ደጋግሞ ማውራት ሳይሆን በሃይማኖት ጸንተን፣ በምግባር ቀንተን፣ የወደቅን ተነሥተንና ንስሓ ገብተን፣ ፍትሐት ዘወልድ ተደግሞልን ነጻ ስንሆን ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታችንን ተቀብሎ በቸርነቱ ይጐብኘን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር