ነቢዩ ዮናስ ክፍል ሁለት

በልደት አስፋው

የካቲት ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም  

እንዴት ናችሁ ልጆች? እኛ እግዚአብሔር ይመስገን በጣም ደኅና ነን፡፡ በትናንትናው ዝግጅታችን እግዚአብሔር አምላካችን ነቢዩ ዮናስን አስተምር ብሎ ወደ ነነዌ ሰዎች እንደ ላከው፣ እርሱ ግን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ላለመቀበል በመርከብ ተሳፍሮ ወደ ሌላ አገር እንደ ሸሸ፣ በነቢዩ ዮናስ ምክንያትም መርከቡ እስኪሰጥም ድረስ ባሕሩ በማዕበል እንደ ተናወጠ፣ በዚህ የተነሣም ተሳፋሪዎቹ ዕጣ ተጣጥለው ነቢዩ ዮናስን ወደ ባሕሩ እንደ ጣሉት ነግረናችሁ ነበር፡፡ ልጆች! ቀጣዩን ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፤

እናም ሰዎቹ ነቢዩ ዮናስን ወደ ባሕር ሲጥሉት እግዚአብሔር ያዘጋጀው ታላቅ ዓሣ ዋጠው፡፡ ነቢዩ ዮናስም በዓሣው ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ቆየ፡፡ በዚያ ጨለማ በኾነ የዓሣ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀን መቆየት አያስፈራም ልጆች? በጣም ነው የሚያስፈራው፡፡ ነቢዩ ዮናስም እግዚአብሔር እንዲያወጣው በዓሣው ሆድ ውስጥ ኾኖ አብዝቶ ጸለየ፡፡ እግዚአብሔርም የነቢዩ ዮናስን ጸሎት ሰምቶ ዓሣውን እንዲተፋው አዘዘው፡፡ ዓሣውም ነቢዩ ዮናስን በየብስ (በደረቅ መሬት) ላይ ተፋው፡፡ ነቢዩ ዮናስም ‹‹ይህቺ አገር ማን ትባላለች?›› ብሎ የአካባቢው ነዋሪዎችን ሲጠይቅ አገሪቱ ነነዌ እንደ ኾነች ነገሩት፡፡ ይገርማችኋል ልጆች! ከዚህ በኋላ ነቢዩ ዮናስ የእግዚአብሔርን ቃል እሺ ብሎ ተቀብሎ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ገብቶ ‹‹በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለባበጣለች (ትጠፋለች)›› ብሎ አስተማረ፡፡

የነነዌ ሰዎችም ቃሉን ሰምተው ከኀጢአታቸው ተመልሰው፣ ማቅ ለብሰው ንስሐ ገቡ፡፡ ከከንጉሡ ጀምሮ ሕፃናትም ጭምር፣ እንስሳትም ሳይቀሩ ምንም ምግብ ሳይቀምሱ፣ ውኀም ሳይጠጡ ለሦስት ቀን ጾሙ፡፡ እንዲምራቸውም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፡፡ እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው መመለሳቸውንና ንስሐ መግባታቸውን አይቶ ይቅር አላቸው፤ ነነዌንም ከጥፋት አዳናት፡፡ ልጆች ነቢዩ ዮናስ እግዚአብሔርን አልታዘዝም ያለው ለምን መሰላችሁ? እኔ ነነዌ ትገለባበጣለች (ትጠፋለች) ብዬ ባስተምር ሕዝቡ ተጸጽቶ ይቅርታ ቢጠይቁ እግዚአብሔር ይቅር ሲላቸው እኔ ውሸታም ነቢይ እባላለሁ ብሎ ፈርቶ ነበር፡፡ ነገር ግን የነነዌ ሰዎች ነቢዩ ዮናስንም ውሸታም ነው አላሉትም፡፡ ትምህርቱን ተቀብለው ከጥፋት በመዳናቸው እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡ እግዚአብሔር ምን ያህል ሩኅሩኅና ቸር እንደኾነ አያችሁ ልጆች? ምንም እንኳን እኛ ብንበድለውም፣ ብናሳዝነውም ተጸጽተን ንስሐ ከገባን የቀደመውን በደላችንን ደምስሶ ኀጢአታቻንን ይቅር ይለናል፡፡

ልጆች ነነዌ ከመቶ ሃያ ሺሕ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሳት የሚኖሩባት ታላቅ ከተማ ነበረች፡፡ እነኚህ ዅሉ ሰዎች ንስሐ ባይገቡ ኖሮ ነነዌን እሳት ይበላት ነበር፡፡ የነነዌ ሰዎች ከበደላቸው ተጸጽተው፣ ንስሐ ገብተው በመጾማቸውና በመጸለያቸው እግዚአብሔር ከጥፋት አድኗቸዋል፡፡ ልጆች! እኛም ዛሬ እግዚአብሔርን ብንበድለውና እርሱ የማይወደውን ክፋት ብንፈጽም እንደ ነነዌ ሰዎች ተጽጽተን ንስሐ ከገባን አምላካችን ቸር፣ ታጋሽ እና ይቅር ባይ አምላክ ስለኾነ ኀጢአታችንን ይቅር ብሎ ከጥፋት ያድነናል፡፡ እኛ ክርስቲያኖች በየዓመቱ ጾመ ነነዌን የምንጾመውም እግዚአብሔር ኀጢአታቻንን ይቅር እንዲለን ነው፡፡ በሉ እንግዲህ ልጆች በሌላ ጊዜ በሌላ ታሪክ እስከምንገናኝ በደኅና ቆዩ፡፡ ሰላመ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይኹን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡