‹‹ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል›› (መዝ. ፹፰፥፲፪)

በትንቢት ‹‹ታቦርና አርሞንኤም በስም ደስ ይላቸዋል›› ብሎ ነቢዩ ዳዊት እንደተናገረው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን በዓሉ በድምቀት ይከበራል፡፡ (መዝ. ፹፰፥፲፪)

በዚህችም ቀን መድኃኒታችን ሦስቱን ደቀ መዛሙርቶቹን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ ታቦር ተራራ ላይ አወጣቸው። መልኩም በፊታቸው ተለወጠ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ፡፡

ስለ እርሱም ጌታችን የሰው ልጅ በጌትነቱ ሲመጣ እስከሚያዩት ድረስ በዚህ ከቆሙት መካከል ሞትን የማይቀምሱት አሉ አለ፡፡ ሰዎች ሁሉ እርሱ ለሙሴ ጌታውና ከሞት ያስነሣው እንደሆነ ለኤልያስም ፈጣሪው እንደሆነና ካሳረገበትም ያወረደው እርሱ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ እነሆ ከጌታ ከኢየሱስ ጋራ እየተነጋገሩ ሙሴና ኤልያስ ወደእርሱ መጡ፡፡ ስለዚህም ጴጥሮስ ጌታችንን እንዲህ አለው፤ ‹‹አቤቱ በዚህ ትኖር ዘንድ ትወዳለህን? ሦስት ሰቀላዎችንም አንድ ላንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ እንሠራ ዘንድ።››

በዚህም ቃል የደካማነትና የትሕትና ምልክት አለበት። ደካማነት የተባለ ጴጥሮስ ጌታችን ከሰማይ የወረደበትን ሥራ ትቶ በተራራ ላይ ይኖር ዘንድና ራሱን የሚሠውርበትን ቤት ይሠራለት ዘንድ የተናገረው ነው። ትሕትና ያልነውም ጴጥሮስ ለራሱና ለባልንጀሮቹ ሐዋርያት ቤት ይሠራ ዘንድ ስለ አላሳበ ነው። ራሱንና ባልንጀሮቹ ሐዋርያትን እንደ ባሮች ነቢያትን ደግሞ እንደ ጌቶች አድርጎ አስቧልና።

ስለ ሐዋርያትም የዕውቀት ማነስ አታድንቅ፤ በዚያን ጊዜ ፍጹማን አልሆኑምና። እንዲህም በሚልበት ጊዜ ጌታችን በሰው እጅ የተሠራ ማደሪያን የማይሻ መሆኑን ለጴጥሮስ ያሳየው ዘንድ እነሆ ደመና ጋረዳቸው።

የጌታችን ጌትነቱን የሚገለጽ በሐዋርያትም ልቡና እምነትን የሚያጸና እንዲህ የሚል ቃል ከደመና ውስጥ መጣ። ይህ የምወደው በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው፤ እርሱንም ስሙት። ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋራ ሲነጋገሩ ተሰሙ። ስለ እርሱ መምጣት የተናገሩትን ትንቢታቸውንም በቸርነቱ አረጋገጠ። ወደ ተራራ ላይ በመውጣቱም ነብያትና ሐዋርያት ደስ አላቸው።

ሁለተኛም የአብን ቃል በሰሙ ጊዜ ከእነርሱ ሥውር የነበረ የወልድ ዋሕድን በእውነት ሰው መሆን በዚያን ጊዜ ተረዱ፤ ያን ጊዜ የጌትነቱ ክብር ተገልጧልና። ሐዋርያትም ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው የሆነ እርሱ ሙሴን ከመቃብር ያስነሣው፣ ኤልያስንም ያሳረገው፣ አውርዶም ያመጣው እርሱ እንደሆነ አወቁ። ከእርሱ በቀር ማንም ማን የሙሴን መቃብር የሚያውቅ የለምና። በሰማይና በምድር ሥልጣን ካለው ከሁሉ ጌታ በቀር ሙታንን አድኖ ሊያስነሣቸው ማንም አይችልም።

ደብረ ታቦርም የቤተ ክርስቲያን አምሳል ሆነች። ከብሉይና ከሐዲስ በውስጧ ሰብስባለችና። የአብንም ቃል በሰሙ ጊዜ በግምባራቸው ፍግም ብለው በምድር ላይ ወደቁ፤ እንደ ሙታንም ሆኑ። ከዓለም አስቀድሞ ከእርሱ ጋራ በህልውና እንዳለ ለልጁ አብ ምስክርን ሆነ፤ ወዲያውኑ ሙሴ ወደ መቃብሩ ኤልያስም ወደ ቦታው ተመለሱ።

ሐዋርያትንም በአነቃቸው ጊዜ ከብቻው ጌታችን በቀር ማንንም አላገኙም። ከባሕርያችን የተዋሐደና ሥጋችንን የለበሰ ፍጹም አምላክ እንደሆነ በዚህ ሐዋርያት አስተማሩ።

እንግዲህ እናስተውል፤ ሰው ካልሆነ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ድንግል ማርያምን በአበሠራት ጊዜ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው እንዴት አላት። አምላክ ካልሆነስ ለመንግሥቱ ፍጻሜ የለውም እንዴት አላት። ሰው ካልሆነ በበረት እንዴት አስተኙት፤ አምላክስ ካልሆነ መላእክት ከሰማይ ወርደው ለእግዚአብሔር በሰማያት ምስጋና በምድርም ሰላም ለሰውም ግዕዛኑ ሊሰጠው እያሉ እንዴት አመሰገኑ። ሰው ካልሆነ ዮሐንስ በውኃ እንዴት አጠመቀው፤ አምላክስ ካልሆነ አልዓዛርን ከመቃብር እንዴት ሊያስነሳው ቻለ።

ይህ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንድ ልጅ አካላዊ ቃል እግዚአብሔር እርሱ ያለመለወጥ ያለመለየት አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው እንደሆነ እናምንበታለን። እርሱም ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ሁልጊዜ አንድ ህላዌ ነው፤ ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ፤ አሜን።

ምንጭ፤ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ነሐሴ፤ ፲፫ ቀን