‹‹ተቈጡ፤ አትበድሉም›› (ኤፌ. ፬፥፳፮)

መጋቢት ፴ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ቊጣ ተገቢ እንደሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ‹‹ተቈጡ፤ አትበድሉም፤ ፀሐይ ሳይጠልቅም ቊጣችሁን አብርዱ›› በማለት ተናግሯል፡፡ ከሰዎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት ውስጥ እውነት ሲጠፋ ወይንም ሐሰት ሲንሰራፋ ኃጢአትን በመንቀፍ መቈጣታችን ተገቢ ነው፡፡ ሰዎችን ከስሕተት እና ጥፋት ለመመለስ መቈጣት የተፈቀደ እንደሆነ በዚሁ እንረዳለን፡፡ ሆኖም ግን ከልክ ባለፈ ቊጣ የሰዎችን ስሜት በመጕዳት መበደል ኃጢአት ነው፡፡ ይህም ማለት ትክክል ያልሆነን ነገር ስንመለከትና ስንሰማ ወይንም ስሕተት ሲፈጸም አይተንና ሰምተን ብንቈጣ ተገቢ ሆኖ ሳለ የመቈጣታችን ስሜት ግን ለመፍትሔ እንጂ ለባሰ ጥፋት የሚዳርግ ከሆነ እንዲሁም የተቈጣንበት ነገር አግባብነት ከሌለው የማይገባ ቊጣ እንደሆነ መረዳት ይኖርብናል፤ የሚገባ ቊጣ ሲሆን ግን ትክክል መሆኑን በዚሁ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ (ኤፌ. ፬፥፳፮)

ቊጣችን በሌሎች ሰዎች ላይ በጥላቻ የተነሣ ሲሆን ጎጂ እና አጥፊ ነው፤ ከእነርሱ ጋር በሚኖረን ግንኙነትም ጥልን ያጭራል፡፡ ስለዚህም ሰዎች የእኛን ሐሳብ አልተቀበሉትም ብለን መቈጣት ተገቢ አይደለም፡፡

አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በሌሎች ላይ ባላቸው ጥላቻ ወይንም በራሳቸው ድክመትም የተነሣ ቊጣቸውን መቈጣጠር ያቅታቸውና ወደ አልተፈለገ ክርክር እንዲሁም ጥል ውስጥ ይገባሉ፡፡ ሥነ ልቡናዊ እንዲሁም አካላዊ ጒዳትም ያደርሱባቸዋል፡፡ በተለይም በዚህ ጊዜ ሰዎች በእውነት መንገድ ላይ በሚጓዙ ክርስቲያኖች ላይ የሚያደርሱት ጒዳት ከፍተኛ ነው፤ ምክንያቱም እውነቱን ከመቀበል ይልቅ በእነርሱ ላይ ጥላቻ ስለሚያድርባቸው ከእነርሱ ጋር ስምምነት ላይ አይደርሱም፡፡ ሐሰታቸው ተቀባይነት በማያገኝበት ጊዜም ባልተገባ ቊጣ ሆነው በክፉ ቃላት ሰዎችን ያሳዝናሉ፤ ያስከፋሉ፤ ይጐዳሉም፡፡ ከዚያም ባሻገር ሥራዬ ብለው በእነርሱም ዘንድ ንዴት በማጫር ወደ ድብድብ ውስጥ እንዲገቡ ይገፏፏቸዋል፡፡ በመሆኑም ከእነዚህ ዓይነት ንዴትና ሰዎች መራቅና መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

ቊጣችንን በኃጢአት እንዳንወድቅ ለመከላከል ልንጠቀምበትም እንችላለን፡፡ በእኛ ውስጥ ስላለው የኃጢአት ምክንያትና ስለሚፈታተነን ነገር በራሳችን ላይ ተቈጥተን በቁጭት ወደ ንስሓ ለመመለስ ይረዳናል፤ ቊጣችንም ከኃጢአት ለመራቅ መጠቀም ተገቢ ነውና፡፡

ከዛሬው እኩይ ተግባራችን ለመመለስና ደካማ ማንነታችንን ለመቀየር በራሳችን ላይ መቊጣታችን ተገቢ ነው፡፡ ራሳችንን ‹‹በእውነት መንገድ እየሄድን ነው?›› ብሎ ለመጠየቅ ብርታት ይሰጠናል፡፡ ‹‹እኔ መሆን ያለብኝ በጐ ሰው ወይንም እውነተኛ ክርስቲያን ነው!›› ለማለትም ይረዳናል፡፡ ኃጢአት መሥራት ጥፋት መሆኑንና ከባድ ቅጣት እንደሚያስከትልም አውቀን ዳግም እንዳንበድል ስናጠፋ በራሳችን መቈጣት አለብን፡፡ ይህም የባሰ ኃጢአት ከመሥራት ለመቈጠብ ያግዘናል፤ በተሳሳተው መንገድም እንዳንጓዝም ራሳችን ለመከላከል ይረዳናል፡፡

ኃጢአት ሰዎችን ከእግዚአብሔር የሚያርቅ መጥፎ ምግባር በመሆኑ ለጥፋት የሚዳርገን ማንኛውም ነገር ሊያስቈጣን ይገባል፡፡ ምክንያቱም ትክክል አለመሆኑን ሁሌም መንቀፍ እንጂ እግዚአብሔር አምላክ ቸር በመሆኑ ለዚህ ብሎ አይቀጣኝም፣ ንስሓ መግባትም በእርጅና ጊዜ ነው ብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም፡፡ በሕይወታችን ከፈጣሪያችን ርቀንና አምላካችንን የሚያሳዝን ሥራ እየሠራን መሆኑ እጅጉን ሊያናድደን ይገባል፡፡ የመዳን ቀን አሁን በመሆኑ አምላካችን የሰጠንን ዕድሜ ሙሉ በበጎ ምግባር ማሳለፍ አለብን፤ ማንኛውንም ኃጢአት መሥራታችን ለከባድ ቅጣት ይዳርገናልና፡፡ ለጠላታችን ሰይጣንም መሸነፍ እንደሆነ በመረዳትና በማመን በራሳችን መናደድ እና መቈጣት አለብን፡፡

ከዚህም በሻገር በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አለመኖራችን ሊያናድደንና ሊያስቆጨን ይገባል፡፡ የምንኖረው ዓለማዊ ሕይወት ከሰው ሰብእና ከማስወጣቱ በተጨማሪ ሕገ እግዚአብሔርን እንድንተላለፍ፣ ትእዛዛቱን እንዳንፈጽምና ሥርዓቱን እንዳንጠብቅ ያደርገናል፡፡ ሕይወታችንን በሙሉ በተሳሳተ መንገድ እንጓዛለን፤ ይህ በጣም የሚያናድድና የሚያስቈጣ ነገር ነው፡፡ አብዛኛው ሰው ግን ይህን ተረድቶ በንስሓ በመመለስ ለሕጉ ተገዢ ሁና በሥርዓቱ ለመኖር አያስብም፡፡ በዚህ ጊዜም የእግዚአብሔር ቊጣ ወደ እኛ ይመጣል፡፡ ይህ በአሁኑ ጊዜ እያየነው ያለ እውነታ በመሆኑ ማናችንም ልንክድ አንችልም፡፡ እግዚአብሔርን በመፍራት መኖር ሲገባን ባለመኖራችን፣ ሕጉን በመተላለፋችንና ትእዛዛቱን ባለመፈጸማችን በኃጢአት ጠፍተናልና በመቅሠፍት እየተቀጣን ነው፤ በዚህም ተጸጽተን ይቅርታና ምሕረትን ልንጠይቅ ይገባል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ከቊጣ እንዲመለስልን መለመን የምንችለው በጸሎት ነው፤ ሆኖም ግን በዚህ ጊዜ መጸለይ እንዳለብን የምናስብም ሆነ በጸሎት የምናምን ጥቂቶች ነን፡፡ በርካቶች ጸሎት አስፈላጊ አይመስላቸውም፤ ለእርሱም ጊዜ አይኖራቸውም፡፡ አላማወቃቸው ነው እንጂ ይህ እጅጉን ሊያስቆጫቸውና ሊያናድዳቸውም የሚገባ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ድኅነት ልናገኝ የምንችልበትን መንገድ ሠርቶልን ሳለ እኛ ግን ይህን እውነት ማወቅም ሆነ መተግበር አቅቶናል፡፡ ጠላታችን ዲያብሎስም የእኛ ድክመት ስለሚያስደስተው በዓለማዊ ሐሳቦችና ምግባራት ሰውነታችንን በመያዙ ከታሰርንበት የኃጢአት አረንቋ መላቀቅ አልተቻለንም፤ በዚህ መናደድና መቈጣት ያስፈልጋል፡፡ ቊጣታችንም ወደ እግዚአብሔር እንድንመለስ ይረዳናል፡፡

ነገር ግን ብዙዎቻችን የጸሎት ጊዜያትን አውቆ ከመጸለይና በአጽዋማት ወቅትም ከመጾም ወደ ኋላ ማለት እንሰንፋለን፡፡ ለምሳሌ ይህን የዐቢይ ጾም በሚገባ እየጾምን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበልንን መከራ ማሰብና መስቀሉን መሸከም ሲገባ ብዙዎቻችን ሰበብ እየፈጠርን ራሳችንን እናደክማለን፡፡ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ከመጾም ይልቅ በበሽታና ሌሎች ሰበቦችን በመፍጠር ሰዓት እያጓደልን እንጾማለን፡፡ ነገር ግን የሚቀርብን ድኅነትም ሆነ በረከት በመኖሩ ይህ ሊያስቆጣን ይገባል፡፡ ራሳችንን እንደደካማ ከመቊጠር ይልቅ እግዚአብሔር አምላክ በአምሳሉና በአርአያው የፈጠረን ክቡር ፍጡር መሆናችንን ተረድተን ለዘለዓለማዊ ሕይወት በጸሎት፣ በጾም፣ በስግደት እየተጋን በሃይማኖት ጸንተን ልንኖር ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር