በጎ አድራጊ ምእመናን ለማኅበሩ ሕንፃ ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አደረጉ፡፡

ግንቦት 22/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

•    የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በዮድ አቢሲንያ ተካሄዷል፡፡
•   “ቅዱስ ሲኖዶስ ከእናንተ ጋር ነው፡፡”ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ
•   “ይህን ቤት ለመሥራት የነበረው ውጣ ውረድ፣ የደረሰባቸሁ መከራ ብ
ዙ ነው፡፡ ብዙውን ፈተና አልፋችሁታል፡፡” ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፡፡

በግንባታ ላይ የሚገኘውን የማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት ሕንፃ ማስፈጸሚያ የሚውል በበጎ አድራጊ ምእመናን አነሣሽነትና አስተባባሪነት ሰኞ ግንቦት 20 ቀን 2004 ዓ.ም. ቦሌ በሚገኘው ዮድ አቢሲንያ የባሕል ምግብ ቤት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ተካሄደ፡፡መርሐ ግብሩ በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡብ ትግራይ ማይጨው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በጸሎት የተከፈተ ሲሆን ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳትና የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የኢሉባቦርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ማኅበረ ቅዱሳንንና የማኅበረ ቅዱሳንን እንቅስቃሴ ለመደገፍ በራሳቸው ፍላጎት የተሰበሰቡትን በጎ አድራጊ ባለሀብቶችንና ምእመናንን አመስግነዋል፡፡ በሰጡት ቃለምእዳን፡፡ “መንፈሰ ጠንካሮች ሁኑ፣ በማንኛውም በኩል እንዳትበገሩ፡፡ እኛ በእናንተ ልበ ሙሉ ነን፡፡ እምነታችሁ ጠንካራ ነው፡፡ ሃይማኖት ካለ ማንኛውንም ነገር መሥራት ይቻላል፡፡ እንመካባችኋለን፡፡ ከእኛ ይልቅ ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቃላችሁ፡፡ ይህ ቤት ለመሥራት የነበረው ውጣ ውረድ፣ የደረሰባችሁ መከራ ብዙ ነው፡፡ ብዙውን ፈተና አልፋችኋል፡፡ በዚህ ሳልፍ በጅምር ያለውን ሕንፃ እያየሁ ገንዘብ አጡ ማለት ነው? አቃታቸው እያልኩ ከራሴ ጋር እሟገት ነበር፡፡ ረዳት አጡ? መቼ ይሆን የሚፈጸመው? እነዚህ ልጆች ያሳፍሩን ይሆን እንዴ እያልኩ እሟገታለሁ፡፡ እኔ ተሸጬ ሁሉም ነገር በሆነ፡፡ ሽማግሌን ማን ይገዛል? እግዚአብሔር ሆይ እርዳቸው፣ ቅድስተ ቅዱሳን በደጅሽ ነው ያሉት በረድኤትሽ እርጃቸው እያልኩ ስጸልይ ነው የኖርኩት፡፡ ተስፋ አለን፡፡ ዛሬ የተሰበሰባችሁት ትጨርሱታላችሁ” በማለት አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ፊልጶስም በሰጡት ቃለ ምእዳን እነዚህ ልጆቻችን በትእግሥት ሁሉን አሳልፈው፣ ድል መትተው፣ ድል ተጎናጽፈው እዚህ በመድረሳቸው እግዚአብሔር ከእነሱ ጋር መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ሰው የሚታወቀው በሥራው በእምነቱ፣ በአቋሙ ነው፡፡ እነዚህ ልጆቻችን ካየናቸው ጊዜ ጀምሮ ወደ ኋላ ያላሉ እንደብረት ምሰሶ የሆኑ፣ አንድነታቸውን አጠናክረው አዋሕደው ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ የማይሉ፣ የመጣባቸውንና የሚመጣባቸውን ሁሉ ፈተና በጣጥሰው ያለፉና የሚያልፉ ለሁላችን አብነት የሚሆኑን ለቤተ ክርስቲያናችን መኩሪያና መመኪያዎች ናቸው፡፡ ታግለው ሩጠው እዚህ በመድረሳቸው እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባል ብለዋል፡፡ ብፁዕነታቸው አያይዘውም ማኅበረ ቅዱሳን ልጆቻችን 20 ዓመታትን ታግላችሁ አልፋችሁ እዚህ ደርሳችኋል፡፡ ወደፊት ደግሞ የት እንደምትደርሱ እግዚአብሔር ያውቃል፡፡ በርቱ ጠንክሩ፡፡ በርትታችሁ ከሠራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእናንተ ጋር ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ ከእናንተ ጋር ነው፡፡ ከእናንተ ጋር ይሠራል በማለት ማኅበሩን ያበረታቱ ሲሆን በጎ አድራጊ ምእመናን አስመልክቶም እግዚአብሔር በሰጣችሁ ለቤተ ክርስቲያናችሁ፣ ለእምነታችሁ ለታሪካችሁ፣ ለባሕላችሁና ለቅርሳችሁ ካላችሁ ላይ መስጠት፣ መለገስ እናንተን ብፁዓን ያሰኛችኋልና ስጡ ብለዋል፡፡

 

የመርሐ ግብሩ አስተባባሪና የበጎ አድራጊዎቹ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደርቤ ሥነ ጊዮርጊስ መርሐ ግብሩ የተዘጋጀበት ዋነኛ ምክንያት ሲገልጹ “ ማኅበረ ቅዱሳንን ለአራት ዓመታት ያህል በጥልቀት የሚሠራውን ሥራ ለመከታተል ጥረት አድርገናል፡፡ ምንድነው የሚሠሩት? እንዴት ነው ሥራቸውን የሚሠሩት ብለን አጠናን፡፡ 7 የቤተ ክርስቲያን ወንድማማቾች በመሠባሰብ ውይይት አደረግን፡፡ እንዴት ዝም ብለን እንመለከታለን? ይህ ሕንፃ ከተጀመረ 10 ዓመት ሞላው፡፡ ሊጨርሱት አልቻሉም ስለዚህ ለምን እኛ አናስጨርሳቸውም? በማለት የማኅበሩን ጥረት ለማገዝ ተስማማን፡፡ በጀታቸውን ለገዳማትና አድባራት፣ ለአብነት ትምህርት ቤቶች ለሕንፃ ግንባታ ያውሉታል፡፡ ሥራቸውን እየሠሩ ያሉት አቧራ እየጠረጉ ነው፡፡ የምንችለውን ሁሉ አድርገን ይህንን ሕንፃ እናስጨርሳቸው የሚል ዓላማ ያዝን ወንድማችን አቶ ትእዛዙ ኮሬ የዮድ አቢሲንያ የባሕል ምግብ ቤት ባለቤትም `ምእመናንን አሰባስቡ የምግብ ቤቱን አዳራሸና ሙሉ የምሳ ወጪውን እችላለሁ´ በማለቱ የዛሬውን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር አዘጋጀነው፡፡” በማለት ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም  20 ዓመታት ምንም ሳይረዱ እዚህ ከደረሱ ሕንጻውን አስጨርሰን የቢሮ መሣሪያዎችን ብናሟላላቸው፣ ከጀርባቸው ሆነን ከደገፍናቸው ታላቅ ሥራ ይሠራሉ ብለን እናምናለን፡፡ ማኀበረ ቅዱሳን በእሳት የተፈተነ ወርቅ ነው፡፡ በዚህ ዘመን የተሰጠን ታላቅ ማኅበር ነው፡፡ በጸሎታችሁ ማኅበሩን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ የምንችለውን ሁሉ አድርገን ማኅበሩን እንደግፍ፣ ከጎኑ እንሰለፍ፡፡ ይህ ኮሚቴ እስከ መጨረሻው ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ለመጓዝ ወስኗል ብለዋል፡፡

 

የዮድ አቢሲንያ የባሕል ምግብ ቤት ባለቤት አቶ ትእዛዙ ኮሬ በበኩላቸው የዛሬውን መርሐ ግብር ለማዘጋጀት ምን እንዳነሳሳቸው ሲገልጹ ሁላችንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ነን፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የሚሠራውን ሥራ በቅርበት ስንከታተል ቆይተናል፡፡ በየገዳማቱ ያሉትን ችግሮች ለማቃለል፣ የአብነት ት/ቤቶችን ለማጠናከር እያደረገ ያለው ጥረት ተመልክተናል፡፡ ከወር ደመወዛቸው እየቆጠቡ የሚያደርጉትን በመመልከት በተለይም በንግዱ ውስጥ ያለነው የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንዴት እንርዳቸው በማለት ለሚፈጽሙት በጎ ሥራ ለማገዝ ነው የተነሳነው፡፡ አቅም በፈቀደ መጠን የድርሻችንን ለመወጣት ይህ ጅምር ነው፡፡ ወደፊት ብዙ ነገሮችን በጋራ እንሠራለን በማለት ገልጸዋል፡፡

 

ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ ቤተ ክርስቲያናችን ወደፊት ምን ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚገባት ያመለከተ ጥናት በአጭሩ አቅርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁል ጊዜ ስንዱ እመቤት ናት፡፡ የጎደላት አለ አንልም፡፡ ነገር ግን ሁለንተናዊ እድገት ያስፈለጋታል፡፡ እድገቱ የሁላችንም እንደሆነና እኛም ቤተ ክርስቲያን ሆና እንድናያት የምንመኘው ደረጃ እንድትደርስ መጣር አለብን ቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ እድገት ያስፈልጋታል ያሏቸውን ዝርዝር ነጥቦችን በመጥቀስ አቅርበዋል፡፡

 

ዶ/ር የራስ ወርቅ አድማሴ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጡትን ምሁራንን በመወከል ባሰሙት ንግግር እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያለ የተደራጀ አካል ሲኖር ቤተ ክርስቲያናችንን ከአደጋ ለማዳን ከጎኑ ልንሆን ይገባል፡፡ ምሁራን የነፃ እውቀት አገልግሎት በመስጠት፣ ባለሀብቱ ደግሞ ገንዘብ በመለገስ ከፍተኛ ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡ የሁኔታዎች መቀያየር ከግንዛቤ በማስገባት በፍጥነት ያለንን የአእምሮ፣ የገንዘብና የጉልበት ኀይል አስተባብረን ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር አብረን መሥራት አለብን በማለት ገልጸዋል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ ላይ የገቢ ማሰባሰቢያ የቃል ኪዳን መግቢያ ሰነድ በአስተባባሪ ኮሚቴው ተሠራጭቷል፡፡ ምእመናንም እንደ አቅማቸው ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ በመጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ የወንጌል ትምህርት የተሰጠ ሲሆን “ለሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት አብረን እንሥራ” በሚል ርእስ በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የተዘጋጀ ገዳማት በአሁኑ ወቅት ያሉበትን አሳሳቢ ሁኔት የሚያስቃኝ ዘጋቢ ፊልም ቀርቧል፡፡ እንዲሁም ተዋሕዶ የተሰኘ መንፈሳዊ ድራማ በታዋቂ አርቲስቶች የቀረበ ሲሆን ሊቀ መዘምራን ኪነጥበብ ወ/ቂርቆስና ዘማሪት ማርታ ኀ/ሥላሴ ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው ታላላቅ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምሁራን፣ ባለሀብቶችና ምእመናን የተገኙ ሲሆን በሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬና ጸሎት መርሐ ግብሩ እንደ ተጠናቀቀ የምሳ ግብዣው ተካሂዷል፡፡