በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን (ጸሎተ ሃይማኖት)

በለሜሳ ጉተታ

ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊት ንጽሕትና ቅድስት የክርስቶስ ማደሪያ ናት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ «በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ እናንተን ጰጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለራሳችሁ እና ለመንጋው ሁሉ ተጠንቀቁ» በማለት ያስጠነቅቃል፡፡ በሰው ልጅ ፈቃድና ሐሳብ ያልተሠራች እግዚአብሔር በደሙ የዋጃት ቅድስት ሥፍራ ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን በሰማይና በምድር ያለች፣ ከሰው ልጅ ዕውቀት ፈቃድና ፍላጎት በላይ የሆነች የእግዚአብሔር ማደሪያ ናት፡፡ እግዚአብሔር የመሠረታት፣ የቀደሳትና የዋጃት፣ ሐዋርያት፣ ነቢያትና ቅዱሳን አበው የሰበኳትና ያጸኗት ቤት ናት፤ ለሰውም በረከተ ሥጋንና በረከተ ነፍስን ታድላለች፡፡

ይህን ሁሉ እያደረገች በጉዞዋ ቤተ ክርስቲያን ከፈተና ወጥታ አታውቅም፡፡ በፈተና ውስጥ ያለፈች የኖረችና ለወደፊቱም የምትኖር ቤት ናት፡፡ የቤተ ክርስቲያን ፈተና የተጀመረው በሰማይ በዓለመ መላእክት ነው፡፡ የቀደመው የመላእክት አለቃ የነበረው ሳጥናኤል አምላክነትን ሽቶ ከቅዱሳን መላእክት ጋር በመዋጋት ተሸንፏል፣ ወድቋል፣ ተዋርዷል ቅድስናውን አጥቶ ረክሷል፤ ከሰማይ ከክብሩ እና ከሥልጣኑም ተባሯል፡፡ ዛሬ ብዙዎች ቤተ ክርስቲያንን የሚዋጉት ለቅድስና ብለው አይደለም፡፡ ዛሬም ምድራዊ ክብርን፣ ዝናንና ሥልጣንን ፈልገው ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑ መናፍቃንና ጀሌዎቻቸው ቤተ ክርስቲያንን ይፈታተኗታል፡፡ እነርሱ ይጠፋሉ እንጂ ቤተ ክርስቲያን ግን ለዘለዓለሙ ትኖራለች፡፡

በተለያዩ ዘመናት በቤተ ክርስቲያን ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች ቅዱሳን አባቶች መንፈስ ቅዱስን ኃይል አጋዥ በማድረግ መልስ ሲሰጡ ነበር፤ አሁንም ይሰጣሉ፡፡ ክርስትና እውነት ነው፣ ከሥልጣን ከክብር ከዝና ከታላቅነትና ከታዋቂነት በላይ ነው፡፡ አባቶች በየዘመናቱ ቤተ ክርስቲያን ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡ በተለያዩ ዘመናት ለተነሡት የቤተ ክርስቲያን ጥያቄዎች መልሶች ተሰጥተዋል፡፡ ከእነዚህ መልሶች ውስጥ የኒቅያ ጉባኤ (፫፻፳፭) የቁስጥንጥንያ ጉባኤ (፫፻፹፩) እና የኤፌሶን ጉባኤ (፬፻፵፩) ጉባኤያት ቀደምትና ዋና ዋና መልሶች የተሰጡባቸው ጉባኤያት ናቸው፡፡ የኒቅያ ጉባኤ በአርዮስ የክሕደት የሐሰት፤ የጥፋትና የምንፍቅና ትምህርትን መሠረት በማድረግ በኒቅያ ከተማ ፫፻፲፰ ቅዱሳን አባቶች የተሰበሰቡበት የቁስጥንጥንያ ጉባኤ ደግሞ የመቅዶንዮስን የስሕተት ትምህርትን መሠረት በማድረግ ፻፶ ሊቃውንት በ፫፻፹፩ ዓ.ም. በቁስጥንጥንያ የተሰበሰቡበት የኤፌሶን ጉባኤ ደግሞ የንስጥሮስን ትምህርት ለማውገዝ በ፬፴፩ ዓ.ም ፪፻ አበው በኤፌሶን ከተማ በመሰብሰብ መናፍቃንን በመለየት እምነትን አጽንተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል የራሱ ቤተ ክህነት ይቋቋምለት በሚል ጉባኤ በማዘጋጀት ከቅዱስ ሲኖዶሱ ዕውቅና ውጪ የሆነ ሐሳብ ማቅረቡ በሚዲያ እየተዘገበ ነው፡፡ የተነሱት ቅራኔዎች በመላው የኦሮሚያ ክልል የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትን ተደራሽ አላደረገም የሚል ሲሆን ይህን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ቅዳሴ፤ ስብከት እንዲሁም ሌሎች መጽሐፎች በኦሮምኛ ቋንቋ መተርጎማቸውንና ለክልሉ ሰዎች ተደራሽም ማድረግ እንደተቻለ በውይይቱ ተገልጿል፡፡ ይህ ሁለተኛው ጥያቄ ክልሉ የራሱ ቤተ ክህነት ይቋቋምለት የሚለው ግን አሁን የተነሳ ሐሳብ ከመሆኑም ባሻገር ከሃይማኖት አባቶች በተማርነው መሠረት ቤተ ክርስቲያን ስለማትገነጠል ቋንቋም ስለማይገድባት ይህን ሐሳብ በመንቀፍ ተቃውሞ ቀርቦባቸዋል፤ አካሄዳቸውንም ማስተካከል እንዳለባቸውና ቅዱስ ሲኖዶስ እንደማይቀበለው አሳስበዋል፡፡

«በቅዱስ ሲኖዶሱ ተወስኖ፤ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ ታምኖበት በውይይት ሐሳብ ይቀርብበታል እንጂ በዘፈቀደ እንዲህ ያለ ጥያቄ አቅርቦ ጉባኤ ማካሄድ አግባብ አይደለም፡፤ ጉዳቱም የሰፋ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ነሐሴ ፳፬፤፳፻፲፩ ዓ.ም. ቀሲስ በላይ መኮንን የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት በክልል ደረጃ ለማቋቋም ያነሱትን ጥያቄ በቅዱስ ሲኖዶሱ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ድርጊቱን እንዲያስቆምልን አጥብቀን እንጠይቃለን» ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ርእሰ ደብር መሓሪ ኃይሉ  ናቸው፡፡

«ቋሚ ሲኖዶስ ይህንን ጉዳይ የተቃወመው፤ ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን ውጪ ስለሆነ  ነው፡፡ ሌሎች ሳይገባቸው በዚህ ዓይነት መንገድ የሚሄዱ አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉም ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ያልተቀበለውና ከቀኖና ውጪ የሆነውን ይህን ሐሳብ በመንቀፍ በደብዳቤ ለመንግሥት እንዳይተላለፍም ተደርጓል፤ መንግሥትም ማስቆም አለበት፡፡ ምክንያቱም ወደ ብጥብጥና ግጭት ስለሚያመራና የራሱን ኃላፊነት ወስዶ ማስቆም እንዳለበት ቋሚ ሲኖዶስ አስገንዝቧል» ሲሉም ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፤የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊና የምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ገልጸዋል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ «ከኛ ወገን ስላልሆኑ ከኛ ወጡ ዳሩ ግን ከኛ ወገን ቢሆኑ ኖሮ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር» (፩ዮሐ.፪፥፲፱) በማለት አንድነታቸውም ከክርስቲያን ወገን እና ከቅዱሳን አንድነት ያለመሆኑን ይናገራል፡፡ ቅዱሳን አባቶች በየጉባኤያቱ ላይ ለተነሱት የሐሰት ትምህርቶች መልስን ሰጥተዋል፡፡ የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት የጌታችንን ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ መሆን የመንፈስ ቅዱስን አምላክነት የእመቤታችንን ወላዲተ አምላክነትም መስክረዋል አስተምረዋል፡፡ ሃይማኖትንም አጽንተዋል፡፡ ልዩ ልዩ ሥርዓትንም ደንግገዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አንድነት የሁሉም መሆኗን ቅድስትና ንጽሕት የሆነች ስለመሆኗም በቁስጥንጥንያ ጉባኤ ላይ የጽሑፋችን መነሻ ርእስ ያደርግነውን ኃይለ ቃል «ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን» በማለት  ደገኛ አባቶች ውሳኔያቸውን አጽንተዋል፡፡ ይህን ስንል ስለ ቅድስናዋ ምስክርነት ሰጡ ማለት እንጂ አስቀድማ ቅድስት አልነበረችም ማለታችን አይደለም፡፡

መጋቤ ሰላም ሰለሞን ቶልቻ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ኃላፊ ይህን አስመልክቶ «ቤተ ክርስቲያን ዘርን፤ ነገድን፤ ጎሳን ማእከል አድርጋ አትሠራም፡፡ የሰው ልጅ ሰው በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ መሆኑን ከዚያም አልፎ በሰብአዊነት ላይም የምትሠራው ሕገ እግዚአብሔርን ማስተማር ነው እንጂ ሰውን በቋንቋና በጎሳ አትለይም፡፡ እንዲህ ሲባል ግን አማኞች በራሳቸው ቋንቋ ትምህርተ ወንጌል እንዲማሩ፤ የቤተክርስቲያንን ሥርዓት እንዲያውቁ ቤተክርስቲያን ሰፊ ሥርዓት ሠርታለች፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መሬት ወራሪ አይደለችም፡፡ አሁን እየተነገረ ያለው መሬት ወራሪ ናት እየተባለ ምእመናንን ወደ አልተፈለገ ቦታ/  መንገድ/ ለመክተት ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልል ተወሮ ቤተክርስቲያን አልተሠራም፡፡  ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አትከፈልም፡፡ ቋንቋ መግባቢያ እንጂ መከፋፈያ አይደለም» ብለዋል፡፡

ከዚህ ላይ እኛም በወንጌል የተማርነውን ትምህርት ማስታወስ ግድ ይለናልና ሦስቱን የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራዊ ትርጓሜዎች እንመልከት፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ስም ሦስት ምሥጢራዊ ትርጓሜዎችን የያዘ ነው፡፡ እነዚህም ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን፣ የምእመናን ኅብረትና የእያንዳንዱ ክርስቲያን አካል ናቸው፤ ቀጥለን እነዚህን በተናጠል እንመልከታቸዋለን፡፡

፩.የክርስቲያን ሰውነት

እያንዳንዱ ክርስቲያን ልዩ እና ድንቅ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ እንዲህ ጽፎልናል፤ «የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና ያውም እናንተ ናችሁ» (፩ቆሮ. ፫፥፲፮-፲፯)

የእኛ በኃጢአት መቆሸሽ ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ለክርስቲያኖች ኅብረት እንቅፋት ነውና፡፡ «ራስን ከኃጢአት መጠበቅና በንስሓ ሕይወት መኖር ይገባናል፡፡ ክርስቶስ ዋጋ ሊተመንለት በማይችል በደሙ ገዝቶናል፤ በዋጋ ተገዝታችኋል የተባልነውም ለዚህ ነው፡፡ በሌላም በኩል ለቅዱስ ጴጥሮስ ግልገሎቼን አሰማራ ጠበቶቼን ጠብቅ በጎቼን አሰማራ ተብሎ ጥብቅ አደራ የተሠጠው ይህንን ያመለክታል (ዮሐ.፪፥፲፭-፲፯)፡፡

፪. የክርስቲያኖች አንድነት፡- በሌላም በኩል የክርስቲያኖች አንድነት ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህ መንፈሳዊ ስብስብ ነው፡፡ ለመልካም ነገር ለአንድነት ለቅድስና ተብሎ የሚደረግ ስብስብ ነው፡፡ ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ስለ ቃለ እግዚአብሔር መስፋፋት ስለ ቤተ ክርስትያን አስተዳደራዊ መዋቅር መጠናከር ስለነፍሳት ድኅነት ተብሎ የሚደረግ ስብስብ ነው፡፡

፫. ሕንጻ ቤተ ክርስያን፡- ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር በፈቀደ  በጭቃ በጨፈቃ፣ በዓለት በገጠር በከተማ፣ በተራራ በዋሻ፣ በዱር በገደል ልትታነጽ ትችላለች፡፡ በተለያዩ ቅዱሳን ስም ልትሰየምም ትችላለች፤ ዓላማዋ ግን አንድ ነው፤ እርሱም ሰዎች የእግዚአብሔርን ልጅነት የሚያገኙበት፣ ጸሎት የሚያደርሱበት ምስጋና የሚያቀርቡበት ሥጋ ወደሙን  የሚቀበሉበት፤ በሕይወታቸው ፍጻሜም እስከ ዳግም ምጽአት ድረስ ሥጋቸው የሚያርፍበት ቅዱስ ቤት ነው፡፡ ይህ ቤት የምስጋና፤ የጸሎት የመሥዋዕት ቤት ነው፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን «ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል» በማለት የተናገረው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በሥጋውያን ሰዎች ብትገለገልም የሚጠብቋት ቅዱሳን መላዕክት ናቸው፡፡ የመረጣት፤ የሚቀድሳትና የሚያከብራት ግን እግዚአብሔር ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገልጋዮች ሊያጠፉ ይችላሉ፤ የሥነ ምግባር ጉድለትን ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡ ይህ ግን የእነርሱ ችግር ነው እንጂ ቤተ ክርስቲያንን የሚገልጽ ጉዳይ አይደለም፡፡

ቤተ ክርስቲያን የማንንም ወገን  (ብሔር፤ ቡድን፤ ጎሳ፤ ዘርን፤ አካባቢን፤ ክልልን) አትወክልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሁሉም ናትና፡፡ ቤተ ክርስቲያን አንዲት፤ ቅድስት፤ ንጽሕት እና ሐዋርያዊት ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካሉ ናት ካልን የቤተ ክርስቲያንን አንድነትን ሊከፋፍሉ/ሊሸረሽሩ/ ከሚችሉ ኢ-ሥነ ምግባራዊ ተግባራትም ከመፈጸም ልንቆጠብ ይገባል፡፡ የግል ሐሳብንና ፍላጎትን የቡድን ዓላማን ለማሳካት ከተለያዩ ከቤተ ክርስቲያን መዋቅር ላይ ካሉ ግለሰቦች ጋር ያለንን ቂምና ጥላቻን እንደማሳያ ለማድረግ ብለን ቤተ ክርስቲያንን ከመክፈል ልንጠበቅ ይገባል፡፡

ቤቱን የመረጠው እርሱ ራሱ መሆኑን ሲናገር «ለዘለዓለም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሸዋለሁ መርጨዋለሁ» በማለት ገልጾታል (፩ነገ. ፱፥፫)፡፡  ቅዱስ ዳዊት የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት ፍላጎት ቢኖረውም የእግዚአብሔር ፈቃድ ግን አልነበረም፡፡ እግዚአብሔርን ማገልገል ቤቱን መጠበቅ መሥራት የራሳችን ምኞት  ቢኖርም  የእግዚአብሔር ፈቃድ ግን ያስፈልጋል፡፡ ገንዘብ ስላለን ጊዜው ስለፈቀደልን ብቻ ቤቱን መሥራት አይቻልም፡፡

ጊዜ ጉልበት ገንዘብ ሀብት ንብረት ጥበብ ዕውቀት የእግዚአብሔር ነውና በተሰጠን ነገር መልካም ነገርን መሥራት ጥሩ ነው፡፡ ቤቱን ማስጨነቅ እግዚአብሔርን ማሳዘን ነውና፡፡ ለዚህ ነው (የሐዋ. ሥራ ፱፥፬ ላይ) «ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ» የተባለው፡፡ ስለቤቱ አንድነት ልዕልና ቅድስና ስናስብ ሰዎችና እግዚአብሔርም ይደሰታሉ፡፡ከዚህ ውጪ ቤተ ክርስቲያን ላይ ክፉ ነገርን ለማድረግ ማሰብ የቤተ  ክርስቲያንን ንብረት፣ ቦታ መውሰድ፣ መንጠቅ ስናስብ እግዚአብሔርም ያዝንብናል ልንመለስ ይገባል፡፡ ጥፋቱም ከእኛ አልፎ ለትውልድ ሁሉም ይደርሳልና ወደ ልቦናችን እንመለስ፡፡ አንድነት የፍቅርና የቅድስና ብሎም የክርስትና መገለጫና መሠረት ነው፡፡ ልዩነት ግን የአሕዛባዊነት ምልክት ነው፡፡

ጳውሎስ የተባለው ሳውል ወደ ክርስትና ሕይወት ከመጠራቱ በፊት የቤተ ክርስቲያን አንድነትን ለማጥፋት ከሚፋጠኑ አሕዛብ ወገን ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ማሳደድ፣  ክርስቶስን ማሳደድ ነው፡፡ አንድነትን፣ ፍቅርን፣ ክርስትናን መጥላት፣ ማሳደድ፣ መከፋፈል የአሕዛባዊነት ምልክት ነውና፡፡ እግዚአብሔር ተገልጦለት «ለምን ታሳድደኛለህ» ብሎ ተናገረው፤ ሳውል ክርስቲያኖችን ለማስገደል፣ ለማሳደድና ለማሳሰር የቤተ ክርስቲያን አንድነትን ኅብረትን ለማፈራረስ ከባለሥልጣናት ደብዳቤን ያጽፍ ነበር፡፡ እግዚአብሔር የፍቅር የቸርነትና የምሕረት አምላክ ነውና በፍቅር ጠራው ንስሓም ገባ፡፡

ቤተ ክርስቲያንን ያሳድድ የነበረው ሰው ክርስቲያን ሆነ ስለ እውነት ስለ ፍቅር ስለ አንድነት ተሰደደ፤ከመሰደድም አልፎ ተሰቀለ፡፡ ዛሬም እርሱ ይፈጽም የነበረውን ተግባርን የምትፈጽሙ ግለሰቦች ወደ ልቡናችሁ ልትመለሱ ይገባል፡፡ ጊዜውንና ሁኔታውን ተገን አድርጋችሁ ክፋትን መሥራት ቤተ ክርስቲያንን ማሳደድ የለባችሁም፡፡ የአንዳንድ ግለሰቦች ታሪክን በተለይም ከዚህ በፊት የነበሩ የአንዳንድ ነገሥታትን (መንፈሳዊና ሀገራዊ መሪዎችን ጭምር) ስሕተታቸውን ብቻ በመፈለግ ከቤተ ክርስቲያን ጋርም በማገናኘት ቤተ ክርስቲያንን የጥፋቱ ሰለባ አታድርጉአት፡፡ ይህ ደግሞ ፍጹም ስሕተተ ነው፡፡ የግለሰቦችን ታሪክ ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጋርም ማያያዝ የለብንም፡፡

መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ኃይለጊዮርጊስ ተረፈ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት አባል ዳኛ እንዲህ ብለዋል፤ «ቤተክርስቲያን አንድነትን እያስተማረች፤ሰላምን እየሰበከች፤ ሁሉን ልጆቼ ብላ ይዛ አያሌ ዘመናትን አሳልፋለች፡፡ ሀገር ወራሪ፤ አጥፊ ሲመጣም ቤተ ክርስቲያን ከልጆቿ ጋርና ከሚመለከተው አካል ጋር ሆና ዛሬ እኛ የምንኖርባትን ሀገር፤ በጸሎት በሕይወት መሥዋዕትም በመክፈል ያስጠበቀች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ነገር ግን አሁን እየሰማን ያለነው ሂደት ፈጽሞ በቤተክርስቲያን ሕግና ሥርዓት ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አንዲትና የሁሉም እናት ናት»

አንዲትና ቅድስት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን መከፋፈል ለምን አስፈለገ? አንድነትን አፍርሶ ስለአንድነት ስለፍቅር ስለሰላም ስለቅድስና ማውራት አይቻልምና፡፡ አንድነትን አፍርሶ ማን በሰላም ያድራል? እርሱ አንድነትን ፍቅር እና ሰላሙን ያድለን፤ አሜን፡፡