Asosa.JPG

በአሶሳ ከማሽ ከአራት ሺሕ በላይ የአካባቢው ተወላጆች ተጠመቁ

በሻምበል ጥላሁን

 
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር ከአሶሳ ሀገረ ስብከት ጋር በመተባበር ባደረገው ሐዋርያዊ ጉዞ ከአራት ሺሕ በላይ ሰዎች የክርስትና ጥምቀት እንዲጠመቁ ማስቻሉን አስታወቀ፡፡

የነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በላከው መረጃ እንዳስታወቀው፤ ሐዋርያዊ ጉዞና ጥምቀቱ የተከናወነው ከታኅሣሥ 16 እስከ 25 ቀን 2002 ዓ. ም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ፣ ሥራ አስኪያጁ ሊቀ መዘምራን ሐረገወይን ጫኔ፣ የከማሽ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ መልአከሰላም ተገኝ ጋሻው በተገኙበት ነው፡፡

Asosa.JPG

የጉሙዝ ተወላጆች የክርስትና ጥምቀት ሲጠመቁ

በአሶሳ ሀገረ ስብከት ከማሽ ለአሥር ቀናት በቆየው ሐዋርያዊ ጉዞ ከአራት ሺሕ በላይ የጉሙዝ ተወላጆች መጠመቃቸውን መረጃው አመልክቷል፡፡

የክርስትና ጥምቀት ያገኙት እነዚህ የአካባቢው ተወላጆች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ በመሆናቸው መደሰታቸውን የጠቆመው መረጃው፤ ሌሎችም   ለመጠመቅ ቤተ ክርስቲያኒቱን እየተጠባበቁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ ምእመናኑን ለማጥመቅ ከአምስትና ስድስት ሰዓታት በላይ በእግር እንደተጓዘ መረጃው አመልክቶ፤ በዞኑ በሚገኙ አሥራ ሰባት የተለያዩ ቦታዎች ምእመናኑን ለማጥመቅ ለተደረገው እንቅስቃሴ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ የከማሼ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ እና የሰበካ ጉባኤ አባላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እና ጥረት ማድረጋቸውን ገልጿል፡፡

ምእመናኑ ለጥምቀት የበቁት ከአካባቢው ማኅበረሰብ በተለያዩ ጊዜ በማኅበረ ቅዱሳንና በጽርሐጽዮን የአንድነት ማኅበር አማካኝነት፤ የስብከተ ወንጌል ሥልጠና በተሰጣቸው የአካባቢው ተወላጆች ተተኪ መምህራን ባደረጉት ጥረት፤ እንዲሁም የከማሼ ቤተክህነት በተለያየ ጊዜ ባዘጋጀው የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ባገኙት ትምህርት እንደሆነም መግለጫው አመልክቷል፡፡

ይሁን እንጂ ጥምቀቱን ያገኙ በከማሽ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ምእመናን፤ እምነታቸውን የሚያጸኑበትና ሥጋና ደሙን የሚቀበሉበት፣ ልጆቻቸውን የሚያስጠምቁበት ቤተ ክርስቲያን በአቅራቢያቸው ስለሌለ በሌሎች የእምነት ድርጅቶች እንዳይወሰዱ ሥጋት እንዳለው የነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በሕገ ልቡና በማመን በናፍቆት እየተጠባበቁ የሚገኙትን የዋሐን ምእመናን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ለመመለስና አገልግሎት የሚያገኙበትን ቤተ ክርስቲያን ለማነጽ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባም ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

ማኅበሩ ወደፊት በራሳቸው ቋንቋ አገልግሎት የሚሰጡ ሃያ ስምንት የአካባቢውን ወጣቶች በመምረጥ በችግሻቅ ገብርኤልና በኮቢ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ግብረ ዲቁና እንዲማሩ መምህር መቅጠሩን መረጃው ጠቁሞ፤ በርካታ ተጠማቂዎች በሚገኙበት አካባቢ የቅድሰት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን እንዲታነጽ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንም አመልክቷል፡፡

ማኅበሩ በቀጣይም በጊዜ እጥረትና በቦታ ርቀት ምክንያት ያልተጠመቁትን ሌሎችም ለመጠመቅ የሚፈልጉትን ለማጥመቅ እንዲቻል ለሁለተኛ ጊዜ ሐዋርያዊ ጉዞ ለማድረግ ዕቅድ መያዙንም ገልጿል፡፡

ለምእመናኑ ጥምቀት መሳካት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና ሥራ አስኪያጅ ያደረጉትን ከፍተኛ ጥረት አመስግኖ፤ በተለይ የክርስትና ጥምቀቱ የተከናወነበት የከማሽ ዞን ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ተገኝ ጋሻውና ሰበካ ጉባኤው ከአሥር ሰዓት በላይ በእግር በመጓዝ ተጠማቂዎችን በማዘጋጀት ያከናወኑት ሥራ ላቅ ያለ መሆኑን አስታውሷል፡፡

ማኅበሩ ለተጠማቂዎቹ ከስምንት ሺሕ በላይ የአንገት ማተብ /ማኅተም/ እና ከአምስት ሺሕ በላይ አልባሳት፣ ለቁርባንና ለጥምቀት የሚያስፈልጉ ንዋያተ ቅድሳት አዘጋጅቶ ወደ ቦታው መጓዙንም መረጃው አመልክቷል፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር