በመንፈሳዊ ሕይወታችን መለወጥ ለምን ተሳነን?

በለሜሳ ጉተታ

እግዚአብሔር ከእኛ የመልካም ሥነ ምግባርና የሃይማኖት ፅናትን ይፈልጋል፡፡ በሃይማኖት የሚኖር ሰው አስተማሪ ሕይወት ያለው ሰው መሆን አለበት፡፡ ሃይማኖቱንም በሥራና በምግባር መግለጽ አለበት፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን  በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል፤ በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ፤” መብራት የተባለው ሃይማኖትና ምግባራችን ነው፡፡ (ማቴ.፭፥፲፫-፲፮)

በሌላም በኩል ፍሬን የማያፈሩ ሰዎች እንደሚጠይቁም መጽሐፍ ይገልጻል፡፡ “በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና  ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት። በለሲቱም ያን ጊዜውን ደረቀች።” በአጠቃላይ እምነት ብቻውን አያድንምና እምነት ከምግባር በተባበረበት ሕይወት ልንኖር ይገባል፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ያዕቆብ “ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ። ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው” ያለን፡፡ (ማቴ.፲፩፥፱፤ያዕ.፪፥፳፭)

ምግባር ማፍራት ያልቻልነው ክርስቲያናዊ ግዴታዎቻችንን መወጣት ያቃተን  በጾም በጸሎትና በንስሓ ሕይወት በአገልግሎት መጽናት ያልቻልነው፣ መንፈሳዊ ሰው መሆን ያቃተን፣ የጊዜ፣ የወቅት፣ የበዓል እና የጉባኤ ሰው ብቻ የሆንነው ለምንድ ነው? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ያስፈልጋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን?” ተብሏል፡፡ ወርሃዊና ዓመታዊ በዓላትን ጠብቆ ብቻ መምጣ መንፈሳዊነት አይደለም፡፡ ቅዳሴ ማስቀደስ አቁመናል፤ ከንስሓ አባቶች ጋር መገናኘት ትተናል፡፡ (፪ኛ ቆሮ.፲፫፥፭)

በሃይማኖት እየኖሩ ምግባርን የማያፈሩ ሰዎች አወዳደቃቸው የከፉ ይሆናል፡፡ ስለዚህም የእግዚአብሔር ቃል፡፡ “እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፥ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም። መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል። ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ፤ ጎርፍም መጣ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፥ ወደቀም፥ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ” በማለት የክፋታችን ፍጻሜ ምን ሊሆን እንደሚችል በምሳሌ ያስተምረናል፡፡ (ማቴ.፯፥፲፯-፳፯)

ፍሬን የማያፈሩ በስም ብቻ የአብርሃም ልጆች ነን እያሉ የሚኖሩትን ጌታችን ፍሬን ማፍራት እንዳለባቸው ሲነግራቸው “አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል” ብሎ አሰተምሮናል፡፡ በመሆኑም “እኔ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጅ ነኝ” እያሉ ብቻ በስም መኖር ሕይወት አይሆንምና ምግባርን ልናፈራ ይገባል፡፡ ክርስቲያን ደግሞ መጽናት (ሃይማኖትን ወደ ሥራ ለውጦ ፍሬና ምግባርን ማፍራት) መገለጫው መሆን ይገባዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህታና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም” በማለት መክሯል፡፡ ስለሆነም በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንዳንለወጥ ያደረጉንን ምክንያቶች በአጭሩ ከዚህ በታች ተራ በተራ ለማየት እንሞክራለን፡፡ (ማቴ.፫፥፲፤ሉቃ.፫፥፱፤ዮሐ.፲፭፥፮፤፪ኛጢሞ.፬፥፪)

የሠራነው ኃጢአት

መንፈሳዊነት ከኃጢአት ርቆ መኖር ነው፡፡ ደግሞም እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ እንደቃሉ ከኖርን ከኃጢአት ርቆ መኖር ይቻላል፡፡ የኃጢአት መጨረሻው ሞት ነው፡፡ ዕለት ዕለት ስለ ሠራነው ኃጢአት ማሰብና ንስሓ መግባት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ማሰባችን ከቤተክርስቲያን እና ከአገልግሎት ለመራቅ መሆን የለበትም፡፡ አንዳንዶቻችን ከአገልግሎትና ከቤተ ክርስቲያን ለመራቅ ስንፈልግ “እኔ ኃጢአተኛ ነኝ” እንላለን፡፡ ኃጢአትን ላለመሥራት ይበልጥ መትጋትና ማገልገል እንዲሁም ራሳችንን ከክፉ ነገር ማራቅ ያስፈልጋል፡፡ ኃጢአት ከመንፈሳዊ ሕይወት፣ ከድኅነት፣ ከበረከትና ከቅድስና ጎዳናም ያወጣል፡፡  በሃይማኖት በጾም፣ በጸሎትና በንስሓ ሕይወትም እንድንዳከም ያደርጋል፡፡ ኃጢአትን ከተለማመዱት መውጫው ከባድ ነው፡፡ ብዙዎቻችን የልብ መለወጥ ያጣነው የሠራነው ኃጢአት ሁል ጊዜ ስለሚወቅሰን ወደ ኋላ በመመለሳችን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የበለጠ ጥፋት ነው፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን አባቶቻችን በመቅረብ በንስሓ ከኃጢአት መንጻት አለብን እንጂ ወደ ኋላ በመመለስ የቀደመውን ጥፋታችንን በማሰብ በከንቱ ጭንቀት ስንናወዝ መኖር የለብንም፤ ይህም ለበለጠ ጥፋት ያጋልጠናልና፡፡

ልባችን ከመንፈሳዊነት ሲርቅ፣ መንፈሳዊ ዝለት ሲያጋጥመን ኃጢአት ሲበረታብን፣ ሲያሸንፈን፣ ሁል ጊዜ እንደማንሞት ብርቱና ጠንካራዎች አድርገን ራሳችንን እንድንመለከት ያደርገናል፡፡ ይህ ደግሞ የጥፋት ምክንያት ስለሆነ ወደ ልባችን ልንመለስ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከቤተ ክርስቲያን፤ ከመንፈሳዊ ጉባኤያት ከአባቶችና ከመንፈሳዊ ተግባራትም እንድንርቅ እንድንሸሽ እንድንደበቅም ያደርገናል፤ ለሞትና ለጥፋትም አሳልፎ ይሰጠናል፡፡ ስለሆነም ወደ ልባችን በንስሓ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ አዳም ኃጢአት በሠራ ጊዜ ጴጥሮስ እግዚአብሔርን በከዳ ጊዜ፣ ይሁዳ ፈጣሪውን በሸጠ ጊዜ መደበቃቸው ኃጢአት ከእግዚአብሔር የሚለያቸው  መሆኑን ስለሚያውቁ ነበር፡፡

ኃጢአት ክፉ ነው፤ ሰላምን ይነሳል፤ የኅሊና ዕረፍትንም ያሳጣል፡፡ በሰማይም ሆነ በምድር ያለንን ጸጋ ወይም ክብር ያዋርዳል፡፡ በረከትን ያሳጣል፤ ራስን አሳልፎ ለሞት ይሰጣል፡፡ ስለሆነም ኃጢአታችን ብቻ በማሰብ ከእግዚአብሔር ጎዳና ከመንፈሳዊነትና ከአገልግሎት ወደ ኋላ መመለስ የለብንም፤ ከኃጢአታችን በፍጹም ንስሓ መመለስና መንጻት አለብን፡፡

እግዚአብሔር መጀመሪያ የሚመለከተው የሠራነውን ኃጢአት ሳይሆን መመለሳችንን ነውና በመንፈሳዊ ሕይወታችን ልንተጋ ይገባናል፡፡ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ የተባልነውም ለዚህ ነውና፤ ቅዱስ ዳዊትም “የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ ባሪያህን ጠብቅ፤ የዚያን ጊዜ ፍጹም እሆናለሁ፥ ከታላቁም ኃጢአት እነጻለሁ። አቤቱ ረድኤቴ መድኃኒቴም የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን” ያለው ይህንን ያመለክታል፡፡ (ሮሜ. ፮፥፲፪፤ መዝ.፲፱፥፲፫)

ከእኛ በታች ያሉ ሰዎችን ደካሞች አድርገን ማሰባችን

እውነት ለመናገር በክርስትና ዓለም በራሱ የመንፈሳዊነት ጥንካሬ የኖረ (የሚኖር) ሰው የለም፡፡ ሁላችንም የምንኖረው በሥራችን ጥንካሬ ልክና መሠረት አይደለም፡፡ ይህንን ብናምንም ባናምንም የምንኖረው  በእግዚአብሔር ምሕረት ቸርነትና ጥበቃ ነው፡፡ የእርሱ ጸጋ፤ የእርሱ በረከት፤ የእርሱ ቸርነት ፍጥረትን ሁሉ ያኖራልና፡፡ እንኳን በመንፈሳዊ ዓይን በሥጋዊ ዓይን እንኳን ብንመለከተው ማንኛውም ሰው በሚያገኘው ገቢ ራሱንና ቤተሰቡን የመምራት አቅም አይኖረውም፡፡ የሚያኖረው የእግዚአብሔር ቸርነትና ምሕረቱ ብቻ ነው፡፡ የሚመግበን የሚጠብቀንም ጭምር የእርሱ ቸርነት ነው፡፡ እንደ እኛ እንደ ሥራችን ክፋት እንደ ኃጢአታችንም ብዛት ቢሆንማ ኖሮ ፀሐይ ብርሃኗን፣ ደመናትም፣ ዝናማትን፣ ባልሰጡን ነበር የምንኖርባትም ዓለም ባልኖረችን ነበር፡፡

የሰው ልጅ ክፋቱና ጭካኔው እጅግ ብዙ ነው፡፡ የበለጠው ክፋቱ ደግሞ ክፋቱንና ጭካኔውን  በማሰብም መጸጸት አለመቻሉ ነው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ከመንፈሳዊነት ስለራቅን ሃይማኖት አልባዎችም ጭምር ስለሆን ነው፡፡ እኛ ነጠላ ለብሰን ቤተ ክርስቲያን ስለተመላለስን ጉባኤ ስለተካፈልን የንስሓ አባት ስለያዝን፣ ገዳማትን ስለተሳለምን ብቻ የመንፈስ ልዕልና ላይ የደረስን መስሎን ይታየናል፡፡ ይህ ግን ከምግባር ጋር ያልተባበረ የማስመሰል ክርስትና በመሆኑ በእጅጉ ልናስብበት ይገባል፡፡

እንደሚታወቀው የብዙዎቻችን ችግር ችግሮቻችንን ማየት ያለመቻል ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ ወጥቶ ማገልገል የአገልግሎትን ጸጋ መጎናጸፍ፣ መዘመር፣ መስበክ የተለያዩ የአገልግሎት ጸጋዎችን መጎናጸፍ፣ ቅዱስነት ወይም ድኅነት አይደለም፡፡ የቅድስናና የድኅነት መንገድ እንጂ፡፡ በመሆኑም ልንታበይ አይገባም፡፡ መንፈሳዊነት በትሕትና በሃይማኖት በምግባር በትሩፋት በእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ሕይወት ጎዳና የሚያደርሰን መንገድ ነው፡፡ ስለሆነም ዛሬ እኛ መቆማችንን በማሰብ እንደማንታመም፣ ቤተ ክርስቲያንም በመመላለሳችን ብቻ  ጽድቃችንን ማስላት ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ ሌላውን ከመኮነን ልንጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ የመንፈሳዊነት ድከመት ወይም ጥፋት መጀመሪያ ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ መመጻደቅ ሌላውን መኮነን ነውና፡፡ ማንም የቆመ ቢመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ ይላልና ቃሉ፡፡ ራስን አለማወቅ (አለመመርመር)፣ ንስሓ አለመግባት ክርስቲናዊ ግዴታዎችን አለመወጣት ከቤተ ክርስቲያንና ከንስሓ አባቶች እንዲሁም ከቃለ እግዚአብሔር መራቅ ራስን ከፍ ከፍ አድርጎ መመልከት መንፈሳዊ ሰዎችን መራቅ የጥፋት መስመር ነውና ወደ ልባችን ልንመለስ ይገባል፡፡  “በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ” የተባልነውም ለዚህ ነውና፡፡ (ዕብ.፲፪፥፫)

ከማይመስሉን ሰዎች ጋር ኅብረትን መፍጠር 

በመንፈሳዊ ሕይወት በአገልግሎትና በክርስቲናዊ ሥነ-ምግባር ለመጽናት የምንውልበት ውሎ ጓደኞቻችን የምናነባቸው ጽሑፎች የምናያቸውና የምንሰማቸው ፊልሞች ራሳቸውን የቻሉ ተጽእኖዎች አሏቸው፡፡ ክርስቲያን ሰውን የሚለውጥ መሆን አለበት እንጂ እሱ ራሱ       በሰው፣ በጊዜና በሁኔታዎች የሚለወጥ ሰው መሆን የለበትም፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ለብዙዎቻችን አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ ወንድሞችና እኅቶች ከማን ጋር ኅብረት (አንድነት) መፍጠር እንዳለባቸው ሳይገነዘቡ ከማይመስሏቸው ጋር ሕብረትን ፈጥረው ያጣናቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ከአዋዋልና ከጓደኛ ተጽእኖ የተነሣ ሃይማኖታቸውን የቀየሩ፣ ከመንፈሳዊ ጎዳና ወጥተው በምግባረ ክርስትና የደከሙና ከአገልግሎት የተለዩ ብዙዎች ናቸው፡፡

ተስፋ በመቁረጥ በመከራቸው ሁሉ የሚያጽናናቸው በማጣት ወደ አላስፈላጊ ሕይወት ውስጥ የገቡትን የሚመልሳቸው መንፈሳዊ አገልጋይ ያስፈልጋል፡፡ በተቻለ መጠን የምንይዛቸው ጓደኞች የምንውልባቸው ውሎና ቦታዎች የምናነባቸው መጻሕፍት የምንመለከታቸው ፊልሞች በመንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ ችግር (ዝለት) የማያስከትሉ ጥቅም እንጂ ጉዳት የሌላቸው መረጃዎችን ሊሰጡን የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡ በሕይወታችን በትዳራችን በትምህርታችን በአገልግሎታችን ላይ ኪሳራን የሚያስከትሉ ከእግዚአብሔር አንድነትና ከቅዱሳን ኅብረት  የሚለዩን የመንፈሳዊ ሕይወት ኪሳራን የሚያመጡብን መሆን የለባቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙዎችን አጥተናልና፡፡

ይህንንም የእግዚብሔር ቃል  “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለው? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል፦ በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። ስለዚህም ጌታ ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ እኔም እቀበላችኋለሁ፥ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል” (፪ኛ ቆሮ.፮፥፲፬-፲፰)፡፡

ስለሆነም መንፈሳዊነትን እንደሞኝነት ከሚቆጥር አላዋቂ ጓደኛ ልንርቅ ይገባል፡፡ ለመንፈሳዊ ሕይወት ሲባል እንኳን ከጓደኛ ከቤተሰብ መለየት ይመጣልና፡፡ መጾም፣ መስገድ፣ ንስሓ አባት መያዝ፣ ማስቀደስ ነጠላ ለብሶ ቤተ ክርስቲያን መሄድና፣  እግዚአብሔርን ማገልገል፣ ሞኝነት የሚመስላቸው በአንፃሩ የነጭን ነገርን መደገፍ (ማምለክ) እንደ ዘመናዊነት ከሚቆጥሩ ሰዎች መራቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ “ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም” በማለት ያስተምረናል፡፡ (፩ቆሮ.፪፥፲፬)

በሌላም በኩል “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና።  ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና” ብሎ ሥጋዊ ጥብበ በእርሱ ዘንድ ዋጋ ቢስ መሆኑን ገልጾታል፡፡ (፩ቆሮ.፲፰-፳፩)

እግዚአብሔርን መፍራት፣ ክርስቲያናዊ ግዴታዎችን መፈጸም፣አዘውትሮ ወደ ቤተ ክርስቲያን መመላለስ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ጥንካሬ መሠረቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ሕይወት ሊያወጡን ከሚያስቡ ሰዎች ግን መራቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም መጽሐፍ “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመድ ክፉ ባልንጀራነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ብሎ ይመክረናል፡፡ (፪ቆሮ.፮፥፲) ተስፋ መቁረጥ፣  በክፉ ሐሳብ መመላለስ፤ ክርስቲያናዊ ግዴታዎችን መፈጸም አለመቻል፣ ወደ ቅዱሳን ቦታዎችም መሄድ አለመቻል በመንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ ዝለትን ያመጣሉ፤ተስፋ መቁረጥ የጥፋት ሁሉ መጀመሪያ ነውና፡፡ (ሚል.፫፥፲፫)

“አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ይላል ቅዱስ ጳውሎስ። ዳዊትም “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል። ክፉዎች እንዲህ አይደሉም፥ ነገር ግን ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ ናቸው። ስለዚህ ክፉዎች በፍርድ፥ ኃጢአተኞችም በጻድቃን ማኅበር አይቆሙም። እግዚአብሔር የጻድቃንን መንገድ ያውቃልና፥ የክፉዎች መንገድ ግን ትጠፋለች” በማለት ክፋታቸው የምታጠፋቸውን የክፉዎችን ፍጻሜ ይነግረናልና፡፡ ራሳችንን ከእነርሱ በመጠበቅ ልንኖር ይገባል። (፩ኛቆሮ.፲፭፥፴፫፤ መዝ.፩፥፩-፮)

የእግዚአብሔርን ውለታ መርሳት

የእግዚአብሔር ውለታ ምሕረትና ቸርነቱ ብዙ ነው፡፡ ያልጠፋነውም በጽድቃችን ሳይሆን በእርሱ ምሕረትና ቸርነት ብዛት ነው፡፡ የምንኖረውም በእርሱ በረከት ኃያልነትና ጥበቃም ጭምር  ነው፡፡ እንደ ሥራችን ቢሆን ኑሮ ዛሬ ዓለም በጠፋች ነበር፡፡ ለምንድነው ብዙ ሠርተን  ወጥተን ወርደን የድካማችን ማግኘት ያልቻነው? ለምድነው በረከት ደስታ ሰላም መረጋጋት ትዕግሥት ማስተዋል እምነት ታማኝነት ቅንነት ደግነት የራቀን? በማለት ራሳችንን ከጠየቅን መልሱ የእግዚአብሔርን ውለታ ማሰብ ስላልቻልን እና በራሳችን ማስተዋል ስለተደገፍን ነው፡፡ በራሳችን  ብርታት የምኖር መስሎን ስለተሰማንና በዚህም ስለምንመካ ነው፡፡ ለዚህ ነው መጽሐፍ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ” የሚለን፡፡ (ምሳ.፫፥፭)

ስለሆነም ወደ ልባችን ልንመለስ ይገባል፡፡ የመንፈሳዊ ሕይወታችን ዝለት ዋናው ምክንያት የእግዚአብሔርን ቸርነትና ውለታ መርሳታችን ነው፡፡ ሰው እግዚአብሔርን ረስቶ በራሱ መመካት መደገፍ ሲጀምር መንፈሳዊነቱ ይደክማል፤ ተስፋ ይቆርጣል፡፡ በእምነት፣ በምግባርና በሃይማኖት ይዝላል፡፡ ሰላም ደስታ ፍቅር ትዕግሥት ማስተዋል መረጋጋት የራቀው ሕይወትንም ይመራል፤ በሕይወት እያለ ይጠፋል፤ በአጠቃላይ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን ያጣል፡፡

የእግዚአብሔርን ውለታ ረስተው በራሳቸው ጉልበት፣ ማስተዋል፣ ሥልጣንና ኃያልነት የተመኩ በዚህም ከነታሪካቸው ስማቸው ከምድር ገጽ የጠፉ፣ ከሰውነት ክብር ወርደው ወደ እንስሳነት የተቀየሩትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካቸውን ማስታወስ ይቻላል፡፡ ክርስትና የትሕትናና የፍቅር ሃይማኖት  ነው፡፡ በተለይም የእግዚአብሔርን ክብር ለሰው መስጠት የጥፋት ሁሉ ጥፋት ነው፡፡ ስለሆንም ማንነታችንን ልናስብ ይገባል፡፡ ከዚህ ጋር አያይዘን መመልከት ያለብን የመንፈሳዊ ሕይወት ዓላማ ጥቅምና ግቡ ማለትም የመጨረሻው ውጤት ምንድነው የሚለው ሲሆን ይህንንም ይበልጥ አንባብያን  መጻሕፍትን በማንበብና አባቶችን በመጠየቅ መንፈሳዊ ዕውቀታቸውን ማሳደግ አለባቸው ተጨማሪ ሃሳቦችንም እንዲገኙ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ መንፈሳዊነት ኑሮ ሳይሆን ሕይወት ነው፡፡ መንፈሳዊነት ቅድስናም ነውና፡፡

መንፈሳዊነት የበረከት ሰው እና ምንጭ በመሆን ራስን ለእግዚአብሔር በማስገዛት፣ከዓለም ሥራ፣ ሐሳብ፣ ምኞትና ተግባርም በመለየት ፍጹም የእግዚአብሔር ሰው መሆን ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔርን መንግሥት በመውረስ የዘላለም ሕይወትን የምናገኝበት ሕይወት ነው፡፡ ራስን ማዳን ለሌሎችም የድኅነት ምክንያት መሆን ነው የመንፈሳዊነት ዓላማው፡፡ ቃለ እግዚአብሔርንና ቤተ ክርስቲያንን በዓለም ላይ ማስፋፋት ነው፡፡ መንፈሳዊነት መለወጥ  በሃይማኖት በጾም በጸሎት በምግባር መጽናት ነው፡፡ እግዚአብሔርን ቤቱን ራስንና ሕዝብን ራስንም ማገልገል ነው፡፡ መንፈሳዊና ሥጋዊ በረከትን የምናገኝበት የበረከትና የሕይወት ምንጭ (መሠረት) ነው መንፈሳዊነት፡፡ ያለ መንፈሳዊ ሕይወት መንፈሳዊ አገልጋይ መሆን አይቻልም፡፡

ስለሆነም ማንም ሰው መጀመሪያ ወደ አገልግሎት ከመግባቱ በፊት ሕይወቱን ራሱንና ኑሮውን መንፈሳዊ ማድረግ አለበት፡፡ መንፈሳዊ ሰው በእግዚአብሔር ሕግ፣ትእዛዝ፣ ፈቃድና ሐሳብ የሚመራ የሚጾም የሚጸልይ፣ንስሓ የሚፈገባ፣ የንስሓ አባት ያለው፣ ክርስቲያናዊ ግዴታዎችንም የሚወጣ (የሚፈጽም)፣ በአርአያነት የተሞላ ሕይወት ያለው ፣ሙሉ እምነት  በእምነት የሚኖር፣ ተስፋ ያለው፣ መንፈሳዊ ፍሬዎችን የሚያፈራ፣ በጉባኤያት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል የሚማር ሰው ነው፡፡ በትሕትና በትዕግሥትና በፍቅር የተሞላ መልካም ክርስቱያናዊ ሕይወት ያለውም ሰው ነው፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ለመለወጥ ውሎና ጎደኛን መምረጥ፣ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ መሳተፍ (ቅዳሴ፣ኪዳን፣ጉባኤያት) መንፈሳዊ ቦታዎችን ወይም ገዳማትን መጎብኘት፣ ክርስቲያናዊ ግዴዎችን መፈጸም (ጾም፣ጸሎት፣ዐሥራት በኵራትን ማውጣት)፣ቃሉን መማርና በሕይወትም መተርጎም፣ ከመንፈሳዊ ወንድሞችና እኅቶች ጋር ያለንን ግንኙነት ማጠናከር፣የንስሓ አባት መያዝ፣ ምሥጢራት ላይ መሳተፍ፣ እምንትና በጎ ሕሊናን ገንዘብ ማድረግ፣ ነገረ ቅዱሳንን እያሰቡ በመኖር፣ ራስን ከኃጢአት መጠብቅ ዋሳኝ ነገሮች ናቸው፡፡ ስለሆነም በመንፈሳዊ ሕይወታችን ተለውጠን ምግባርና ሃይማኖትን አፅንተን ይዘን መንግሥቱን ለመውረስ እንድንበቃ የእርሱ የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡