ስዱዳን ለስዱዳን

ሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም

በዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ

ባለፈው ጽሑፌ በገባሁት ቃል መሠረት በባዕድ ምድር የሚኖሩ ወገኖች፤ የስደት ሕይወትን ከጀመሩበት አንሥቶ የጠበቁትን በማጣታቸው ችግር ውስጥ የገቡትን ወገኖቻቸውን እንዴት መርዳት እንዳለባቸው ለመጻፍ አሳቦቼን እያብላላሁ ነበር፡፡ ግንቦት ሃያ ቀን ምሽት እኔና ቤተሰቤ አልፎ አልፎ በምናየው የኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ አንድ ቃለ ምልልስ ተመለከትኩ፡፡ ቃለ ምልልሱን ያደረገችው በጣቢያው «ሄለን ሾው» የተሰኘ ሳምንታዊ ፕሮግራም ያላት ሄለን አሰፋ ነበረች፡፡ የዕለቱን ውይይት ያደረገችው ትእግሥት ከተባለች በመካከለኛው ምሥራቅ ነዋሪ ከሆነች ኢትዮጵያዊት ጋር ነበር፡፡ ትዕግሥት በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ትገኛለች፡፡

እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊት ወጣት ሠርታ ለመለወጥና ቤተሰቦቿን ለመለወጥ ወደ ዐረብ አገር ተሻግራ ለዓመታት የቆየች ናት፡፡ ትዕግሥት ከሄለን ጋር ባደረገችው ውይይት እንደገለጸችው ወደ የመን ከተሻገረች በኋላ እንደ አብዛኛዎቹ እኅቶቻችን በሰው ቤት ተቀጥራ ብዙ ችግሮችን አልፋለች፡፡ በአሠሪዎቿ ምግብ ከመነፈግና ከመራብ ጀምሮ እስከ መደብደብና መታሠር፤ በመጨረሻም እስከ መባረር ደርሶባታል፡፡ ከብዙ ድካም በኋላ በዐረብ አገር የሚሠሩ እኅቶቻችንን ሥቃይ አልፋበት ያየችው ትዕግሥት ላቧን አንጠፍጥፋ ያጠራቀመቻትን ገንዘብ ይዛ በእሷ የደረሰ እንዳይደርስባቸው የኢትዮጵያውያን እኅቶቻችንን ሥቃይ ቢቻል የሚያጠፋ ባይቻል ደግሞ የሚያቃልል ድርጅት ለማቋቋም ትወስናለች፡፡ በዚህ እንቅስቃሴዋ ላይ አንድ መቀመጫውን በኒውዮርክ ያደረገ በስደተኞች ላይ የሚሠራ ድርጅት ጋብዟት ወደ አሜሪካ እንደተሻገረች በቃለ መጠይቁ ገልጻለች፡፡

ትዕግሥት በዐረብ አገር ስለሚገኙ እኅቶቻችንና ሳይፈልጉ ስለሚወልዷቸው ሕጻናት ሥቃይ ስትገልጽ በዕንባም ጭምር ነበር፡፡ በዚያ የሚኖሩ እኅቶች በአጋጣሚ ስሕተት ወይም ተገደው የሚወልዷቸው ሕጻናት የመማርና እንደ ሕፃን የመጫወት መብት ተነፍጓቸው ከወላጆቻቸው ጋር እንደሚመቱ፣ እንደሚራቡና እንደሚታሰሩ ስትገልጽ ሐዘን በሰበረው ድምፅ በዕንባ እየታጠበች ነበር፡፡ ይህች እኅት እነዚህን በከፋ ችግር ላይ ያሉ ሕፃናትና ወላጆቻቸውን ለመርዳት በምታደርገው እንቅስቃሴ በአሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያን ምን እንዲረዷት እንደምትፈልግ ተጠይቃ አጽንኦትና ትኩረት ሰጥታ የተናገረችው ከወላጆቻቸው ጋር እየተሠቃዩ ያሉ ሕፃናት መጠለያ የሚያገኙበትን፣ ተምረውና እንደ ልባቸው የሚያድጉበትን ዕድል እንፍጠር፤ ወላጆቻቸውንም እንርዳ የሚል ነበር፡፡

ይህ የትዕግሥት መልእክት የዚህ ጽሑፍም የመጀመሪያ መልእክት ነው፡፡ ከብዙ ድካም በኋላ የስደት ሕይወታቸው የሠመረላቸው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው በልዩ ልዩ ምክንያት ተሰደው ወደሚኖሩበት አገር ሲመጡ በግልም በማኅበርም ሆነው መርዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ የተቀደሰ ተግባር ደግሞ በየሚኖሩበት አገር በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ተሰባስበው የሚገለገሉና የሚያገለግሉ ምእመናን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል ማለት ይቻላል፡፡ የተቸገሩትን ስለመርዳት፣ ሀገርና ወገንን ስለመውደድና ስለ ፍቅር አብዝታ በምታስተምር ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ናቸውና፡፡

ባለፈው ጽሑፋችን እንዳየነው በልዩ ልዩ ምክንያት አገር ወገናቸውን ትተው ወደ ባዕድ ምድር የሚሔዱ ወገኖች ስለሚሰደዱበት አገር ነባራዊ ሁኔታ መረጃ አይሰበስቡም፡፡ በብዛት እንደ ሚታየው ከሔዱም በኋላ በቀላሉ የተለያዩ መረጃዎችን የሚያገኙበት ዕድል የላቸውም፡፡ እንዴትና የት ሥራ እንደሚያገኙ፣ ኑሮአቸው እስከሚ ስተካከልና ራሳቸውን እስከሚችሉ አገሩ ያዘጋጃቸው የዕርዳታ ዕድሎች መኖር አለመኖራቸውን፣ ቋንቋ የትና እንዴት በቀላሉ መማር እንደሚችሉ ወዘተ ቀድመው የሔዱ ኢትዮጵያውያን በግልም በማኅበርም ሆነው ለአዳዲስ ስዱዳን ወገኖቻቸው ማካፈል ይገባቸዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በውጭው ዓለም በነበረው ቆይታ ያረጋገጠው ለአዳዲስ ስዱዳንም ሆነ እዛ በቆዩ ኢትዮጵያውያን መካከል ያለው የመረጃ ልውውጥ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በእጅጉ ያነሰ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ነገር ወደፊት መሻሻል አለበት፡፡ ወገኗን ብቻ ሳይሆን ባዕዳኑን በየዘመኑ በአክብሮት እየተቀበለች፣ ከገጠማቸው ችግርም እየታደገች ከኖረችና ካለች አገር የሔዱ መሆናቸውን ሊያስታውሱ ይገባል፡፡

የስደት ሕይወት እስከሚለምዱት ድረስ ከባድ ነው፡፡ ተወልደው ካደጉበት ቀዬ፣ ባሕልና ቋንቋ ተለይተው፣ ከቤተሰብ ሙቀትና ክብካቤ ርቀው የሚጀምሩት ሕይወት ነውና፡፡ በብዙ ቦታዎች እንደሚታየው በዚህ ፈታኝ ወቅት ተገቢውን ዕርዳታ ያገኙ ወገኖች በስደት ሕይወታቸው ሁሉ ከወገናቸው ርቀው የሚኖሩ፣ በመንገዳቸው እንኳን ኢትዮጵያዊ ካዩ ወይ መንገድ ቀይረው የሚሔዱ ካልሆነም ሰላምታም ሳይሰጡ የሚያልፉ፣ በጥቅሉ የተገለሉ ናቸው፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በልዩ ልዩ መንገዶች እንደ ሰማነው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ረጅሙን በረሐ በሕገ ወጥ መንገድ አቋርጠው፤ ከዚያም አደገኛ በሆነ ሁኔታ ውቅያኖስን አቋርጠው ወደ ጣልያንና ሊባኖስ ይሻገራሉ፡፡ በዚህ ዓይነት ከሚሔዱት ሩብ ያህል የሚሆኑት በመንገዳቸው በሚገጥማቸው አደጋ የበረሃና የውኃ ሲሳይ ሆነው ይቀራሉ፡፡ እግዚአብሔር ጠብቋቸው በረሃውን አልፈው፣ ውቅያኖሱን ዘልቀው ጣልያን የሚደርሱት ወገኖች የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው እንደነበር የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አስተውሏል፡፡ ከሚገጥሟቸው ችግሮች ውስጥ አንዱ በዚያ በሚኖሩ መናፍቃን የሚፈጠርባቸው ችግር ተጠቃሽ ነው፡፡ የጽሑፉ አዘጋጅ በቅርበት እንደተመለከተው በተለይ ጣልያን ያሉ ኢትዮጵያውያን ፕሮቴስታንት አዳዲስ ስዱዳን ወገኖቻችንን በልዩ መንገድ እየተቀበሉ፣ በችግራቸው እየገቡ እምነታቸውን ያስለውጧቸዋል፡፡ ከብዙ ድካምና ሰቀቀን በኋላ ወደማያውቀው አገር የገባ ሰው እንኳን በመልክ የሚመስለው ቋንቋውን እያወራ ልርዳህ ብሎ የቀረበው ሰው አግኝቶ ማንንም ቢሆን መቀበሉ አይቀርም፡፡

በዚህ የተነሣ በጥምቀት ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅጸነ ዮርዳኖስ ተወልደው የእናት ቤተ ክርስቲያንን ጡት እየጠቡ ያደጉ ወገኖች፤ በደጇ ተመላልሰው ዕንባቸውን እያፈሰሱ ያደጉባትን ቤተ ክርስቲያን ትተው ሔደዋል፡፡ እየሔዱም ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በዚያ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን አስተባብራ፣ ስዱዳን ልጆቿን ተቀብላ ማጽናናትና ማስተናገድ አለመቻሏ ነው፡፡

በደሙ የመሠረታት አምላክ የተመሰገነ ይሁንና ዛሬ ቤተ ክርስቲያችን በዓለም ሁሉ የተበተኑ ልጆቿን እየተከተለች ያልደረሰችበት የዓለም ክፍል የለም፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ይህንን ሥርጭት ያደረገችው በምናውቃቸው ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች አልፋና እያለፈች እንደሆነ ቢታወቅም ሐዋርያዊ ጉዞዋ ካለው ችግር አንጻር ሲመዘን የሚያስደስት እንጂ የሚያሳዝን አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ምንም እንኳን ሁሉም ናቸው ባይባልም በአብዛኛው አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎታቸው በቤተ መቅደስ ብቻ የተወሰነ ነው፡፡ ነገር ግን ቤተ  ክርስቲያን ሐዋርያዊ እጇ ረጅም መሆን አለበት፡፡ በመሆኑም ወደ አካባቢዋ የመጡ ልጆቿን ወዳሉበት ሔዳም የመሰብሰብ አገልግሎት መፈጸም ይጠበቅባታል፡፡ ይህ ተልእኮዋ በተለይ አዲስ ስዱዳንን በመሰብሰብና ከወገናቸው ጋር እንዲተዋወቁ፣ የሀገሩን ባሕልና ቋንቋ እንዲለምዱ ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ ለዚህ ደግሞ በባዕድ ምድር ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ይህንን ደገኛና በእጅጉ አስፈላጊ የሆነ ተግባር እንዲያከናውኑ የሚያደርጋቸውን ዕቅድና አሠራር መዘርጋት አለባቸው፡፡

ማጠቃለያ
በጽሑፉ እንደተመለከትነው ሕይወታቸውን በስደት መሥርተው የቆዩ ወገኖች ወደ አካባቢያቸው የሚመጡ ስዱዳንን በመቀበል ሊኖራቸው የሚገባቸውን ሚና በአጭሩ ተመልክተናል፡፡ ከምእመናኑም በተጨማሪ የእነሱ ኅብረት የሆነች ቤተ ክርስቲያንና አስተዳደሯ ይህንኑ ደገኛ ተግባር በመፈጸም ረገድ ልትከተለው የሚገባትን አቅጣጫ አሳይተናል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ ከተሰነዘሩት ጥቂት አሳቦች የበለጠ ኑሮአቸውን በስደት ካደረጉ ወገኖች ሊቀርቡ የሚችሉ አሳቦች እንደሚኖሩ ይታመናል፡፡

በመሆኑም በተደጋጋሚ እንደገለጽነው ይህ ዓምድ የተከፈተው ከዝግጅት ክፍሉ ከሚጻፉ ትምህርቶች በተጨማሪ ኑሮአቸውን በውጭው ዓለም ያደረጉ ምእመናን የሕይወት ልምዳቸውንና ተሞክሯቸውን በመለዋወጥ እንዲማሩ ለማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ወገኖቻችን ይህንን ዕድል በመጠቀም አገልግለው በረከት እንዲያገኙ ዛሬም ግብዣችንን እናስተላልፋለን፡፡
 

  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 20ኛ ዓመት 18 ከሰኔ 1-15 ቀን 2005 ዓ.ም.