‹‹ሰላምን ፈልጉ ስለ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ›› (ት.ኤር. ፳፱፥፯)

ዲያቆን ዘአማኑኤል አንተነህ 

ሰላም ‹‹ተሳለመ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጒሙም መፋቀር፣ መዋደድ ማለት ነው፡፡ ሰላም በሕይወት ስንኖር ልናጣቸው ከማይገቡ ነገሮች የመጀመሪያው ነው፡፡ ሰላም የፍጥረታት ሁሉ የሕይወት መርህ ነው፡፡ ሰላም/ፍቅር/ የሕግ ሁሉ ፍጻሜ ነው፡፡ ሰላም የሕይወት ማጣፈጫ ቅመም ነው፡፡ በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ ለማኅበራዊ ኑሮ መሠረቱ ሰላም ነው፡፡ ሰላምን በዋጋ መተመን በወርቅ በብር መግዛት አይቻልም፡፡ ሰው እርስ በእርስ በሰላም በፍቅር በአንድነት የማይኖር ከሆነ ምሥጢረ ሥጋዌን /የአምላክን ሰው መሆን/ ምሥጢራዊነት አለመረዳት ነው፡፡ ክርስቶስ ሰው የሆነው የሰውን ዘር ሁሉ ለማዳን ነውና፡፡ ከሦስቱ የቀጰዶቅያ አባቶች አንዱ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ የክርስቶስ ልደት የመላው ሰው የልደት ቀን ነው፡፡ በማለት አስረድቷል፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ሰው የሆነው ለሰው ልጆች  ሁሉ ሰላም ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያንም ሁልጊዜ በአስተምህሮዋ በቅዳሴዋ ‹‹ሰላም ለኵልክሙ/ሰላም ለሁላችሁ ይሁን›› እያለች ትሰብካለች፡፡ ሰላም የተጀመረው በጥንተ ተፈጥሮ ነው፡፡ መላእክት ከተፈጠሩ በኋላ ሁሉም መላእክት ማን ፈጠረን እያሉ በተረበሹ ሰዓት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በያለንበት እንጽና/አትረበሹ/ተረጋጉ በማለት የመጀመሪያውን የሰላም ብሥራት አብሥሯል፡፡ ስለዚህ የሰላም አስተማሪ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ አባቶቻችን ስለ ሰላም ብዙ ጽፈዋል፣ ብዙ መሥዋዕት ከፍለዋል፡፡

ስለ ሰላም ከአባቶቻችን ምን እንማራለን?

እንደ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ያሉ አባቶቻችን ከሰው አልፎ ከአራዊት ጋር ኑረው አሳይተውናል፡፡ እኛ ግን መኖር ያቃተን ከአራዊት ጋር ሳይሆን ከወንድሞቻችን ጋር ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ እንዲህ ብሏል ‹‹ዮሐንስ ምስለ ቶራት በገዳም ልሕቀ›› /ዮሐንስ ከቶራዎች ጋር በገዳም አደገ/፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ከልጅነቱ ጀምሮ የኖረው በበረሃ ነው በልጅነቱም ያጠባችው ቶራ የምትባል የዱር እንስሳ ነች፡፡ ብዙውን ጊዜ የኖረው በበረሃ ነው፡፡ ታዲያ የአባቶቻችን አካሄድ ይህ ሁኖ እያለ እኛ እንዴት ከራሳችን ጋር መኖር ያቅተናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን ራሱ ጌታችን ከሴቶች ከተወለዱት መካከል እንደ ዮሐንስ መጥምቅ አልተነሳም ብሎ መስክሮለታል፡፡እነ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ የኖሩት ከአንበሳ ጋር ነው ዕድሜያቸውን በሙሉ የጨረሱት በተጋድሎ ነው፡፡ እነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የኖሩት ከነብሮች ጋር ነው፡፡ የአባቶቻችን አካሄድ ይህ ሁኖ እያለ እንዴት ከወገኖቻችን ጋር መኖር ያቅተናል፡፡

አባታችን አብርሃም ዘመኑን በድንኳን ኑሮ አሳለፋት፡፡ እኛ ደግሞ ሰባ ወይም ሰማንያ ዘመን ተሰጥቶን አብሮ መኖር አቃተን፡፡ ዓለሙኒ ኃላፊ፣ ንብረቱኒ ኃላፊ፣ ፍትወቱኒ ኃላፊ፣ እስመ ኵሉ ኃላፊ ውእቱ ተብሎ የተፈጸመውን የእግዚአብሔር ቃል ተገንዝበን ሁሉም ነገር ኃላፊ መሆኑን መረዳት ተሳነን፡፡ አብሮ መኖርም አቃተን፡፡

ሰላምን በተግባር የሚገልጽ ሰው፡-

ክርስትና የሚያስተምረው በቃላት መዋደድን ወይም የአንደበትን ፍቅር አይደለም በድርጊት የሚታይ በሥራ የሚተረጎመውን ሰላም ነው፡፡ ውስጣዊ የማፍቀርን ባሕርይ ግልጽ የሚያደርገው ደግሞ ተግባር ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአንዳንድ የሀገራችን ቦታዎች ሰላም ጠፍቶ ኀዘን በዝቷል፡፡ ሰላምን የያዘ ሰው የሥነ ምግባርን ሕጎች አይተላለፍም፤ የሰውን ሕይወት አያጠፋም፤ ሰው የተባለውን ሁሉ አይጠላም፤ የሌላውን ሀብት እና ንብረት አይመኝም፤ የሰውን መልካም ስም አያጎድፍም ሌላው ሰው ባለው ነገር አይቀናም፤ ራሱን ብቻ አይወድም፤ በማንም ሰው ላይ ክፉ ሥራ አይሠራም፤ በራሱ ላይ ሊደርስበት የማይፈልገውን በሌላው ላይ እንዲደርስ አይፈልግም፤ በሀብቱ እና በጤንነቱ ጊዜ የሚወደውን ወንድሙን በችግሩ እና በሕመሙ ጊዜ አይጠላውም አይንቀውም አያገለውም፡፡

የሰላም ትሩፋቶች

ሰላማዊ መሆን በጎነት ነው፡፡ ጻድቁ ኢዮብ እንዲህ ይለናል፡፡ ‹‹አሁንም ከእርሱ ጋር ተስማማ ፣ሰላምም ይኑርህ፣ በዚያም በጎነት ታገኛለህ፡፡›› (መ.ኢዮብ ፳፪፥፳፩) ሰላማዊ መሆን ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ነው፡፡ ያለ ሰላም እግዚአብሔርን ማስደሰት አይቻልም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከሁሉ ጋር ወደ ሰላም ሩጡ›› (ዕብ. ፲፪፥፲፬)

ሰላማዊ ሰው መሆን ፍላጎትን ማሳኪያ መንገድ ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ‹‹ትእዛዜን ብትሰማ ኑሮ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር ዘርህም እንደ ባሕር አሸዋ የሆድህም ትውልድ እንደ ምድር ትቢያ በሆነ ነበር፡፡›› (ት.ኢሳ. ፵፰፥፲፰) በማለት እንደተናገረው፣ ሰላማዊ መሆን ለራስም ለሌሎችም ደስታን መፍጠር ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል›› እንዲል፡፡ (መዝ. ፴፮፥፲፩) ሰላማዊ መሆን ከመለያየት ይልቅ አንድነትን ማምጣት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ወንድሞች ሆይ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብ እና በአንድ ሐሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጅ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ›› በማለት በአጽንኦት ይመክረናል፡፡ (፩ኛ.ቆሮ. ፩፥፲)

ስለ ሰላም ምን እናድርግ?

ጸሎት ስናደርግ ሰላም እንዲሆን ሁሉም መጸለይ አለበት፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ ‹‹ሰላምን ፈልጉ ስለ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ›› እንዲል፡፡ (ት.ኤር. ፳፱፥፯)

ነቢዩ ዘካርያስ ‹‹እውነትን እና ሰላምን ውደዱ›› ብሏል፡፡ (ት.ዘካ. ፰፥፲፱) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ሰላምን እንያዝ›› (ሮሜ. ፭፥፩)፡፡ ቅዱስ ዳዊት ደግሞ ‹‹ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎ ዘመንን ማየት የሚወድ ማነው? አንደበትህን ከክፉ ከልክል፣ ከንፈርህም ሽንገላን እንዳይናገር፣ ከክፉ ሺሽ፣ መልካምንም አድርግ፣ ሰላምን ሻት ተከተላትም፡፡ (መዝ. ፴፫፥፲፪) ቅዱስ ያሬድም ‹‹ጥቅምን መሠረት ሳያደርግ ባልጀራውን የሚወድ ከእግዚአብሔር ነው›› እንዳለ፡፡ (ድጓ)

በተቀደሰ ሰላምታ ሰላም መባባል በዕለት ከዕለት ኑሮአችን ሰላምን መተግበር/ሰላምታ መለዋወጥ/ጠብ ጫሪ፣ ነገር ፈላጊ አለመሆን አምላክችን ኢየሱስ ክርስቶስ በየትኛውም ቦታ በሔድንበት ሁሉ ሰላም መባባል እንዳለብን ሲያስተምረን ‹‹ወደ ማንኛውም ሰው ቤት ስትገቡ ሰላምታ አቅርቡ፡፡›› (ማቴ. ፲፥፲፪)፣ ‹‹አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ›› ብሏል፡፡ (ማቴ. ፭፥፪)፣ ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹እንግዲያስ ሰላም የሚቆምበትን እርስ በርሳችንም የምንታነጽበትን እንከተል›› እንዳለን፡፡ (ሮሜ. ፲፬፥፲፱)

በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ሰላምን ከሚነሱ ምክንያቶች አንዱ ዘረኝነት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘረኝነት በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስቀጣ ነው፡፡ ሙሴ ኢትዮጵያዊቷን በማግባቱ እኅቱ ማርያም እና ወንድሙ አሮን ተቃውመው ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች የሙሴን ድርጊት በመቃወማቸው እግዚአብሔርን አስቆጡት እግዚአብሔርም ተቆጥቶባቸው ሄደ ደመናውም ከድንኳኑ ተነሣ እነሆም ማርያም ለምጻም ሆነች ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ (ዘኁ. ፲፪፥፩)

ቅዱስ ጳውሎስ ዘረኝነትን ደጋግሞ አውግዞ አስተምሯል፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ አንድ እንደሆነ አንድነትን አምልቶ እና አስፍቶ አስተምሯል፡፡ ‹‹አይሁዳዊንና አረማዊን አለየም አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና (ሮሜ. ፲፥፲፪)፣ እኛ ሁላችንም በአንድ መንፈስ አንድ አካል ለመሆን ተጠምቀናል አይሁድ ብንሆን፣ አረማውያንም ብንሆን፣ ባሪያዎች ብንሆን፣ ነጻዎችም ብንሆን ሁላችን አንድ መንፈስ ጠጥተናልና፡፡›› (፩ኛ.ቆሮ. ፲፪፥፲፫)፣ ‹‹ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፡፡ ወንድም ሴትም የለም ሁላችሁም በክርስቶስ
ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና›› እንዲል፡፡ (ገላ. ፫፥፳፰)

ማንም ሰው ራሱ ስለፈለገ አልተወለደም፡፡ ራሱም ስለመረጠ ከፈለገው ጎሳ አልተወለደም፡፡  ማንም ሰው ስለፈለገ ጥቁር ወይም ነጭ አይሆንም፡፡ ሰው ሁሉ አንድ ነው፡፡ ልዩነት ከቤታችን ጀምሮ አለ፡፡ አንዱ ቀይ፣ አንዱ ጥቁር፣ አንዱ ቀይ ዳማ፣ አንዱ ጠይም ወ.ዘ.ተ ይሆናል፡፡ ልዩነት ከስምም ጀምሮ ከቤት ይጀምራል፡፡ ስለዚህ ልዩነት ያለ የሚኖር ጉዳይ ነው፡፡ ግን ይህ ልዩነት ለጠብ የሚዳርግ አይደለም፡፡

ሰላማዊ ሰው አለመሆን በማኅበራዊ ሕይወት የሚያስከትለው ችግር

መንግሥተ እግዚአብሔርን አለማግኘት

ሰላምን የሚያደፈርሱ ሰዎች በአምላክ መንግሥት ሥር እንዲኖሩ አይፈቀድላቸውም፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ሚክያስ ‹‹በመኝታቸው ላይ በደልን ለሚያስቡ ክፋትንም ለሚያደርጉ ወዮላቸው›› (ት.ሚክ. ፪፥፩)፣ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ዐመፃን የወደዳት ግን ነፍሱን ጠልቷታል›› (መዝ. ፲፥፭)

ረኀብ

በአንድ ወቅት የሶርያው ንጉሥ ወልደ አዴር ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት ብሎ ሰማርያን በከበበ እና በጦርነትም ባስጨነቃት ጊዜ እስራኤላውያን ለጆሮ የሚቀፍ እና ለኅሊና የሚሰቀጥጥ ታሪክ ተፈጽሞባቸው አልፏል፡፡ የሶርያ ንጉሥ ወልደ አዴር ሠራዊቱን ሁሉ ሰበሰበ ወጥቶም ሰማርያን ከበባት በዚያም ተቀመጠ በሰማርያም ታላቅ ረኀብ ሆኖ ነበር፡፡እነሆም የአህያ ራስ በኀምሳ ብር የድርጎ አንድ አራተኛ የሚሆን ኩስሐ ርግብም በአምስት ብር እስኪሸጥ ድረስ ከበቡአት የእስራኤልም ንጉሥ በቅጥር ላይ ሲመላለስ ጊዜ አንዲት ሴት ጌታዬ ንጉሥ ሆይ እርዳኝ ብላ ወደ እርሱ ጮኸች እርሱም እግዚአብሔር ካልረዳሽ እኔ እንዴት እረዳሻለሁ ከአውድማው ወይስ ከመጭመቂያው ነውን? አለ፡፡ ንጉሡም ምን ሁነሻል አላት እርስዋም ይህች ሴት ዛሬ እንድንበላው ልጅሽን አምጪ ነገም ልጄን እንበላለን አለችኝ፡፡ ልጄንም ቀቅለን በላነው በማግስቱም እንድንበላው ልጅሽን አምጪ አልኳት ልጅዋንም ሸሸገችው ብላ መለሰችለት የእስራኤልም ንጉሥ የሴቲቱን ቃል ሰምቶ ልብሱን ቀደደ/አምርሮ አዘነ/፡፡ (፪ኛ.ነገ. ፮፥፳፬)

ከዚህ ታሪክ የምንማረው እጅግ ለኅሊና የሚከብድ የአህያ ራስ እና ኩስ ሰው የተመገበበትን፣ ሰዎች እርስ በርስ የተበላሉበትን ታሪክ ነው፡፡ አሁንም ሰላም ከሌለ ይህን ታሪክ በዘመናችንና በሕይወታችን ላለመደገሙ ምንም ዋስትና የለንም፡፡

ሃይማኖታዊ መሆን በሰው ሥቃይ የምንደሰትበት እና ነፍስ አጥፍተን ገነት የምንገባበት ሕይወት ሳይሆን ‹‹የቀኑ ለማኝ ለማታው ለማኝ ይተርፋል›› እንዲሉ ለወገናችን የምንተርፍበት ሕይወት ነው፡፡›› በአሁኑ ሰዓት ቤተ ክርስቲያን ምጥ ላይ ናት፣ ሀገር ምጥ ላይ ናት፣ ወላጅ ምጥ ላይ ነው፡፡ ጉረቤት እና ጉረቤት ሳይጠያየቅ የሚኖረው፣ ወላጅ እና ልጅ ሳይጠያየቅ የሚኖረው፣ወንድምና እኅት ሳይስማማ የሚኖረው ሰው ሁኖ አብሮ የመኖርን ትርጒም ያለመረዳት እንዲሁም የክርስቶስን ሰው መሆን አለመገንዘብ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሁሉም ሰላሙን አጥቶ እየተቸገረ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ምጥ ለመውጣት ቅዱስ ጳውሎስ ሰላምን አጥብቀህ ተከተል እንዳለ፡፡ (፪ኛ.ጢሞ. ፪፥፳፪) እንደ ኢዮብ ትዕግሥትን፣ እንደ አብርሃም ደግነትን፣ እንደ ይስሐቅ ታዛዥነትን፣ እንደ ያዕቆብ ቅን አገልግሎትን፣ እንደ ዮሴፍ ኃዳጌ በቀልነትን ገንዘብ አድርገን እርስ በእርሳችን እየተሳሰብን ተዋደን ተፋቅረን እንኖር ዘንድ አምላካችን ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ፳፯ዓመት መስከረም ፳፻፲፪ ዓ.ም.