ርእሰ ዐውደ ዓመት

እንኳን ለዘመነ ማርቆስ አደረሰን!

ጳጉሜን ፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

በጊዜ ሥጦታ ቀናት ተፈጥራዊ ዑደትን ተከትለውና ወራትን ተክተው ዘመንን ይፈጥራሉ፤ የዘመናት ለውጥም አዲስ ዓመትን ይተካሉ፤ ይህ ሁሉ ግን በእግዚአብሔር አምላክ ቅዱስ ፈቃድ ሆነ፤ እኛም ለአዲሱ ዓመት ዘመነ ማርቆስ እንደ ቸርነቱ ደረስን፡፡

ርእሰ ዐውደ ዓመት (የዘመን መለወጫ) በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት መስከረም አንድ ቀን እንድናከበር ስላደረሰንም ለተሰጠን ሥጦታና ዕድል በታላቅ ምስጋናና በክብር እናከበር ዘንድ ይገባል፡፡ በአዲስ ዓመት ወይም በዘመን መለወጫም ክብረ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን እያወሳን ዕለቱን በድምቀት እናከብራለን፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም ይህን አስመልክቶ እንደነገረን ‹‹ርእሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ ወላዴ መጥቅዕ ወአበቅቴ፤ የዓመት በዓል ራስ ዮሐንስ መጥቅዕና አበቅቴን የምትወልድ ነህ›› እየተባለ ይዘመርለታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ያስተማረውን ትምህርትና ገድሉን የሚያመለክት ስብከት ይሰበካል፤ ትምህርቱም ይሰጣል፡፡ ስለዚህም ከመስከረም አንድ እስከ ስምንት ባሉት ዕለታትም ቅዱሱን የሚያወሱ መዝሙራት እየዘመርን እናከብራለን፡፡

ቅዱስ ዮሐንስም «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ›› ብሎ እንዳስተማረውና የንስሓ ጥምቀት እንዳጠመቀው ሰዎች በሕይወት ዘመናችን ላይ የተጨመረልንን ዕድሜ ኃጢአት ከሠራን ንስሓ እንድንገባና አምነን ተጠምቀን እንድንድን ማሳሰቢያ የዘመን ጅማሮ ነው፡፡ በነቢያት መጨረሻ በሐዋርያት መጀመሪያ ተነሥቶ ዘመነ ሐዲስን እንደሰበከና ከዘመነ ብሉይ ወደ ዘመነ ሐዲስ መሸጋገሪያ ጊዜ ላይ ስለነበረ ያለፈውን ዘመን የምንሸጋገርበት የዘመን መለወጫ ቀን የቅዱስ ዮሐንስ መታሰቢያ እንዲሆንም እንደተደረገ ከዚሁ ጋር ልናጤን ይገባል፡፡ (ማር.፩፥፪-፭)

ቅዱስ ማርቆስም በወንጌሉ እንዳስተማረን ‹‹እነሆ÷ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፡፡ የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ፤ ጥርጊያውንም አስተካክሉ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ የአዋጅ ነጋሪ ድምጽ፤ ዮሐንስም በምድረ በዳ ያጠምቅ ነበር፤ ኃጢአትንም ለማስተስረይ የንስሓ ጥምቀትን ይሰብክ ነበር፡፡ የይሁዳና የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይሄዱ ነበር፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ሁሉንም ያጠምቃቸው ነበር፡፡»  (ማቴ.፫፥፪)

የዘመን መለወጫ አቆጣጠር የነበረው ጠቀሜታ በተስፋ ይጠብቁት የነበረውን የጌታችንን መድኃኒታችን ኢየሱስን ክርስቶስ የመምጫ ጊዜ ለማወቅ ነበር፡፡ ለአዳም የገባለት ቃል ኪዳን  አንደተፈፀመ ግን በዓላትና አጽዋማት በዓመቱ የሚወሉበትን ዕለት በዘመን ቆጠራ ማወቅ ተችሏል፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያም የዘመን መለወጫ ዕንቁጣጣሽ ተብሎም ይጠራል፡፡  የቃሉም ፍቺም  እንግጫ (እርጥብ ሣር) ማለትም ነው፤  በዓሉም ይህንን ስያሜ ያገኘው በንግሥተ ሳባ ዘመነ መንግሥት እንደነበር ታሪክ ይዘክራል፡፡ ንግሥቷ የጠቢቡ  ሰሎሞንን ጥበብ ለማወቅና ለመፈተኝ በጉብኝት በሄደችበት ወቅት ከንጉሡ ወንድ ልጅ በመውለዷ ወደ ሀገሯ ስትመለስ ሕዝቡ ንጉሥ ተወለደ በማለት ቀዳማዊ ምኒልክንና ንግሥቲቷን ሲቀበሉ  እልል እያሉ «አበባ ዕንቁ (አብረቅራቂ ድንጋይ) ጣጣሽ (ገጸ በረከት)» እያለ ገጸ ሥጦታ አበረክተዋልና በዚህ ዘመን ያለንን ኢትዮጵያን አንስትም ለዘመን መለወጫ በዓል የአበባ ገጸ በረከት እያቀረብን እናከብራለን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ዘመኑን የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት ያድርግልን፤ አሜን፡፡