Aba Heruye

ማኅበረ ቅዱሳን ከአዲሱ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ ጋር ስለ ቀጣዩ የአገልግሎት ዘመን ተወያየ፡፡

ኅዳር 8/2004 ዓ.ም

በዲ/ን ኅሩይ ባየ

ማኅበረ ቅዱሳን ከአዲሱ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ መልአከ ጽዮን ቆሞስ አባ ኅሩይ ጋር ኅዳር 7 ቀን 2004 ዓ.ም ስለ ቀጣዩ የአገልግሎት ዘመን ተወያየ፡፡
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በሰ/ት/ቤቶች ማደሪጃ መምሪያ ቢሮ በተደረገው ውይይት፣ ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የተነሣባቸውን ወደ ዐሥራ ሁለት የሚሆኑ ነጥቦችን በማብራራት የማኅበሩ ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም ንግግር ያደረጉ ሲሆን ለአዲሱ የመምሪያ ሓላፊ የማኅበሩን አጠቃላይ አሠራር በተሰጠው ሕግና መመሪያ መሠረት እንዲቆጣጠሩና በቅርብ እንዲከታተሉ ጨምረው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
Aba Heruye
መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይም ከዐሥራ ሁለት ዓመት የውጭ ሀገር አገልግሎት በኋላ በፈቃደ እግዚአብሔር በቅዱስ ፖትርያርኩና በብፁዓን አባቶች ይሁንታ እንዲያገለግሉ ሲጠሩ ደስታ እንደተሰማቸው በመግለጥ፣ “የሰው ልጆች ጠባይ እንደ መልካችን የተለያየ ቢሆንም እንደ አመላችን ሰብስባ የያዘችን ቤተ ክርስቲያን ናት፣ የቤተ ክርስቲያናችን የአሠራር መንገዱ አንድ ነው፤ ስለዚህ የተገናኘነው በቤተ ክርስቲያንና ስለ ቤተ ክርስቲያን ስለሆነ በአባቶቻችን ጸሎት እየታገዝን እናገለግላለን” ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የከምባታ፣ ሀድያና ስልጤና ጉራጌ አህጉረ ስብከት እንዲሁም የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ እንዳስታወቁት ማኅበረ ቅዱሳን ራሱን ደሴት አድርጎ ለብቻው የሚጓዝ ተቋም ሳይሆን በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ያለ ማኅበር ነው፡፡ በመሆኑም በመደማመጥ እና በመወያየት ከሠራን ችግር አይኖርም፡፡ መለያየት ለጠላት ያመቻል፡፡ አንድ ከሆንን ግን ልዩነታችንን የሚፈልጉ ሰዎች መግቢያ አይኖራቸውም፤ ስለዚህ ለመልካም ነገር በሮቻችንን እየከፈትን ለመጥፎ ነገር ደጃችንን ልንዘጋ ይገባል ብለው፣ የምንሠራው ሥራ ውጤታማ የሚሆነው በመፈቃቀር፣ በመቀራረብ፣ በመወያየትና የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር ጠብቀን ስንሠራ ነው በማለት አሳስበዋል፡፡
ብፁዕነታቸው አያይዘው መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይን የተሰጣቸውን ትልቅ ሓላፊነት በእውነትና በሐቅ እንዲወጡ አባታዊ ምክር አስተላልፈዋል፡፡
በውይይቱ የማደራጃ መምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ የማደራጃ መምሪያው ኃላፊ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ መሸሻ፣ የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ጉባኤ፣ ሥራ አስፈጻሚ፣ ኦዲትና ኢንስፔክሽን፣ የኢዲቶሪያል ቦርድ አባላትና የሚዲያ ክፍል አገልጋዮች እንዲሁም ልዩ ልዩ የማኅበሩ አባላት ተገኝተዋል፡፡
መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ከሰ/ት/ቤት ወጣቶችና በሥራቸው ካሉ ማኅበራት ጋር ተግባብተው እና ተናበው አገልግሎታቸውን እንደሚወጡ ይጠበቃል፡፡