መፃጒዕ

መጋቢት ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

በዘመነ ሥጋዌ በኢየሩሳሌም ውስጥ ይኖሩ የነበሩ በተለያየ ሕመም ይሠቃዩ የነበሩ ሰዎች ለመፈወስ የሚሰበሰቡባት ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፡፡ አምስትም መመላለሻ ነበራት፡፡  በዚያም ብዙ ድውያን ይተኛሉ፤ ከእነርሱም ውስጥ የታወሩ፣ አንካሾች፣ የሰለሉ፣ ልምሹ የሆኑ፣ በየእርከን እርከኖች ላይ ይተኙ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልአክም ውኃውን ለመቀደስ በሚወርድ ጊዜ ድምፁ እስኪያስተጋባ ድረስ ውኃው ይናወጣል፡፡ ድውያኑም በዚያ ሥፍራ ተኝተው የውኃውን መናወጥ ይጠባበቃሉ፡፡ ምክንያቱም በዕለተ ሰንበት (ቀዳሚት) ውኃው ሲናወጥ ቀድሞ ወደ ውኃው የገባ አንድ ሰው ከደዌው ይፈወስ ነበርና፡፡

ከእነርሱም ውስጥ መፃጒዕ የተባለ ለ፴፰ ዓመት በክፉ ደዌ ተይዞና በአልጋ ቊራኛ ታስሮ የኖረ አንድ ሰው ነበር፡፡ እርሱም ወደ መጠመቂያው የሚያወርደው ሰው ስላልነበረ ቀድሞ ገብቶ መፈወስ አልቻለም ነበር፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ወደዚያች መጠመቂያ በሄደበት ጊዜ መፃጒዕን አገኘው፡፡ ጌታችንም ይህን ሰው በአልጋ ተኝቶ ባየው ጊዜ መዳን እንደሚፈልግ ዐውቆ ጠየቀው፤ «ልትድን ትወዳለህን?» መፃጒዕም «አዎን ጌታዬ ሆይ፤ ነገር ግን ውኃው በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያው የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ እኔ በምመጣበት ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል፤ አለው፤» ጌታም «ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ» አለው፤ ወዲያውኑም ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ ይህችም ዕለት ሰንበት ነበረች፡፡ (ዮሐ.፭፥፮-፱)

በዚህም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው አራተኛው ሳምንት መፃጒዕ ብሎ ሠይሞታል፡፡ መፃጒዕ ‹‹ጐባጣ›› ማለት እንደሆነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተባለ መጽሐፋቸው ይገልጹታል፡፡ (ገጽ ፮፻፭)

በዚህችም ዕለተ ሰንበት ከዋዜማው ጀምሮ ‹‹አሕየዎ ኢየሱስ ለመፃጒዕ ለ፴ወ፰ ክረምት ሐመ፤ ፴፰ ዓመት ሽባ ሆኖ የታመመውን መፃጒዕን ኢየሱስ አዳነው›› እየተባለ ይዘመራል፡፡ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው ዕለቱን በዚህ ዝማሬ እያከበሩ ጌታችን  መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያመሰግናሉ፡፡ (ጾመ ድጓ)

መፃጒዕ ለ፴፰ ዓመት ከአልጋ ላይ መነሣት እንኳን ከማይችልበት ሁኔታ ያዳነው ጌታችን ኢየሱስ በመጀመሪያ መዳን እንደሚፈልግ ጠይቆት ነበር፡፡ አልጋውን ተሸክሞ እንዲሄድ ባዘዘው ጊዜ ያለ ምንም ድካም ተፈውሶ ተነሥቶ መሸከም ችሏል፡፡ ይህን ማመን ከሁሉ ክርስቲያን ይጠበቃል፤ ምክንያቱም እኛም ካለብን ሕመም እና በሽታ እንድንፈወስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመፃጒዕ ያደረገውን ተአምር ልናምን ይገባል፡፡ በቤተ ሳይዳም ተጠምቀው እንደዳኑት ሕዝቦች ጸበል በመጠመቅ ፈውሰ ሥጋን ማግኘት እንደምንችል ማመን ያስፈልጋል፡፡

ሰው በእምነት መኖር ካልቻለ የሃይማኖትን ትምህርት መረዳትም ሆነ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ዐውቆ መተግበር አይችልም፤ ምክንያቱም ከሁሉም አስቀድሞ በፈጣሪያችን እምነት ሊኖረን እንደሚገባ መረዳት አለብን፡፡

በቤተ ሳይዳ ይገኙ የነበሩ ሕሙማንም በእምነት ስለሚጠመቁ ይድኑ ነበር፤ እኛም ከማንኛውም በሽታ ለመፈወስ ስንሻ እምነት ሊኖረን ይገባል እንጂ በ ‹‹እስኪ ልሞክረው›› ጸበል ቦታ ሄደን የምንጠመቀው ከሆነ ሁሉን የሚያይ ፈጣሪ ልባችን ውስጥ ያለውን ጥርጣሬም ሆነ የእምነት ጒድለት ያውቃልና አንፈወስም፡፡

በተለያዩ ዘመናት ሰዎች ከያዛቸው በሽታና ደዌ ሲፈወሱ ሰምተን፣ አይተን ወይንም ስለ እነርሱ አንብበን ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህም እነርሱን ያዳነ እና በቸርነቱ የፈወሳቸው አምላካችን እግዚአብሔር እኛንም እንደሚፈውሰን አምነን ልንኖር ይገባል፡፡ አለበለዚያ ግን ማንም ሰው ፈውስን ማግኘት አይችልም፡፡

በዚህ ጊዜ አብዛኛው ሰው ጤነኛ አይደለም፤ በከባድም ሆነ በቀላል ሕመም ይያዛል፡፡ በመሆኑም የትኛውም የሳይንሳዊ ሕክምና ሊፈታው የማይችል በሽታ ቢይዘን እንኳን በእምነት በመጠመቅ መዳን እንደሚቻል ማመን ያስፈልጋል፡፡

ነገር ግን ብዙዎቻችን እምነት ይጎድለናል፤ አይሁድ መፃጒዕ ጌታችን ያደረገለትን ተአምር ባለማመን በሰንበት ቀን አልጋ ተሸክሞ መሄድ ዕለቱን አለማክበር እንደሆነ መፃጒዕን ለማሳመን ሞክረው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ስሙን የማያውቀው ሰው እንዳዳነው ሊያስረዳቸው ቢጥርም በዓይናቸው ካላዩ እንደማያምኑት አስጨነቁት፡፡

ከዚህም በኋላ መፃጒዕ ጌታችንን በቤተ መቅደስ ውስጥ ሲያስተምር አገኘው፤ ጌታም እንዲህ አለው ‹‹እነሆ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ተጠንቀቅ፡፡›› እርሱም የተባለውን ሰምቶ አይሁድ ካሉበት ስፍራ በመሄድ ያዳነው ሰው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ነገራቸው፡፡ (ዮሐ.፭፥፲፬)

ሆኖም ግን አይሁድ የነገራቸውን ሰምተው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በምቀኝነት ሊገድሉት ፈለጉ፡፡ ለዚህም ሰበብ ፈልገው ሰንበትን ይሽራል የሚል ክስ መሠረቱበት፡፡

መፃጒዕን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቢፈውሰውም መልሶ ክዶታል፤ እርሱ በጌታ እጅ የተፈወሰ ሰው ቢሆንም በእምነቱ ጒድለት የተነሣ ፈጣሪውን ክዷል፡፡ እኛም የተደረገልንን በማስታወስ ክሕደትን ሳንፈጽም በእምነት ልንኖር ይገባል፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ስለ እምነት በወንጌል ሲያስተምር በተለይም ችግርና መከራ በሚጸናብን ጊዜ በእምነት እንድንጸና ነግሮናል፡፡ ሆኖም ግን አብዛኛው ሰው ችግር እና መከራ ሲመጣ በእምነት ከመጽናት ይልቅ ከችግሩ ለመገላገል ወደ ተሳሳተ መንገድ ወይንም እግዚአብሔር አምላክን ረስቶ ባዕድ አምልኮን እስከመከተል ድረስ ይደርሳል፡፡ ይህ ግን የሞት ሞት ነው፡፡ ምክንያቱም ችግራችን ለጊዜው የተፈታ ቢመስለንም የባሰ መከራ ውስጥ ይከተናል፤ የተወሳሰበ ኑሮ ውስጥም እንገባለን፡፡ ስለዚህም ወደ እግዚአብሔር አምላካችን የመመለሻው መንገድ ይጠፋብናል፡፡

በመሆኑም በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለን ድኅነትን እንድናገኝ ችግርና መከራን ተቋቁመን መኖር እና በእምነት መጽናት አለብን፡፡ በሕይወታችን ውስጥም የምናደርጋቸው ማንኛውንም ተግባራት በእምነት ልናደርግ እንደሚገባ ማወቅ አለብን፡፡ እምነት ያለው ሰው እግዚአብሔር አምላክ ከእርሱ ጋር ይኖራል፤ በሃይማኖት ይጸናል፤ ፈውሰ ሥጋ ፈውሰ ነፍስን ያገኛል፤ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳል፡፡

አምላካችን  እግዚአብሔር በእምነት እንድንጸና ይርዳን፤ አሜን፡፡