‹‹መጠራጠር የእምነትና የጽናት ጉድለት ነው›› ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ

መጠራጠር የእምነትና የጽናት ጉድለት ነው፤ መድኃኒታችን ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመጣ ጊዜ ምትሐት ምስሎአቸው ታወከው በፍርሃት ጮኹ።  ጌታችን ኢየሱስም ‹‹አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ አትፍሩ›› አላቸው፤  ቅድስ ጴጥሮስም መልሶ፥ አቤቱ፥ አንተስ ከሆንህ በውኃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ›› አለው። እርሱም ‹‹›› አለው። ጴጥሮስም ከታንኳው ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውኃው ላይ ሄደ።  ነገር ግን ነፋሱ በርትቶ ባየ ጊዜ ፈራ፥ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ ጌታ ሆይ፥ አድነኝ ብሎ ጮኸ። ወዲያውም ጌታችን ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘው ‹‹አንተ እምነት የጎደለህ፥ ስለምን ተጠራጠርህ?›› ብሎታል፡፡ መጠራጠር ያለመጽናት፣ ያለማመን ውጤት ነውና፡፡ (ማቴ. ፲፬፥፳፬-፴፩)

መጠራጠር ወደ ሰው ልቡና በቀላሉ ሊገባ ይቻላል፤ ከዚያ ሰው ግን በቀላሉ አይወጣም፡፡ መጠራጠር የሰውን ሰላምና የኅሊና ዕረፍት ያሳጣል፡፡

 የእግዚአብሔርን ህልውና መጠራጠር

መጠራጠር በእግዚአብሔር ህልውና ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ በአንድ ወቅት በዲያብሎስ የተጠነሰሰና በሰው ሕይወት ውስጥ ጣልቃ የሚገባ ረቂቅ ውጊያ ነው፡፡ ይህ የሚመጣውም በዚህ ዙሪያ የተጻፉ መጻሕፍትን ከማንበብ፣ እግዚአብሔር የለም ብለው ከሚያምኑ ሰዎች ጋር ከመወዳጀትና ከኅሊና በላይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከመፈላሰፍ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ውጊያ ከተለያዩ የፍልስፍና እና የሳይንስ የምርምር መስኮች ወይም ስለ ህዋና አፈጣጠሩ ከተጻፈ ታሪክ ወይም ደግሞ ታዋቂ ለመሆን ፈልገው ሰዎችን ከሚቃወሙ አካላት የሚመጣም ነው፡፡

ምናልባትም መጠራጠር የእግዚአብሔርን ህልውና ከመጠራጠር ላይነሣ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ርዳታውንና ጥበቃውን፤ ፍቅሩን እና ቃል ኪዳኑን ወይም የጸሎትን ጥቅም ተንተርሶ ይነሣል፡፡ ርብቃ እግዚአብሔር ያዕቆብን ለመባረክ የገባውን ቃል ኪዳን ስለ ተጠራጠረች ይስሐቅን ለማታለል ሰው ሰውኛውን የማታለል ዘዴ ተጠቅማለች፡፡ (ዘፍ. ፳፯፥፭-፲፯)

ዶግማን መጠራጠር  

የዚህ መጠራጠር ውጤት የሚመጣው በሌሎች የእምነት ድርጅቶች አማካይነት ነው፡፡ የጸና እምነት የሌለው ሰው የእነርሱን ስብሰባ በመካፈል፣ የእነርሱን መጻሕፍት እና በራሪ ጽሑፎች በማንበብ የውጤቱ ተካፋይ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በጆህቫውያኖች መካከል ተገኝቶ ስብከት ሊያዳምጥ ይችላል፡፡ ወይም ኦርቶዶክሳውያን ባልሆኑ ሰዎች ስብከት ተጽዕኖ ሊደርስበት ይችላል፡፡ እነዚህን በማድረጉ ጥርጣሬ ወደዚህ ሰው ልብና ኅሊና ዘልቆ ይገባል፡፡

ሰው በእምነቱ በዓለት ላይ እንደ ተመሠረተ ቤት ጽኑ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አንዳንድ ሰዎች የዶግማ ጥናት ስለሚከብድ ከመንፈሳዊነት የተራቆተ ነው በማለት ያስታሉ፡፡ ማጥናትን ካቆመ በኋላ ሰው ከአንድ አስቸጋሪ ጥያቄ ጋር ሲጋፈጥ መጠራጠር ውስጥ ይገባል፡፡ እኛ የምንመክረው ግን መንፈሳዊ፣ የዶግማ  እና የሥነ መለኮት መጻሕፍትን እንዲያነብ ነው፡፡ (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፭)

ቅድስናን መጠራጠር

አንድ ሰው የጾም አስፈላጊነቱ ምኑ ላይ ነው? የሥጋ ቅድስና ምን ዋጋ አለው? የመቆጠብ ጥቅም ምን ይፈይዳል? የድንግልና ጥቅሙስ ምንድን ነው? እግዚአብሔር ከእኛ ጸሎትን ሳይጠባበቅ የሚያድነን ከሆነ ጸሎት ማድረሱ ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው? በማለት በጥርጥሬ ሊሞላችሁ ይችላል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ሰው ‹‹የቅድስና ጥቅሞች ምንድን ናቸው? ተራ ተግባራት ወይም ሕግጋት ናቸው እኮ!! ሰው ደግሞ በሕግ አያጸድቅም!!›› ብሎ እስከመናገር ይደርሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ‹‹እስካመንህ ድረስ የወደድኸውን ማድረግ ስለምትችል ምንም ዓይነት ቅጣት አይደርስብህም! ሌላው ቢቀር ሰባት ጊዜ ብትወድቅ እንኳ ሰባት ጊዜ ልትነሣ ትችላህ›› በማለት ይናገራል፡፡

መጠራጠር ዘመናዊ የፈጠራ ግኝቶች ማለትም እንደ ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ ሲኒማና ሙዚቃን አስመልክቶ ተፈቅዷል ወይስ ተከልክሏል? በማለት ያጠራጥራል፡፡ በኅብረተሰቡ መካከል እንግዳና አዲስ የሆኑ ነገሮችን ማለትም እንደ እርግዝና መከላከያንና ከማኅፀን ውጪ ተገርዘው የሚወለዱ ልጆችን በማስመልከት ጥርጣሬ ሊያመጣ ይችላል፡፡ እንዲህ ያሉት ነገሮች እንደ መረዳትና እንደ ጥናት ጥልቀት እንጂ እንደ ፊደል ባይሆኑ መልካም ነው፡፡ ለምሳሌ ሲኒማ ሊፈቀድም ሆነ ሊከለከል የሚገባው ከሚሰጠው ጥቅምና ጉዳት አንጻር ተመዝኖ ነው፡፡ ቴሌቭዥን፣ ሬዲዮ፣ ተውኔት የምንጠቀምባቸው ለበጎ ነው ወይስ ለክፉ? ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡

አገልግሎትን መጠራጠር

አንድ አገልጋይ አገልግሎቱ ስኬታማ ነው? አገልግሎቱ መቀጠል ይሁን ወይስ ማቋረጥ እንዳለበት መወሰን አቅቶት አብዝቶ ይጠራጠራል፡፡ ፈጥኖ የሚደርሰውን ፍሬ ለማየት ከመጓጓት የተነሳ እንደነዚህ ዓይነት ጥርጣሬዎች በውስጡ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ፍሬውን ማየት ካልቻለ ግን የአገልግሎቱን ስኬታማነት ይጠራጠራል፡፡ ይህን አስመልክተን ከተክል አስተዳደግ ትምህርት ልንወስድ እንችላለን፡፡ አንድ ዘር ለማደግ፣ ለመጠንከርና ዛፍ ለመሆን ጊዜ ያስፈልገዋልና፡፡

የመጠራጠር መንሥኤዎች

የመጠራጠር መንሥኤዎች ከራስ የሚመጡ ውስጣዊ ወይም ውጪያዊ ናቸው፡፡ ወደሚያጸና መፍትሔ ለመድረስ እንችል ዘንድ እነዚህን መንሥኤዎች እንመለከታለን፡፡

አንዳንድ ጊዜ ግን ጥልቅ ሀሳብ ወደ ምክንያታዊነት ስለሚመራ የልብን ገራገርነት ያሳጣል፡፡ ከዚህ በኋላ ይህ ሰው መለኮታዊና መንፈሳዊ ምሥጢራትን በውሉን ሕሊናው አቅም ሊረዳቸው ስለሚናፈቅ ጥርጥር ውስጥ ይወድቃል፡፡ ብዙ ጊዜ ፈላስፎች ጥርጥሬ ውስጥ የሚወድቁት በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ፍርሃት

ብዙ ጊዜ ፍርሃት እና መጠራጠር አይነጣጠሉም፡፡ አንዱ ለሌላው ምክንያትም ውጤትም ሊሆን ይችላል፡፡ ፍርሃት ወደ መጠራጠር ይመራል፤ መጠራጠር ደግሞ ፍርሃትን ያስከትላል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በባሕር ላይ መራመድ ከጀመረ በኋላ ተጠራጠረ፤ መጠራጠሩ ፍርሃት አስከትሎበታል፡፡ ፍርሃቱ እየጨመረ ሲመጣም መስጠም ስለ ጀመረ ድምፁን አውጥቶ ጮኋል፡፡ (ማቴ. ፲፬፥፴)

የዲያብሎስ ውጊያዎች

መጠራጠር ከዲያብሎስ የሚቃጣ ጥንታዊ ውጊያ ነው፡፡ እርሱ በመጀመሪያ ቀደምት አባታችን ወደተከለከለችው ዛፍ በጥርጥር መርቷቸዋል፡፡ የመብላታቸውን ውጤትም እንዲጠራጠሩ አድርጓቸዋል፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ዲያብሎስ በጥርጥሬ ሊዋጋው ቢሞክርም ስላልቻለ ወድቋል፡፡ በመስቀል ላይ እያለም እንዲህ ብሎታል ‹‹…የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ከመስቀል ውረድ…፡፡›› ዲያብሎስ ቅዱስ እንጦንስን በጥርጥር ከምንኩስና ለማራቅ ሞክሮ ነበር፡፡ ሰው በሞቱ አፋፍ ላይ እያለ እንኳ ዲያብሎስ ወደ ቅጣት ሊያስገባው ወደ መጠራጠር ይከተዋል፡፡ (ማቴ. ፳፯፥፵)

ዲያብሎስ ዓለሙን እያሳተ ያለው ጥርጣሬን ከጥንት ጀመሮ ከማወቁም በላይ እንዴት በእነርሱ መዋጋት እንደሚችል በሚገባ ስሚያውቅ ነው፡፡ ስለሆነም በሁሉም ነገር ላይ ጥርጣሬን ይተክላል፤ እርሱ በእምነት ላይ እንኳ ጥርጣሬን ያመጣል፡፡ ሌላውን ለማደናር ከሌሎች ጋር ይወዳጃል፤ ሌላውን ደግሞ ያሳፍራል፤ መጠራጠር ከዲያብሎስ ብቻ ሳይሆን ከአካባቢም ይመጣል፡፡

በሰዎች አሉባልታ የሚመጣ ጥርጣሬ

መግደላዊት ማርያም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከትንሣኤው በኋላ ብትመለከተውና እርሱም ቢያነጋግራት እንኳ አይሁድ በየሥፍራው በነዙት የተሳሳተ አሉባልታና ጥርጥሬ መካከል ራስዋን ስታገኝ ተጠራጥራ ነበር፡፡ (ዮሐ. ፳)

እምነትና መታመን ከአማኝና ከጽኑ ጓደኛ እንደሚወረስ ሁሉ መጠራጠርም ከተጠራጠረ ባልንጀራ ይወረሳል፡፡ ስለሆነም ከእነዚህ ሰዎች ጋር ባልንጀራ ከመሆን መራቅ ይገባል! ይህን ልናደርግ ባንችል እንኳ ንግግራቸውን በንቃት በማዳመጥ የሚሉትን በሙሉ አለማምን ያስፈልጋል፡፡

የመጠራጠር  ምንጮች ከሆኑትና ጥርጥሬን ከሚያነሳሱት ነገሮች መካከል አንዱ ንባብ ነው፡፡ መጠራጠር ያለባቸውን መጻሕፍት ሙሉ ለሙሉ ከእኛ አስወግደን ሊገነቡን የሚችሉ መጻሕፍትን መርጠን ማንበብ እንጂ እምነትንንና ሞራልን የሚያጠፉ መጻሕፍትን ማንበብ  አያስፈልግም፡፡ አንዳንድ ጸሐፊዎች የጸኑ ጻድቃንን በመቃወም በአንባብያን ውስጥ ጥርጥሬን ያነሣሣሉ፡፡ ይህን ሲያደርጉ ሌሎች የማያውቁትን እነርሱ እንደሚያደርጉት አድርገው ያቀርባል፡፡ ሌላው የጥርጥሬ መንሥኤ በአብዛኛው ሐሰት ሆኖ የሚገኘው ሐሜት ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዙሪያ የሚነጋገሩ ወሬዎችን ማመን የለብንም፡፡ እኛም እነዚህን ሐሜቶች እንደ ገደል ማሚቶ ደጋግመን አናስተጋባ! ይህን የምናደርግ ከሆነ በጥርጥሬ የተሞላን ሰዎች እንሆናለን፡፡

ከዚህ አንጻር የአባታችን የአብርሃምን ታሪክ ስንመለከት እርሱ ለረዥም ዓመታት ምንም ልጅ ሳይወልድ ቆይቷል፡፡ አንድ መከራ ወይም ችግር ገጥሞአቸው ለረዥም ጊዜ ያለ ምንም መፍትሔ የሚቆዩ ሰዎችም በዚህ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡

በመከራ የሚመጣ መጠራጠር

ጌዴዎን በጥርጥሬ ውስጥ በነበረ ጊዜ የእግዚአብሔርን መልአክ የጠየቀው ጥያቄ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል፡፡ ‹‹… እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ እግዚአብሔር ከግብጽ አውጥቶናል ብለው ይነግሩን የነበረ ተአምራቱ ወዴት አለ?›› (መሳ.፮፥፲፫)

ከፊት የተጋረጠ ታላቅ አደጋ ወይም መከራ ሰውን ጥርጥሬ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርገዋል፡፡ የእስራኤል ሠራዊት በጎልያድ ፊት የነበራቸው የጥርጥሬ ስሜት ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ግን ከሠራዊቱ በእምነት ምንም ዓይነት ጥርጥሬ ሳያድርበት በሙሉ ልብ ሆኖ ጎልያድን ‹‹እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል…›› ብሎታል፡፡(፩ኛ ሳሙ. ፲፯፥፵፮)

መከራ ለረዥም ጊዜ ሲረዝምና አንድ ሰው በጥርጥሬ ማዕበል ውስጥ ሲወድቅ የእግዚአብሔርን ምሕረት ይጠራጠራል፤ ወይም ሰውየው በእርሱ ላይ ጥንቆላ እንደተደረገበት አድርጎ ስለሚቆጥር የሚመጣበትን ችግር ለማስቆም ወደ ጠንቋዮች ቤት ይሄዳል፡፡ መከራና ረዥም ጊዜ በሀሳብና በጥርጥር ያልተሞላ ብርቱ ልብ ይፈልጋል፡፡

ጥርጣሬ የሰውን ልጅ እምነት ከሚሸረሽሩ ዋነኛ መሰናከያዎች ውስጥ በመሆኑ ውስጣችን እንዲኖር መፍቀድ የለብንም፤ ከእግዚአብሔር የሚያርቀን እና ለጥፋት የሚዳርገን እንዲሁም ከአምላካችን ደኅነትን እንዳናገኝም የሚያግተን በመሆኑ ልንጠራጠር አይገባም፡፡ በዚህ ጊዜም ከመጣው ቸነፈር እና መከራም ፈጣሪያችን ሊጠብቀን በፍጹም ልብ ማመን እንጂ መጠራጠር አይገባም፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን በፍጹም እምነት እንድናምን ይርዳን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፤ የዲያብሎስ ውጊያዎች (፪ኛ መጽሐፍ)፤ በግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ፤ ትርጉም አያሌው ዘኢየሱስ