‹‹መልአኩን ልኮ ያድነናል››

ሊቀ ልሳናት ቀሲስ ከፍያለው ጥላሁን

በመጽሐፍ ቅዱስ ይህን ያነሳነውን ርእስ እግዚአብሔር በሊቀ ነቢያት ሙሴ አድሮ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹በመንገድ ይጠበቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁልህም ሥፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአኬን በፊትህ እልካለሁ፡፡ ራስህን ጠብቅ፣ ስማው፣ እንቢም አትበለው፤ ስሜ በእርሱ ስለሆነ ይቅር አይልምና››፡፡ (ዘፀ. ፳፫፥፳)

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስንዱ እመቤት ስለሆነች ይህ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል በወቅቱ ለእስራኤል ዘሥጋ መሆኑን በኅዳር ዐሥራ ሁለት ቀን ትመሰክራለች፡፡ በዚህ ዕለት ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ሕዝበ እስራኤልን እየመራ ከግብፅ ምድር ከፈርዖን ግዛት ማውጣቱን ትዘክራለች፡፡

ጥንተ ነገሩንም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ይመሰክራሉ፤ አብርሃም ይስሐቅን ይወልዳል፣ ይስሐቅም ያዕቆብን ይወልዳል፣ ያዕቆብም ይሁዳንና ዐሥራ አንድ ወንድሞቹን ወልዷል፡፡ ዐሥራ አንደኛው ዮሴፍ ነው፡፡ ‹‹ለሰው ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል›› ተብሏልና፡፡ (ማቴ. ፲፥፴፮) ዮሴፍን የገዛ ወንድሞቹ ጠልተው ተመቅኝተው ለእስማኤላውያን በሃያ ብር ሸጡት፡፡ እስማኤላውያንም ወደ ግብፅ ወስደው ለፈርዖን ቢትወደድ ለጲጥፋራ በሠላሳ ብር ሸጡት፡፡ ምሥጢሩ ግን ለበጎ ነው፡፡ ለሕዝቡ ምግብ ይሰጣቸው ዘንድ እግዚአብሔር ከዮሴር ጋር ተሸጠ እንዲል አባ ጊዮርጊስ፡፡

ዮሴፍ ለዐሥር ዓመታት በጌታው በጴጥፋራ ቤት በቅንነትና በታማኝነት ያገለግል ስለነበር ‹‹እግዚአብሔር የግብፃውያን ቤት በዮሴፍ ምክንያት ባረከው፤ የእግዚአብሔር በረከት በውጭም በእርሻውም ባለው ሁሉ ላይ ሆነ››፡፡ (ዘፍ. ፴፱፥፭) ጠቢቡ ሰሎሞን ስለዚህ ሲመሰክር ‹‹በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው›› ብሏል፡፡ (ምሳ. ፲፥፮) እግዚአብሔር ስለ ጻድቁ ዮሴፍ ብሎ የጌታውን ቤት በበረከት ሲመላ ጌታው ጲጥፋራም ‹‹ያለውንም ሁሉ ለዮሴፍ በእጁ አስረከበ፤ ከሚበላው እንጀራ በቀር ምንም የሚያውቀው አልነበረም››፡፡ (ዘፍ. ፴፱፥፮)

፩  ከነዓን ረኃብ በጸና ጊዜ ዮሴፍ በንጉሡ ፈርዖን ፈቃድ ተሹሞ ለረኃብ ዘመን የሚሆን እህል አከማችቶ ነበርና የሸጡት ወንድሞቹ እህል ለመሸመት ወደ ግብፅ ሀገር መጥተው፣ በፊቱ ሰግደው፣ እህል ሸምተው ዮሴፍ በሕይወት እንዳለ ለአባቱ ሲነግሩት፤ አባቱ ያዕቆብ ከሞተ እንደተነሳለት ቆጥሮ፤ ልጆቹን  የልጅ ልጆቹን ይዞ ወደ ግብፅ ወርዶ በምድረ ጌሴም ተቀምጧል፡፡

ከብዙ ዘመናት በኋላ ዮሴፍን ያላወቀ ፈርዖን ነገሠ፡፡ ሕዝበ እስራኤል ከእኛ ከግብፃውያን ይልቅ በዝተዋል፤ ጠላት ቢነሳብን ተደርበው ከጠላቶቻችን ጋር ወግነው ያጠፉናል ብሎ አገዛዝ አጸናባቸው፤ ፍርድ አጓደለባቸው፤ ሕዝበ እስራኤል መከራ እየተቀበሉና እየተሠቃዩ ኖሩ፡፡

እግዚአብሔር ሕዝቡን ለማዳን ምክንያት ይፈልጋልና ራሔል የምትባል ዕብራዊት ሴት ባሏ ሮቤል ሞቶባት የንጉሡን ትዕዛዝ አክብራ ጭቃ ለመርገጥ በወጣችበት ወቅት ነፍሰ ጡር ነበረችና በሥራ ላይ እያለች ከሥራው ክብደት የተነሣ የፀነሰቻቸው ልጆች ከማሕፀኗ ወጥተው ከእግሯ ሥር ሲወድቁ ደንግጣ ብትቆም የፈርዖን ሹም ልጆቿን ከጭቃው ጋር እንድትረግጣቸው አዘዛት፡፡ ራሔልም በዚህ ግፍ እጅግ አዝና አልቅሳ ዕንባዋን ወደ ሰማይ ረጨችው፡፡ እንዲህም አለች፤ ‹‹ኢሀሎኑ በዝ ሰማይ አምላከ እስራኤል፤ በእውነት የእስራኤል አምላክ ሁሉን ቻይ በዚህ ሰማይ የለምን? ይህን ግፍ አይመለከትምን?›› አለች፡፡

፪   የራሔል ዕንባ ቅድመ እግዚአብሔር ደረሰ፤ ይህን ነቢዩ እንዲህ ገልጾታል፤ ‹‹የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምጽ በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ድምጽሽን ከልቅሶ ዓይንሽን ከዕንባ ከልክይ ለሥራሽ ዋጋ ይሆናልና፡፡ ከጠላትም ምድር ይመለሳሉ፡፡ ለፍጻሜሽም ተስፋ አለ›› በማለት ቃል ኪዳን ገብቶላታል፡፡ (ኤር. ፴፩፥፲፭-፲፮)

እግዚአብሔርም ስለ ቃል ኪዳኑ ታማኝ ነውና በሊቀ ነቢያት ሙሴ አድሮ፤ በፈርዖን ፊት ዘጠኝ ታላላቅ መቅሠፍት አድርጎ፤ በዐሥረኛ ሞተ ሰኩር  ዐሥራ አንደኛ ስጥመተ ባሕር እስራኤላውያንን ከግብፅ ምድር ከፈርዖን ግዛት እንዲወጡ አድርጓል፡፡ በጉዞአቸው ወቅት እስራኤላውያንን ይመራቸው የነበረው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ነበር፡፡

በሦስተኛው ቀን ፈርዖን ከሰገነቱ ሆኖ ከተማው ጭር እንዳለ በማየቱ እስራኤላውያን የተጓዙበትን የሦስት ቀን ጎዳና እርሱ በፈረስ በሠረገላ ሆኖ ሠራዊት አስከትሎ በአንድ ቀን ተጉዞ ደረሰባቸው፡፡ እስራኤላውያን ወደፊት እንዳይሔዱ የኤርትራ ባሕር መልቶ ከኋላም ፈርዖን ጦር ሰብቆና ጎራዴ መዞ ሲደርስባቸው ተጨንቀው ወደ ነቢዩ ሙሴ ጮኹ፡፡ እርሱም የሕዝቡን ጩኸትና መከራ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር አቀረበ፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹የቅኖች ጸሎት በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው›› በማለት እንደመሰከረው፡፡ (ምሳ. ፲፭፥፰) በሊቀ ነቢያት ሙሴ ጸሎት ባሕረ ኤርትራ ከሁለት ተከፍሎላቸው እስራኤላውያን ተሻገሩ፡፡ ፈርዖንም በትዕቢት መንፈስ ተይዞ ወደ ባሕሩ ከነሠራዊቱ ቢገባ አሁንም በሙሴ እጅ በነበረችው በትር ውኃው ወደ ቦታው ተመልሶ ፈርዖንና ሠራዊቱ በኤርትራ ባሕር ሠጥመው የዓሣ አንበሪ ቀለብ ሆነዋል፡፡ በዚህን ጊዜ የሙሴ እኅት ነቢይት ማርያም ባሕር ከፍሎ ላሻገራቸው እና ጠላቶቻቸውን በባሕር ለጣለላቸው እግዚአብሔር በዝማሬ ምስጋና አቀረበች፡፡

በዚህ ሁሉ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ይረዳቸው እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይነግረል፤‹‹ሠራዊቱና ፈርዖንም ባሳፈሯችሁ ጊዜ ፈጽማችሁ ወደ ሙሴ ጮኻችሁ ሙሴም ፈጽሞ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ ከፈርዖን ሠራዊት ጋር እንዳትገናኙ በመልአኩ ጠበቃችሁ›› እንዲል፡፡ (፩ኛ መቃ. ፲፫፥፳፪)

እግዚአብሔር ከደመና መና አውርዶ ከዓለት ውኃ አፍልቆ እየመገበ ከአርባ ዘመን ጉዞ በኋላ እስራኤላውያን ምድረ ርስት ከነዓንን ወረሱ፡፡ ይህ ድርጊት ለእስራኤል ዘነፍስ ለክርስቲያኖችም አስተማሪ ስለሆነ ክርስቲያኖች ርትዕት ሃይማኖትን ይዘው በኃጢአት ቢወድቁም በንስሓ ሳሙና ታጥበው ሥጋውን ደሙን ተቀብለው ገነት መንግሥተ ሰማያት እስኪገቡ በጉዞአቸው የእግዚአብሔር መልአክ እንደሚረዳቸው ያምናሉ፤ ስለዚህ ይማጸኑታል፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል›› ተብሏልና፡፡ (መዝ. ፴፫፥፯)