ልደቱ ለቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ

ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን ዘካርያስ የሚባል ካህን ነበር፤ ሚስቱም ኤልሣቤጥ መካን ስለነበረች ልጅ አልነበራቸውም፤ እርሷም የመውለጇ ዘመን አልፎ ነበር፡፡ ሆኖም ሁለቱም በእግዚአብሔር የታመኑ ጻድቃን ነበሩ፡፡

ከዕለታት በአንድ ቀንም ካህኑ ዘካርያስ ወደ ቤተ መቅደስ ለአገልግሎት በገባበት ሰዓት በዕጣን መሠውያው በቀኝ በኩል የእግዚአብሔር መልአክ ቆሞ ታየው፤ በዚያን ጊዜም በፍርሃት ተሞላ፤ መልአኩም እንዲህ አለው፤ ‹‹ዘካርያስ ሆይ፥ አትፍራ፤ ጸሎትህ በእግዚአብሔር ፊት ተሰምቷልና፤ ሚስትህ ኤልሣቤጥም ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ፡፡ ደስታና ሐሤትም ይሆንልሃል፤ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል፡፡ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናልና የወይን ጠጅና የሚያሰክርም መጠጥ ሁሉ አይጠጣም፤ ከእናቱ ማሕፀን ጅምሮም መንፈስ ቅዱስ ይመላበታል፡፡ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎቹን ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ይመልሳቸዋል፡፡ እርሱም የአባቶቻችን ልብ ወደ ልጆች፥ የከሓዲያንንም ዐሳብንም ለእግዚአብሔር የተዘጋጀ ያደርግ ዘንድ በኤልያስ መንፈስ ቅዱስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል፡፡›› ዘካርያስም መልአኩን እንዲህ አለው፤ ‹‹ይህ እንደሚሆን በምን አውቃለሁ? እነሆ፥ እኔ አርጅቻአለሁ፤ የሚስቴም ዘመንዋ አልፏል፡፡›› መልአኩም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህንም እነግርህና አበሥርህ ዘንድ ወደ አንተ ተልኬአለሁ፡፡ አሁንም በጊዜው የሚሆነውንና የሚፈጸመውን ነገሬን አላመንኽኝምና ይህ እስኪሆን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ፤ መናገርም ይሳንሃል፡፡›› (ሉቃ.፩፥፲፫-፳)

ከዚህም በኋላ ሚስቱ ኤልሣቤጥ ፀነሰች፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፀንሳ እናቱ ኤልሣቤጥን ለመጠየቅ በሄደችበት ወቅት በማሕፀኗ ውስጥ ሳለ ሕፃኑ ለእግዚአብሔር ልጅ ሰገደ፡፡ (ሉቃ.፩፥፴፱-፵፩)

በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈው ኤልሣቤጥ የመውለጃዋ ጊዜ በደረሰ ጊዜ ወንድ ልጅን ወለደች፡፡ መውለዷን የሰሙ ዘመዶቿና ጎረቤቶቿም ደስ ተሰኙ፤ ልጁንም ስምንት ቀን በሞላው ጊዜ ሊገረዙት መጡ፤ ስሙንም በአባቱ ስም ዘካርያስ ብለው ሊሰይሙት ወደዱ፤ ነገር ግን እናቱ ዮሐንስ ተብሎ መጠራት እንዳለበት ተናገረች፡፡ ሆኖም ግን ከዘመዶቿ መካከል ስሙ ዮሐንስ የሚባል ባለመኖሩ አባቱ እንዲወስን ካህኑ ዘካርያስን በጠየቁት ጊዜ መናገር የተሣነው ዲዳ ነበርና ብራና ለምኖ ስሙ ዮሐንስ ይባል ብሎ ሲጽፍ ሁሉም ተደነቁ፤ በዚያን ጊዜም የዘካርያስ አንደበት ተፈታ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነ፡፡ (ሉቃ.፩፥፶፪-፷፬)

ካህኑ ዘካርያስም መንፈስ ቅዱስ በመላበት ጊዜ እንዲህ ብሎ ትንቢት መናገር ጀመረ፤  ‹‹ይቅር ያለን፥ ለወገኖቹም ድኅነትን ያደረገ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ከባርያው ከዳዊት ቤት የምንድንበትን ቀንድ አስነሣልን፤ ከጥንት ጀምሮ በነበሩ በቅዱሳን በነቢያት አፍ እንደ ተናገረ፡፡ ከጠላቶቻችን እጅ፥ ከሚጠሉንም ሁሉ እጅ ያድነን ዘንድ፤ ቸርነቱን  ከአባቶቻችን ጋር ያደርግ ዘንድ፤ ቅዱስ ኪዳኑንም ያስብ ዘንድ፤ ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሐላ ያስብ ዘንድ፤ ከጠላቶቻችን እጅ ያድነን ዘንድ ያለ ፍርሃት፥ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ በዘመናችን ሁሉ እንድናመልከው ይሰጠን ዘንድ፤ አንተም ሕፃን፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፡፡ መንገዱንም ትጠርግ ዘንድ በፊቱ ትሄዳለህና፡፡ ኃጢአታቸው ይሰረይላቸው ዘንድ መድኃኒታቸውን እንዲያውቁ ለአሕዛብ ትሰጣቸው ዘንድ፤ ከአርያም በጎበኘን በአምላካችን በይቅርታውና በቸርነቱ፤ በጨለማና በሞት ጥላ ለነበሩት ብርሃኑን ያሳያቸው ዘንድ፥ እግሮቻቸውንም ወደ ሰላም ጎዳና ያቀና ዘንድ ወጣ፡፡››(ሉቃ.፩፥፷፰-፸፱)

ከዚህም በኋላ ንጉሡ ሄሮድስ ጌታችን ኢየሱስን ለመግደል ይፈልገው ስለነበር የተወለደ ወንድ ሁሉ እንዲገደል በወሰነው መሠረት ሕፃኑ ዮሐንስን እንዲገድሉት ጭፍሮችን ወደ ካህኑ ዘካርያስ ላከ፤ በዚህም ጊዜ አባቱ በትክሻው ተሸክሞ ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ በመሠዊያው ጠርዝ ላይ ካኖረው በኋላ ወታደሮቹን መውሰድ ከቻሉ ከዚያ እንዲወስዱት ነገራቸው፡፡ ከመቅጽበትም የእግዚአብሔር መላክ ነጥቆ ወደ በረሀ ወሰደው፡፡ ወታዳሮቹም ሕፃኑን ባጡት ጊዜ አባቱ ዘካርያስን ገደሉት፡፡ ዮሐንስም አድጎ በሀገረ እስራኤል እስከተገለጠበት ጊዜ በበረሀ ኖረ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ሴቶች ከወለዱአቸው መጥምቁ  ዮሐንስን የሚበልጠው የለም›› ብሎ የመሠከረለት ነቢይ፣ ሐዋርያ፣ ሰማዕት ነው፡፡  (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ ፴ ገጽ ፬፻፸፱- ፬፻፹)

የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አማላጅነት እና ተራዳኢነት አይለየን፤ ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፤ አሜን።