‹‹ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ
አታድርጉ›› (ፊልጵ. ፪፥፫)

መምህር ቢትወደድ ወርቁ
መስከረም ፳ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ወገንተኝነትን አሉታዊ በሆነ መልኩ ስንገነዘበው ለወገን፣ ለዘመድ፣ ለጓደኛ፣ ወይም የራስ ለሚሉት አካል ማድላት ነው፡፡ አያሌ ተቋሟት ዓላማና ግቦቻቸውን በሚገልጡበት ጊዜ ከሚያስቀምጡዋቸው ዕሤቶቻቸው መካከል አንዱ አለማዳላት ነው፡፡ አለማድላት ደግሞ ወገንተኝነትን የሚኮንንና ፍጹም ተቃራኒው የሆነ ታላቅ ዕሤት ነው፡፡ ወገንተኝነት ወገኔ ለሚሉት አካል ጥፋት ሽፋን በመስጠት ይገለጣል፡፡ ቆሜለታለሁ ለሚሉትም አላግባብ ቅድሚያ መስጠት ሌላኛው መገለጫው ነው፡፡

ወገንተኝነት ሀገራችንን ብሎም ዓለማችንን ወደ መታወክ የከተተ ሁነት ለመሆኑ ዛሬ ከምናየው ክስተት በላይ ምስክር የለም ብለን መናገር እንችላለን፡፡ አለአግባብ የሆነ ወገንተኝነት ዐይነ ልቡናን ያሳውራል፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተያዘባትና ለፍርድ በቀረበበት በዕለተ ዐርብ ንጹሑን በግ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል እንዲሰቀልና ወንበዴው በርባንን ነፃ እንዲወጣ ያደረገው ጭፍን ወገንተኝነት ነው፡፡ ወገንተኝነት ምን? ከሚለው ይልቅ ማን? የሚለው ላይ ብቻ እንድናተኩር ካደረገን ከእግዚአብሔር ያጣላናል ከእውነትም ጎዳና እንድንወጣ ያደርገናል፡፡ በመሆኑም አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት ለወገኔ ከሚል አስተሳሰብ ራሳችንን እንድንጠብቅ ያስገነዝቡናል፡፡ ይህን በተመለከተ ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስተምረን ‹‹ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ›› በማለት አስጠንቅቆናል፡፡ መጽሐፍ በወገንተኝነት እንዳንያዝ እንዲህ ቢያስተምረንም ታላቁን መጽሐፍ መመሪያችን ብለን የተቀበልን ክርስቲያን ሳንቀር ብዙዎቻችን ዛሬ በወገንተኝነት በሽታ ታመናል፡፡ (ማቴ.፳፯፥፳፩፣ፊልጵ.፪፥፫)

ወገንተኝነት የእውነት ጠላት የፍትሕም እንቅፋት ነው፡፡ የክርስቲያን ወገንተኝነቱ ለእውነት እንጂ ለሌላ ሊሆን አይገባም፡፡ የገዛ ወገንህ እንደበደለ እንዳጠፋና ችግር እንደፈጠረ እያወቅህ በሌላው ላይ የምትፈርድ፣ ሌላውንም ጥፋተኛ የምታደርግ፣ ጥፋቱንም ቢገልጡ ሰዎች ላይ በቁጣ የምትነሣሣ ከሆንክ ክርስቲያን ነኝ ብለህ እንዴት ታምናለህ? ወገንተኝነታችን በደምና በሥጋ ዝምድና፣ የቆምንላቸው ወገኖች በሚሰፍሩልን ጥቅማ ጥቅም፣ በሚከፍቱልን የሥራና ሌሎች ዕድሎች፣ በወጣንበት መንደርና ጎጥ ላይ የሚመሠረት ከሆነ ከእውነት ጋር ያላትመናል፡፡ ወገንተኝነታችን ለእውነት ሲሆን መርማሪዎች እንሆናለን፤ ግራ ቀኝም ለማየት ዕድል እናገኛለን፡፡ ከዚህም ባሻገር ለእውነት ስንወግን ማን ላይ ምን ተከሰተ? ከሚለው ወጥተን ለምን ተከሰተ? ወደሚል የፍትሕ በርን ወደሚከፍት ጥያቄ እንመጣለን፡፡ ለእውነት ሳይሆን ወገኔ ለሚለው አካል የሚወግን ሰው ወገኔ የሚለው አካል የሚፈጽመውን ስሕተት አይመለከትም፤ መመልከትም አይፈልግም፡፡ በሌላው ስሕተት ለመፍረድ ሌላውን ለመወንጀል ፈጣን የወገኑን ስሕተት በመሰወር ግን ራሱን እንደ ፍትሐዊና ‹‹ከባቴ አበሳ፣ በደልን በፍቅር የሚሸፍን›› አድርጎ የሚቆጥርና ወገኔ ያለውን አካል ጥፋት ለማረም እንኳን ተነሣሽነት የሌለው ነው፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍትና በታሪክ ውስጥ ከእውነት ጎን በመቆም ወላጆቻቸውን፣ ወንድሞቻቸውን፣ ባልንጀራዎቻቸውን የገሠፁ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህም ለወገንተኝነት ጀርባቸውን ከሰጡ ደገኛ ሰዎች የጥቂቶቹን ታሪክ እዚህ ማንሣት ተገቢ ይሆናል፡፡

ሊቀ ነቢያት ሙሴ
ሊቀ ነቢያት ሙሴ ትውልዱ በግብፅ ዕድገቱ በፈርዖን ቤተ መንግሥት ነበር፡፡ ሙሴ ያደገውም የመፃተኛ ልጅ ሆኖ ሳይሆን በንጉሥ ቤተ መንግሥት የንጉሥ የልጅ ልጅ ተብሎ በልዩ እንክብካቤና በቅንጦት ነው፡፡ አሳዳጊው የነበረችው እናቱም ከልጅነቱ ጀምሮ ማንነቱንና ወገኖቹ እስራኤላውያን በግብፅ ስለሚደርስባቸው መከራ ስለሚፈጸምባቸውም ግፍ በየዕለቱ ትነግረው ነበር፡፡ እናቱ ለሙሴ ትነግረው የነበረው ነገር እውነት እንጂ ሐሰት አልነበረም፡፡ ያየችውን እውነት በእውነትነቱ ልክ እንጂ እውነቱን ከሐሰት ጋር ቀላቅላ፤ የተከሰተውን አጋንና ጨማምራና አሰማምራ አልነበረም፡፡ ከልጅነቱም ጀምራ ወገንተኝነቱ በሥጋ ዝምድናና በጓደኝነት ወይም በሌላ ዓይነት ግኑኝነት ሳይሆን እውነትን መሠረት አድርጎ ሊሆን እንደሚገባው ታስተምረው ነበርና ሙሴ ካደገ በኋላ የቤተ መንግሥትን የቅንጦትና ምቾት ኑሮ፣ ባለጠግነት፣ የንጉሥ የልጅ ልጅነት ጠልቶ ለእውነት ቆመ፡፡ ሙሴን ካደገ በኋላ ከወገኖቹ ጎን እንዲቆም ያደረገው ጭፍን ያለ ወገንተኝነት ሳይሆን ከወገኖቹ ጋር የነበረው እውነት ነበር፡፡ እውነቱም የግብፃውያን መጠን አልባ ግፍ ሠሪነትና የወገኖቹ የእስራኤላውያን የግብፃውያን ግፍና መከራ ሰለባ መሆን ነበር፡፡ ፍትሐዊ ስንሆን ከሰዎች ጀርባ ላለው እውነት እንጂ ሌላ ለምን እንቆማለን? ሙሴ ለወገኖቹ የቆመው በዘረኝነት ታውሮ፣ በጎጠኝነትና በመንደርተኝነት ሰክሮ፣ በሰፈር ልጅነት ነሁልሎ፣ በአንድ ዓይነት ቋንቋ ተናጋሪነት ታጥሮ ሳይሆን እውነትና ፍትሐዊነት የተባሉ ሁለት በትሮችን ተመርኩዞ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ሙሴ በሥጋ ወገኖቹ የሆኑ እስራኤላውያን እውነት ባይኖራቸውና ግፍ ባይፈጸምባቸው ይህንም እውነት እግዚአብሔር ባወቀ ከእናቱ ባይማር ኖሮ ወገኖቹ ስለሆኑ ብቻ ከጎናቸው ባልቆመም ነበር፡፡ ይህን የሙሴን እውነትንና ፍትሐዊነትን መሠረት ያደረገ ወገንተኝነት አስመልክቶ ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስተምር፣ ‹‹ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፡፡ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቶአልና፡፡ የንጉሡን ቁጣ ሳይፈራ የግብፅን ሀገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና›› በማለት ተናግሮዋል፡፡ ሙሴን ከወገኑ ጋር እንዲቆም ያደረገው ከእውነተኛው እምነት የሚመነጩ ፍትሐዊነትና እውነት እንጂ የቆዳ ቀለም መቀራረብ፣ የቋንቋ አንድነት፣ የሰፈር ልጅነት፣ ከአንድ ጎሳ መወለድ፣ በአንድ አካባቢ ማደግ አይደለም ያልነውም በዚህ ምክንያት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ የወገንተኝነት ሚዛናችን እንደ ሙሴ እውነት ይሁን! ያን ጊዜ ሙሴን ሆነን ሰዎችን ከጥፋት ወደ ልማት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከመሞት ወደ መኖር፣ ከመተላለቅ ወደ መተሳሰብ፣ ትርጉም ከሌለው ጦርነት ትርጉም ወዳለው ኅብረትና ሰላም ማሻገር እንችላለን፡፡ (ዕብ.፲፩፥፳፬-፳፯)

ወልደ ሳኦል ዮናታን
ዮናታን ሳኦል ወላጅ አባቱ ሲሆን ዳዊት ደግሞ ጓደኛው ነው፡፡ ከዝምድና አንጻር ናታን ከጓደኛው ይልቅ አባቱ ይቀርበዋል፡፡ ዳዊት በታዳጊነት ዕድሜው ሳኦል ንጉሥ በነበረበትና ይመራት የነበረችው እስራኤል በፍልስጥኤምና ይመራት በነበረው ዕብሪተኛ በጎልያድ ዛቻና የጥፋት እልህ ስጋት ውስጥ በገቡበትና ራሱ ንጉሥ ሳኦልም በተጨነቀበት ጊዜ መጥቶ ጎልያድን አሸንፎ ከስጋትና ከሽንፈት አድኗቸው ነበር፡፡ (፩ኛሳሙ.፲፯፥፩)

ይህን ብቻ ሳይሆን ንጉሥ ሳኦል በክፉ የሰይጣን መንፈስ ይሠቃይ በነበረበት ጊዜ ይኸው ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት መጥቶ በገና እየደረደረ ከክፉ መንፈስ ያድነው ነበር፡፡ ሳኦል ዳዊትን ባሳደደውና እግዚአብሔር በእጁ ጥሎለትና ወዳጆቹ ግደለው ባሉት ጊዜ እንኳን ሊገድለው ሲችል ‹‹እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን አላነሣም›› ብሎ ራርቶ ትቶታል፡፡ ሳኦል ይህን ሁሉ መልካም ባደረገለት በዳዊት ላይ በጠላትነት ተነሣበት አላግባብም ይገደሉት ዘንድ መልእክተኞችን ላከ፡፡ ይህን የተመለከተ የሳኦል ልጅ ዮናታን የሳኦል የአባትነት ወገንተኝነት ሳያሸንፈው ለእውነት ቆመ፡፡ ተገቢ ያልሆነ ወገንተኝነትንም አሸነፈ፡፡ አባቱንም ‹‹እርሱ (ዳዊት) አልበደለህምና ሥራውም ለአንተ እጅግ መልካም ሆኖአልና ንጉሡ ባሪያውን ዳዊትን አይበድለው፤ ነፍሱንም በእጁ ጥሎ ፍልስጥኤማዊውን ገደለ÷ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ሁሉ ታላቅ መድኃኒት አደረገ፤ አንተም አይተህ ደስ አለህ፤ በከንቱ ዳዊትን በመግደልህ ስለምን በንጹሕ ደም ላይ ትበድላለህ?›› በማለት በአባቱ በንጉሡ በዳዊት ፊት በመቆም እውነቱን መሰከረ፡፡ (፩ኛሳሙ.፲፮፥፩፣፳፬፥፩-፳፬፣፲፱፥፬)

የሳኦል ልጅ ዮናታን እውነትን መርሕ ያደረገ ጭፍን ወገንተኝነትን የተጠየፈ ነውና ለወገኔ ከሚለው አስተሳሰብ ወጥቶ እውነትን ተናገረ፡፡ በዚህም አባቱን ከስሕተት ጓደኛውንም ከመገደል አዳነ፡፡ ዮናታን የቆመው ለዳዊት ሳይሆን ዳዊት ስለያዘው እውነት ነው፡፡ በመሆኑም ዮናታን በሞተ ሥጋ በተወሰደ ጊዜ ዳዊት ‹‹ወንድሜ ዮናታን ሆይ÷ እኔ ስለአንተ እጨነቃለሁ፤ በእኔ ዘንድ ውድህ እጅግ የተለየ ነበረ፤ ከሴት ፍቅር ይልቅ ፍቅርህ ለእኔ ግሩም ነበረ›› በማለት ቅኔ እየተቀኘ አልቅሶለታል፡፡ (፪ኛ.ሳሙ.፩፥፳፮)

ፈያታዊ ዘየማን
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዐርብ በሁለት ወንበዴዎች መካከል ተሰቀለ፡፡ በዚህን ጊዜ በግራውና በቀኙ የተሰቀሉት ሁለቱ ወንበዴዎች የሐሳባቸውን ይናገሩ ነበር፡፡ በግራ የተሰቀለው ወንበዴ በሞት ደጃፍ ቆሞ እንኳን ክፉ ከመናገር የከለከለው አንዳች ማስተዋል አልነበረውም፡፡ በዚህም ምክንያት ጌታችንን እየነቀፈና እያሽሟጠጠ ‹‹አንተስ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን›› ብሎ ነበር፡፡ በቀኙ የተሰቀለውና የረጅም ጊዜ ጓደኛው ጥጦስ ግን የባልንጀርነት ወገንተኝነት ስሜት ሳያንበረክከው፣ በይሉኝታም ሳይሸነፍ የረጅም ጊዜ ጓደኛውንና የውንብድና ሥራ ባልደረባውን ‹‹አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? ስለአደረግነው የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም›› በማለት ገሠፀው፡፡ (ሉቃ. ፳፫፥፴፱-፵፩)
ፍትሐዊነትን ከሚሰብኩ፣ ወገንተኝነትን ከሚያወግዙ፣ ፍትሕም ከሚጠበቅባቸው አካላት ወገንተኝነት ነግሦ ፍትሐዊነት ከወንበዴ ዘንድ ሲገኝ በእውነት ያስገርማል፡፡ ለሰዎች ለተቋማትና ለቡድኖች ሳይሆን ለያዙት እውነት መቆም እንደሚገባ የታላቁ ሰው የዮናታንና የዚህ የቀኙ ወንበዴ (ፈያታዊ ዘየማን) ታሪክ ያስተምረናል፡፡ ወገንተኝነትን ስናስወግድ የሰዎች ግርማ፣ የምጣኔ ሀብት አቅም፣ ፖለቲካዊ ኃያልነት፣ የአሻጥረኝነታቸው አደገኛነት፣ የተከታዮቻቸው መብዛትና ስድብ አያስፈራንም፡፡ በእኛ እውነትን በተላበሰ ወገንተኝነት ምክንያት በወገናችን፣ በሀገራችንና በራሳችንም ላይ ሊመጣ የሚችለውንም ጥፋት እናስቀራለን፡፡

አቤቶ ፋሲል
በዐሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በንጉሥ ዓፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት ንጉሡ ዓፄ ሱስንዮስ በሮም ካቶሊካውያን በእነ አልፎንሱ ሜንዴዝ ተንኮልና ሤራ ተጠልፈው ‹‹ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ሃይማኖት ይርከስ፤ የሮም ካቶሊካዊ ሃይማኖት ይንገሥ›› የሚል ዐዋጅ ዐወጁ፡፡ ‹‹አልቀበልም የአባቶቼን ሃይማኖት አልተውም!›› ያለውንም እስከ ስምንት ሺህ የሚጠጋ የመናገሻ ከተማቸውን የጎንደርን ገበሬ በግፍ አስፈጁ፡፡ ይህን የንጉሡን ዕብሪትና ዐውቅልሃለሁ ከአብራካቸው የተከፈሉት ልጃቸው አቤቶ ፋሲል አልተቀበሏቸውም፡፡ አቤቶ ፋሲል የአባትነት ወገንተኝነትና ዝምድና ሳይዛቸው የአባታቸውን የግፍ ሥራ ተቃወሙ፡፡ አባታቸውም ከዚህ ክፉ ሥራቸው እንዲመለሱ በሕዝቡም ላይ ከሚያደርጉት የግፍ ሥራ እጃቸውን እንዲሰበስቡ አሳሰቡ፡፡ በዚህም ሊመጣ ያለን አያሌ ጥፋት መልሰዋል፡፡ የምትሠራበት ተቋም፣ ወንድምህ፣ እኅትህ፣ ልጅህ፣ ዘመድ አዝማዶችህ የተገፋሁ የተበደልኩ ክስና አቤቱታ ይዘው ሲመጡ ወገንተኛ ሳይሆን ፍትሐዊ ሆነህ ጉዳዩን ተመልከት፡፡ ፍትሐዊ ስትሆን ዐይነ ልቡናህ የንሥር ዐይን ይሆናል፡፡ አላግባብ አጥፍተው ተበደልን የሚሉ ወገኖችህንም ከስሕተትና ከጥፋት ትታደጋለህ፡፡ ወገንተኝነታችን ለእውነት ሲሆን ፍትሐዊነት ይነግሣል፡፡ እግዚአብሔርንም እንመስለዋለን፡፡ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ፍትሐዊ አምላክ ነው፡፡ ከሰማያት የወረደው ከእመቤታችን ተወልዶ ያዳነው የተወሰነ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ሳይሆን ሰውን ሁሉ ነው፡፡ ፀሐይ የሚያወጣው፣ ዝናብ የሚያዘንበውም ላመኑት ብቻ ሳይሆን ላላመኑትም ጭምር ነው፡፡ ንስሓን የሰጠው፣ መንግሥተ ሰማያትን ያዘጋጀው፣ ሥጋውን የቆረሰው ደሙንም ያፈሰሰው፣ በዚህም ወገኖቼ ያለው ጥቂቶችን ሳይሆን ዓለምን በሙሉ ነው፡፡ ሲፈርድም ሚዛኑ ማነህ? ሳይሆን ‹‹አይቴ ነበርከ- የት ነበርክ፤ ምንተ ገበርከ- ምን ሠራህ?›› በሚለው ነው፡፡ (የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ አባ ጎርጎርዮስ ገጽ ፶፯)

መልካም ከሠራን ይፈርድልናል ክፉ ከሠራን ይፈርድብናል፡፡ ሰው ከፍ ሲልም ክርስቲያን ከሆንን ለእውነት እንጂ ወገኔ ለምንለው አካል አንቆምም፡፡ በዓለም በሚደረጉ የእርስ በእርስ መጠፋፋቶችና ጦርነቶች ላይ የራሳችንን ጥናት አድርገን ፍትሐዊ ዘገባ እናቀርባለን የሚሉና ገለልተኞች ነን የሚሉ አያሌ ዓለም አቀፍ ተቋማት ‹‹ከወገንተኝነት የጸዳ ዘገባችን ይኸው›› ይበሉ እንጂ ወገንተኝነታቸው ለእውነት ሳይሆን ለገዛ ራሳቸው ጥቅም ነው፡፡

አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ጭፍን ከሆነና እውነትና ፍትሐዊነት ከጎደሉት ወገንተኝነት በቸርነቱ ይሰውረን፤ አሜን፡፡