ሁሉን መርምሩ መልካሙን ያዙ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአምልኮተ እግዚአብሔር ከሦስት ሺሕ ዘመን ላላነሰ የቆየውን የኢትዮጵያውያንን የሃይማኖት ሕይወት ስትመራና አሁንም በመምራት ላይ ያለች ከመሆኑ አንጻር ዘርፈ ብዙ የጥናትና ምርምር ሥራ እንዲደረግባት የምትጋብዝ ናት፡፡
ቤተክርስቲያናችን በታሪኳ ከፍተኛ የሥነ-ሕንፃና ሥነ-ጽሑፍ፣ የፍልስፍና፣ የሕግና የአስተዳደር፣ የዘመን አቆጣጠር፣ ከፍተኛ የማኅበራዊ ግንኙነትና የባህል መሠረት ናት፡፡

ቤተክርስቲያናችን በቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርትና ቀኖና፣ በትምህርተ ሃይማኖት፣ በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን፣ በትውፊትና ታሪክ በኩልም ለጥናትና ምርምር የሚጋብዝ ከፍተኛ ክምችት አላት፡፡ የዚህ ክምችት ኃይልም ቤተክርስቲያኒቱን የሀገሪቱ የጥናትና ምርምር ዒላማ አድርጓታል፡፡ በሀገራችን ያሉ የኢትዮጵያ ጥናት ላይ የሚያተኩሩ ተቋማት የምርምር ትኩረት በአብዛኛው በቤተ ክርስቲያናችንና ባሏት ዘርፈ ብዙ ቅርሶች ላይ እንዲሆንም አስገድዷል፡፡

በተለይም ሀገራችንና ቤተክርስቲያናችን በታሪክ ዘመን ውስጥ ብዙ ወርቃማ ዘመናትን ቢያሳልፉም፤ በዮዲት፣ በግራኝ፣ በዘመነ መሳፍንት፣ በጣሊያንና በእርስ በእርስ ጦርነቶች የተፈጠረው ምስቅልቅል በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብት ቅብብሎሽ ላይ የፈጠረው ክፍተት ለበርካታ ሊቃውንት የጥናት ጉዳዮች ምንጭ ነው፡፡ በሃይማኖት ትምህርት በኩልም የአይሁድ፣ የካቶሊካውያን፣ የቅባትና የጸጋ ሌሎች የሥጋ ፍልስፍናዎችና የሟርትና ጥንቆላ ሥራዎች በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያና ውስጥ ሆነው እውነተኛውን አስተምህሮ ሲፈታተኑት በመኖራቸው እነርሱን በመከላከል በኩል የተደረጉ ተጋድሎዎችና ያረፉ ተጽዕኖዎች ለጥናት የሚጋብዙ አንኳር ጉዳዮች ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ የጥናትና ምርምር ሥራን ዘመናዊ ከማድረግና የራሳችንን ታሪክ ባህልና አጠቃላይ ገጽታ ከማጥናት አንጻር ሚና የነበራቸው ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ፣ በሃይማኖትም ኦርቶዶክሳውያን ያልሆኑ ወገኖች ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ ተመራማሪዎች በጥናቶቻቸው በሚሰጧቸው ድምዳሜዎች ኢትዮጵያውያን ጥያቄ እንዲያነሡባቸው፤ በጥርጣሬም እንዲታዩ አድርጓል፡፡ ከኢትዮጵያውያን ውጪ የሚደረጉ ጥናቶች ላይ ሁሉ ጥርጣሬ ማሳረፍ አግባብ ባይሆንም የኢትዮጵያውያን የጥናት ተሳትፎ በሚፈለገው ልክ ባለመሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በኢትዮጵያ ሊቃውንት ትኩረት ማግኘት እንዳለባቸው ግን ሁሉንም ያግባባል፡፡
 
መጽሐፍ ሁሉን መርምሩ መልካሙን ያዙ እንዳለ በሊቃውንቱ መካከል በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የገለጻ ወይም የሐሳብ ልዩነት ሲፈጠር ያለ ግጭት ለመፍታት አንድነትንም ለማጽናት በጥናትና ምርምር ሥነ-ምግ ባር ላይ ተመሥርተው የሚዘጋጁ ጥናትና ምርምሮች ፍቱን መድኃኒቶች ናቸው፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን በራሳቸው ፈቃድና በቅጥረኝነት ተነሣሥተው የቤተክርስቲያናችንን አዋልድ መጻሕፍት፣ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን፣ ታሪክና ትውፊት ለሚያብጠለጥሉ ከዚያም በግርግር ቤተክርስቲያንን አንድነቷን ለማናጋት ለሚጥሩ የተሐድሶ መናፍቃን ልጓም ያበጃል፡፡ ጠንካራ የጥናትና ምርምር ተቋማት ለቤተ ክርስቲያናችን የሊቃውንት ጉባኤም ለቅዱስ ሲኖዶስ አገልግሎት ግብዓት ከማቅረብ አንጻርም ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ በመሆኑም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን፣ ዘመናዊ ትምህርትንም የተከታተሉ ክርስቲያን ምሁራን ላይ የተመሠረቱ የምርምር ተቋማት መመሥረት እንዳለባቸው ማኅበራችን የጸና እምነት አለው፡፡ ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት ጥናትና ምርምር ጊዜው የሚጠይቀውና የቤተ ክርስቲ ያናችንን አንድነት በሀገራችንም ውስጥ ያላትን ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እንድትችል አዎንታዊ ሚና እንዳለው ተገንዝበው አስፈላጊውን ሁሉ ሊፈጽሙ ይገባል እንላለን፡፡

የቤተክርስቲያን አስተዳደርም የጥናትና ምርምር ተቋማትን መሥርተው ለመንቀሳቀስ ለሚፈልጉ የክር ስቲያን ወገኖች ምቹ ሁኔታ መፍጠርና እነርሱን የሚያስተናግድ አሠራርና መዋቅራዊ ሁኔታ ማመቻቸት ይገባዋል፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነትና አህጉረ ስብከቶች ጥናቶች እየተዘጋጁ የሚቀርቡባቸው ጉባኤዎችን በተወሰኑ ጊዜዎች ሊያዘጋጁ ይገባል፡፡ ጥናትና ምርምር የራሱን የአስተዳደሩን የመፈጸም አቅም የበለጠ የሚያጠናክር በመሆኑ ተግባሩን መደግፍ ብልህነት ነው፡፡ በጥንቃቄና በብዙ ሊቃውንት የተዘጋጁ የጥናት ውጤቶችም ጥቅም ላይ እንዲውሉ መጣር አለበት፡፡ ጥናትና ምርምር ተቋምን መመሥረት ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ቢያንስ ለጥናትና ምርምር ተግባር የሚያግዙ ቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ መዛግብትና ሙዚየሞችን በየደረጃው ማደራጀትና ማስፋፋት ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም፡፡

ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንና ሌሎች ክርስቲያን ምሁራን ይህንን ተግባር ለመደገፍ ያሉበት የዕውቀት ደረጃና ሙያ ግድ ይላቸዋል፡፡ ሊቃውንት ያለጥናትና ምርምር ተቋም ዕውቀታቸውን ማዳበር፣ ዕውቀታቸውን ማካፈል አዳዲስ መረጃዎችንም መስጠት አይችሉም፡፡ በመሆኑም ጥናትና ምርምር ተቋማት እንዲስፋፉ ግፊት ከማድረግ ጀምሮ የሚመሠረቱበትን ብልሀት፣ ከተመሠረቱም በኋላ የሚጠናከሩበትን በዘላቂነት የሚሠሩበትን መላ በመዘየድ፣ በጥናትና ምርምር ሥራዎች በመሳተፍ የጥናትና ምርምር ሥራዎችንም በማስተዋወቅ ሰፊ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል እንላለን፡፡

በአጠቃላይ ሕዝበ ክርስቲያኑ የጥናትና ምርምር ተቋማትን ከመመሥረት ጀምሮ እስከ ማጠናከር ድረስ በሚደረገው ርብርብ በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸው፣ በዕውቀታቸውና አስፈላጊውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይገ ባቸዋል፡፡ ቤተክርስቲያናችን ካላት ክብር፣ ታሪክና ቅርስ አንጻር አንድ እንኳን ጠንካራ የምርምር ተቋም ማጣቷ ቆጭቶን አስፈላጊውን ሁሉ ልንፈጽም ይገባል፡፡ ቤተክርስቲያናችን አሉባት የምንላቸውን ችግሮች ሁሉ ለመፍታት ጥናትና ምርምር ያለውን ወሳኝ ሚና በመረዳት የክርስቲያን ወገን ሁሉ ሊረባረብ ይገባዋል፡፡ ቅርሶቻችን እየጠፉ፣ መጻሕፍቱ እየተበረዙ፣ እየተመዘበሩ፣ በአስተዳደራዊ ችግሮች እየታመስን ባለንበት ወቅት፤ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች የቤተ ክርስቲያን አስትዋጽኦ ተፈላጊ በሆነበት በዚህ ጊዜ የጠራና የነጠረ ሐሳብ ይዘን መራመድ ካልቻልን የሚያ ጋጥመን ፈተና ቀላል አይሆንም፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራትም ባሉበት ደረጃ ከቤተ መጻሕፍት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የምርምር ተቋም ድረስ በቤተ ክርስቲያናችን የማስፋፋት ርእይ ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳንም ይህንን ወሳኝ ተግባር ከመፈጸም አንጻር አርአያ ለመሆን ጥረት እያ ደረገ ይገኛል፡፡ ለሚያደርገው ጥረትም ማሳያ የሚሆን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ጥናት መጽሔት /Journal/ በቅርቡ ማውጣቱ የዚህን ተግባር ወሳኝነት ለማጉላት ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም የሚመለከታቸው ወገኖች በየደረጃው የጥናትና ምርምር ተቋማትን ለጥናትና ምርምር መመሥረት አስተዋጸኦ የሚያደርጉ ሌሎች የመረጃ ማእከላትን ማቋቋም ይገባቸዋል እንላለን፡፡