‹‹ሁሉን መርምሩ፤ መልካሙን ያዙ›› (፩ተሰ.፭፥፳)

በዮሐንስ ተመስገን  

መስከረም ፯ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤ ሁሉ ግን አይጠቅምም›› ብሎ እንደተናገረው  በዚህ ዓለም ያለውን ቢፈቅደውም ሁሉም የሚጠቅም ግን አይደለም፡፡ የሰው ልጅ በተፈጠረባት ምድር ላይ በተፈጥሮ ማለትም እግዚአብሔር አምላክ በፈጠረለት ነገሮችን ሁሉ እንዲጠቀም ነገር ግን መልካሙን ዐውቆና የተፈቀደለትን ወይም የሚጠቅመውን ነገር ለይቶ እንዲይዝ ሐዋርያው አስተምሮናል፡፡ (፩ቆሮ.፲፥፳፫) ስለዚህም እነዚህን ነጥቦች ልብ ማለት ይገባል፦

ሀ. ፈቃዱ ለእግዚአብሔር ለ. ስምረቱ ለእግዚአብሔር

ሀ. ፈቃዱ ለእግዚአብሔር

በዚህ ዓለም ያለውን ሕይወት የሚሰጠንንም ይሁን ለሞት የሚዳርገንን የኃጢአትም ተግባር እንድንፈጽም ምርጫ አለን። ይኸውም በምን ይታወቃል ካልን የፍጥረትን ነገር በሚናገረው መጽሐፍ መልካምና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ እንዳይበላ አዝዞ ‹‹ከበላህ ግን ሞትን ትሞታለህ›› በማለት የሚሞትበትንና የሚድንበትን የሕይወት መንገድ በራሱ እንዲመርጥ ነጻነት ሰጥቶታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ሁሉ ተፈቅዶልኛል እንዳለው ማለት ነው፡፡ (ዘፍ.፪፥፲፯፣፩ቆሮ.፲፥፳፮)

ለ. ስምረቱ ለእግዚአብሔር

ይህ ማለት ደግሞ እግዚአብሔር የሚወደው ማለት ነው። በዘፍጥረት መጽሐፋችን እግዚአ ዓለማት አቤልንና ቃየልን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ፈቀደላቸው፤ የሁለቱንም ግን አልወደደውም ነበር:: መርጦ ተቀበለ እንጂ፤ ንዋይ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ሁሉ ተፈቅዶልኛል›› ካለ በኋላ ‹‹ሁሉ ግን አይጠቅመኝም›› ያለው ነጻ ፈቃዴን ተጠቅሜ  የማደርገው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ አይሆንም ማለቱ ነበር። (ዘፍ. ፬፥፬)

አስተውሉ! በዚህ ዓለም ሁሉ ተሰጥቶናል። ሁሉ ግን እንደ ሀሳቡ ወይም እንደ ሚወደው ካልሆነ ይፈረድብናል። በመንገዳችን መልካምና ክፉ ሊሆን ይችላል። ‹‹እሳትና ውኃ ቀርቦልሃል፤ ወደመረጥክው እጅህን ስደድ›› በመረጥንበት ጎዳና እንድንጓዝ ምርጫ ተሰጥቶናል።

በምንኖርባት ዓለም መጥፊያውም ሆነ መዳኛውም ከፊት ለፊታችን ነው። ባለንበት ቦታ ሁነን እግዚአብሔር የወደደውን እናደርጋለን ወይም እኛ የወደድነውን እናደርጋለን። የምንሠራቸውን ነገሮች ልንመረምራቸው ይገባል፤ በእግዚአብሔር የተወደደ መሆኑን ማለት ነው። ካልሆነ መጥፊያችንን እያደረግን መሆኑን ማወቅ አለብን።

የስልኮቻችን አጠቃቀም፣ አዋዋላችን፣ አለባበሳችን፣ አመጋገባቸን፣ አነጋገራችን፣ ወዘተርፈ ሃይማኖት እንደሚፈቅድልን ወይስ እንደእኛ ደስታ የሚለውን ሊመረመር ይገባል። እግሮቻችን ወደ ቤተ እግዚአብሔር ከሄዱ ስንት ጊዜ ሆናቸው? እጆቻችን ቅዱሳት መጻሕፍቱን የገለጡበት ጊዜስ? ዐይኖቻችን ከጉልላቱ ላይ መስቀሉን የተመለከትንበት ጊዜስ? አፋችን የእግዚአብሔርን ነገር የተናገርንበት ጊዜስ! ጆሯችን ቃለ እግዚአብሔር የሰማበት ጊዜስ? አንደባታችን (ጉሮሯችን) ቅዱስ ቁርባን የተቀበሉበት ጊዜስ? ሕዋሳቶቻችንን እንደተፈጠሩለት ዓላማ ያዋልንበት ጊዜ መቼ ነው?

ዛሬም በዐይኖቻችን ፊልምና መዳራት እያየንባቸው ነው? ካፋችንስ አስጸያፊና የክህደት ንግግሮች እስከ ዛሬ ይሰማሉ? መጽሐፍ በአንድ ሥፍራ እንዲህ ይላል ‹‹ሰውን የሚገድለው ወደ አፍ የሚገባ ሳይሆን ከአፍ የሚወጣ ነው። ጆሮዎቻችንስ አሁንም ዘፈን እየሰሙ ናቸው?  ግያዝን አስታወሳችሁት! መምህሩን የሚሰማ ደገኛ ደቀ መዝሙር ነበር። በዚህም በመምህሩ ጸሎት ዐይኖቹ ተከፍተው ስውራኑን ማየት ቻለ፤›› ግያዞች ልንሆን ይገባል። (፪ነገ.፮፥፲፮)

ኮምፒውተሮቻችንና ስልኮቻችንን ለጥፋት ነው ወይስ ለመልካም እየተጠቀምንባቸው ያለነው። አጋደልንባቸው ወይስ አስታረቅን፤ ቃለ እግዚአብሔር ሰማንባቸው ወይስ ኃጢአት።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን ለዲያብሎስ ግብር ማለትም ክፋት ዝሙት ርኩሰት ወይም ቅሚያን እንድናደርግ ከሚገፋፉን ተግባራት እራሳችንን ልንገታ ይገባል፡፡ ዓለም በኃጢአት ማዕበል በተጥለቀለቀችበት በዚህ ጊዜ በተለይም ሰው ሠራሽ የሆኑት የዘመናዊ ቁሶች፣ የመገናኛ አውታሮችና የአኗኗር ዘይቤዎች ወደ ዓለማዊ አስተሳሰብና ግብር የሚወስዱ በመሆናቸው እነዚህን አጥፊ ነገሮችን ለይተየን ማወቅና ከእኩይ ተግባራት መጠንቀቅ ከእኛ ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ ሰዎችን ከክብራቸው አዋርዶ ለጥፋት የሚዳርግበት ዋነኛ መሣሪያዎቹ በመሆናቸው በዓለማዊ ብልጭልታ እንዲሁም በሥጋዊ ድሎት ላለመታለል ልንጠንቀቅ ይገባል፡፡

ተወዳጆች ሆይ! መጀመሪያ ራሳችንን እንይ፤ እየኖርን ያለነው እንዴት ነው ብለን ዙሪያችንን እንመርምር፤ ክፉና መልካሙን እንለይ፤ የሚጣለውን እንጣል፤ የሚጨመረውን እንጨምር፤ እንደ እግዚአብሔር ሀሳብ የምንኖርበትን ጊዜ እንናፍቅ፤ ሁሉን መርምረን መልካምን እንያዝና ለቅዱስ ቁርባኑ እንብቃ።

ቸር እንሰንብት!