“ደቀ መዛሙርት የቤተ ክርስቲያን ደጀን ናቸው።” ሲሉ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ ተናገሩ።
ብፁዕነታቸው ይህን ያሉት የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ለሁለት ዓመታት ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት ባስመረቀበት ዕለት ነው።
ማኅበረ ቅዱሳን ያስገነባውና ለሀገረ ስብከቱ ያስረከበው ብቸኛው የጭሮ ደ/ሰ/ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አዳሪ አብነት ት/ቤት ነሐሴ 17/ 2018 ዓ/ም 22 ደቀ መዛሙርትን ለሁለተኛ ግዜ አስመርቋል።
በምርቃት መርሐ ግብሩ ተገኝተው ቃለ በረከት የሰጡት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ ‘’ ደቀ መዛሙርት ለቤተ ክርስቲያን ደጀን ናቸው’’ በማለት ተመራቂዎች ቤተ ክርስቲያን የጣለችባቸውን ኀፊነት እንደሚወጡ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ብፁዕነታቸው አያይዘውም ደቀ መዛሙርቱ ለዚህ ደረጃ ለመድረስ ብዙ ግዜና ፈተናዎችን አሳልፈው መሆኑን ገልጸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
የምዕራብ ሐረርጌ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ቆሞስ አባ ፍቅረ ዮሐንስ ብርሃኑ በበኩላቸው ተመራቂዎች በሀገረ ስብከቱ በሚገኘው አዳሪ አብነት ት/ቤት ላለፉት ሁለት ዓመታት ፊደለ ሐዋሪያና ወንጌለ ዮሐንስ ፣የዘወትር ጸሎት እና ውዳሴ ማርያም፣ መዝሙረ ዳዊት፣አንቀጸ ብርሃንና እና ይዌድስዋ፣ ሥርዓተ ቅዳሴ እና ሰዓታት ተምረው ለምርቃት መብቃታቸውን ተናግረዋል።
የአገልጋይ ካህናት እጥረት ባሉባቸው እና በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሥር ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ደቀ መዛሙርትን አስተምሮ ለአገልግሎት ማሠማራት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።
ተመራቂዎች ቤተ ክርስቲያንን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እንዲያገለግሉ ኀላፊነት የተጣለባቸው ሲሆን የተማሩበትን የምስክር ወረቀት ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ እንጦንስ ተቀብለዋል።
የደቀ መዛሙርቱ የምርቃት መርሐ ግብር የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እና የየመምሪያ ኀላፊዎች በተገኙበት መከናወኑን ለማወቅ ተችሏል።
መረጃው የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሚዲያ ክፍል ነው።
