በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

     

“ዮም ፍሥሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም፤ በማርያም ልደት ምክንያት ዛሬ ደስታ ሆነ!” (ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ)

በመምህር ብንያም

“አነ ጽጌ ገዳም ጽጌ ደንጎላት ዘውስተ ቄላት ወከመ ጽጌ ደንጎላት በማእከለ አስዋክ-እኔ የምድረ በዳ አበባ ነኝ በቆላ ውስጥ ያለ በሾህ መካከል የበቀለ የሱፍ አበባ ነኝ።” (መኃ.፪፥፩) ብሎ ነቢዩ ሰሎሞን እንደተናገረ ግንቦት አንድ ቀን በምድረ በዳ በአድባረ ሊባኖስ የበቀለችውን አማናዊት ንጽሕት የሱፍ ፣ የጽጌረዳ አበባ የሆነችውን በመዓዛዋ ጣዕም የዓለምን የኀጢአትን ሽታ ያስወገደችውን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ልደት እናከብራለን፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን አስቀድሞ በመንፈሰ እግዚአብሔር ተቃኝቶ በመዝሙሩ ፮፥፲ ላይ “መኑ ይእቲ ዛቲ እንተ ትሔውጽ ከመ ጎሕ ሠናይት ከመ ወርኅ ወብርህት ከመ ፀሐይ” (ይህቺ እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጐበኝ፣ እንደ ጨረቃ የተዋበች፤ እንደ ፀሐይም የጠራች፣ ዓላማ ይዞ እንደተሰለፈ ሠራዊት የምታስፈራ ማን ናት?) በማለት እንደ ፀሐይ የሞቀ፣ እንደ ጨረቃ የደመቀ፣ ንጽሕናዋና ቅድስናዋ የመልኳ ደም ግባት በነቢያት ትንቢት አስቀድሞ የተጐበኘላት የእውነት ፀሐይ የክርስቶስ እናት የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብርና ደም ግባቷን እንደተናገረ፤ በሊባኖስ ተራራ በግንቦት ፩ በተወለደች ጊዜ ፊቷ በእጅጉ ያበራ ነበር፤ መዓዛዋም ከሽቱ ሁሉ ይበልጥ ነበር፡፡ የእመቤታችን ዜና ልደት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ አይደለም ፡፡በብዙ ሕብረ አምሳል እና ትንቢት ሲነገርላት የመጣች ምልዕተ ምሥጢር ናት እንጂ፡፡

ይኸውም ልደቷ በሦስት ክፍል ተነግሮላታል ፡፡

ሀ. በልበ ሥላሴ 

“እግዝእትነ ማርያም ነበረት እምቅድመ ዓለም በኅሊና አምላክ-እመቤታችን ዓለም ሳይፈጠር አስቀድማ በአምላከ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር” ተብሎ ተነግሮላታል።  እግዚአብሔር ይህን ዓለም ሳይፈጥረው ግብሩን ያውቀው ነበር እና የሚድንበትንም ከፍጥረት አስቀድሞ  በኅሊናው ያውቅ ነበር። እንዲህ ሲባል ግን ማወቅ እና ማሠራት ይለያያል። አወቀው ማለት አዳምን ክፉ አሠራው ማለት ግን አይደለም፡፡ ስንኳን እመቤታችንን ስለእኛ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር፦ “ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ መረጠን።” (ኤፌ.፩፥፬) ብሎ ተናግሯል፡፡ “እስመ እግዚእ ኀረያ-ጌታ መርጧታልና” እንድትመረጥ ሁና ብትገኝ ተመረጠች ብሎ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም ተናግሮላታል፡፡

ለ.በሥነ ፍጥረት ተነግሮታል፦ እመቤታችን በበርካታ ሥነ ፍጥረት ምሳሌ ተመስላለች።

ከረቂቁ  እስከ ግዙፉ ዓለም ድረስ ፡፡

ግብር እምግብር (ከተፈጠረ ነገር የተገኙ) ከተፈጠሩ ፍጥረታት በሰዓት እስከ ሚቆጠሩ ዕለታት ድረስ ፡፡

ከባሕር እስከ  የብስ፣ ከየብስ እስከ ባሕር ድረስ፡፡

ከዓለመ መላእክት እስከ ዓለመ ሰብእ ድረስ፡፡

ለዚህ ነው ሊቁ አባ ሕርያቆስ፦

“በመኑ በአምሳለ መኑ ናስተማስለኪ-በምን እና በምን እንመስልሻለን?” በማለት የተናገረው።

ሐ.በሕገ ልቡና እና በሕገ መጻሕፍት ተነግሮላታል።

ይህም በብዙ ኅብረ አምሳል እና በብዙ ኅብረ ትንቢት የተነገረው  ነው።

ኅብረ ትንቢት እንደሚከተለው ነው፦

“በአንተና በሴቲቱ በዘርህ እና በዘሯ መካከል ጠላትነትን አደርጋለው።” (ዘፍ.፫፥፲፭)

“ቀስቴን በደመና አደርጋለሁ” (ዘፍ.፱፥፲፫)

“እግዚአብሔርም በሴም ድንኳን ይደር።” (ዘፍ.፱፥፳፯)

“በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ትወልዳለች።” (ኢሳ.፯፥፲፬)

“ከእሴይ በትር ትወጣለች” …(ኢሳ.፲፩፥፩) ወዘተ በማለት ትንቢት ተናግረዋል።

በተለይም በጠቢቡ ሰሎሞን “ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስዩ” (መኃ ፬፥፰ ) ብሎ በአድባረ ሊባኖስ እንደምትወልድ በሚደንቅ ትንቢት ተናግሯል።

በብዙ ኅብረ አምሳል ደግሞ እንደሚከተለው ሲሆን በአምሳለ ሰዋስው (መሰላል) ለያዕቆብ (ዘፍ.፳፯፥፲፯)…በአምሳለ ሐመልማል ለሙሴ (ዘጸ .፫፥፫)

“በአምሳለ መሶበ ወርቅ፤ በአምሳለ ተቅዋመ ወርቅ፤ በአምሳለ ማዕጠንተ ወርቅ፤በአምሳለ ታቦት”ለሙሴ፡፡

በጠቅላለው በኦሪት ውስጥ የተመሰሉ ምሳሌዎች ለእመቤታችን አምሳል ናቸው፡፡

በዘመነ መሳፍንት እና በዘመነ ነገሥትም በብዙ ተመስላለች።

“በአምሳለ ጸምር ለጌዴወን” (መሳ.፮፴፭)

“በአምሳለ መሶብ ለኤልያስ” (፩.ነገ.፲፱፥፮)

“በአምሳለ ንግሥት ለዳዊት”(መዝ.፵፬፥፱)

“በአምሳለ መርዓት ‹ሙሽራ›ለሰሎሞን (መኃ፬፥፰)

“በአምሳለ ፈጣን ደመና ለኢሳይያስ” (ኢሳ.፲፱፥፩) ወዘተ በመሳሰሉ ምሳሌያት እየተመሰለች እየተነገረች ዘመነ አበውን በምሥጢር  እያለፈች አበውን በተስፋ እያጽናናች የመጣች እርሷ ናት፡፡

“ይእቲኬ መድኃኒት እንተ ኀሠሥዋ ወዖድዋ ነቢያት-ነቢያት የሿት እና የፈለጓት መድኃኒት ይህች ናት።” (፩.ጴጥ.፩፥፲) ብሎ ቅዱስ ጴጥሮስ እንደነገረን፡፡ ራሱ ባለቤቱ እግዚአብሔር ለአባታችን ለአዳም የሰጠው ዘለዓለማዊ ተስፋ የሚፈጸመው በእርሷ በኩል ነው።”ተስፋ ሕይወት ተሠርዐ-የሕይወት ተስፋ ተሠራልን።” ቅዱስ ያሬድ የሕይወት ተስፋም በድንግል ማርያም ተፈጽሟል።

“ተፈጸመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል-የአበው ተስፋ በድንግል ማርያም ተፈጸመ።”እንዲል ደራሲው ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም. ስለሆነም ቀን ሲደርስ አንባ ይፈርስ እንዲሉ፦

አማናዊ ቃል ኪዳን ሊጻፍባት አማናዊት ብራና ፤

አማናዊ ካህን ሊያገለግልባት አማናዊት መቅደስ፤

አማናዊ ፀሐየ-ጽድቅ ክርስቶስ ለሚወጣባት አማናዊት  ሰማይ፤

አማናዊ ስንዴ ሊበቅልባት አማናዊት  ምድር።

ግንቦት አንድ ቀን ከቅድስት ሐናና ከቅዱስ ኢያቄም በፈቃደ እግዚአብሔር በብሥራተ መልአክ በሊባኖስ ተራራ  ተወለደች፡፡ ባሕርየ ሰብእን የፈጠረ ባሕርይዋን ሊዋሐድ ንጽሕት እናቱን ፈጠረ ፡፡ ፅንሰቷ በዘር በሩካቤ ቢሆንም ባሕርይዋ ሳያድፍ ጥንተ በደል ሳይደርስባት ተወለደች፡፡”እምጽቡር ጽሩየ ገብራ-ንጽሕት አድርጎ ሠራት።” “ከፈጠራት ጀምሮ በምንም በምን ከድንግልናዋ አልተለወጠችም።” (ሃይ.፶፫፥፳፪) ብሎ ሊቁ ቅዱስ ቴዎዶጦስ እንደተናገረ ፡፡አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም፦”ዐቀባ መንፈስ ቅዱስ እምከርሠ እማ-መንፈስ ቅዱስ ከእናቷ ማሕፀን ጀምሮ ጠበቃት።” (መ.ምሥ.፳፥፲)

ቀዳማዊት ሔዋን ያጣችውን ንጽሕና እመቤታችን ግን ሳይጎድልባት ይዛ ተወለደች፡፡

ስለዚህም ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም፦ ወመሠረተ ንጽሕነ ኮነ በማርያም ድንግል-የንጽሕናችን የቅድስናችን መሠረትስ በማርያም ድንግል ተደረገልን” አለ፡፡

አምላካችን ከበረከተ ልደቷ ያሳትፈን፡፡አሜን፡፡ይቆየን