ቅድስት ቤተ ክርስቲያን

ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ቤተ ክርስቲያን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ዋጅቶ የመሠረታት፣ በክርስቶስ ክርስቲያን ለተባልን በሙሉ መሰብሰቢያችን የተቀደሰች ቤታችን ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስንልም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን፣ የክርስቲያን ወገን፣ የምእመናን አንድነት ወይንም ማኅበረ ምእመናን እንዲሁም እያንዳንዱ ምእመናን ማለታችን ነው፡፡

ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አምልኮተ እግዚአብሔር የምንፈጽምባት የእግዚአብሔር ማደሪያ ናት፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን መላእክት ፈጣሪያቸውን የሚያገለግሉባት የክብሩ መገለጫ የሰማያዊት ኢየሩሳሌም ምሳሌ በመሆኗ አባቶቻችን በአሠራሯ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያደርጉ ሲሆን የሕንፃዋ ቤተ ክርስቲያን አሠራርም በሦስት ዓይነት ቅርጽ ሊሆን ይችላል፡፡

፩.ክብ
በፊልጵስዩስ የተሠራችው የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ክብ ቅርጽ ነበራት፡፡ የሙሉ ክብነቷ ትርጓሜም የፍጹምነቷ ምልክት ነው፤ በዚህም መሠረት በአብዛኛው ቤተ ክርስቲያናት በክብ ቅርጽ ይታነጻሉ፤ የዚህ ዓይነት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንም ዙሪያው ክብ ሆኖ ውስጡ በሦስት የተከፈለ ሰሆን ሦስት በሮችም አሉት፤ ቤተ ንጉሥ ቅርጽም ይባላል፤ አንድ ጉልላት ሲኖረው ከጉልላቱም ላይ መስቀል ይኖራል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚሣሉት ቅዱሳንም ዓይንና ፊታቸው ክብ ሆኖ የሚሣለው ሃይማኖትን ከምግባር አዋሕደው የተገኙና ከሕግ በላይ የሆኑ ፍጹማን መሆናቸውን ለመግለጽ ነው፡፡

፪.ሰቀላማ ወይም ሞላላ ቅርጽ ማዕዘን ቅርጽ

የዚህ ዓይነት የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ አሠራር ጠቢቡ ሰሎሞን ያሠራውን ቤተ-መቅደስ መሠረት ያደረገ ነው፤ ለዚህ ምሳሌ በሀገራችን የአክሱም ጽዮን፣ የጎንደሩ ደብረ ብርሃን ሥላሴ እና ደብረ ዳሞ፣ ዐፄ ዮሐንስ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ያሠሩት የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ዐሥራ ስምነት ጉልላት ያላቸውን ሰቀላማ ቅርጽ ያላቸውን አብያተ ቤተ ክርስቲያናትን መጥቀስ ይቻላል፤ በሞላላ ቅርጽ የታነፁ አብያተ ቤተ ክርስቲያናት መሠረታቸው የመስቀል ቅርጽ ያለው በመሆኑ በዚህ ቅርጽ የመታነፃቸው ምሥጢር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት በመስቀል ላይ የፈጸመውን የድኅነት ሥራ እንድናስብበት ነው፡፡ ለሰው ልጆች ሲል መከራ ተቀብሎ፣ ተሰቅሎና ሞትን ድል አድርጎ ማረጉን ያመለክታል፡፡ ከላይ የጠቀስናቸው ሰቀላማ ቅርጽ አብያተ ክርስቲያናት በተጨማሪ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያንና ምስካየ ኀዙናን መድኃኔዓለም ገዳማት ለሰቀላማ ቅርጽ አብያተ ክርስቲያናት በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

፫. ዋሻ ቅርጽ

የዚህ ዓይነት ሕንፃ ቤተ ክርስቶያናት ሰማዕታት ከዓላማውያን ነገሥታት ሸሽተው በዋሻ ሲሸሸጉ የጀመሩት አሠራር ዓይነት ነው፡፡ አንድ በርም አለው፤ በአብዛኛውም ጊዜ በውስጡ ያሉትን ክፍሎች በመጋረጃ ይከፈላል፡፡ ሆኖም ግን ጉልላት የለውም፤ ተራራ በመፈልፈል በዋሻ ውስጥ ሲሆን ለብቻው የቆመ ድንጋይን (አለትን) በመፈልፈል ሊሠራ ይችላል ምሳሌ፡-አቡነ ሀብተ ማርያም ገዳም፣አዳዲ ማርያም፣የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ምሳሌዎች ናቸው፡፡

አንድነታቸውና ልዩነታቸው

አንድነታቸው

ሁሉም አብያተ ቤተ ክርስቲያናት ቅኔ ማኅሌት፣ ቅድስትና መቅደስ አላቸው፡፡ በውስጣቸው የሚፈጸመው የቅዳሴ፣ የማኅሌት፣ የሰዓታት፣ የጸሎት ሥርዓት አንድ ዓይነት ነው

ልዩነታቸው
ሰቀላማና ክብ ቅርጽ አብያተ ቤተ ክርስቲያናት ጉልላት ሲኖራቸው ቅርጽ ቤተ ክርስቲያን ዋሻ ግን ጉልላት የለውም፡፡ ሰቀላማና ዋሻ ቅርጽ በመጋረጃና በደረጃ ሲከፈሉ ክብ ቅርጽ ግን በግድግዳ ይከፈላል፡፡ በሰቀላማና ዋሻ ቅርጽ የሴቶችና የወንዶች መቆሚያ ሲኖረው የሚከፈለውም በመጋረጃ ነው፡፡ ነገር ግን በክብ ቅርጽ ግን የተለያየ ቦታ አላቸው፡፡

የቤተ ክርስቲያን ክፍሎችና ትርጓሜያቸው

ቤተ ክርስቲያን ሦስቱ ክፍሎች ያሏት ሲሆን እነዚህም ቅኔ ማኅሌት፣ ቅድስትና መቅደስ በመባልም ይታወቃሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ክፍሎች ክፍሎቿም ጎልተው የሚታዩት በክብ ቅርጽ በታነፀ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ክፍሎችም ሦስት የሆኑበት ምክንያት አንደኛው በሦስቱ ዓለማተ መላእክት ማለትም በኢዮር፣በራማ፣በኤረር ምሳሌ መሆኑ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ በሦስቱ መዓረጋት ክህነት ዲቁና፣ቅስና፣ኤጲስቆጶሳት ምሳሌ ሲሆን በሦስቱ ጾታ ምእመናን፡ ማለትም ካህናት፣ ወንዶች፣ ሴቶች የሦስቱ ኆኅተ ገነት (የገነት በሮች) ምሳሌም በመሆኑ ነው፡፡

አገልግሎታቸው
፩. ቅኔ ማኅሌት

በዚህ ክፍል ውስጥ መዘምራን፣ ደባትር ካህናት ማኅሌተ እግዚአብሔር ያደርሱበታል፡፡ በመስዕ (ሰሜን ምሥራቅ) ንዑሰ ማዕዘን በኩል ቀሳውስትና ዲያቆናት በመንፈቀ ሌሊት ሰዓታት በነግህ ኪዳን ያደርሱበታል፤ ለጥምቀት ለቊርባን ያልበቁ በትምህርት በንስሓ የሚፈተኑ /ንዑሰ ክርስቲያን/ ‹‹ፃኡ ንዑሰ ክርስቲያን›› እስከሚባል ድረስ የሚቆዩበት ክፍልም ነው፤ ወንዶች ምእመናንም ቆመው ያስቀድሱበታል፤ በሌብ /ደቡብ ምሥራቅ/ ንዑስ ማእዘን በኩል የሚገኘው ቦታ የሴቶች መቆሚያ ነው፡፡ ከውጭ ወደ ቤተ መቅደስ ስንገባ የምናገኘው የመጀመሪያው ክፍል ሲሆን ሦስት በሮችም አሉት፤ የካህናት፣ የወንዶችና የሴቶች ምእመናት መግቢያዎች ናቸው፡፡

፪.ቅድስት
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማእከላዊ ክፍል ቅድስት ይባላል፡፡ ካህናት በድርገት ጊዜ ምእመናንን የሚያቆርቡበት ክፍል ሲሆን በስብከተ ወንጌል ጊዜም መምህራን ቆመው ያስተምሩበታል ክፍል፡፡ በተክሊልና በቊርባን አንድ ለሚሆኑ ሙሽሮች ጸሎት የሚደርስበትና በካህናት እጅ የሚባረኩበት በዚህ ክፍል ውስጥ ነው፡፡ በስቅለት ዕለት ሥርዓተ ጸሎት ይፈጸምበታል፤ በምዕራብ በኩል ቆሞሳት፣ ዲያቆናት፣ ቀሳውስት ይቆሙበታል፤ በሰሜን መነኮሳትና የሚቈርቡ ወንዶች ምእመናን ይቆሙበታል፤ በደቡብ የሚቆሙት ደናግል መነኮሳይያት፣ የቀሳውስትና የዲያቆናት ሚስቶች ናቸው፤ በምሥራቅ በምዕራብ በሰሜንና በደቡብ ዐራት በሮች ይኖሩታል፤  ነገር ግን የማይቆርቡ ምእመናን በዚህ ክፍል ቆመው አያስቀድሱም፡፡

፫.መቅደስ
በብሉይ ኪዳን ቅድስተ ቅዱሳን በሚል ስያሜ ይጠራ የነበረው የቃል ኪዳኑ ታቦት የሚገኝበት ክፍል መቅደስ ነው፡፡ ንዋያተ ቅድሳትም ከመንበረ ታቦቱ ጋር በዚህ ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በምዕራብ በሰሜንና በደቡብ ሦስት በሮች ሲኖሩት እያንዳንዱ በር በመንጦላዕት ወይም በመጋረጃ የሚጋረድ ነው፡፡ ከዲያቆናትና ሥልጣነ ክህነት ካላቸው በቀር ወደ መቅደሱ ማንም መግባት አይችልም፡፡ በዚህ ክፍል ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት ቆመው ያስቀድሱበታል፤ የጌታችን ሥጋና ደም የሚፈተተው በዚሁ ክፍል ውስጥ ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የሚሠሩና አገልግሎት የሚሰጡ ቤቶች

ቤተ ልሔም፡- በቤተ ክርስቲያን ምሥራቅ አቅጣጫ ዲያቆናቱ ለመሥዋዕት የሚሆነውን ኅብስትና ወይን የሚያዘጋጁበት ሁለተኛ ቤት ቤተ ልሔም ይባላል፡፡ ጌታችን የተወለደበትን ቤተ ልሔም ያስታውሰናልና፤ መቅደሱ ደግሞ የቀራንዮ ምሳሌ ነው፡፡

የግብር ቤት፡ ለመሥዋዕት የሚቀርበው (መገበሪያ) የሚሰየምበት ሌላኛው ክፍል ነው፡፡ የተገነባውም በምሥረቅ አቅጣጫ ነው፡፡

ዕቃ ቤት፡ የቤተ ክርስቲያን ንዋተ ቅድሳት የሚቀመጡበት ዕቃ ቤት ይባላል፡፡ የቤተ ክርስቲያን መገልገያ የሆኑት አልባሳትም ሆነ መጻሕፍትም የሚቀመጡት በዚህ ቤት ውስጥ ነው፡፡ (ሕዝ. ፵፬፥፲፱፣ ፍት.መን. ፲፮)

ክርስትና ቤት

ክርስትና ቤት ሥርዓተ ጥምቀት የሚፈጸምበት የማጥመቂያ ቤት ነው፡፡ ካህናትና ዲያቆናት ከቅዳሴ በኋላ የሚመገቡበት ቤት ነው፤ በጥንት ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን መግቢያ በር ጋር ተያይዞ የሚሠራ ነበር፡፡

ሰንበቴ ቤት፡ ከቤተ ክርስቲያን ፵ ክንድ ርቆ የሚሠራ ሲሆን በዕለተ ሰንበት ምእመናን ተሰብስበው የሰንበትን ጽዋ እየጠጡ ከካህናት የሚሰጠውን ትምህርት የሚከታተሉበትና የሚጠያየቁበት ቤት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም እንደ ቤተ ክርስቲያኗ የገንዘብ እና የምእመኑ አቅም የሚሠሩ ቤቶች አሉ፡፡ እነርሱም የሰበካ ጉባኤ ጽሕፈት ቤት፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ክፍሎች፣ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ፣ የእንግዶችና የካህናት ማረፊያ ቤቶች፣ የመንፈሳዊ ትምህርት ቤትና የተግረ እድ መማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ-መጻሕፍት፣ የንዋየ ቅድሳትና ጧፍ ዕጣን መሸጫ ክፍሎች ወዘተ… ናቸው፡፡

የቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ ክፍሎችና ምሳሌዎች (ከመሠረት እስከ ጉልላት)

አዕማድ፡ ምሰሶ ማለት ሲሆን በቤተ ክርስቲያን በውስጣዊ ክፍል በኩል የሚተከሉ ናቸው፡፡ ምሳሌነታቸው አንደኛ የቅዱሳን መላእክት ነው፤ መላእክት በእግዚአብሔር ፊት በቤተ መቅደስ ዙርያ ለምስጋና ጸሎትን ለማሳረግ ለጥበቃ ሌትና ቀን ሳያርፉ እንደሚቆሙ ሁሉ ምሰሶዎቹም ሌትና ቀን ተተክለው ይታያሉና፡፡ ሁለተኛ በቅዱሳን ሐዋርያት ይመሰላሉ፤ ቅዱሳን ሐዋርያት ሌሊትና ቀን በአገልግሎት ጸንተው ቤተ ክርስቲያን እንዳገለገሉ ለማሳየት ምሰሶዎቹም ጸንተው ይታያሉና፡፡ (ራእ. ፬፥፰፣ገላ. ፪፥፱)

ጉበን ወይም /ደረጃ/ወደ ቤተ-መቅደስ የሚመራ ሲሆን  የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አርአያ አብነት አድርገን የምንኖር ስለሆነ ምሳሌው የእርሱ ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን ሳር ክዳን፡ ንጉሥ ሄሮድስ በጭካኔ ያስፈጃችው የቤተ ልሔም ሕፃናት ምሳሌ ነው፡፡ (ማቴ. ፪፥፲፮)

የቤተ መቅደስ ቅጽር (የግቢው ከለላ) የቅዱሳን መላእክት ምሳሌ ሲሆኑ ዕጽዋት ብዙ ሆነው በቤተ ክርስቲያን ቅጽር እንደሚታዩ ሁሉ ቅዱሳን መላእክትም በብዛት ሆነው ሰውንም ሕንፃውንም ይጠብቃሉ፤ ዕጽዋትም ሞገስ ይሆናሉ፡፡ (መዝ. ፺፥፲፩)

ማገር፡ የቅድስት ሥላሴ ምሳሌ ሲሆን  ሕንፃውን ከክዳኑ ጋር አገናኝቶና አጽንቶ ያቆማል፡፡ ቅድስት ሥላሴም ቤተ መቅደስ በሆነው በሰው ሰውነት ላይ አድረው ሃይማኖት አጽንተው ይኖራሉና፡፡

የቤተ ክርስቲያን መክፈያ ግድግዳ፡ የነቢያት ምሳሌ ሲሆን የቤተ መቅደስ ግድግዳ ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላ ስንሸጋገር የምናገኘው ነው፡፡ ነቢያትም ከዘመን ዘመን ‹‹መሢሕ ይወርዳል ይወለዳል›› እያሉ ትንቢት በናገሩት መሠረት የተገኙ ናቸው፡፡ (ማቴ.፫፥፩)

የተጠረቡ ድንጋዮች፣ የለዘቡ እንጨቶች፡ እነዚህ የሰማዕታት ምሳሌዎች ሲሆኑ ድንጋዮችና እንጨቶች ተጠርበው በቤተ መቅደስ ሥራ ይውላሉ፡፡ ሰማዕታትም በእሳት እየተፈተኑ በስለት እየተመሩ ለሃይማኖታቸው ማገር ምሰሶ ግድግዳ ሆነዋልና፡፡ (ዕብ.፲፩፥፴፮)

ጉልላት፡ የቀራንዮ ምሳሌ ሲሆን በቤተ ክርስቲያን አናት ላይ እንደተራራ ሆኖ የምናየው ጉልላት ይባላል፤ ጌታችን የሰውን ልጆች ለማዳን የተሰቀለበት የቀራንዮ ኮረብታ ምሳሌ ነውና፡፡ (ዮሐ.፲፱፥፲፯)

በጣሪያው ዙርያ የሚደረጉ የሚን መርገፎች፡ የቅዱሳን መላእክት ምሳሌ ሲሆኑእየተወዛወዙ ድምጽ እንደሚያወጡ ሁሉ ቅዱሳን መላእክትም በቤተ ክርስቲያን ዐጸድ ሌሊትና ቀን ያሸበሽባሉ፤ ይዘምራሉም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ንጉሥ ሄሮድስ በጭካኔ ያስፈጃችው ሕጻናት ምሳሌም ናቸው፡፡ (ዘፍ.፳፰፥፲፩-፲፯)

የሰጎን እንቊላል፡ የዚህ ዓይነቱ አሠራር በአሁኑ ጊዜ በብዙዎች ሕንፃ አብያተ ክርስቲያናት ጉልላት ላይ ባይስተዋልም በገጠር አብያተ ክርስቲያናት ጉልላት ላይ ይገኛል፤ ተምሳሌቱም ሰጎን እንቁላሏን እንዲፈለፈል የምታደርገው በመታቀፍ ሳይሆን ወዲያ ወዲህ ሳትል ትኩር ብላ በማየት ነው፡፡ ሰጎን እንቁላሏን ያለማቋረጥ እንደምትመለከት እግዚአብሔርም ፍጥረቱን የማይረሳ፣ በጸጋውና በረድኤቱ ከፍጥረቱ የማይለይ መሆኑን ለማጠየቅ የሰጎን እንቊላል በቤተ ክርስቲያን አናት ላይ ይሰቀላል፡፡

ሦስቱ በሮች፡ እነዚህ በሮች በምሥራቅ፣ በሰሜንና፣ በደቡብ የሚገኙ የገነት በሮች ምሳሌዎች ናቸው፤ ገነት ሦስት በሮች ስለነበሯት በምሥራቁ በር እግዚአብሔር ይገባበታል፤ በሰሜኑ በር አዳም፣ በደቡብ በር ደግሞ ሔዋን ትገባበት ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት አሁንም በቤተ ክርስቲያናችን በምሥራቁ በር አዕይንተ እግዚአብሔር ካህናት፣ በሰሜን ወንዶች በደቡብ ደግሞ የሴቶች መግቢያዎች ሆነው ያገለግላሉ።

 የክርስቲያን ወገን፣ የምእመናን አንድነት ጉባኤ ወይንም ማኅበረ ምእመናን

ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያን ወገን፣ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ የምእመናን አንድነት ጉባኤ ተብሎ ይጠራል፡፡ ለዚህም በምሳሌነት የምንጠቅሳቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፉ ቤተ እስራኤል፣ ቤተ ያዕቆብ፣ ቤተ አሮን ሲል የእስራኤል ወገን፣ የያዕቆብ ወገን፣ የአሮን ወገን እንደ ማለት ነውና፡፡ የክርስቲያኖች መሰብሰቢያ መገናኛ፣ ክርስቲያኖች በአንድነት ተሰብስበው የሚጸልዩባት፣ የሚያስቀድሱባት፣ የሚሰግዱባት እንዲሁም ሥጋ ወደሙ የሚቀበሉበት ቤት ማለት ነው፡፡ (ኢሳ.፶፮፥፯፣ኤር.፯፥፲-፲፩፣ማቴ.፳፩፥፲፫፣፲፮፥፲፰፥፲፯፣ማር.፲፩፥፲፯፣ሉቃ.፲፱፥፵፮፣የሐዋ.ሥራ ፲፰፥ ፳፪፣ ፳፥፳፰)

ምእመናን ቤተ ክርስቲያን ናቸው

ቤተ ክርስቲያን ምእመናንንም ትወክላለች፤ ክርስቲያኖች የክርስቶስ ማደሪያዎች ናቸውና ቤተ ክርስቲያን ማለት የክርስቶስ ማደሪያ የሆኑ ክርስቲያኖችን /የክርስቲያኖችን ሰውነት/ የሚያመለክት ነው፡፡ ሆኖም ግን የእግዚአብሔር ማደሪያ እንሆን ዘንድ በሕጉ መመራት፣ ትእዛዛቱን መፈጸምና አምልኮተ እግዚአብሔርን መፈጸም ያስፈልጋል፤ በዚያም ምእመናን የክርስቶስ ማደሪያ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ (፩ቆሮ.፫፥፲፣ራእ.፫፥፳)

እግዚአብሔር አምላክ ቤተ ክርስቲያናችንን ሰላም ያድርግልን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፤ ‹‹የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራትና ሥርዓት›› በመምህር ፈቃዱ ሣህሌ፤ ገጽ ፪፻፲፩- ፪፻፴፩፣ ‹‹ሥርዓተ  ቤተ ክርስቲያን›› በቀሲስ ጌታቸው ደጀኔ ገጽ ፩-፶፱፥ ‹‹ቃለ ዐዋዲ- የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ደንብ›› ገጽ ፲፩