ጼዴንያ

መስከረም ፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዝግጅት ክፍሉ

maryam

በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ መስከረም ፲ ቀን ከሚዘከሩ በዓላት መካከል የእመቤታችን በዓል አንደኛው ሲኾን ይኸውም ጼዴንያ በምትባል አገር ከሥዕሏ ተአምር የተደረገበት ዕለት ነው፡፡ በተአምረ ማርያምና በመጽሐፈ ስንክሳር እንደ ተመዘገበው ቅዱስ ሉቃስ ከሣላት ሥጋ የለበሰች ከምትመስል የእመቤታችን የሥዕል ሠሌዳ ቅባት ይንጠፈጠፍ ነበር፡፡

እመቤታችን ድንግል ማርያምን የምትወድና በሚቻላትም ኹሉ የምታገለግላት፣ ቤቷንም ለእንግዳ ማደሪያ ያደረገች አንዲት ማርታ የምትባል ሴት ነበረች፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አባ ቴዎድሮስ የሚባሉ መነኵሴ ከእርሷ ዘንድ በእንግድነት አድረው በማግሥቱ ከቤቷ ሲወጡ ማርታ የሚሔዱበትን አገር በጠየቀቻቸው ጊዜ  እርሳቸውም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው ቅዱሳት መካናትን እንደሚሳለሙ ነገሯት፡፡

ማርታም ከእርሷ ገንዘብ ወስደው የእመቤታችንን ሥዕል ገዝተው ይዘውላት እንዲመጡ ለመነቻቸው፡፡ መነኵሴውም በራሳቸው ገንዘብ ሥዕሉን ገዝተው እንደሚያመጡላት ቃል ገቡላት፡፡ አባ ቴዎድሮስ ኢየሩሳሌም ደርሰው ቅዱሳት መካናትን ከተሳለሙ በኋላ ሥዕሏን ሳይገዙ ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡ ያን ጊዜም ‹‹ሥዕል መግዛትን ለምን ረሳህ?›› የሚል የሚያስደነግጥ ቃልን ሰምተው ወደ ገበያ ተመልሰው መልኳ ያማረና የተወደደ የእመቤታችን ማርያምን ሥዕል ገዝተው በሐርና በንጹሕ ልብስ ጠቅልለው ይዘው እየተጓዙ ሳሉ ከሚያስፈራ ዱር ውስጥ ሲደርሱ ወንበዴዎች ተነሡባቸው፡፡ ሊሸሹ ሲሉም ‹‹መንገድህን ሒድ›› የሚል ቃል ከሥዕሏ ወጣ፤ መነኵሴውም መንገዳቸውን በሰላም ተጓዙ፡፡ ሁለተኛም አንበሳ ሊበላቸው በተነሣባቸው ጊዜ ከዚያች ሥዕል የሚያሥፈራ ድምፅ ወጥቶ አንበሳውን አባረረላቸው፡፡

አባ ቴዎድሮስ ይህን ኹሉ ድንቅ ተአምር ባዩ ጊዜም ያቺን ሥዕል ለማርታ ከመስጠት ይልቅ ወደ አገራቸው ሊወስዷት ወደዱ፡፡ በመርከብ ተሳፍረው በሌላ አቅጣጫ ሲሔዱም ታላቅ ነፋስ ተነሥቶ ወደ ማርታ አገር ወደ ጼዴንያ ወሰዳቸው፡፡ ከመርከብም ወርደው ከብዙ እንግዶች ጋር ወደዚያች መበለት ቤት ደረሱ፡፡ ነገር ግን ማንነታቸውን ለማርታ አልገለጡላትም፤ እርሷም አላወቀቻቸውም ነበር፡፡

በማግሥቱም ተሠውረው ወደ አገራቸው ሊሔዱ ሲሉ የቅፅሩ ደጃፍ ጠፍቶባቸው ሲፈልጉ ዋሉ፤ በመሸባቸው ጊዜም ወደ ማደሪያቸው ተመለሱ፡፡ ማታ ማታ በሩን ያዩታል፤ ነግቶ መሔድን ሲሹ ግን የበሩ መንገድ ይሠወርባቸዋል፡፡ እንዲህም ኾነው እስከ ሦስት ቀን ድረስ ቆዩ፡፡ ማርታም ‹‹አባቴ ሆይ አእምሮህ ተነክቷልን? ስትቅበዘበዝ አይሃለሁና ምን ኾነህ ነው?›› ሰትል ጠየቀቻችው፡፡ እርሳቸውም ከእመቤታችን ሥዕል የተደረገውን ተአምር ኹሉ ነገሯት፤ ራሳቸውንም ገለጡላትና ሥዕሏን ሰጧት፡፡ እርሷም የእመቤታችንን ሥዕል ተቀብላ የተጠቀለለችበትን ልብስ በፈታችው ጊዜ ወዝ ከሥዕሊቱ ሲንጠፈጠፍ አገኘች፡፡ ከደስታዋ ብዛት የተነሣም የአባ ቴዎድሮስን እጃቸውንና እግራቸውን ሳመች፡፡

ከዚህም በኋላ ያቺን ሥዕል ወደ ጸሎት ቤቷ ወስዳ በታላቅ ክብር አኖረቻት፡፡ ማንም እንዳይዳስሳትም የነሐስ መስኮትን ሠራችላት፡፡ በቀንና በሌሊትም የሚያበሩ መቅረዞችን በፊቷ ሰቀለች፤ ከመቅረዞች ውጭም የሐር መጋረጃን ጋረደች፡፡ ከሥዕሊቱ በታችም እየተንጠፈጠፈ የሚወርደው የወዝ ቅባት የሚጠራቀምበት ከዕብነ በረድ የተሠራ ወጭት አኖረች፡፡ እኒያ መነኰስም እስከሚሞቱበት ቀን ድረስ የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ሥዕል እያገለገሉ ኖሩ፡፡

የአገሩ ሊቀ ጳጳስም የእመቤታችን ሥዕል ሥጋ የለበሰች ኹና ባገኙና ተአምሯንም በተመለከቱ ጊዜ ከዚህ አምላካዊ ግብር የተነሣ አደነቁ፡፡ ከሥዕሏ ከሚንጠባጠበው ቅባት ቀድተው ለበረከት ሲካፈሉም ወዲያውኑ በወጭቱ ውስጥ መላ፡፡ ሥዕሊቱን ወደ ሌላ ቦታም ሊወስዷት በፈለጉ ጊዜም ንውጽውጽታ ኾኖ ብዙዎች በድንጋጤ ወደቁ፡፡ ሥዕሊቱም እስከ ዛሬ ድረስ በዚያች አገር (በጼዴንያ) ትገኛለች፡፡

‹‹እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /መዝ.፷፯፥፴፭/ እግዚአብሔር አምላካችን በልዩ ልዩ መንገድ ለሰው ልጅ ተአምራቱን ይገልጣል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቦ እንደምናገኘው እግዚአብሔር ከዓለት ላይ ውኃ እያፈለቀ ሕዝቡን ያጠጣል፡፡ ከግዑዝ ዓለት ውስጥ ውኃ የሚያፈልቅ አምላክ ከሥጋዋ ሥጋ፤ ከነፍሷ ነፍስ ተዋሕዶ ካከበራት ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ወዝ እንዲፈስ ቢያደርግ ምን ይሳነዋል? እንደዚሁም ቅዱሳን ሐዋርያት በቃላቸውም፣ በልብሳቸውም፣ በጥላቸውም ሙታንን በማስነሣት፤ ሕሙማንን በመፈወስ ተአምራትን ያደርጉ ነበር፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጴጥሮስ በጥላው፤ ቅዱስ ጳውሎስም በልብሱ ቅዳጅ ያደርጓቸው የነበሩ ተአምራትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ሐዋርያት ከእግዚአብሔር ዘንድ በተሰጣቸው ጸጋ በልብሳቸውና በሰውነታቸው ጥላ ተአምራትን ማድረግ እንደ ተቻላቸው ኹሉ አምላክን በማኅፀኗ የተሸከመችው ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያምም በሥዕሏ ወዝ ብዙ ሕሙማንን መፈወስ ይቻላታል፡፡ ከቅዱሳን ልብስና ጥላ የእርሷ ሥዕል ይከብራልና፡፡ ስለዚህም ነው በየዓመቱ መስከረም ፲ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት የሚከበረው፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፤ የልጇ፣ የወዳጇ የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡