ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ለሚኒስትሮችና ለካቢኒ አባላት በሰጡት የወቅታዊ ጉዳይ ማብራሪያ አስመልክቶ ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ። ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም.

May be an image of 10 people, people standing and indoor

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠመግለጫ።
በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ምልዓተ ጉባኤ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሶዶ ደሙ ወረዳ ሀሮ በዓለወልድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጸመውን ኢ-ሲኖዶሳዊ የሆነ የሃይማኖት፣ የቀኖናና የአስተዳደር ጥሰት አስመልክቶ በሰፊው ተወያይቶ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የሃይማኖት ልዩ ልዩ ሕግጋት ውጭ ጳጳስ ሾመናል ባሉ አካላት እና ተሹመናል በሚሉት አካላት ላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግጋት በሚፈቅድለት መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸው ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት በመሻር አውግዞ የለያቸው ሲሆን፣ በዕለቱ ይኸው ውግዘት በመላው ዓለም ለሚገኙ የዕምነቱ ተከታዮች ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምዕመናን ውግዘቱን እንዲያውቁት መንግሥትም በዚህ ጉዳይ የሚፈጠር ችግር እንዳይኖር ሰላም እንዲያስከብር ዓለም በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ መረጃ ኖሮት ቤተ ክርስቲያን ለወሰነችውም ውሳኔ ግንዛቤ እንዲወስድ በመግለጫ ማሳወቃችን ይታወሳል፡፡
     በዚህ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታይ የሆኑ አገልጋይ ካህናት እና ምዕመናን በመላው ዓለም የሚገኙት ደስታቸውን በመግለጥ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ሳይሸራረፍ እንደሚያስፈጽመ በልዩ ልዩ መንገድ እየገለጹ ይገኛል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚገኙ የልዩ ልዩ ሃይማኖት ተቋማትና ሲቪክ ማኅበራት የተፈጸመውን ድርጊት በመቃወም እና ቤተ ክርስቲያኒቱ የወሰነችውን ውሳኔ በመደገፍ ከጎናችን እንደሆነ እና አብረውን እንደሚሰሩ በልዩ ልዩ መንገድ እየገለጹልን ይገኛል፡፡ በዚህ ቤተ ክርስቲያናችን ከጎናችን ለቆሙትና ድጋፋቸውን ለገለፁልን ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ የሃይማኖት እና የሲቪክ ተቋማት ምስጋናዋን አቅርባለች።
     እነዚህ በሕገ ወጥ መንገድ ተሹመናል የሚሉት አካላትም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከማዕከላዊ መዋቅር ውጭ ተወግዘው ተለይተው እያለ በሌላቸው ሥልጣን ወዳልተፈቀደላቸው የአገልግሎት በታዎች በመግባት በሚያደርጉት ግብ ግብ በዕምነቱ ተከታዮች፣ በማህበረ ካህናትና ምዕመናን ላይ ሁከት እየተፈጠረ መሆኑን ለመረዳት ችለናል። በዚህ ጉዳይ ላይ ቤተ ክርስቲያናችን ለመንግሥት ያቀረበችው ሕግን የማስከበር እና የዜጎችን ሰላም የማስፈን ሥራ ጥሪ ተቀብሎ በሕገወጦች ላይ የወሰደው ምንም ዓይነት እርምጃ እየታየ አለመሆኑም ታውቋል፡፡
     ይህ ሁሉ ድርጊት ሲፈፀም መንግሥት ሰምቶ እንዳልሰማ በዝምታያለፈውን ጉዳይ በጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ለሚኒስትሮችና ለካቢኔዎቻቸው በሰጡት የወቅታዊ ጉዳይ ማብራሪያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሰተውን ወቅታዊ ችግር በማንሳት ልዩ ልዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡
     ይኸውም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅዱስ ሲኖዶሱ እና ውጭ ባሉ አባቶች መካከል ሲካሄድ የነበረውን የዕርቅ ሒደት እልባት እንዲያገኝ ማድረጋቸው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይዞታዎችና ሕንጻዎች መካከል 4ኪሎ የሚገኙትን ሁለቱን ቀደምት ሕንጻዎች ለቤተ ክርስቲያን መመለሳቸው፣ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ሀገረ ስብከት ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ መሥሪያ ቦታ ማድረጋቸው! የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሀገር መሆኗን መግለጻቸው፣ የቤተ ክርስቲያኗ መዳከም ጉዳቱ ለቤተ ክርስቲያኗ ብቻ ሳይሆን ለሀገረ መንግሥቱም ጭምር መሆኑን መግለጻቸው፣ አግባብነት ያለውና ለዚህም : አድራጎታቸው ቤተ ክርስቲያናችን በወቅቱ በእውቅና ሽልማት አጅባ አመሰግናለች፡፡ሆኖም ግን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም በተለያዩ የመንግሥት ሚዲያዎች በተላለፈው 36 ደቂቃ በሚፈጀው በሰላምና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለሚኒስትሮች ካቢኔ አባላት የሰጡትን ማብራሪያ ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንዖት ተመልክታዋለች፡፡ በመሆኑም በቀረበው ማብራሪያ ላይ ቤተ ክርስቲያናችን ያላትን አቋም እንደሚከተለው በዝርዝር እንገልጻለን፡፡
      ፩. መንግስት በቤተ ክርስተያናችን የተፈጠረውን ሃይማኖታዊ እና ቀኖናው ጥሰትን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያን የሰጠችውን ሲኖዶሳዊ ውሳኔ ሊያመጣ የሚችለውን ውጤት አቅልለው በአሁኑ ወቅት በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተፈጠረው ጉዳይ በጣም ቀላል ነው” በማለት ያዩበት መንገድ፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ ጉዳዩ ቀላል እና በንግግር የሚፈታ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህ አገላለጽ በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ውስጥ ጣልቃ እንደመግባት እና ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፋቸውን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ውሳኔዎች ያላቸውን ውጤት ወደ ጎን የተወ መሆኑን ቤተ ክርስቲያን ታምናለች፡፡ ከዚህም አልፎ ሁለቱም ወገን ውስጥ እውነት አለ፣ ሁለቱም አባቶቻችን ናቸው፣ ለማንም አንወግንም፤ ማንም የካቢኔ አባል እዚህ ውስጥ እጁን እንዳያስገባ፣ የሚሉት አገላለጾች በሕግ እውቅና የተሰጣትን ቤተ ክርስቲያን እና በሕጋዊቷ ቤተ ክርስቲያን ላይ በሕገ ወጥ መንገድ የተነሱትን ሕገ ወጥ ቡድኖች በአቻ እይታ ተመልክተው ሊወያዩ ይገባል በማለት የስጡት ማብራሪያ ሕገ ወጥነትን የሚያበረታታ፣ ለሕጋዊ ተቋማት መንግሥት ያለበትን የመጠበቅና ዋስትና የመስጠት ኃላፊነቱን ወደ ጎን ያደረገ፣ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ተቋማት በሕገ ወጥ ቡድኖች እንዲታመሱና እንዲተራመሱ ይሁንታ የሚሰጥ፣ ሕግንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥንታዊ ታሪክና የሀገር ባለውለታነትዋን ያላገናዘበ፣ ማብራሪያ በመሆኑ ሊታረም የሚገባ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያሳስባል።
      ከዚህም በተጨማሪ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትኛውም ካቢኔ በዚህ ጉዳይ እጁን እንዳያስገባ በማለት የሰጡት የሥራ መመሪያ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕጋዊ ሰውነት አክብረው እና የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ያሉትን በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ የሚያደርግና በሕገመንግሥቱ ለአስፈጻሚው አካል የተሰጠውን ሥልጣን የሚሽር፤ ሥርዓተ አልበኝነትን የሚያበረታታ፤ የሕግ የበላይነትን ጥያቄ ውስጥ የሚጥል አድራጎት በመሆኑ ይህ አድራጎት እንዲታረምና መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን የሕግ የበላይነትና የተቋማትን ደህንነት የማረጋገጥ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያሳስባል፡፡
         በሕገ መንግሥቱ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸው በግልጽ የተደነገገ እንደመሆኑ መጠን መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ላይ እጁን ማስገባት እንደሌለበት የምናምንበት ሐቅ ሲሆን ከዚህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ውጭ በሆነ መንገድ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የተፈጸመውን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊ እና አስተዳደራዊ ጥሰትን እንደተራ ግጭት እና የግለሰቦች አለመግባባት በመቁጠር ትንታኔ ለመስጠት የተሄደበት ርቀት ሲታይ በአሁኑ ሰዓት ሕጋውያን የሆኑትን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ተልዕኳቸውን ከኤርፖርት ታግተውና ለሃይማኖታዊ አምልኮ የተሰበሰበውን ሕዝበ ክርስቲያን አዝኖ እንዲበተን በማድረግ ለአንድ አንጋፋና የሀገር ባለውለታ ሊቀጳጳስ የማይመጥን እንግልትና ማዋከብ መደረጉ ሳያንስ ይባስ ብሎ ለሕገወጡ የቡድን አባላት ለአብነትም ያህል በምዕራብ ወለጋ፤ በምሥራቅ ወለጋ፣ በቄለም ወለጋና ሆሮጉድሩ ዞኖች በኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የልዩ ኃይል አባላት ልዩ የፓትሮል እጀባና እንክብካቤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕጋዊ ተቋማት በሕገወጥ መንገድ ተደፍረው እንዲገቡ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ የአምልኮና የአስተዳደር ተቋማት ተሰብረው በሕገወጥ ቡድኖች እንዲወረሩ መደረጋቸው፤ ይህን ሕገወጥ አድራጎት የተቃወሙትን የቤተ ክርስቲያኒቱን የሃይማኖት አባቶችና የአስተዳደር ሠራተኞች ለእስር እንዲዳረጉ መደረጉ፣ ሕጋዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ የአገልግሎት ተሽከርካሪ መኪኖች ለማንኛውም
    አገልግሎት እንዳይንቀሳቀሱ፣ በክልሉ መንግሥት አመራር ተሰጥቷል በሚል እገታ መከናወኑ ሲታይ መንግሥታችን ሕገመንግሥታዊ ጥስት በመፈጸም በሃይማኖታዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱንና በእርሱም ይሁንታ መፈንቀለ ሲኖዶስ እየተከናወነ እንዳለ እምነት የሚያሳድር በመሆኑ ይህ አድራጎት እንዲታረምና መንግሥት ኃላፊነቱን በመወጣት የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ልዕልናና መብት እንዲያስከብር ንብረቶቿ በሕገወጥ ቡድኖች ከመወረር እንዲጠብቅ፣ በሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ መዋቅራዊ አደረጃጀት መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቱ ብፁዓን ሊቃነጳጳሳትና የሥራ ኃላፊዎች ያለምንም እንግልትና የደህንነት ስጋት ተመድበው ሲሠሩባቸው በቆዩበት አህጉረ ስብከት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መንግሥት አስፈላጊውን ጥበቃና የሕይወት ዋስትና እንዲያረጋግጥ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል፡፡
፪. ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ቀደምት ሥርዓተ መንግሥታትን በዋቢነት አሁናዊው የብልጽግና መንግሥት በውጭ የነበረውን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ቅዱስ ሲኖዶስ በእርቅ አንድ ማድረጋቸውን ሲገልጹ በሀገር ውስጥ ሁለት መንበርና ሁለት የፕትርክና መሪነት እንደነበረ የሰጡትን ማብራሪያ በተመለከተ፡- በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊ መዋቅር በወቅቱ በነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ የተከሰተውን ልዩነትና የሲኖዶስ መከፈል በእርቀ ሰላም ማለቁ የማይካድ ሐቅ ቢሆንም በተፈጸመው የእርቅ ስምምነት ውሳኔ መሠረት በግልጽ እንደሰፈረው ሁለት ፓትርያርክ በአንድ መንበር ላይ የነበረ ሳይሆን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ክብራቸው ተጠብቆ በጸሎትና ቡራኬ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በአባትነት እንዲያገለግሉ እንዲሁም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ደግሞ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ የመሪነት ሥራን በአባትነት እንዲመሩ በግልጽ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተወስኖ በውሳኔው መሠረት ተግባራዊ የሆነና በሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር የሚታወቀውን እውነታ በሚንድ መልኩ ቤተ ክርስቲያኒቱ በአንድ መንበር ሁለት ፓትርያርክ ሲመራ ቆይቷል ተብሎ የተገለጸበት አካሄድ በእውነታ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን
    በአሁኑ ሰዓት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ አሠራር በመጣስ በሕገ-ወጥ መንገድ የተፈጸመውን “ሢመተ ጵጵስናና መፈንቅለ ሲኖዶስ ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት የተደረገ ከመሆኑም በተጨማሪ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተወግከው የተለዩት ግለሰቦች ቀድሞውንም ሹመቱን ፈጽመን በዕርቅ እና በድርድር አንድ እንሆናለን : በሚል ሲገልጹት የነበረውን ሀሳብ የሚያረጋግጥና አሁንም በድርድር ሃይማኖታዊ መመሪያችሁን ጥሳችሁ ቀኖናዊ ሥርዓታችሁን አፍርሳችሁ፤ አስተዳደራዊ መዋቅራችሁን ንዳችሁ ተቀብሏቸው እንደማለት የሚያስቆጥር ማብራሪያ አዘል መመሪያ እርምት እንዲሰጥበት ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
፫ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተፈጸመው የእርቀ ሰላም ሂደት ወቅት በውጭ ሀገር የነበሩት አባቶች ሹመታቸው ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ሀገር ሊገቡ የቻሉት በየደረጃው አገልግሎት ሲሰጡ በመቆየታቸው ነው በማለት የሰጡትን በተመለከተ፡- በውጭ የነበሩ ብፁዓን ሊቃነጳጳሳት በእርቀ ሰላሙ ወደሀገር ተመልሰው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሊሆኑ የቻሉትና ተቀባይነት ያገኙት ሹመታቸው የተከናወነው በቀኖና ጥሰት ሳይኖን በሕጋዊ ፓትርያርክ የተፈጸመ ሲመት ከመሆኑም በላይ በስደት ሊቆዩም የቻሉት በወቅቱ በተፈጠረው የፖለቲካ ጫና እየታወቀና ከአሁኑ ሕገወጥ፣ ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ መሠረት የሌለው ሹመት ጋር ግንኙነት የሌለው ሆኖ እያለ ሕጋዊውን ከሕገወጡ ጋር በማቀላቀልና በማነጻጸር የተሰጠው ማብራሪያ እርምት እንዲሰጥበት ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያሳስባል።
0 ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው በቋንቋ የመገልገል መብትን መንግሥት ማፈን አይችልም በማለት የተሰጠው ማብራሪያ በተመለከተ፡- እናት ቤተ ክርስቲያን ዘመን ተሻጋሪ ታሪኳ እንደሚያረጋግጠው የቋንቋ አገልግሎትን በሕጎቿ እውቅና የሰጠች፣ ከዚህም አልፎ በተለይም ግለሰቦች በተደጋጋሚ በሚጠቅሱት በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ለሚኖሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ የእምነት ተከታዮች የቋንቋ አገልግሎት ስትሰጥ የቆየች በመሆኑ በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን
የአምልኮና የሥርዓት መጻሕፍቶች በኦሮምኛ ቋንቋ በማስተርጎም ለአገልግሎት ያበረከተች፣ ሕገወጥ ሹመቱን ከፈጸሙት ሦስቱ የተሻሩት ሊቃነጳጳሳት ጨምሮ በርካታ የቋንቋው ተናጋሪ ብፁዓን ሊቃነጳጳሳትን በክልሉ ባሉ አህጉረ ስብከት መድባ አገልግሎት እየሰጠች የክልሉን ተወላጆች በቋንቋቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን እውቀት ቀስመው ለአገልግሎት ብቁ እንዲሆነ መንፈሳዊ ኮሌጆችን በመክፈት፤ በሁሉም አህጉረ ስብከት የካህናት ማሠልጠኛ ተቋማትን አደራጅታ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ አገልጋይ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ እና _ ሰባክያነ ወንጌል አስተምራ ለአገልግሎት አሰማርታ እያለች የቋንቋ አገልግሎትን እንደተቃወመችና ለአገልግሎቱም በሯን እንደዘጋች በሚያስቆጥር ሁኔታ የተሰጠው ማብራሪያ ከእውነታቸው የራቀና የሕገወጥ ሥልጣን ፈላጊዎችን ሕገወጥ አካሄድና መግለጫ እውቅና የሚሰጥ አድራጎት በመሆኑ እርምት እንዲሰጥበት ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያሳስባል።
፭. ለቤተ ክርስቲያን ተሰጠ ስለተባለው ይዞታና ስለ ደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን የተሰጠውን ማብራሪያ በተመለከተ፣ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ከአምልኮ ሥፍራ የመሬት ይዞታ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለፉት አራት ዓመታት ከሌሎች ቤተ እምነቶች በተሻለ መልኩ ከአንድ አንድ ሚሊዬን አርባ አምስት ሺህ ካሜ ይዞታ በላይ እንደተሰጣትና ይህም የይዞታ ስፋት ለሌሎች ቤተ እምነቶች በድምሩ ከተሰጠው በሦስት እጥፍ እንደሚበልጥ እና አዲስ ይዞታ እንደተሰጠ ተደርጎ በማስመሰል የተሰጠው ማብራሪያ ፍጹም ስህተት እና ሕዝብን የሚያሳስት በመሆኑ ሊታረም ይገባል፡፡ ይኼውም ለቤተ ክርስቲያን ተሰጠ የተባለው ይዞታ ቤተ ክርስቲያን ቀድሞውን በእጂ አድርጋ ለዘመናት ስትጠቀምበት የነበረውን ሕጋዊ ይዞታዋ እና ይሄው በካርታ ተረጋግጦ እንዲሰጥ ስትጠይቅ የቆየች ንብረቷ እንጂ እንደ አዲስ በሊዝ አዋጁ መሠረት በምደባ ያገኘችው አይደለም፡፡
ምንም እንኳን በተገለጸው ልክ አልተሰጣትም እንጂ ቢሰጣት እንኳን ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሕዝብ ውስጥ ከ75% በላይ የሚሆነውን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ እንደመሆኑ መጠን ከሌሎች ቤተ እምነቶች በተሻለ የሰፋ ይዞታ ማግኘቷ እንደልዩ ጥቅም የሚያስቆጥር አይደለም፡፡
            የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም ቅርስ መሆኑ እየታወቀ፣ የውጪ መንግሥታት በዕርዳታ ለመሥራት ፈቃዳቸውን መስጠታቸው በራሳቸው በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንደበት የተገለጸ ሆኖ እያለ፣ መንግሥት ቋሚ የገቢ ምንጭ የሚያገኝበት የቱሪስት መዳረሻ መሆኑ እየታወቀ የቤተ ክርስቲያን ሀብት ብቻ ተደርጎ ከፈረንሣይ መንግሥት የተገኘውን ድጋፍ ለቤተ ክርስቲያን እንደተሰጠ ልዩ ጥቅም በማድረግ ማቅረብ አግባብነት የለውም፡፡
         ፮ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልል ትግራይ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ በክልሉ ለሚኖሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች በወቅቱ ሰጥተውን የነበረውን መግለጫ አንድም ተቃውሞ ሳይቀርብበት አሁን በኦሮምያ ለተከሰተው ይህን ያህል ተቃውሞ አግባብ አይደለም በማለት የሰጡትን ማብራሪያ በተመለከተ፡- በመጀመሪያ ደረጃ በክልል ትግራይ የሚኖሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ከሰጡት መግለጫ መረዳት እንደሚቻለው እና መላው ሕዝበ ክርስቲያን እንደሚያውቀው የቤተ ክርስቲያኒቷን ሕጎችና ቀኖናዎች ጥሰው ሕገወጥ ሲኖዶስ አልመሠረቱም፤ ጳጳሳትንም አልሾሙም፣ እውነታው ይህ ሆኖ እያለ አሁን የተፈጸመውን ሕገወጥ ሹመትና መፈንቅለ ሲኖዶስ ሕጋዊ ሽፋን እንዲኖረው ለማድረግ በሚያስመስል ሁኔታ ሁለቱ የማይገናኙ ድርጊቶችን በንጽጽር የተሰጠው ማብራሪያ እርምት እንዲሰጥበት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል፡፡
             በመጨረሻም መንግሥታችን በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ልዕልና፣ በሕግ የተሰጣትን መብትና ጥቅም በማስከበር ሕገወጡን ድርጊት ተገቢውን እርምት በመስጠት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ እያሳሰበ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነጳጳሳት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋይ ካህናትና ምእመናን ጭምር የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ በማካሄድ በደላችንን ለዓለም ሕዝብ ችግሩ ተፈቶ የቤተ ክርስቲያኒቱ መብት እስኪረጋገጥ ድረስ ያለማቋረጥ እስከ ሕይወት መስዋዕትን ድረስ በመክፈል የምናሳውቅ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶሱ ይገልጻል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ
ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ

   በእንተ ሢመተ ኤጲስ ቆጰሳት

 

 በመ/ር  እንዳልካቸው ንዋይ

ክህነት “ተክህነ” ከሚለው የግዕዝ ግሥ የወጣ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም አገለገለ ተሾመ መንፈሳዊ ሥልጣን ተቀበለ ማለት ነው፡፡በአጠቃላይ ዘይቤያዊ ትርጉሙ አገልግሎት ማለት ሲሆን በምሥጢር ለሹመት መመረጥን ያመለክታል፡፡

ካህን ማለትም በቁሙ ሲተረጎም ቄስ ጳጳስ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሕዝብ መሪ አስተማሪ መንፈሳዊ አባት ማለት ነው፡፡

ክህነት እግዚአብሔር ለሰው ከሰጠው ሀብት አንዱና ዋናው ነው፡፡ ክህነት ከእግዚአብሔር የሚገኝ ጸጋ መለኮታዊ ጥሪ እና ሰማያዊ ምርጫ ነው፡፡ ክህነት እንደ ምድራዊ ሹመት በዘፈቀደ የሚታደል አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ባወቀ ተመርጠው የሚሾሙበት ጸጋ እንጂ ሁሉ ገንዘብ የሚያደርገው ሥልጣን እንዳልሆነ ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ እንዲህ አለ

‹‹ ወደ ተራራም ወጣ ራሱም የወደዳቸውን ወደርሱ ጠራ ወደ እርሱም ሄዱ ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው ድዉዮችንም ሊፈወሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለቱን  አደረገ›› (ማር.፫፡፲፭ )

የመጀመርያው ሰው አዳም ከእግዚአብሔር ከተሰጡት ፯ ሀብታት በአንዱ ሀብተ ክህነት ነው፡፡ ለዚህም ነው በገነት እያለ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቀርብ እንደነበር የተጻፈው ሕጉን ትእዛዙን አፍርሶ በሰይጣን በተታለለ ጊዜ  ደሙን  አእዋፍ  ለምግቡ ከመጣለት ፍሬ ከስንዴ ጋር ቀላቅሎ መሥዋዕት አቀረበ ፡፡

እግዚአብሔርም ዓለም የሚድነው በአንተ ደም ሳይሆን በእኔ ደም ነው ብሎታል፡፡ይህ የክህነት አገልግሎት በሦስቱ ዘመናት ማለትም በዘመነ አበው በዘመነ ኦሪት በዘመነ ወንጌል የተለየ መልክና ሥርዓት ይዞ መጥቷል፡፡

በዘመነ አበው በአበው ዘንድ የክህነቱ ሥራ እየተሠራ ኖሯል፡፡በተራራ ላይ አበው መሥዋዕት እየሰው እግዚአብሔርን እያመለኩ ኖረዋል፡፡ በዘመነ ኦሪትም በምስክሩ ድንኳን በአሮን እና በአሮን ወገኖች ይፈጸም እንደነበር ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ በሐዲስ ኪዳን ግን ራሱ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ በላምና በበግ የነበረው መሥዋዕት በአማናዊው በግ በክርስቶስ ተተክቶ አምላካችን በሾማቸው በ12ቱ ሐዋርያት የሐዲስ ኪዳኑ የክህነት አገልግሎት ይቀጥላል፡፡

በሐዲስ ኪዳን ካሉት የክህነት ደረጃዎች አንዱ ኤጲስ ቆጶስነት ነው፡፡

ኤጲስ ቆጳስነት የአገልግሎቱ ስም ሲሆን ባለቤቱ ኤጲስ ቆጰስ ይባላል፡፡ኤጲስ ቆጶስነት ከፍተኛው የክህነት ደረጃ ነው፡፡ ትርጉሙም የበላይ ጠባቂ መምህር ማለት ነው፡፡በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ኤጲስ ቆጰስ የሚሾመው ከቆሞሳት መካከል በትምህርቱ በትሩፋቱ ልቆ የተገኘ አባት ነው፡፡ የሚመረጠውም በሲኖዶስ ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስ ስለ ጵጵስና ሲጽፍለት ለዚህ ከፍተኛ ማዕርግ የሚመረጠው አገልጋይ ሊያሟላቸው የሚገቡ ጉዳዮችን አብሮ ጽፎለታል፡፡እንዲህ ሲል እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል … (፩.ጢሞ ፫፡፩-፯)

የማይነቀፍ

   ከፍተኛው የቤተ ክርሰቲያን መዓርግ ስለሆነ የእግዚአብሔርም እንደ ራሴ ቤተ ክርስቲያንንም የሚጠብቅ ነውና ለዚህ ሹመት የሚመረጠው አገልጋይ የሚነቀፍ ጠባይ ሊኖረው አይገባም፡፡

                      ድንግል መነኮስ የሆነ

   ቅዱስ ጳውሎስ ለልጁ ለጢሞቴዎስ ኤጲስ ቆጶስ የአንዲት ሚስት ባል እንዲሆን ጽፎለታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም ይህን ሲተረጉም ሐዋርያው ይህንን ትእዛዝ እንደ ግድ መስፈርት አድርጎ አላስቀመጠውም ነገር ግን ከአንድ በላይ ሚስት ያገቡትን ከዚህ ሹመት ለማገድ ነው፡፡

ይህንንም ማድረጉ በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ጊዜያት በመሥፈርቱ ልክ የሚሆን ሰው ስላልነበረ በጊዜው ከነበሩት ሰዎች የተሻለ ቅድስናና ንጽሕና የያዙትን ለመምረጥ ነው፡፡ የድንግልና የገዳማዊ ሕይወት ከተጀመረ በኋላ ግን ከደናግል መነኮሳት መካከል ተመርጦ ይሾማል፡፡ ብሏል በቤተ ክርስቲያናችንም በ325 ዓም በኒቅያ ጉባኤ  ከአገልግሎቱ ትልቅነት የተነሳ ጳጳስ ድንግላዊ እንዲሆን ተወስኗል፡፡

                                     ልበኛ

ስለአገልግሎቱ ጥንቁቅና ንቁ መሆን አለበት ቤተ ክርሰቲያንን የሚያይበት ብዙ አይኖች ያሉት የትናንቱን የዛሬውንና የነገውን አርቆ ማየት የሚችል መሆን አለበት፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም አንድ ጳጳስ አንድ ጦርን ከሚመራ የጦር መኮንን በላይ ጥንቁቅ መሆን አለበት፡፡

ራሱን የሚገዛ

ራስን መግዛት ትልቁ የኦርቶዶክሳዊነት መለኪያ ነው፡፡ ሐዋርያውም በመልእክቱ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ በማለት ገልጾታል፡(ገላ ፭፡፳፫) ራስን መግዛት ለአንድ ምዕመን በጣም አስፈላጊ ከሆነ ለምዕመናን ጠባቂማ እጅጉን አስፈላጊ ይሆናል ፡፡ ራሱን የገዛ ዓለምን መግዛት ይችላል አዳም በገነት ሲኖር ራሱን በመግዛቱ ፍጥረታት በመላ ተገዙለት ራሱን መግዛት ቢሳነው ግን ፍጥረታት በመላ ጠላት ሁነው ተነሱበት፡፡ አምላክም ሰው የሆነው ሰውን ራሱን መግዛት ወደሚችልበት መዓርግ ለመመለስ እና ከራሱ ጋር አስታርቆ ፍጥረት ሁሉ እንዲወዳጀው ለማድረግ ነው፡፡

እንደሚገባው የሚሠራ

  የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ እንደመሆኑ ሊሠራ የሚገባውን ሥራ ሐዋርያት በሲኖዶስ ሠለስቱ ምዕትም በፍትሐ ነገሥት እንዲሠራ የተናገሩትን በትጋት በአግባቡ የሚሠራ  መሆን ይኖርበታል፡፡ ከመዓርጉ የተነሳ ሊሠራ የማይገባውን ከማድረግ መከልከል ይኖርበታል ምክንያቱም ምዕመናን አብነት እንዳያጡ እርሱም የማይገባ ሥራ ሠርተዉ እንደተቀጡ እንደ ናዳብና አብዩድ እንዳይቀሰፍ መጠንቀቅ ይገባዋል (ዘሌ.፲፡፩)

                                ገንዘብ የማይወድ

የአንድ አባት ገንዘቡ ቤተ ክርስቲያንና ምዕመናን ናቸው፡፡ ጌታም ለቅዱስ ጴጥሮስ አደራ ጠብቅ ብሎ የሠጠው ገንዘብ በጎች ጠቦቶችና ግልገሎች ናቸው፡፡ማለትም ከታናሽ እስከ ታላቅ ያሉ ምዕመናንን መጠበቅ ዋናው ተግባሩ እንደሆነ ያሳያል ( ዮሐ.፳፩፡፲፭-፲፯)  ከላይ በተወሰነ መልኩ ያየናቸው የአንድ ኤጲስ ቆጶስ መገለጫዎች ሲሆኑ የሚሾምበትን ሥርዓት ተመልክተን የጽሑፋችን ሐሳብ እንቋጫለን፡፡

ሥርዓተ ሢመተ ኤጲስ ቆጳሳት

ኤጲስ ቆጶስ ከ፶ ዓመት በታች እንዳይሾም ተከልክሏል ‹‹ወዘኢኮነ ሕይወቱ ሕፁፀ እም ፶ ዓመት›› ፍት.ነገ አን ፭/ ዲድ .፬

ብሉይና ሐዲስ የተማረ

  የሚሾመውም በሚሾምበት ሀገር በምእመናን ምርጫና በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ (ፓትርያርኩ) ፈቃድ ነው፡፡ካህናቱና ሕዝቡ እንዲሾምላቸው ኤጲስ ቆጶስ የሚሆነውን ቆሞስ መርጠው ሲያቀርቡ ስለ ደግነቱና ትሩፋቱ ስለንጽሕናውና ከነውር የራቀ ስለመሆኑ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሦስት ጊዜ እየመላለሰ ማረጋጋጫ ይጠይቃቸዋል፡፡ ሕዝቡም አረጋግጠው የሚገባው ነው ብለው ሦስት ጊዜ መልስ ይሰጣሉ በሦስተኛው ሕዝቡ መልስ ሲሰጡ እጃቸዋን አንስተዉ ይገባዋል እያሉ ያጨበጭባሉ፡፡

                        ደግነቱ ያልታወቀ አይሾምም

ሲሾም ካህናቱም ሕዝቡም በሙሉ ተገኝተዉ እየመሰከሩለት ነው የሚሾመው ‹‹ወኩሎሙ ሰብእ ይንበሩ በእንተ ተሠይሞቱ ሕዝብኒ ወካህናት እንዘ ስምዐ ይከውኑ ሎቱ›› በአንድ ዘመን በአንድ ወንበር ሁለት ሰዎች  ፓትርያርክ  ሆነው አይሾሙም፡፡

-ርእሰ ሊቃነ ጳጶሳት ሲሾም ሊቃነ ጳጳሳት ኤጲስ ቆጰሳት ይገኛሉ፡፡ይህ ሹመት ያለ ኤጲስ ቆጶሳት ጉባኤ አይደረግም (ፍት.መን አን.፬ ) ሊቀ ጳጳሳቱ ወይም ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የታመመ እንደሆነ እስከሚድን የታሠረ እንደሆነ እስከ ሚፈታ ይጠበቃል ሹመቱ ለሌላ አይሰጥም፡፡ (ፍት.መን. አን 4)

በአጠቃላይ ከብዙ በጥቂቱ ሥርዓተ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ይህን ይመስላል፡፡አሁን በአለንበት ጊዜ ግን እነዚህን ሥርዓታት ባለመከተል ከሐዋርያት ሲኖዶስ እና ከፍትሐ ነገሥት ትምህርት ውጭ ኤጲስ ቆጶሳትን ሾምን የሚሉ አካላት እየመጡ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ይህን ትምህርት በማወቅ ክፉውን ከደጉ ሃይማኖቱን ከክህደት ጽድቁን ከኃጢአት ሥርዓቱን ሥርዓት ካልሆነው በመለየት በአባቶቻችን ትምህርት መጽናት ይገባል፡፡  የእግዚአብሔር ቸርነት የወላዲተ አምላክ አማላጅነት የቅዱሳን ጸሎት ይርዳን፡፡

   ምንጭ ፡ፍትሐ ነገሥትና

            -ድዲስቅልያ

 

 

ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የተላለፈ መልእክት

የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት መልእክት በብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ እንዲሁም በብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተላለፈ ሲሆን ፣ በመልእክቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በማያወቀውና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ባልጠበቀ መንገድ በእነ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የተሰጠውን ሕገ ወጥ ሢመተ “ኤጲስ ቆጶሳት” በማስመልከት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ባስተላለፉት ጥሪ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ነገ ጉባኤ ረቡዕ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በሚደረግ ሥርዓተ ጸሎት የሚጀመር መሆኑ ተገልጽዋል፡፡
                በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የሚገኙ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እየገቡ እንደሚገኙ በመልእክቱ ተወስቷል፡፡ መንግሥት እንደተለመደው ለጉባኤው ጥበቃ እንዲያደርግ መልዕክት ያስተላለፉት ብፁዕነታቸው ፤ ምእመናን በያሉበት በጸሎት እንዲበረቱ ጠይቀዋል፡፡
አንዳንድ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት ከፍተኛ የአውሮፕላን ቲኬት ችግር እንደገጠማቸው ተረድተናል ያሉት ብፁዕነታቸው ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚበርባቸው መስመሮች ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቅድሚያ እንዲሰጥ ትብብር ተጠይቋል፡፡ በርካታ አህጉረ ስብከት እና መንፈሳዊ ማኅበራት የተፈፀመውን የቀኖና ጥሰት አስመልክቶ ውግዘት እያስተላለፉና እንደማይቀበሉት እየገለፁ ይገኛሉ፡፡
@EOTC TV

የሚዛን ቴፒ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ቢሮ መታሸጉ ተገለጸ።

በነ ‘አባ’ ሳዊሮስ ሕገ ወጥ ሹመት ኤጲስ ቆጶስ ሆነው የተሾሙት የሚዛን ቴፒ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ አባ ሚካኤል ገብረ ማርያም ቢሮ መታሸጉ ተገልጿል።
በትናንትናው ዕለት የሿሚዎቹን ጳጳሳት ማረፊያ ቤትን ጨምሮ የተሿሚዎች ቢሮዎች እየታሸጉ መሆኑን መግለጻችን ይታወሳል።

የሰሜን አሜሪካ ካህናት ማኅበር መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ ካህናት ማኅበር መግለጫ

ከርእሰ አድባራት ዱባይ ሻርጃ አጅማን ቅድስት ማርያም ወቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት የተሰጠ ወቅታዊ ማሳሰቢያ።

ከርእሰ አድባራት ዱባይ ሻርጃ አጅማን ቅድስት ማርያም ወቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት የተሰጠ ወቅታዊ ማሳሰቢያ።

ከምሁር የኢየሱስ ገዳም የተሰጠ የአቋም መግለጫ፡፡

የገዳማችን የበላይ ጠባቂ መስሎ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነትን ለመናድና ምእመናንን ለማወናበድ የታቀደውን ሴራ ስለመቃወም ከምሁር የኢየሱስ ገዳም የተሰጠ የአቋም መግለጫ፡፡

ከነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር የተሰጠ መግለጫ

ኢ-ቀኖናዊ በሆነ መልኩ የተፈጸመውን ”ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት” አስመልክቶ ከነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር የተሰጠ መግለጫ

 

ቀኖና እና ሥርዓት ውጭ በሆነ መልኩ ተሰጠ የተባለውን “ሢመተ ኢጲስ ጶጶስ” እንደማይቀበል የጅማ ሀገረ ስብከት አስታወቀ!

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና እና ሥርዓት ውጭ በሆነ መልኩ ተሰጠ የተባለውን “ሢመተ ኢጲስ ጶጶስ” እንደማይቀበል የጅማ ሀገረ ስብከት አስታወቀ!