የማኅበረ ቅዱሳን ቁ. ፩ አማርኛ መዝሙር ከ፳፱ ዓመታት በኋላ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጉሞ በሰሜን አሜሪካ ማእከል ግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ተዘጋጅቶ በምስል ወድምፅ መቅረቡን የማእከሉ ጽ/ቤት አሰታወቀ፡፡

የማእከሉ ጽ/ቤት ለዝግጅት ክፍላችን ባደረሰን መረጃ የመዝሙሩ አልበም “Foregive me, ማረኝ” በሚል ርእስ የቀረበ ሲሆን በሆሣዕና ዋዜማ መጋቢት ፴ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በሰሜን አሜሪካ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ መምህራን፣ ካህናት እና ምእመናን በተገኙበት ከቀኑ ፯ ሰዓት ጀምሮ በድምቀት ይመረቃል፡፡

ይህ መዝሙር የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በመላው ዓለም ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት ውስጥ አንድ የአገልግሎት አካል መሆኑን ዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው ኦርቶዶክሳውያን የገለጹ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳን በምድረ አሜሪካ ርቀት ሳይገድበው የሚያከናውነው አገልግሎት ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በሀገር ውስጥ ፬፻፳፱፣ በአሜሪካ ፲፫፣ ሩቅ ምሥራቅ ፰፣ ደቡብ አፍሪካ ፩፣ አውሮፓ ፩ ግቢ ጉባኤያት እንዳሉት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡