“የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ ሃይማኖታዊ ክህደት፣ ቀኖናዊ ጥሰት እና አስተዳደራዊ ግድፈት የታየበትን የወሊሶውን “ሹመት” አወገዘ፡፡” የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ

የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ ዛሬ ጥር ፲፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም በሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰብሳቢነት በአካሔደው አስቸኳይ ጉባኤ ሃይማኖታዊ ክህደት፣ ቀኖናዊ ጥሰት እና አስተዳደራዊ ግድፈት የታየበትን የወሊሶውን “ሹመት” ማውገዙ ተገለጸ፡፡
ጉባኤው በቤተ ክርስቲያን ላይ በተፈጸመው ሁሉን አቀፍ ክህደት ዙሪያ ሰፊ ውይይት ያደረገ ሲሆን ክህደቱን የፈጸሙት አካላት ሥልጣን የሰጣቸውን መዋቅር (ተቋም) በመካድ የፈጸሙት ድርጊት እጅጉን አሳዛኝ ነው ብሏል።
የተፈጸመው ጉዳይም ሕገ ወጥና ቤተ ክርስቲያንን የማፍረስ ወንጀል ነው ያለው አስተዳደር ጉባኤው በምንም መመዘኛ ይህን ከፈጸሙ አካላት ጋር መደራደር በተዘዋዋሪ የቤተ ክርቲያናችንን ሕግና ሥራዓትን ማፍረስ ነው ብሏል።
በማያያዝም ጎሰኝነት ኑፋቄ መሆኑን የገለጸው አስተዳደር ጉባኤው ይህን በመሰለ ተመሳሳይ ጉዳዮች ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙ ክህደቶች በዓለም አብያተ ክርስቲያናት መነቀፋቸውን በማንሳት በቋንቋ መማርና ማስተማር ችግር እንዳልሆነ በመረዳት ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያስተምሩ አባቶችን በመሾም አገልግሎት እንዲሰጡ ስታደርግ መቆየቷን ሕገ ወጥ ድርጊቱን ከፈጸሙ አካላት በላይ ማስረጃ አይኖርም ብሏል።
ጉባኤው ለቅዱስ ሲኖዶስ የውሳኔ አካል ሊሆኑ የሚችሉ የውሳኔ ሐሳቦችን ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን እና ከሕግ አንጻር በመነሳት የጠቆመ ሲሆን የተፈጸመው ክህደት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያንና ከሕግ አንጻር እንዴት እንደሚገለጽ የሚያመለክት ሰፊ የሚዲያ ሥራ እንዲሠራ በመወሰንና በቂ ማብራሪያ የሚሰጡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን በመመደብ ከዛሬ ጀምሮ በሁሉም ቋንቋዎች ማብራሪያ እንዲሰጥ ወስኗል።
ሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ተቋማቱን በንቃት መጠበቅና ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚተላለፍ መመሪያን በትጋት መጠበቅ እንደሚገባና አስፈላጊው መመሪያ በአስቸኳይ እንዲተላለፍ የወሰነው አስተዳደር
ጉባኤው በቤተ ክርስቲያን ላይ ክህደት የፈጸሙ አካላት ወይም የሿሚና ተሿሚ ነን ባዮች ደመወዝ እንዲታገድ፣ በተቋማችን ውስጥ የሚገለገሉባቸው ቢሮዎችና ማረፊያ ቤቶች በአገግባቡ እንዲጠበቁ ትእዛዝ የሰጠ ሲሆን መንግሥትም እያደረገ ያለውን የቤተ ክርስቲያንን ጥበቃ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጉባኤው ጠይቋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ምእመናንና ምእመናት ከጸሎት በተጨማሪ መዋቅራዊ መመሪያዎችን በትዕግሥት እንዲጠብቁ አደራ በማለት የዕለቱን ስብሰባ በጸሎት አጠናቋል።
@የኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት
0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *